>
5:16 pm - Sunday May 24, 6139

የሀገራችንና የሱዳን የድንበር ውዝግብ፣ የዐፄ ምኒልክ ስምምነትና በአገዛዙ የተፈጸመብን የሀገር ክህደት!!!  (አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

የሀገራችንና የሱዳን የድንበር ውዝግብ፣ የዐፄ ምኒልክ ስምምነትና በአገዛዙ የተፈጸመብን የሀገር ክህደት!!!

 

 አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሱዳንና ግብጽ ሳይሆንላቸው ቀረ እንጅ እንደነሱ ሐሳብማ ቢሆን በእንግሊዝና ቱርክ የቅኝ ገዥዎቻቸው ዘመን ጀምሮ ነበር እኮ ጣናንና አካባቢውን አሀገራችን ቆርሰው ወይም ከኢትዮጵያ ነጥቀው የግዛታቸው አካል በማድረግ ዓባይን በቁጥጥር ስር በማዋል የውኃ ዋስትናቸውን በአስተማማኝ መልኩ ማረጋገጥ እንዲሁም ለምና ሰፊ የእርሻ መሬትን ማግኘት ነበረ እኮ ምኞታቸው!!!
ይሄንን ስስትና ሲበዛ ራስወዳድነት የተጣባውን ሐሳብ ለማስፈጸም በቅኝ ግዛት ከነበሩበት ዘመን ጀምሮ ብዙ ደክመዋል ብዙ ተገቢ ያልሆነ መሥዋዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል!!!
ከጊዜ በኋላ ደግሞ “ለጊዜው ይሄንን ማድረግ ባንችል እንኳ!” በማለት እንደምታዩዋቸው የ1902ዓ.ምሕረቱን የሻለቃ ጎየንን የተወናበደ፣ የተናጠልና ለአንድ ወገን ያደላ የድንበር አከላለል ሙከራን በማንሣት “ከጎንደር እስከ ጋምቤላ ያለውን ሰፊና ለም መሬት ከኢትዮጵያ ነጥቀን የእኛ እናድርግ!” በማለት ሲንቀሳቀሱ እንደኖሩ ይታወቃል!!!
በዚህ ዘመን ተሟጋች፣ ተከራካሪና ተቆርቋሪ መንግሥት ስለሌለን ነው እንጅ ታሪክ እናንሣ ከተባለማ እኛ ከእነሱ የሻለቃ ጎየን የድንበር መስመር መሰመር በፊት ሱዳን በእንግሊዝ ቅኝ ከመያዟ በፊት ድንበራችን እስከ ካርቱም ድረስ እንደነበርና በቆየው ታሪካችን ደግሞ እስከ ላዕላይ ግብጽ (ደቡባዊ ግብጽ) ድረስ ግዛታችን እንደነበረ የሚያረጋግጥ ስንት መረጃዎች ነበረን አይደለም ወይ???
ሱዳንና ግብጽ ውኃችንን በነጻ መጠጣታቸውና በውኃችን የግብርና ምርታቸውን ማምረታቸው ሳያንስ ጭራሽ መሬታችንን መከጀላቸው ለምን ይመስላቹሃል??? አለቅጥ ጅል ሆነን ስላገኙን ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ለመቁረጥ አይመስላቹህም???
እነሱ በዚያም በዚህም ብለው በውለታ ካሰሩት፣ ከፈስፋሳውና ከከሀዲው የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ ጋር ስምምነት ፈጽመው ድንበር ተሻግረው መሬታችን ላይ በመስፈር ወስደውታል፡፡ ቀሪውን መውሰድ የሚፈልጉትን መሬት ደግሞ አገዛዙ መሰንበቻውን ሕዝቡን ለማግባባት ካድሬዎቹን በየአቅጣጫው አሰማርቶ “በድንበር አካባቢ ዘላቂ ሰላም መስፈን ስላለበት የሱዳንና የኢትዮጵያን ድንበር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሠለጠነ መንገድ ተደራድረን መወሰንና ድንበሩን መካለል ይኖርብናል!” እያለ እንዳለው ድርድር በተባለው የኢትዮጵያን መሬት አሳልፎ በመስጠቱ አሻጥር ቀሪውን የሚፈልጉትን መሬት በድርድሩ ተሰጥቷቸው ገበሬው ለሽዎች ዓመታት ከኖረበት ሀገሩ፣ ቀየውና መንደሩ ተፈናቅሎ መሬቱን እንደሚወስዱ እየጠበቁ ይገኛሉ!!!
አያሳዝንም??? አይገርምም??? አያቃጥልም??? አያሳርርም???
ያን ከወሰዱ በኋላ ደግሞ መጠየቃቸውን የሚያቆሙ እንዳይመስላቹህ፡፡ ምክንያቱም ግስጋሴያቸው “የሆነ ወቅት ላይ ዓባይን ገድበውብን ጉድ እንሆናለን!” ከሚል ሥጋት ለመውጣት ዓባይን ከምንጩ ጣናንና አካባቢውን የግዛታቸው አካል በማድረግ የዓባይን የውኃ አቅርቦት በአስተማማኝ መልኩ ለዘለዓለሙ ማረጋገጥ ነውና ዓላማቸወሸ በዚያም በዚህም ብለው ይሄንን የቆየ ዓላማቸውን እስኪያሳኩ ድረስ ግስጋሴያቸውን ይቀጥላሉ!!!
ደግሞ ምን ይገርመኛል መሰላቹህ አገዛዙ ለምን ሱዳን የጠየቀችውን መሬት እንደሰጠ ሲናገር “የዓባይን ግድብ መጨረስ ካለብን የሱዳን ድጋፍ ወይም አጋርነት በእጅጉ ስለሚያስፈልገን ነው!” ማለቱ ነው!!!
አገዛዙ ኢትዮጵያ ዓባይን የመገደብ በዓባይ የመጠቀም ሕጋዊ መብቷን ከዓለም አቀፉ ፍትሐዊና ምክንያታዊ (Equitable and Reasonable) የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ሕግ እንድታገኝና እንድታስከብር ሳይሆን የሚፈልገው በትጥቅ ትግሉ ወቅት ለሱዳን ቃል የገባውን መሬታችንን የመስጠት ክህደት ለመፈጸም እንዲመቸው ይሄንን ሕጋዊ መብታችንን በሱዳንና ግብጽ እጅ ላይ ጥሎ ከሱዳንና ግብጽ በልመናና ተማጽኖ እንድናገኝ ማድረግ ነው የሚፈልገው!!!
እጅግ አያሳዝንም??? አይገርምም??? አያቃጥልም??? አያሳርርም???
ይሄው ጉደኛ ከሀዲ አገዛዝ ለዚህ ወደር የለሽ የሀገር ክህደት ተግባሩ ሌላም የሚጠቅሰው ነገር አለው “ዐፄ ምኒልክ የዓባይን ወንዝ ላለመገደብ ከወቅቱ የግብጽና የሱዳን ቅኝገዥ ጋር ስምምነት ስለፈጸሙ ግብጽንና ሱዳንን አግባብተን አስፈቅደን ከመሥራት ውጭ አማራጭ የለንም!” የሚለው ነገር አለው!!! አይገርምም???
ሲጀመር ዐፄ ምኒልክ ከማንም ጋር እንዲህ ዓይነት ስምምነት አላደረጉም!!! በ1902ዓ.ም. እንግሊዝ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከባድ ጫና በማድረግ ስምምነት እንዲፈረም ሞክራ ነበረ የሚባለው ነገር ምንድን ነው መሰላቹህ “ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ እንዳታስር (not to arrest the river nile)” እና “ሀገሪቱ በዓባይ ወንዝ ላይና በጣና ሐይቅ ላይ ያለ እንግሊዝ መንግሥት ፈቃድ የልማት ሥራ እንዳትሠራ!” የሚል ወይም የሚከለክል ስምምነት ነበር ለማድረግ ተሞክሮ የነበረው!!!
ይሁንና ዐፄ ምኒልክ የስምምነቱ ሰነድ ከደረሳቸውና ካዩት እንዲሁም እንደ ውጫሌ ውል የአማርኛውና የእንግሊዝኛውን ቅጅ ትርጉም መለያየቱን ከተረዱ በኋላ በከፍተኛ ደረጃ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት የሚዳፈር ስምምነት ሆኖ ስላገኙት “ውድቅ አድርጌዋለሁ!” ብለው ወዲያውኑ ውድቅ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል!!!
ከዚህም በተጨማሪ ሀገራችን አሁን በዚህ ዘመን በዚያ ውድቅ በተደረገ ስምምነት ልትገዛ የማትችልበት ሦስት ጠንካራ ሕጋዊ፣ ሞራላዊና አመክንዮአዊ ምክንያቶች አሉ፦
1ኛ. ምንም እንኳ ስምምነቱ ወዲያውኑ ውድቅ የተደረገ ቢሆንም ያ ስምምነት በዚህ ዘመን ሊሠራ የማይችለው ስምምነቱ የተደረገው ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በመሆኑና አሁን ላይ እንግሊዝ በግብጽና በሱዳን ላይ የቅኝ ገዥነት ሥልጣል ወይም ሁኔታ ስለሌላት ወይም ቅኝ ገዥነቷ ስላከተመለት ያ ስምምነትም ቅኝ ገዥነቷ ከማክተሙ ጋር አብሮ አክትሞለታል!!! ባከተመለት ስምምነት ደግሞ ልንገዛ አንችልም ወይም አንገደድም!!!
እንግሊዝ በጫና እና በማስፈራሪያ ያንን ስምምነት ለመፈጸም የሞከረችው ለራሷ ጥቅም እንጅ ለሱዳንና ለግብጽ ሕዝብ ጥቅም አይደለም፡፡ ይሄ ለሁሉም ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም የእኛ ጉዳይ ወይም ግንኙነት የነበረው ከእንግሊዝ ጋር እንጅ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር አይደለም፡፡ ሱዳንና ግብጽማ ጥቅማቸውን፣ ነጻነታቸውን፣ ሉዓላዊነታቸውን ማስጠበቅ መከላከል ተስኗቸው በእንግሊዝ ቅኝ ገዥ መዳፍ ስር የወደቁ ደካማ ሀገሮች ናቸው!!! ከእንግሊዝ ጋር የነበረው ጉዳያችን ደግሞ የእንግሊዝ ቅኝ ገዥነት ሲያከትምለት አብሮ አክትሞለታል፡፡ የዚያ የ1902ዓ.ም. ስምምነት ነገር እዚህ ላይ ያልቅለታል!!!
2ኛ. ሕግ “ያለ ነጻ ፈቃድ በኃይል ወይም ጫናና በጉልበት የተፈጸመ ስምምነት በሕግ ፊት አይጸናም!” ይላል፡፡ ስለሆነም በማስፈራራት፣ በጫናና በጉልበት በማጭበርበርም ጭምር ለማስፈጸም የተሞከረው ያ ስምምነት ሕጋዊ ሊሆን አይችልም!!!
3ኛ. ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያላረጋገጠ ስምምነት በጉልበት ብቻ ካልሆነ በስተቀር በሕግ ሊከበርና ተፈጻሚ ሊሆን እንደማይችል ዓለማቀፋዊ ሕጎችና ስምምነቶች ይደነግጋሉና ነው!!!
በመሆኑም ያ የ1902ዓ.ም. ስምምነት በዚህ በእኛ ዘመን ሊሠራ አይደለም ሊጠቀስ ሊታወስ እንኳ የሚችል ስምምነት አይደለም፡፡ መንግሥት እንደሌለን ስለሚያውቁ ወይም አገዛዙ የእነሱ ኩሊ ስለሆነና ጅሎች ሆነን አግኝተውን ነው እንጅ!!!
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! አገዛዙ የሀገራችንን መብትና ጥቅም በግብጽና በሱዳን እጅ ጥሎ ከእነሱ እጅ በልምምጥና በልመና እንድናገኝ የሚያደርገው ጥረት ሁሉ ጠብታ ውኃ የማይቋጥርና ክህደት የተሞላ ተግባር መሆኑን አውቀህ ተነሥ!!!
Filed in: Amharic