>

አንባገነን የመፍጠር ፕሮጀክት!!! (አዲሱ ጌታነህ)

አንባገነን የመፍጠር ፕሮጀክት!!!

አዲሱ ጌታነህ
* የዘር ፖለቲካ በህግ እንዲታገድ እየጠየቁ የዘር ፖለቲካ አስቀጣዩ በኢህአዴግ ብጥስጣሽ የተመሰረተው ብልፅግና እንዲቀጥል መፈልጋቸው ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ጤነኝነታቸውም ያጠራጥራል። በእርግጥ እነዚህ ሰዋች ሲታገሉ የነበረው ለዴሞክራሲያዊ መንግስት ምስርታ ወይስ የህወሃት ጥላቻ? የሚያስብል ነው!
ጠሚ አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ለዴሞክራሲያዊ መንግስት ግንባታ ሲታገሉ የምናውቃቸው ሰዎች፣ ኢዜማ/ግንቦት 7 እና ኢሳት የጠሚ አብይ ስልጣን እንዲራዘም ቀዳዳ በመፈለግ ተጠምደዋል። እነዚህ አካላት አንዳንድ ጊዜ ኮሮናን  ሌላ ጊዜ ምንም አይነት ግንኙነት የሌለውን የህገ መንግስቱን አንቀፅ 60ን በመጥቀስ የአብይን ስልጣን ለማራዘም ይኳትናሉ። መከራከሪያቸው ውሃ የማይቋጥር መሆኑ ሲረዱት ደግሞ የሽግግር መንግስት ምስረታ “አስቸጋሪነትን” በመጥቀስ ሊያስፈራሩን ይዳዳቸውል።
በመሰረቱ የጠሚ አብይ መንግስት ከህወሃትና ኦነግ የሚለይበት ምክንያት የለም። የጠሚ አብይ መንግስት ሃገራችን አሁን ለምትገኝበት ምስቅልቅል የዳረጋትን ህገ መንግስት እንዲቀጥል በመፈለግ ከህወሃትና ኦነግ ቢበልጥ እንጅ አያንስም። ይህንንም እራሳቸው ጠሚሩ በተደጋጋሚ የተናገሩት ነገር ነው።
በመሆኑም ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ሲታገሉ የነበሩት ከላይ የጠቀስኳቸው አካላት ይህ ስርዓት እንዲቀጥል የፈለጉበት ምክንያት ሊገባኝ አልቻለም። የዘር ፖለቲካ በህግ እንዲታገድ እየጠየቁ የዘር ፖለቲካ አስቀጣዩ በኢህአዴግ ብጥስጣሽ የተመሰረተው ብልፅግና እንዲቀጥል መፈልጋቸው ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ጤነኝነታቸውም ያጠራጥራል። በእርግጥ እነዚህ ሰዋች ሲታገሉ የነበረው ለዴሞክራሲያዊ መንግስት ምስርታ ወይስ የህወሃት ጥላቻ? የሚያስብል ነው።
በኢትዮጵያ “ህገ መንግስት” የመንግስትን ስልጣን ማራዘም አይቻልም። የህገ መንግስቱ አንቀፅ 60 ዋና ዓላማ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለሚበተንበት ሁኔታ እንጅ ስለ ስልጣን ማራዘም አይደለም። አንቀፅ 60 ንዑስ አንቀፅ 1 የጠቅላይ ሚንስትሩ ስልጣን ከመጠናቀቁ በፊት በስምምነት ፓርላማውን በመበተን በተገደበ ስልጣንና ጊዜ ምርጫ እንደሚደረግ የሚደነግግ ነው። በዚህ ንዑስ አንቀፅ ሶስት መሰረታዊ ነገሮች አሉ። እነዚህም “የጠሚ ስልጣን ከማለቁ በፊት፣ አዲስ ምርጫ ለማካሄድ፣ በምክር ቤቱ ፈቃድ” የሚሉት ናቸው። በመጀመሪያ  ምክር ቤቱን ለመበተን የምክር ቤቱ ስምምነት አስፈላጊ ነው። ይህም ማለት የምክር ቤቱ ስልጣን ከመጠናቀቀ በፊት እንደሆነ መረዳት ይቻላል። የምክር ቤቱ ስምምነት የሚያስፈልገውም ለአምስት ዓመት የህዝብ ውክልና የተሰጠው በመሆኑ ነው። ስለዚህ በተጠናቀቀ የስልጣን ዘመን የምክር ቤቱ ስምምነት አስፈላጊ አይደለም ማለት ነው።
በመሆኑም አሁን በስራ ላይ ያለው ምክር ቤት በመጭው መስከረም የሚጠናቀቅ በመሆኑ ከጠሚሩ ጋር በመስማማት የሚበትነው ነገር አይኖረውም። የሌለ ስልጣንን ለመበተን ስምምነት አያስፈልግም።
ሌላው “የጠሚሩ ስልጣን ከመጠናቀቁ በፊት” የሚለው ነው። በዚሁ ህገ መንግስት መሰረት የጠቅላይ ሚንስትሩ የስልጣን ዘመን የህዝብ ተወካዮች የሥልጣን ዘመን እንደሆነ የሚደነግግ በመሆኑ በመጭው መስከረም ይጠናቀቃል። ስለዚህ የጠሚሩም ሆነ የምክር ቤቱ ስልጣን የተጠናቀቀ በመሆኑ በስምምነት የሚበተን ምክር ቤት የለም። በነገራችን ላይ ጠሚሩ ምክር ቤቱን በመበተን ከመስከረም በኋላ ይቆያሉ ማለት የአንድ የምርጫ ተርም ጊዜ 5 ዓመት ከስድስት ወር ነው እንደማለት ነው።
በዚሁ ህገ መንግስት መሰረት የህዝብ ስልጣን መያዝ የሚቻለው በምርጫ ብቻ ነው። ምርጭ ማድረግ ደግሞ አልተቻለም። መጀመሪያውንም በዚህ ህገ መንግስት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ አይቻልም ነበር። አሁን ካለንበት ችግርም በምርጫ መውጣት አይቻልም። ስለዚህ የመንግስትን ስልጣን ማራዘም የሚቻልበት መንገድ በሌለበት ሁኔታ የጠሚ አብይ መንግስት እንዲቀጥል ማድረግ ሃገራችንን ለትርምስ የሚዳርግ ነው። መፍትሔው ሁሉን አቀፍ ውይይት ብቻ ነው።
በመሆኑም በህገ ወጥ መንገድ የጠሚሩ ስልጣን እንዲቀጥል ቀዳዳ የምትፈልጉ ሰዎች አንባገነን እየፈጠራችሁ ነውና ብታስቡበት መልካም ነው። ከወዲሁ ውይይት እንዳይጀምር በማድረግ በቀጣይ ሃገራችን ወደ ትርምስ ብትገባ ሃላፊነቱን ከመንግስት እኩል እንደምትወስዱ ልታውቁት ይገባል።
Filed in: Amharic