>

"ሀዘናችሁ ሀዘናችን እምባችሁም እምባችን ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ያያል ይፈርዳልም!!!" (እስክንድር ነጋ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፕሬዝዳንት)

“ሀዘናችሁ ሀዘናችን እምባችሁም እምባችን ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ያያል ይፈርዳልም!!!”

እስክንድር ነጋ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፕሬዝዳንት
ትናንት ሚያዝያ 15 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ወረዳ 05 ልዩ ስሙ ካባ  እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ከትላንት ሌሊት 9 ሰዓት ጀምሮ በመንግስት በተደራጁ ሃይሎች ቤቶች እየፈረሱ መሆኑን የአማራ ሚዲያ ማዕከል መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በዚህ አስከፊ የኮሮና ተህዋሲ ወረርሽኝ ወቅት ችግር ላይ መውደቃቸውን ከገለፁት ነዋሪዎች መካከልም ወጣት መንሱር አንዱ ሲሆን “እንቅልፍ የለንም 24 ሰዓት ሙሉ አልተኛንም ቤታችሁ  ይፈርሳል ተብለን ሜዳ ላይ ወድቀን እየጠበቅን ነው፤ እኛ ኢትዮጵያዊ አይደለንም እንዴ?” በማለት በእንባ እየተራጨ ተናግሯል፡፡
ወ/ሮ አበበች በበኩላቸው “ወልጄ ገና 15 ቀን ሳይሞላኝ ነው ቤቴን በዶዘር እላዬ ላይ ያፈረሱት፡፡ አሁን ጎዳና ላይ ወድቄያለሁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋረደኝ” ስትል የገዥዎችን የጭካኔ ጥግ አሳይታለች።
ነዋሪዎቹ ሲቀጥሉ “በየጊዜው ማልቀስ ሰለቸን፤ ዜግነታችን እየተጠራጠርን ነው፤ በገዛ ሀገራችን መሄጃ አጣን፤ ለሚመለከተው አካል አቤት በሉልን፤ የኛ ችግር ተሰምቷችሁ እዚህ በመምጣታችሁ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም እናመሰግናለን።” ብለዋል።
ተፈናቃይ ወገኖች ቤታችን በመንግስት ፈርሶ ሜዳ ላይ ወደቅን ሲሉ ስለፍትህ መጮሀቸውን ተከትሎም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች እቦታው ድረስ በመሄድ ተፈናቃዮች የደረሰባቸውን በደል በመጠየቅ ያፅናኑ ስለመሆኑ ታውቋል።
በስፍራውም የባልደራስ ፕሬዝዳንት አቶ  እስክንድር ነጋን ጨምሮ የፓርቲው ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ገለታው ዘለቀ  እንዲሁም የድርጅቱ ጉዳይ ሃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል ተገኝተው ሁኔታውን ታዝበዋል፡፡
ተፈናቃዮችን ያነጋገሩት አቶ እስክንድር ነጋ በዚህ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በሌላ በኩል በረመዳን ፆም ወቅት የድሆችን ቤት በማፍረስ ዜጎችን ሜዳ ላይ ጥሎ ማስለቀስ ተገቢ አይደለም፤ ዘላቂ መፍትሄ ይሻል ብለዋል።
እስክንድር ነጋ ሲቀጥሉ ዛሬ ወደዚህ ያመጣን እንባችሁ የኛም እንባ ነው! ሀዘናችሁ የኛም ሀዘን ነው፤ ከለሊት ጀምሮ ያሰማችሁት የድረሱልን ጥሪ እንደ ሰዉ ተሰምቶን ነው።”ሲሉም ተደምጠዋል።
ከዚህም ባሻገር “ወደዚህ የመጣነው የፖለቲካ ትርፍ ይዘን ሳይሆን በሰብአዊነት ብቻ ነው፤ መፈናቀሉ እንዲቆም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፣ ለመንግስትና ለአለም ሕዝብ በቅርብ እየተከታተልን እናሳውቃለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም አቶ እስክንድር “እምባችሁ እምባችን ነው! የኢትዮጵያ ህዝብ ያያል፤ ይፈርዳል፤ ድምጻችሁ በከንቱ አይቀርም፤ ለመፍትሄዉ በጋራ እንሰራለን፤ ይህ በደል በቀጣዩ  ምርጫ ያበቃል ብለን እናምናለን።”በማለት ተፈናቃይ ወገኖችን በማፅናናት ከጎናቸው እንደማይለዩ አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚህ ሳምንት ብቻ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ወረዳ 05 በተጨማሪ በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 12 የወረገኑ አካባቢ ነዋሪዎችን በርካታ መኖሪያ ቤቶችን በማፍረስ ንፁሀንን ማፈናቀሉ ይታወቃል።
አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
ሚያዝያ 16 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ
Filed in: Amharic