>

የግል ስሜትና ብሄራዊ ምልክት...!!! (በእውቀቱ ስዩም)

የግል ስሜትና ብሄራዊ ምልክት…!!!

 

 

በእውቀቱ ስዩም
ባገራችን  ህዝብ ከገዥ ጋር ተማክሮ የመረጠው ብሄራዊ ምልክት ኖሮ አያውቅም  ፤ ያገር ገዥዎች  የሆነ የስልጣን  ምልክት ይመርጣሉ፤  ያ ምልክት  በውድም ሆነ በግድ  ብሄራዊ ምልክት ሆኖ ይቀራል ፤ገዥው አምራቹን ህዝብ( ገበሬውን፤አንጣሪውንና  ነጋዴውን) አማክሮ የመረጠው ምልክት መኖሩን የሚያስረዳ ታሪክ ካለ አቅርብልኝ!  የእድሜ ልክ ተማሪነኝና ሀሳቤን ለመቀየር አላቅማም!
 አንበሳ የአራዊት ንጉስ ነው ተብሎ ይታሰብበት በነበረበት ዘመን ነገስታት አምሳላቸው አድርገው መርጠውታል፤ አንድም፤  የክርስቶስ ምልክት ስለሆነ የክርስትያን ነገስታት ምልክት ሆኖ ቆይቷል
   ይሁን እንጂ ሁሉም ነገስታት ተመሳሳይ ልማድ አይከተሉም ነበር   ፤ለምሳሌ  ዳግማዊ  ቴዎድሮስ አንበሳ ማህተም የነበረው ሲሆን ተተኪው  አጤ ተክለጊዮርጊስ ነብርን በምልክትነት  መርጧል:: ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ርግብን (የኖህ ርግብ) የማህተሟ ምልክት አድጋለች ፤
 ታሪክን ትንሽ ብንበረብር  በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር ከአዋፋት ጋር የተቆራኙ  ጌቶች  ማግኘታችን አይቀርም፤   የካፋ  ነገስታት እንደ ጥንታዊ ግብፃዉያን   በላባ ያጌጠ ዘውድ ነበራቸው ፤ላባው ከየትኛዋ ወፍ አይነት እንደተነቀለ አላወቅሁም፤    ንጉስ  ምኒልክ የሀረሩን ኢሚር  አብዱላሂን በጦርነት አሸንፎ  ከያዛቸው ምርኮዎች መካከል ለማዳ ውሻና ለማዳ ወፍ ይገኙበታል፤
“የምኒልክ ነገር 
ይመስለኛል ተረት 
አሞራው በቀፎ
ውሻው በሰንሰለት” ብላ የዘፈነችው  ገንቦኛ የወፉን አይነት ለይታ አልነገረችንም፤ ግን የተሸናፊውን ያክል አሸናፊው የማረከው ብርቅ ወፍ  ቢሆን ነው!
የጠቅላይ ምኒስትር አብይ  አህመድ  ጣዖስ  የዘመኑን መንፈስ የሚያስረሳ ክርክር ቀስቅሳለች  ፤  አንዳንዱ በሚያነሳው ክርክር ላይ  አንዳች ፍሬ አይጠፋውም  ፤  ስራ ከምፈታ ልጄን ላፋታ  ብሎ የተሰማራም ሞልቱዋል   ፤   ስለ ጣኦስም ሆነ ስለ አንበሳ ትርጉዋሜ  በሰፊው እመለስበታለሁ ፤
   አይበልብኝና ስልጣን  ላይ ብወጣ  የአንበሳንም ሆነ የጣኦስን ሀውልት  አላፈርስም፤    በነበረው ላይ የራሴን ብሄራዊ ምልክት እመርጣለሁ ፤ ከበሬ ሌላ ማንን ልመርጥ እችላለሁ?  የሚወዱኝ ለምልክቱ ጥሩ ጥሩ ትርጉም እየሰጡ ይደግፉልኛል፤ በውቄ ለመጀመርያ ጊዜ አርሶ አደሩን የሚያከብር ብሄራዊ ምልክት  አስተዋወቀ እያሉ ያወድሱኛል፤ የሚጠሉኝስ?  “በሬ”   የሚለው ቃል ባንድ አዳር  ስድብ አድርገውት ያድራሉ፤  ችግሩ ከምልክቱ አይደለም፤ ለምልክቱ ባለቤት ካለን አስተያየት ነው፤   ስሜት ከአእምሮ በላይ እንደሚበረታ ለማስረዳት  ሾፐናወርንና ብጤዎችን መተንተን አይጠበቅብኝም ! እነዚህን ያገራችን  ተረቶች ብቻ ማየት ይበቃል;
 -ሰውን ሲወዱ ከነ ንፍጡ ! 
-ጠላት ይቀባል ጥላት !
Filed in: Amharic