>

"ገዥዎች ሆይ ሌሊት እያፈረሱ ቀን ዘይትና ሳኒታይዘር  ማንጠለጠሉ  ለታይታ እንጂ ለምርጫ አይበጃችሁም!!!"  (ከመስከረም አበራ) 

“ገዥዎች ሆይ ሌሊት እያፈረሱ ቀን ዘይትና ሳኒታይዘር  ማንጠለጠሉ  ለታይታ እንጂ ለምርጫ አይበጃችሁም!!!”

ከመስከረም አበራ
         ሃገርን ከተፈራራቂ አምባገነኖች የሚታደጋት የዲሞክራሲ ተቋማት መገንባትና መጎልበት ነው፡፡ ህወሃት ከተባረረ በኋላ በሃገራችን የመጣው መንግስት እንደ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አይነት በግሌ ትልቅ ቦታ የምሰጣቸውን፣በተግባር የተፈተነ ለዲሞክራሲ ምፅዓት የመታገል ታሪክ ያላቸውን ሰዎች በማምጣት ለሃገራቸው ዲሞክራሲ ስፍነት እንዲሰሩ ማድረጉ ትልቅ ተስፋ የሚያጭር ነገር ነው፡፡ በህወሃት ዘመን ስለ ዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት ተናግረው የማይጠግቡ ስደተኛም ሆኑ አገርቤት የከተሙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ ሃገርቤት ሲገቡም ለዲሞክራሲ መዳበር ትልቅ ግብዓት እንደሚሆኑ ተስፋ ተደርጎ ነበር፡፡
ሆኖም እነዚህ ፓርቲዎች ህወሃት ገና በልቡ ስላሰበው ነገር ሳይቀር እየተነተኑ ተቃውሟቸውን ሲያዘንቡ እንዳልነበር ዛሬ በበሽታ ወቅት ሰው ከቤቱ የሚያፈናቅለውን መንግስት አንዳች ማለት አልቻሉም፡፡ ይህ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው! በበኩሌ በሃገሪቱ ያለው ተፎካካሪ ፓርቲ ህዝብን የሚፈልገው በምርጫ ወቅት ድምፁን እንዲሰጠው ብቻ እንጅ ከዛ ውጭ ከህዝብ ሰብዓዊ ሆነ ዲሞክራሲያዊ መብት መከበር ጋር ጉዳይ ያለው አልመስል ካለኝ ሰነባብቻለሁ፡፡ስለዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምን ህዝብ ላይ እንዲህ ያለ ግፍ ሲሰራ ዝም አሉ ለማለት አይዳዳኝም …..
መጠየቅ የምፈልገው በሃገራችን ያሉ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን ነው፡፡ ከሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጀምሮ በሰብዓዊ መብት ስም ትልልቅ ተቋማትን የሚመሩ አካላት በዚህ ክፉ የበሽታ ጊዜ ሰዎች ከቤታቸው ወጥተው መንገድ ላይ ሲበተኑ ዝም ማለታቸው ለምን ይሆን? የሰዎቹ ህገወጥነት/ህጋዊነት ተነስቶ ለሚነሳው ክርክርስ ጊዜው አሁን ነው ወይ! ይህ የሞት ጆፌ የሚያንዣብብበት ዘመን አልፎ መነጋገር አይቻልም ወይ …….! ይህን ይህን ካልሰሩ በተቋም ደረጃ መቀመጥ ትርጉሙ ምንድን ነው…..
በስተመጨረሻም በካሜራ ፊት ዘይት ፣ ዱቄት ፣ ሳሙናና ፣ ሳኒታይዘር  እየያዘ የሚዞረው ከንቲባም ሆነ ጠቅላይ በጥምርት የሚሰሩት ግፍ ዱቄት ይዞ በመዞር ግብዝነት ሊካካስ የማይችል እጅግ አስተዛዛቢ፣ተስፋ አስቆራጭ እንደሆ ለማንም እንደማይጠፋው ሊታወቅ እንደሚገባ ማስመር እፈልጋለሁ፡፡ዙፋን ላይ ተቀምጠው ሲያዩን ምን እንደምንመስል ባላውቅም ከብቶች እንዳልሆንን መታወቅ አለበት!
Filed in: Amharic