>

የሌሊት ወፍ፣ ጭልፊት እና እርግብ ! ( ውብሸት ታዬ)

የሌሊት ወፍ፣ ጭልፊት እና እርግብ !

(ከ*ውስጥ የተገኘ ምስጢራዊ መረጃ)

ውብሸት ታዬ

  በአንድ ወቅት አዕዋፍት ጭቆናና በደል በዛባቸው። በወቅቱ የነበረው አምባገነናዊ ሥርዓትየጭልፊት ስርዓት ስለነበር ነጥቆ መብላት ብቻ እንጂ ማካፈል ያልፈጠረበት፣ አዕዋፍቱን በየዝርያቸው ከፋፍሎ ማጋጨት ልዩ መገለጫው የሆነ ነበር።
   በነፃነት መንቀሳቀስ፣ ጭልፊት ወይም የጭልፊት ዝርያ ካልሆኑ በአዕዋፍነት ብቻ ተከብሮ መኖር የማይታሰብ ሆነ። ግፍና በደል በዛ። እናም ‘በቃን!’ አሉ።
  ሆኖም ‘በቃን!’ ማለት ብቻውን በቂ አልነበረምና ጭልፊታዊውን ሥርዓት ከላያቸው ላይ ስለሚያስወግዱበት መንገድ በሳይታዩ ምሽት ላይ በሕቡዕ ለመምከር ቀጠሮ ያዙ።
  አመሻሽ ላይ አንድ ወርካ ላይ ተሰባስበው በደንብ እስኪጨላልም ከጠበቁ በኋላ አድማው ተጀመረ። ምክር ተደረገ፤ የትግል ስልቶች ተነደፉ። በመጨረሻ ማን ይህን ትግል ይምራ? የሚለው አጀንዳ ሆኖ ቀረበ።
  በትግል ወቅትም ቢሆን ስልጣን ተፈላጊ ነገር ነውና አንድ ሁነኛ መሪ ለመምረጥ ስምምነት ላይ መድረስ አቃታቸው። በዚህ መሐል አንድ ድምጽ “እኔ ልምራችሁ!” ሲል ተሰማ። ጭለማ ስለነበር አዕዋፍቱ አቅጣጫውን እንጂ የተናጋሪውን ማንነት መለየት አልቻሉም።
   ተናጋሪው ግን በዚያ ጭለማ ውስጥ ስለእያንዳቸው አቀማመጥ እና ቀለም ይተነትንላቸው ያዘ። ‘እንኳን በቀን በጨለማ አጥርቶ የሚያይ!’ የሚል ስም አተረፈ። ይህ እራሱን ለመሪነት ያጨ ወፍ ‘የሌሊት ወፍ’ ነበር።
  እውነትም በጨለማ የሚካሄደውን ትግል እየመራ አይነኬ የመሰለውን የነጥቆ አደር ጭልፊቶች ስርዓት ገረሰሰው። ጭልፊቶቹ ሕዝብን በመበደልና  በወንጀል የተጥለቀለቁ ስለነበር የአዕዋፍቱን ፍርድ በመፍራት ተጠራርገው አንዲት ደሴት ላይ መሸጉ።
  የጨለማው ዘመን አክትሞ የብርሃን ቀን መጣ። ሆኖም የሌሊት ወፍ እንዳሰበው የነፃነቱ ማግሥት የአዕዋፍት መሪ መሆን አልቻለም። ስለዚህ አመጽ ቀስቅሶ በጠራራ ፀሐይ አድመኞቹን አዕዋፋት ሊመራ ቢሞክርም ተፈጥሯዊ ሁኔታው በሌሊት ለመመልከት የሚያስችል አልነበረምና ጥቂት እንደበረረ እሱ ከግንብ ሲላተም አምነው በተከተሉት ላይ የተለያየ ጉዳት ደረሰ።
  አዲሱ የአዕዋፍት መሪ ሆኖ የተሾመው እርግብ ቢሆንም በማይገመት ሁኔታ በሞገዱ ውስጥ ሆኖ ከአጋሮቹ ጋር መከረ። እንሰረው? እንምከረው ይሆን? ወዘተ? ተባባሉ። በአብላጫ ድምጽ ውሳኔም፤ ብዙሐኑ አዕዋፍት ባልተረዱበት ጥበብ የሌሊት ወፍን *የቁም እስረኛ አደረገው። ብዙ አዕዋፍት፣ የቅርብ ደጋፊዎቹ ሳይቀሩ ይህን ምስጢር አያውቁም!
  በእርግጥ… ጭልፊቶች ካሉበት ቦታ ሆነው በሽለላ አየሩን ቢንጡትም በተጨባጭ የቀራቸው ነገር ቢኖር ጩኸታቸውና ጭንቀታቸው ብቻ በመሆኑ የሌሊት ወፍ በአንዳንድ የቀድሞ ጆሮ ጠቢዎች አማካይነት ”ቋሚ ጠላትም ቋሚ ወዳጅም የለም” ለላከው የእባካችሁ እንተባበር መልዕክት አጥጋቢ መልስ ማግኘት አልቻለም። በሚያሳፍር ሁኔታ ታግሎ ለጣላቸው ጭልፊቶች “I stand with Hawk” የሚል ዘመቻ ሳይቀር ተቀላቅሏል።
  እየመሸ… እየነጋ…
Filed in: Amharic