>

ሰይጣን ለአመሉ ጥቅስ ይጠቅሳል (ከይኄይስ እውነቱ)

ሰይጣን ለአመሉ ጥቅስ ይጠቅሳል

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

በርትዕት (ኦርቶዶክስ) ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን (ርተቤክ) ታሪክ ዘመነ ሰማዕታት ተብሎ በሚታወቀው ጊዜ ከነበሩ አላውያን ነገሥታት አንዱ የሮሙ ዲዮቅልጥያኖስ ነበር፡፡ ይህ ፀረ-ቤተክርስቲያን ‹‹አብያተ ክርስቲያናት ይትዐጸዋ፤ አብያተ ጣዖታት ይትረኀዋ›› (ቤተክርስቲያኖች ይዘጉ፤ የጣዖታት ቤቶች ይከፈቱ) የሚል ዓዋጅ አስነግሮ ምእመናን በሰማዕትነት ያለቁበት፣ አብያተ ክርስቲያናት የተቃጠሉበት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳት የጠፉበት ለክርስቲያኖች የመከራ ጊዜ ነበር፡፡ ከሰማዕትነቱ የተረፉ ክርስቲያኖች ሥርዓተ አምልኳቸውን በግበበ ምድር (ዋሻ ውስጥ) ብቻ የሚፈጽሙበት ጊዜ ነበር፡፡ 

አፅራረ ቤተክርስቲያን በየዘመኑ ይነሳሉ፡፡ ዓለሙ ኹሉ ከሃይማኖት ፈቀቅ ባለበትና አልቦ እግዚአብሔር ባዮች በበዙበት በዚህ ዘመን ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያም ከውስጥም ከውጭም ከባድ ፈተና ገጥሟታል፡፡ ከውስጥ – ዓለምን ንቀው ወደ ገዳም እስከመሄድ የደረሱ ነገሥታት በተሰየሙበት መንበር – ወያኔ ኢሕአዴግ የተሰኘ የወንበዴ ቡድን ከዛሬ ሠላሳ ዓመት በፊት የኢትዮጵያን መንበረ ሥልጣን በጉልበት ተቈጣጥሮ  የኢትዮጵያን ርተቤክ እስከነሙሉ ሀብቷና ቅርሷ ለማጥፋት ምሎ ተገዝቶ ሲገዘግዛት ቈይቷል፡፡ የአገዛዙን ካድሬዎች ከዲቁና እስከ ጵጵስና ሰግስጎ በማስገባት፣ አንዳንዶችንም ለሥጋ ፍላጎታቸውና ለዘር ቈጠራ እንዲያድሩ በማድረግ፣ ጥቂት የማይባሉ ለፈረንጅ ባርነት ያደሩ መናፍቃን መፈንጫ በማድረግ ጭምር መሠረተ-እምነቷን እና ቀኖና ሥርዓቷን በእጅጉ እንዲሸረሸር አድርጓል፡፡ ምእመናን በዐሥራት፣ በሙዳየ ምጽዋትና በመባዕ መልክ የሰጡትን ገንዘብ፣ በገንዘብ የማይተመኑ ሀብቶችና ቅርሶቿን ሙልጭ አድርጎ ዘርፏል፡፡ 

የወያኔ ወራሽ የሆኑት ተረፈ-ወያኔዎች (ኦነግ/ኦሕዴድ) ደግሞ ምእመናንን እና ካህናትን በጠራራ ፀሐይ በመግደልና አብያተ ክርስቲያናትን በማቃጠል ድንቁርናና ዕብደታቸውን ከፍ አድርገው ግልጽ የጥፋት ዘመቻ እያደረጉባት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ኢትዮጵያውያን ነን ብለው የሚያምኑ ከሆነ ሊቁ የኔታ ሣኅለማርያም ተፈራ እንዳሉት የኢትዮጵያ ‹ነፍስ› የሆነችውን ቅድስት ቤክ ለማጥፋት ሌት ተቀን ባልደከሙም ነበር፡፡ ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በቀጥታ ቅኝ ግዛት ሊቈጣጠሩ ያልቻሏትን ኢትዮጵያ ‹ባለ ዘውድ ሪፐብሊካኖችን› በባንዳነት በመጠቀም – ኢትዮጵያን አዳክሞ ዝንተ ዓለም የነሱ ፍርፋሪ ለቃሚ ለማድረግ የጸጋው ግምጃ ቤት የሆነችውን ጥንታዊት፣ ታሪካዊት፣ ብሔራዊት ርተቤክንን ካጠፋን ሌላው ዕዳው ገብስ ነው ብለው በመነሳት – የእጅ አዙር ውጊያውን ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ ኢሕአዴግ የሚባለው ወራዳ አገዛዝ ሥልጣንን ለማስጠበቅ – ብሔራዊ ጥቅማችንን ሁሉ ለአሳዳሪዎቻቸው እጅ መንሻ አድርጎ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑ – ምን ያህል ርቀት እንደሚሄድ ፈጣሪው ወያኔ እና ወራሹ ኦሕዴድ/ብልጽግና አሳይተውናል፤ አሁንም እያየን ነው፡፡

ዛሬ በየመንደሩ የፈሉት ‹የጸሎት ኪዮስኮች› የገንዘብ ምንጫቸው ከየት እንደሆነ ላስተዋለ ብዙ ይናገራል፡፡ እዚህ ላይ አንባቢ እንዲገነዘብ የምሻው ከነዚህ ‹ኪዮስኮች› ጀርባ ያለውን የጥፋት ተልእኮና በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሰለባ የሆኑትን ‹አማኞች› ለማንሳት እንጂ ማንም ሰው ሲፈልግ ድንጋይ አለዝቦ ወይም እንጨት ጠርቦ የኔ ‹አማልክት› እነዚህ ናቸው ብሎ የማመን ምርጫና ነፃነቱ የራሱ መሆኑን ለመጋፋት አይደለም፡፡ ሀገረ ኢትዮጵያ ግን የጋራ ‹ቤተመቅደሳችን› ናት፡፡ ህልውናዋ የማያሳስበው ኹሉ ምርጫውን ጥፋቷን ከሚመኙላትና ከአስፈጻሚዎቹ ጋር አድርጓል፡፡ እሷ ከሌለች ቤተ እምነቶች የአምልኮት ሥርዓታቸውን በጋራ መፈጸም አይችሉም፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ርተቤክ የተጀመረው ነገ በሌሎች እንደሚቀጥል ለወያኔ ኢሕአዴግ ከአሳዳሪዎቹ የተሰጠው ተልእኮ እንደሆነ ከራሳቸው የውስጥ ሰዎች ሰምተናል፡፡ ወራሹ ኦነጋዊው ኦሕዴድም የዚሁ ተልእኮ ወራሽ ነው፡፡ 

ዛሬ ‹የሙሉ ዓለም› ፍልስምና (ግሎባላይዜሽን) ዓለምን በእምነት ረገድ መደዴ/‹አሕዛብ›/አረማዊ ማድረግ እንደሆነ እየታዘብን ነው፡፡ የሰው ልጅ ልኩን/ዐቅሙን አላውቅ ብሎ፣ ለእጁ ሥራ (ሥጋዊ ፍልስምና፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ ) ተገዝቶ፣ የነፃነት ወሰኑ ጠፍቶበት፣ ነፃ ፈቃዱንና ምርጫውን እንዴት መጠቀም እንዳለበት ግራ ተጋብቶ ጉልበተኞች የፈጠሩት ፍትሕና እኩልነት÷ ግብረገብና ሥነምግባር የጠፋበት ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ እንገኛለን፡፡ ይህን ሥርዓት ያጣ ዓለም፣ የተከሠተው ቸነፈር ልክ ያስገባው እንደሆነ በድኅረ ወረርሽኙ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ አዝማሚያውን ሳየው ግን ዓለም ለመማር ዝግጁ አይመስልም፡፡ የሥልጣንና የንዋይ ፍቅር ናላቸውን ያዞራቸው መምዕላዮች ከቸነፈሩ ለማትረፍ ሲሯሯጡ እየታየ ነው፡፡ ዓለሙ በጨንገር ሳይሆን በጊንጥ መገረፍን ለመጋበዝ ዳር ዳር እያለ ይመስላል፡፡

ነገርን ነገር እያነሳው ትንሽ ሸርተት አልኩ መሰል፡፡ ዋናው ጭብጤ የኢትዮጵያ ርተቤክ የገጠማት ፈተና ነው፡፡ ቤተክህነቱ ራሱን ሳያስተካክል ከነአደፍ ጉድፉ ምሕላ ዓውጇል፡፡ ምሕላው ባልከፋ እሱንም በሥነሥርዓት ማካሄድ አቅቶት (በቢሊየን የሚቈጠር ብር የሚዘረፍባት ተቋም የራሷን የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀጣይነት ባለው መልኩ በዐቅም ማጠናከር አለመቻሏ ያስተዛዝባል) ባገዛዙ ጣቢያዎች እጅ ወድቆ በጣቢያዎች ፍለጋ ባዝነናል፡፡ የቤተክህነቱን ‹ፖለቲከኞች› ያሳሰባቸው ምእመኑ ከቤተእግዚአብሔር መቅረቱ ሳይሆን የገቢ ምንጫቸው መጉደሉ መሆኑን እየታዘብን ነው፡፡ መንፈሳዊ ወኔ የሌለው የቤተክህነት አስተዳደር ቤተመንግሥት ከተቀመጡና ቤክ ላይ ከዘመቱ ከድዮቅልጥያኖስ ያልተናነሱ መምዕላዮች ጋር በዝምታ ተባብሮና ወረርሽኙን ተከልሎ አድባራትና ገዳማትን አዘግቷል፡፡ ቤክ መደበኛና የማይቋረጥ አገልግሎት አላት፡፡ ወደዚህች ምድር ስንመጣ የእግዚአብሔር ልጅነትን በመስጠት በ40እና በ80 ቀናችን በሥርዓተ ጥምቀት የምትቀበልን፣ ዐረፍተ ዘመናችን ሲገታ ደግሞ በጸሎተ ፍትሐት የምንሸኝባት ቅዱስ ሥፍራ ናት፡፡ 

ዜጎችን ከቤታቸው እያፈናቀለ መንገድ ላይ የሚወረውር አገዛዝ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ቅፅር ግቢ ፖሊስ አቁሞ ምእመናን ብቻ ሳይሆን ካህናትን አላስገባም ማለቱ ለዜጎች ደኅነነት ተጨንቆና ከእምነታቸው የበለጠ ዋስትና ሆኖ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ወረርሽኙንና ይህንንም ተከትሎ ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ከለላ አድርጎ ሸፍጥ እየሠራ መሆኑ ባስቸኳይ ጊዜ እንኳን (በወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥትም› ሆነ ይኸው ሰነድ ተቀብዬ የአገሪቱ የሕግ አካል አድርጌዋለሁ በሚለው ዓለም አቀፉ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ስምምነት) የማይደፈረውን በሕይወት የመኖር መብት በመተላለፍ በመዲናችን የሰው ሕይወት ማጥፋቱ ምስክር ነው፡፡ 

እኔን የገረመኝና ያሳዘነኝ የአገዛዙ ወጥነት ያለው ቤተክርስቲያኒቱን የማጥቃት፣ ቤተክህነቱን እና ምእመናኑን የመናቅ ተግባር ሳይሆን በቤተክህነቱና አንዳንድ መምህራን ነን በሚሉ ሰዎች ቤተክርስቲያን በአገዛዙ ውሳኔ የመዘጋቷን አግባብነት በቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅስ ድጋፍ ለመስጠትና ምእመኑም ይህንን እንዲቀበል የሄዱበት ርቀት ነው፡፡ ይህንን ድርጊት ጌታ 40 መዓልት 40 ሌሊት በገዳመ ቆሮንቶስ ጾምን ለመቀደስ በወረደ ጊዜ ሰይጣን ካቀረበለት በመጽሐፍ ጥቅስ ከተደገፈ ፈተና ነጥሎ ለማየት ይከብደኛል፡፡ ዓሣ በጾም ይበላል እያለ ለሆዱ ጥቅስ እንደሚያዘጋጅ ከንቱ ሰው ማለት ነው፡፡ በርካታ ምእመናን የሚገኙበትን ክብረ በዓላትን ብቻ አስቀርቶ የአዘቦት አገልግሎትን ሥርዓት አበጅቶ ምእመናን ማስተናገድ እየተቻለና ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትም ቅጽረ ግቢዎቻቸው አመቺ ሆኖ ሳለ ቤተክርስቲያንን መዝጋት የአገዛዙን ድፍረትና ሲዘጋም ዝም ብሎ መመልከት ወይም ልመና/ልምምጥ ውስጥ መግባት እውነተኛ እረኛ የመጥፋት ምልክት ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ አሜሪካ ወይም አውሮጳ አይደለችም፡፡  እኛ ‹መንግሥትም ሕግም› የለንም፡፡ አገዛዙ ፈረንጅ አሳዳሪዎቹ የሚነግሩትን ሁሉ እኛ ላይ እያመጣ የሚጭንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ብንራብ ብንጠማ ዞር ብሎ የሚያየን የለም፡፡ ብቸኛ አለኝታችንና መመኪያችን እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ መድኃኒቴ ቤተክርስቲያን ነች የሚለውን ሕዝብ በጥንቃቄ በሥርዓት አድርጉት ይባላል እንጂ እንዴት ከመድኃኒቱ ታቆራርጠዋልህ?

ጊዜው ትንሽ ራቅ ቢልም የቤተክህነቱን አስተዳደር በሚመለከት አንድ ጽሑፌ (https://www.ethioreference.com/archives/9549) እንዴት የኢትዮጵያ ርተቤክ ከ1600 ዘመን በላይ ስትለምን ትኖራለች? የሚል በውስጤ ሲጉላላ የነበረ ጥያቄ አንስቼ ነበር፡፡ በገንዘብ፣ በሰው ሀብትና በንብረት አስተዳደር በኩል ያላት ዝርክርክነትና ዘመኑን ያለመዋጀት አሁንም ጭምር መሠረታዊ ችግር ነው፤ እንደ ጥንታዊነቷ በብዛትም ሆነ በጥራት ጎልቶ የሚታይ የልማት ሥራ አላት ወይ? ምስካየ ኅዙናን (የድሆች መጠጊያ) የተባለች ቤክ ከራሷ አልፋ ስንት ኢትዮጵያውያንን ከድህነት አላቀቀች? ለስንቱ የሥራ ዕድል ፈጠረች? ዛሬ በከተሞች ያሉ አብያተክርስቲያናት ዙሪያ የሚታየው የንግድ ሥራና ሕንፃ የቤክንን መንፈሳዊ ድባብ አጥፍቶ ምእመናን ከፈጣሪያቸው ጋር በጽሞና እንዳይነጋገሩ የኹከትና ግርግር ቦታ መስሏል፡፡ ይሄም ንግድ የዘራፊዎች ሲሳይ ሆነ እንጂ ራሷን አላስቻላትም፡፡ ባለቤቱ በመዋዕለ ሥጋዌው ቤቴን የቀማኞችና የወንበዶች ዋሻ፤ የሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ መለወጫ አደረጋችሁት እንዳለ፡፡ ዛሬ ቤተክርስቲያን ‹የሚያገለገል› አስተዳዳሪ ሆነ መምህር፣ ሰሞነኛም ሆነ መዘምር፣ የተማረውም ሆነ ‹ነፋስ ጋራጁ› (አውደልዳዩ)፣ ሕጋዊው ካህንም ሆነ መነኩሴው (ገብርኄር/ታማኝና መንፈሳዊ አገልጋይ ባለቤቱ ከሚያውቃቸውና በጣት ከሚቈጠሩ በስተቀር በመጥፋታቸው) በምን ተግባር እንደተሠማራ ኹሉን ለሚያየው ፈጣሪ ራሱን ያስፈትሽ? እኛ ምእመናንም እንደዚሁ፡፡ ሊቃውንተ ቤክ እንደሚሉት ኹላችንም እንደ ፈረስ ጆሮ እንደ ሰላጢን/ጦር ጕረሮ ተካክለን በድለናልና፡፡

የክርስቶስ ልብሶች፣ የቤተክርስቲያን ገንዘቦች፣ ጌጥና ፈርጦች ምእመናን ናቸውና አሁንም ቤተክህነቱ መንፈሳውያን መሪዎች ካላችሁ ከዘመኑ ዲዮቅልጥያኖሶች ፈቃድ ሳትሹ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ኢትዮጵያዊ በጉያዋ ያቀፈች ቤተክርስቲያን ይዛችኋል፡፡ ለአላውያንና መናፍቃን መንበርከኩን አቁማችሁ ባስቸኳይ ወደ መደበኛ አገልግሎቷ እንድትገባ ማድረግ ይኖርባችኋል፡፡ በእናንተ ድክመት የባዘነውን ‹መንጋ› ወደ ‹በረት› ቤክ አሁኑኑ መልሱት፡፡

Filed in: Amharic