>
11:54 am - Sunday December 4, 2022

የእስክንድርን የፖለቲካ ስብዕና ማጥፋት ...!? (መሀመድ አሊ መሀመድ)  

የእስክንድርን የፖለቲካ ስብዕና ማጥፋት …!?

መሀመድ አሊ መሀመድ  
ይህች ትናንትም የነበረችና የተለመደች ጨዋታ ናት። ተጫዋቾቹ ዛሬም አሉ። ደግሞም ከነሱ የተሻሉ ብልጣ ብልጦችን አፍርተዋል። ግርርር ብለው ይነሱና እስክንድር ላይ ይዘምታሉ። ሰውዬው “ጤንነቱ ያጠራጥራል ህክምና ያስፈልገዋል” በማለትም ያሟርታሉ። “ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል” የሚለውን ብሂል በተግባር እያረጋገጡት ነው። ትናንት “ልደቱ ካሃዲ ነው” የሚለውን ስሞታ በስፋትና በቀጣይነት በማነብነብ አንድን ትንታግ ፖለቲከኛ ከጨዋታ ውጭ ማድረግ ችለዋል። በርግጥ በዚያ ውስጥ እስክንድርም ነበረበት። እነሆ “በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም” እንዲሉ ነውና ዛሬ ደግሞ የእሱ ተራ ነው።
እስክንድር ነጋ የቁርጥ ቀን ወዳጄ ነው። ይሁንና በፖለቲካ አመለካከት የምንለያይባቸው ጉዳዮች ነበሩ። ይህን ያኔም ዝናው ጣራ በነካበት በግፍ እስር ላይ እያለና ሲፈታምተናግሬዋለሁ። እኔና እስክንድር በአንዳንድ ጉዳዮች ዙሪያ ስንነጋገር ዱላ ቀረሽ ጭቅጭቅ ውስጥ የምንገባበት ጊዜ ነበር። ለዚህ የጋራ ወዳጆቻችን ፋሲል ፀጋዬና ብርሃኑ ደቦጭ ምስክር ሊሆኑ ይችላሉ።
እስክንድር ደረቅ ነው። የሆነ ነገር ከያዘ አይመለስም። ደግሞ የምሩን ነው። ማስመሰል አያውቅም። ስሜቱን መደበቅም አይችልበትም። ያመነበትን ነገር ይዞ ፊት ለፊት ይጋፈጣል።በሰሜት ሲናገር የደም ስሮቹ ይገታተራሉ። ሲበዛ እልኸኛ ነው። ባመነበት ነገር በምክንያትና የምሩን ይሞግታል። አንዳንዴ አንፃራዊ ቢሆንም እስክንድር እውነት ይዞ ነው የሚከራከረው። ደግሞም መረጃ የመሰብሰብ ብቃት አለው። የመረጃ ምንጩም ሰፊ ነው።
ይሁንና እስክንድር ቅን ነው። ሲበዛ ትሁትና ሰው አክባሪ ነው። እናም አዛኝና ሩህሩህ ነው። የሰው ችግር ሳይነገረው ይገባዋል። የምርና ከልብ ይቆረቆራል። ደግሞም ቸርና ያለውን ተካፍሎ መብላት የሚወድ ሰው ነው። ከፖለቲካ ጭቅጭቃችን በመለስ እስክንድር ጋር ጥሩ የጓደኝነት ጊዜ ነበረን። እውነቱን ለመናገር እስክንድር በግሉ ጥሩ ሰብዕና ያለው ሰው ነው።
ፖለቲካው ላይ ግን አጉል የዋህነትና የምላስ ወለምታ ያጠቃዋል። ይህን ራሱም ከLTV ጋዜጠኛዋ ቤተልሔም ታፈሰ ጋር በነበረው ቃለ-ምልልስ አምኗል። ቤቲ እሱን ለማዋረድ ተልዕኮ የተሰጣት፣ የእስክንድር ተቀናቃኞች የራስጌ ዱላ ነበር የሆነችበት። እናም እስክንድር በዚያ ቃለ-ምልልስ የሰው መኝታ ቤት ዘሎ እንደገባ ሰው ነው የተደበደበው። እሱ ተለሳልሶ በመቅረብ ልጅቷን ሊያለዝባት ሞክሮ ነበር። እሷ ግን ሆን ብላ ቃለ-ምልልሱ ወደ ተራ ጭቅጭቅ እንዲያመራና ያልተፈለገ አምባጓሮ እንዲፈጠር አደረገች። ከጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር ባፈነገጠ አኳኋን ልታዋርደው ተዘጋጅታ ነበር ወደ ስቱዲዮዋ የጠራችው። ከመሬት ተነስታ ቱግ አለችበት። ፊቱን በጥፍሯ ልትቧጥጠው ምንም አልቀራት። ያን አድርጋ ግን በቴሌቪዥን ጣቢያው የተለመደ ሥራዋን ቀጠለች። ማንም የገሰፃት ያለ አይመስልም። እንዳውም ተልዕኮዋን በአግባቡ ስለተወጣች “አበጀሽ” ሳትባል አትቀርም። እስክንድር የረባ የፖለቲካ አጀንዳ የሌለው “ጀዝባ” መሆኑን አሳይታለች።
በርግጥ ተቀናቃኞቹ እንደሚሉት፣ እስክንድ “ጀዝባ” ነው? በፍፁም፤ ይህን እነሱም አሳምረው ያውቃሉ። ይልቁንም ዕረፍት የማይሰጥ የእግር አሳት ነው የሆነባቸው። ድንገት ተነስቶ ያልተጠበቀ ራስ ምታት ፈጠረባቸው። ስለሆነም በመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥባቸውን አዳራሾች በመከልከል ከህዝብ ጋር እንዳይገናኝ መሰናክል ፈጠሩበት። ራሱ በተከራየው ቢሮ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሚሰጥበት ወቅትም ነውጠኞችን በመላክ ሆን ብለው አስረበሹት። ያም አልበቃ ብሎ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ልዩ ኃይል አዘመቱበት። እነ “ማሜ ማሜ” በጥላቻ ተነሳስተው እስክንድርን ፍለጋ በሞተር ሳይክል ከተማውን ሲያስሱ ታይተዋል። ድርጊታቸው በግልፅ የሚታይ ወንጀል ቢሆንም ማንም የጠየቃቸው አልነበረም። ቢሆንም እስክንድር በዚህም አልተበገረም።
ስለሆነም ተቀናቃኞቹ ሌላ መላ መዘየድ ነበረባቸው። የእስክንድርን አጀንዳዎች ማጣጣልና በግል ሰብዕናው ላይ መሳለቅ! ለዚህ ማህበራዊ ሚዲያው አመች መድረክ ሆኖ ተገኝቷል። በእስክንድር ላይ ሊዘምት የሚችል ግሪሳም ተፈጥሯል። አይበጅም ባይ በሌለበት እንደጉድ ሲረባረቡበት ይታያል። እንዳውም የተሻለ ከፍታ ላይ የምናስቀምጣቸው ወዳጆቻችን ሳይቀር እስክንድርን ከነማሜ ማሜ፣ የ8ኛው ሺህ ንጉስ ነኝ ከሚለው ሰውና ከነእስራኤል ዳንሳ ጋር ሲያሰልፉት ማዬት በጣም የሚያስገርምና የሚያስተዛዝብም ነው። ከዚህም ባለፈ በቅርቡ በመታሰሩ እንዳንዶች ጮቤ ሲረግጡና በሰብዕናው ላይ ሲሳለቁ “ተው ነውር ነው” በማለታችን፣ የዘመኑ አፈ-ቀላጤዎች “ለምን ከኤጄቶው መሪ ጋር ባንድ ሚዛን ላይ አላስቀመጥከውም?” በሚል እኛንም አብረው ሊወቅጡን ተረባርበውብናል።
እስክንድር ደግሞ የረባ ሰው ከጎኑ ያለ አይመስልም። እንዳውም አንዳንዶቹ liability ሳይሆኑበት አልቀሩም። እነዚህን በጊዜ avoid ቢያደርጋቸው ኖሮ ግራ ቀኙን ማዬትና ስህተቶቹንም በራሱ ማረም ይችል ነበር። እስክንድር ሰው ነውና ይሳሳታል። ደግሞስ ሰው ሆኖ የማይሳሳት ማን አለ? የማይሳሳተው ምንም የማይሰራና በአጉል ጥንቃቄ ተሸብቦ የሚኖር ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ እስክንድር “ጀዝባ” አይደለም። እስክንድር ለእውነት የቆመና ብዙ ዋጋ የከፈለ ሰው ነው!!
Filed in: Amharic