>
5:13 pm - Saturday April 18, 9372

ይድረስ... ለሥርዓቱ ደጋፊም ነቃፊም ተዋናዮች…! መጥኔ! መጥኔ! (አሰፋ ሀይሉ)

ይድረስ… ለሥርዓቱ ደጋፊም ነቃፊም ተዋናዮች…! መጥኔ! መጥኔ!

አሰፋ ሀይሉ
 
* ‹‹ጊዜውስ አይቀር ማለፉ
እርሱ መች እንደሰው ክፉ!››
 
* “እውነት ትዘግይ እንጂ ጊዜዋን ጠብቃ መውጣቷ አይቀርም! ለዘለዓለም የኖረ የግፍ ሥርዓት፣ ለዘለዓለም የኖሩ የግፍ ሥርዓት ተዋንያን በምድር ታይተው አይታወቁምና!”
የወያኔ-ኢህአዴግ ምርጫ ቦርድ ኮሮጆ ገልብጦ በሕዝብ ድምጽ ሲቆምር፣ ይህን ወራዳ ተግባር በቪዲዮ ጭምር ማስረጃ የያዙት የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዚደንት የነበሩት ግለሰብ፣ ወደ አሜሪካ ሄደው ጥገኝነት ጠይቀዋል፣ ለኮንግረስ ማስረጃቸውን አቅርበው ለአሜሪካኖች የወያኔን መንግሥት እንዳሻቸው የሚያዙበትን መሣሪያ አስረክበዋቸዋል! አሁንም እኚያ ሰው እና ባልደረቦቻቸው በሕይወት አሉ፡፡ ነፃ መድረክና ነፃ ሥፍራ ቢያገኙ እውነቱን ይናገራሉ፡፡ የአሁኖቹም ሆኑ የቀድሞዎቹ የሕዝብ ተወካዮች ተብዬዎች በፓርላማ አዳራሽ ጉብ ብለው የተገኙት – በዚህ መሰል ሰሜን ኮርያዊ የኮሮጆ ሸፍጥ ነው! ይሄ እኮ ዓለም ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ እና አስር ጊዜ ፓርላማ፣ ፓርላማ የሚባልለት – ስለየትኛው ፓርላማ ነው? ያ የምርጫ ኮሮጆ እየተደፋለት ጉብ ስላለው ፓርላማ ነው? ወይስ ሌላ ፓርላማ አለ?
‹‹ደል›› ይላሉ ፈረንጆች ሲናደዱ፡፡ ‹ደል› ማለት በድን ወይ ድንጋይ ወይ አርሶ አርሶ  እንዳረጀ በሬ ‹ሙትቻ› ማለት ነው፡፡ ‹ደል› በሆኑ – በእንስሳት ጥናት ፕሮፌሰርነት እንደ ድርጎ በፓርላማ እንደ ተሰጣቸው እንደእነ መርጋ በቃና በመሳሰሉ – ‹ደል› በሆኑ – ህሊናቢሶች ሲመራና የውሸትና የዝርፊያ ፋብሪካ ሆኖ የከረመ የምርጫ ቦርድ አይደለም እንዴ ይዘን የኖርነው? ያ የምርጫ ቦርድ አይደለም እንዴ – የኢህአዴግን የፓርቲ ተላላኪዎች ‹‹የፓርላማ አባላት›› የሚል የአጨብጫቢነት ማዕረግ እየቀባ – ህዝብ ሳይመርጣቸው – በሰውም በእግዜርም ሳይመረጡ – የፓርላማ አባል እገሌ እገሊት እየተባሉ – ሥርዓቱን ህጋዊ ቅቡልነት ያለው ለማስመሰል – ከዓመት ዓመት በዓይናችን ላይ ፍጥጥ ያለ የድርቅና ድራማ ሲሰሩ የኖሩት? እና ስለ የትኛው የተወካዮች ምክር ቤት ነው የምናወራው? ስለየትኛው ፓርላማ ምርጫ ነው አፍን ሞልቶ መናገር የሚቻለው?
አሁን ከጃዋር ጋር ገጥሞ – በወረደ ጎጠኛ እንቶፈንቶ ውስጥ የተዘፈቀው – እና ያኔ እንደ እነ መርጋ በቃና ለሥርዓቱ ስላላደገደገ የፕሮፌሰርነት ማዕረጉን ተነፍጎ የኖረው ዶ/ር መረራ በአደባባይ ተናግሮት ጨርሶታል እኮ – ያውም በሰው በላዎቹ በእነ በረከት ስምዖንና ቅጥረኞቻቸው ፊት፡፡ መረራ ምንድነው ያላቸው፡- ‹‹እስቲ ኢህአዴግ ምርጫ ቦርድንና ጠብመንጃዋን ትጣልና፣ በነፃ ተወዳድራ ሕዝብ ከመረጣት፣ በበኩሌ ከአሁን በኋላ ለመቶ ዓመት ኢትዮጵያን እንድትገዛ እፈርምላታለሁ!›› ብሎ እኮ የጨረሰው ጉዳይ ነው – ዶ/ር መረራ! እና ያኔ እንዲህ እንደ መረራ ህሊና ያለው ሰው በአደባባይ የተናገረውን እውነት – አሁን ሰዉ ሁሉ እንዲህ አስመሳይና ህሊና-ቢስ ሆኖ – ስለየትኛው ህጋዊ ተመራጭ፣ ስለየትኛው ቅቡል ፓርላማ፣ ስለየትኛው ሃቅ ነው – ቱልቱላ የሚነፋው? ህሊናና እውነትን የሙጥኝ ማለት ነውር ሆነ፣ ቀረ ማለት ነው? ወይስ አለማወቅ? ወይስ ህሊናችንን ሆዳችን ውስጥ ቀብረን?
የሆነ ሆኖ – ይሄኛውን ፓርላማ ተብዬ ጨምሮ – በየትኛው ተዓማኒ ድምፅና ምርጫ ተመርጠው ነው እንደ ትልቅ የተከበረ ዲሞክራሲያዊ አካል የሚቆጠሩት? ድምፅ እንደ ብፌ እየተዘረፈለት በምልመላ ፓርላማ በገቡ አባላት የተሞለው – እና 100 ፐርሰንት ኢህአዴግ አሸነፍኩ ብሎ የተቆጣጠረው – እና ሕዝብ እንደወከለው ቢጤ ራሱን ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት›› ብሎ የሚጠራ ‹‹ፌክ›› የሆነ ፓርላማ አይደለም እንዴ አሁንስ በድራማው ወንበር ላይ ተጎልቶ ያለው? እና – ከመቼ ወዲህ ነው ህጋዊ ቅቡልነት አግኝቶ የሚያውቀው? እና አሁን ጊዜው ስላለፈበት ህጋዊ ቅቡልነቱን ያጣል የሚባለው? ቀድሞ ነገር ከየት ያመጣውን ህጋዊ ቅቡልነት? በጠብመንጃ ኃይል ያገኘውን? ወይስ በማን-አለብኝነት 100 ፐርሰንት አሸነፍኩ ብሎ ዓይኑን በጨው አጥቦ በመገገም የቀረበውን? ስለየትኛው ፓርላማና ከየት ስላገኘው ሌጂትሜሲ (ህጋዊ ቅቡልነት) ነው የምንበጠረቀው?
ደሞ የሚገርመው እኮ ‹‹ፓርላማ፣ ፓርላማ… የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት.. ምናምን›› እያለ… ስለ ደህና ነገር እንደሚናገር ቢጤ አፉን ሞልቶ የሚበጠረቀው ሰው መብዛቱ ብቻ እኮ አይደለም! ይሄ ፌክ እና በፓርቲ ተላላኪ ሎሌዎች የተሞላው ፓርላማ – የሆነ የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን የሚመለከት – የመንግሥትን ህጋዊ ቅቡልነት የሚመለከት ጥያቄ ሲያጋጥመው – ወደ ‹‹ፌዴሬሽን ምክር ቤት›› ህገመንግሥታዊ ትርጉም እንዲሰጥበት ጉዳዩን መራው… ምናምን እየተባለ የሚደሰኮረው ነገር እኮ ነው ይበልጥ በሳቅ ፍርስስስ የሚያደርገው! እንዴ! ምን ነክቶናል!? የፌዴሬሽን ምክር ቤት ራሱ ማን ነውና ነው – ከፌኩ ፓርላማ ተሽሎ – ትርጉም ሰጪና ፍትሃዊ ዳኛ ሆኖ የተገኘው?
የፌዴሬሽን ምክርቤት አባላት እነማን ናቸው ለመሆኑ? ከማን ከማን የተውጣጣ አካል ነው ይሄ ፌዴሬሽን ምክርቤት የሚባለው? እያንዳንዱ የጎጠኛውን ሥርዓት የመሰረቱት – እና እያንዳንዱን የጎሳ ክልል የተቆጣጠሩት የጎሳ ፓርቲዎች – በቀጥታ ጉዳያችንን ፈጽሙልን አስፈጽሙልን ብለው የሚልኳቸው ተላላኪ ተወካዮች አይደሉም እንዴ – የፌዴሬሽን ምክርቤት አባላት? የአንድ ሠፈር ሰዎች ተጠራርተው ክልልነት የተሰጣቸው ‹‹የሐረሪ›› ክልል ተላላኪ፣ የዘረኛው ሥርዓት አፄ የወያኔ ተላላኪ፣ ከወያኔ ጋር ተለጣፊ ሆኖ የገዛ ወገኑን እየወጋ በወያኔ ታዝሎ ‹‹የአማራ›› ክልልን የተቆጣጠረው የብአዴን ተላላኪ፣ ከቀድሞ የደርግ ምርኮኛ ወታደሮች ተውጣጥቶ የኦሮሞን ሕዝብ በኦሮሞ አማካይነት ለመግዛት በወያኔ የተፈጠረው የኦህዴድ ተላላኪ፣…
…ብዙ ቤር-ቤረሰቦችና ጎጦች በአንድ የአቅጣጫ ጠቋሚ ቃል ተጨፍልቀው የወያኔ እና ሌላ ቀርቶ የእነ በረከትና አዲሱ ብአዴን ተላላኪዎች ሆነው ደቡብ ኢትዮጵያን በጎሳ ሥርዓት ሰጥ ለጥ አድርገው ሲገዙ የኖሩት የደኢህዴን ተላላኪ፣ ሁሌ በኢህአዴግ ልጓም ሥር ሆነው አጋር ተብለው በታዛዥነት የኖሩት የእነ አፋር ፓርቲ ተላላኪ፣ የሶማሊ የኢሶዴፓ ተላላኪ፣ በተላላኪ መዓት የተሞላ – አዲስአበባ ሄደው ፖለቲካችንን ያውሩልን ተብለው በየፓርቲው ተመልምለው የተላኩና – ካስፈለገም ዝንፍ ሲሉ የሚፈነገሉ – የፖለቲካ ተጠቃሚዎችና ተላላኪዎች – ከእነዚህ የየክልሉ የጎሰኛ ፓርቲዎች ተላላኪዎች ተውጣጥቶ የተመሰረተ የፓርቲ ተላላኪዎች ስብስብ ነው – የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚባለው አቅመ-ቢስ አካል! ያ መለስ ዜናዊ እንኳ – የአቅም ማነስ ያለበት፣ ብቃትም የሌለው ብሎ የወረፈው – ለወያኔም ራሱ አንሶበት የተገኘ – ከፌኩ ፓርላማም ያነሰ የወረደ ሚና የሚጫወት – ደቃቃ የተላላኪዎች ስብስብ አካል ነው – ይሄ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚባለው!
እና ስለየትኛው ፓርላማ፣ ስለየትኛው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ስለየትኛው ህገመንግሥት፣ ስለየትኛው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው የምናወራው? የቱን እና ምኑን ነው የምንተረጉመውና የምናስተረጉመው? ዛሬ ላይ አሉን የምንላቸው የሕዝብ ወገንተኝነት ያላቸው ፓርቲዎችና ግለሰቦች፣ አዋቂዎችና አላዋቂዎች ጭምር – በሚያሳዝንና በሚያስተዛዝብ መልኩ የዚህ በዘረኞች፣ ለዘረኞች እንዲመች ተደርጎ የተቀረፀ ሥርዓት ግንባር ቀደም ተዋንያን ሆነው ትወናቸውን በያቅጣጫው በትጋት ሲያከናውኑ ማየት – እጅግ ያሳፍራል! አንገት ያሰብራል!
አንድ እንኳ ህሊና ያለው ፖለቲከኛ እንዴት ይጠፋል? አንድ እንኳ ስለ እውነት የሚቆም፣ አንድ እንኳ ይሄ ዘረኛና አድሎአዊ ሥርዓት መፈራረስ ነው ያለበት የሚል፣ አንድ እንኳ የዚህ ፓርላማ ቅቡልነት የመነጨው ከተገለበጠ ኮሮጆ ነው – ብሎ በአደባባይ የሚቆም የህሊና ሰው በሀገር እንዴት ይጠፋል!? እንዴት – ደጋፊውም ነቃፊውም – ሁሉም ያው አንድ – የአንድ የበሰበሰ ሥርዓት ተዋናይ ሆኖ ይገኛል!? ያሳዝናል በእውነት – ህሊና ከሀገር ሲሰወር! ህሊና ለእውነት ሲታወር! እንዲህ እውነት መግቢያ መውጫ አጥታ በለፍላፊዎችና አውቃለሁ ባይ ተቦጥራቂዎች ጩኸትና ትንተና ሀገር ምድሩ ሲሞላ!
‹‹ፊደላውያን!›› ነበር ያሏቸው ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ የዘንድሮዎቹን ያገራችንን ልሂቃን ነን ባዮች፡፡ ‹‹አልፋቤቲሺያንስ!››፡፡ መለፍለፍ ብቻ! አርቲ ቡርቲ መቀባጠር ብቻ ሆኗል የአዋቂነት ፍቺው! ‹‹ደብተራዊ ፖለቲካዊ ምሁራዊ ባህል!›› ነገሠ፡፡ እውነት እና ለእውነት የሚታገል ጠፋ! እውነትም ፊደላውያን! ፊደላውያን ደብተሮች ብቻ!
በ60ዎቹ የአብዮት መባቻ ወቅት – ምሁር ሁሉ – አቃፊውም ነቃፊውም – ሁሉም ህሊናውን ኋላ ኪሱ ወሽቆ ባደባባይ በዚህ በዚያ እያለ ሲተረተር፣ ሲተረተር፣ ሲተረተር… ማብቂያ የሌለው ‹‹ስልቻ ቀልቀሎ›› ሲሆንበት ጊዜ – በብዕር ስሙ ‹‹ገሞራው›› እየተባለ የሚታወቀው ገጣሚ ኃይሉ ገብረዮሐንስ – የዘመኑን ደጋፊም፣ ነቃፊም እንዲህ ሲል ፍርጥ አድርጎ በግጥሙ ገልጿቸው ነበረ፡-
‹‹ቀልቀሎ ስልቻ – ስልቻ ቀልቀሎ
ማንን ይመርጡታል – ማን ከማን ተሽሎ?
ስልቻ ቀልቀሎ – ቀልቀሎ ስልቻ
ምን ደህና አለበት – ሁሉም አራሙቻ!››
ወያኔ ‹‹ለምን በድፍረት ተናገርከኝ›› ብሎ ጀርባው እስኪላጥ ገርፎ እንደለቀቀው የሚነገረው – ፋሲል ደመወዝ የተባለው ልበ ሙሉው ጎንደሬ የባህል አቀንቃኝ – ይህን አሁን ተርጓሚዎችና አስተርጓሚዎች፣ ተንታኞችና አስተንታኞች የተሰለፉለትን ይህን ግፈኛ የዘረኝነት ሥርዓት – በአንድ ወሳኝ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበረ በዜማ ስንኞች የገለፀው፡-
‹‹ዳኛውም ዝንጀሮ – መፋረጃው ገደል
እምን ላይ ተሁኖ – ይነገራል በደል››
እውነቱን ነው፡፡ ዳኛውና መጋኛው አንድ በሆነበት ሥርዓት፡፡ የአካዳሚክ ማዕረግን ለተላላኪነት አገልግሎት ድርጎ አድርጎ የሚከፍል የእነ መርጋ በቃና ዘራፊ ምርጫ ቦርድ፡፡ በዚያ ምርጫ ቦርድ ኮሮጆ እየተገለበጠለት የፓርላማን መቀመጫ 100 ፐርሰንት ተቆጣጥሬያለሁ የሚል ባለጠብመንጃ ዘረኛ ቡድን ገዢ ፓርቲ ሆኖ በአደባባይ ራሱን የሚያነግሥበት ሥርዓት፡፡ ያ ኮሮጆ ገልብጦ ፓርላማን የተቆጣጠረ ያፈጠጠ ያገጠጠ የጎሰኞች ኃይል – አብላጫ መቀመጫ አግኝቼያለሁ – መንግሥት እመሰርታለሁ ብሎ – ራሱ የጠቅላይ ሚኒስትር የሚሾምበት፣ ያ ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ የመንግሥት ሚኒስትሮችን እጩ አቀረብኩ ብሎ ለዚያው ኮሮጆ ገልብጦ ለሾመው ፓርላማ አፅድቁልኝ ብሎ የሚሾምበት ያፈጠጠጠ የፌክ ትያትር የሚከወንበት ሥርዓት፡፡ ይሄው ነው ሥርዓቱ!
ህገመንግስቱ ተጣሰብኝ ስትል – ህገመንግሥቱን ተርጉምልኝ ተብሎ የሚቀርብለት – ከጎሰኞቹ የተላኩ ልፍስፍስ የፓርቲ ተላላኪዎች የተሰበሰቡበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚል ስም ተሰጥቶት በስላቅ እያሽካካ የሚጠብቅህ ሥርዓት፡፡ በዚሁ በኮሮጆ ገልባጭ ፓርላማ የሚሾሙ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች – በሥርዓቱ ዓይን ስትመጣ – በፍትህ ስም ዓይንህን አውጥተው የሚመልሱበት ሥርዓት! ይሄ የተደራጁ ዘረኞች – በህግ ሥም – በህገመንግሥት ስም – በሥርዓት ስም – ያለማንም ከልካይ – እንዳሻቸው – በልዩ ልዩ ስም ራሳቸውን እየጠሩ – አንዳቸው ለሌላኛቸው እየተቀባበሉህ በነፍሰ ስጋህ የሚጫወቱበት – ህዝብን በነፍሱ የሚጫወቱበት – ዳኛውም ዝንጀሮ – መፋረጃውም ገደል – ሁሉም ያው ራሱ አንዱን – አንዱም ሁሉንም የሆነበት አፍና አፍንጫው የማይለይ አንድ የውንብድና ሥርዓት – ቀልቀሎውም ስልቻ፣ ስልቻውም ቀልቀሎ የሆነው – ይሄው የግፈኞች፣ የዘረኞች፣ የባለ ጠብመንጃዎችና የአምባገነኖች ሥርዓት –  ይሄው ነው ሥርዓቱ!
እና አሁን ደርሶ ዲሞክራሲ ኖሮን እንደሚያውቅና እንዳለን ሁሉ – ልክ ዲሞክራሲ እንደነገሰበት ልዩነትን እንደሚያስተናግድ ፍትሃዊ ሥርዓት ሁሉ – ልክ ዲሞክራሲያዊ ህገመንግሥት ባለበት ሀገር ውስጥ እየኖርን እንዳለን በማስመሰል – ልክ ዲሞክራሲያዊ አካል ተብሎ ሊጠራ የሚበቃ ሕዝብ ያመነውና የመረጠው አንዳች አካል ያለን ለማስመሰል – የሥርዓቱ ተጠቃሚ ደብተራዊ ፖለቲካዊ ምሁሮች – የዘመናችን የለየላቸው ፊደላውያን ‹አልፋቤቲሺያንስ› – አሁን ልክ በትያትር ላይ ‹‹አንታጎኒስት›› እና ‹‹ፕሮታጎኒስት›› ብለህ በተቃራኒ አቅጣጫ እንደምታሰልፋቸው የምናቡ ዓለም ገጸባህርያት ሁሉ – ተቃራኒ ጎራ ከፍለው – ሲለፋለፉ – ትንተና ሲያስተነትኑ – ህገመንግሥቱን ሲያጣቅሱ – ስለ ፓርላማው ሲተንትኑ – ስለ ፌዴሬሽን ትርጉም ሲጠርቁ – ይህን ሁሉ የትወና ጉድ የምትታደምበትን ያሁኑን አስቂኝም አሳዛኝም የዳንቴ ኮሜዲ የመሰለ እውነተኛ የአደባባይ ትወናና ለሥርዓቱ አለሁ ባይነት የምታይበትን – ይህን ያሁኑን ጊዜ ስትመለከት – በቃ… በሃፍረት፣ እና በሀዘን፣ እና እጅግ ከፍ ባለ ግርምት ብዛት… አንገትህን ከመድፋት በቀር ምን ማድረግ… ወይ ምን ማለት ትችላለህ?
መጥኔ – አልነበር ያለው ለሀቅ፣ ለህዝብ፣ ለፍትህ ቆሞ – አንድም ሰው ከጎኑ ያልቆመለትና ብቻውን ያሰቀለው ምስኪኑ ጄ/ል መንግሥቱ ነዋይ?! እውነቱን ነው! መጥኔ! መጥኔ! መጥኔ የግፍ ሥርዓቱን የግፍ ወንጌሎችና የትወና ተቋማት እያጣቀሳችሁ እንጀራችሁን በፍትህና በእውነት እጦት በሚሰቃየው ሕዝብ ላይ ተቀምጣችሁ ለምትጋግሩ እናንት የግፍ ትያትር ተዋናዮች! መጥኔ! ይብላኝ ለእናንተ! እውነት ትዘግይ እንጂ ጊዜዋን ጠብቃ መውጣቷ አይቀርም! ለዘለዓለም የኖረ የግፍ ሥርዓት፣ ለዘለዓለም የኖሩ የግፍ ሥርዓት ተዋንያን በምድር ታይተው አይታወቁምና – ይሄ የምትለፈልፉለት፣ የምታጣቅሱት፣ የምትተነትኑት፣ የምትተረጉሙት፣ የምታስተረጉሙት፣ የምትሟገቱለት የግፍ ሥርዓትም፣ እናንተም የግፍ ተዋንያኑም፣ እኛም ሁላችንም በጊዜ ሂደት መክሰማችን፣ ማለፋችን አይቀርም መቼም! ጊዜ ያልፍና – ለመተዛዘብ ያብቃን! የሚታዘብ ህሊና ያለው ትውልድ ይፍጠርባችሁ! መጥኔ ለናንተ!
‹‹ጊዜውስ አይቀር ማለፉ
እርሱ መች እንደሰው ክፉ!››
Filed in: Amharic