>

በአክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች ዘንድ የተገፉትና የተረሱት አፍሪካዊው የጦር ጀነራል፣ ኢትዮጵያዊ፣ አርበኛ ሌፍተናት ጀነራል ጃጋማ ኬሎ፤ (ተረፈ ወርቁ)

በአክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች ዘንድ የተገፉትና የተረሱት አፍሪካዊው የጦር ጀነራል፣ ኢትዮጵያዊ፣ አርበኛ ሌፍተናት ጀነራል ጃጋማ ኬሎ፤

 

በተረፈ ወርቁ

 

የቢቢሲ ቴሌቭዥን ጣቢያ የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ/Analyst የነበረው ማርቲን ፕሎት ከአሥር ዓመታት በፊት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተካሄደበትን 70ኛ ዓመት በታሰበበት ወቅት፤ “African Forgotten Soliders in the Second World War” በሚል አርእስት ስለ እውቁ ኢትዮጵያዊ አርበኛ፣ ሌፍተናት ጃጋማ ኬሎ እና የሌሎች አፍሪካውያንን ጀግኖች- የፀረ-ፋሽስት እና የፀረ’ቅኝ ግዛት አኩሪ ተጋድሎአቸውን በተመለከተ አንድ ሰፋ ያለ ታሪካዊ ዘገባ አስነብቦ ነበር።

 

በተመሳሳይም የዚሁ የቢቢሲ ቴሌቭዥን ጣቢያ ባልደረባ የሆነችው  ኤልዛቤት ብላንት የተባለች ጋዜጠኛ፤ “የበጋው መብረቅ” በመባል የሚታወቁትን ኢትዮጵያዊውን፣ አርበኛ፣ ጀነራል ጃጋማ ኬሎን ሰፋ ያለ ቃለ መጠይቅ ካደረገች በኋላ፤ “Ethiopian General Who Fought Fascism” በሚል አርእስት ባስነበበችው ዘገባ፣ “ጀነራል ጃጋማ ኬሎ በኢትዮጵያ ነፃነትና በአፍሪካውያን የፀረ-ቅኝ ግዛትና የፀረ-ፋሽስት ተጋድሎ ታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ስማቸው በጉልህ የሚነሳ ታላቅ፣ ኢትዮጵያዊ/አፍሪካዊ ጀግና መሆናቸውን፤” አስመልክታ አስደናቂ የሆነ ምስክርነቷ ሰጥታ ነበር።

 

“የበጋው መብረቅ” በመባል የሚታወቁት ዕውቁ ኢትዮጵያዊው አርበኛ፣ አፍሪካዊ የጦር ጀነራል/መሪ፣ ሌፍተናት ጀነራል ጀጋማ ኬሎ- በአምስቱ ዓመታት የፀረ-ፋሽስትና የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ስማቸው ከፍ ብሎ ከሚነሱ፤ የኦሮሚያ ምድር ካፈራቻቸው ጀግኖች፣ አርበኞች መካከል ስማቸው በግንባር ቀደምትነት የሚነሳ ታላቅ፣ ኢትዮጵያዊ፣ ብሎም አፍሪካዊ ጀግና ናቸው።

 

ከሦስት ዓመት በፊት በእኚህ ታላቅ ጀግና የአስክሬን ሽኝትና በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በነበረው ብሔራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙትና በአሁን ሰዓት በጀርመን ሀገር የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የሆኑት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን- በአፋን ኦሮሞ ባሰሙት ወኔን በሚቀሰቅስ ጌራርሳ፣ (ፉከራና ሽለላ)- ለአፍሪካ፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያን፣ ለአፍሪካና በአጠቃላይም ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት በሆነው የኢትዮጵያውያን የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ ምዕራፍ እንደ ጀነራል ጃጋማ ኬሎ ያሉ የኦሮሞ ምድር ያፈራቸው ጀግኖች- ለኢትዮጵያዊነት ብሎም ለሰው ልጆች የነፃነት ክብር፣ በደማቸው የጻፉትን አኩሪ ታሪክና የነፃነት ተጋድሎ በኢትዮጵያዊነት ወኔና የጀግንነት መንፈስ በኩራት ዘክረውት ነበር።

እኚህን በበርካታ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ትልቅ ክብርና ስፍራ ያላቸው ታላቅ ኢትዮጵያዊ፣ አፍሪካዊ የጦር መሪ፣ ጀግና፣ አርበኛ ሌፍተናት ጀነራል ጀጋማ ኬሎ በአክራሪ ኦሮሞ ብሔርተኞች ዘንድ ግን ሆን ተብለው የተገፉና ቦታ የተነፈጋቸው ናቸው። ይህን እውነታ በይበልጥ ለመታዘብ የቻልኩበት አጋጣሚ በአጭሩ ይህን ይመስላል።

ከሦስት ዓመት በፊት እኚህን ኢትዮጵያዊ አርበኛና ጀግና፣ የጦር መሪ፣ ጀነራል ጃጋማ ኬሎን- ለታሪካቸውና ለክብራቸው የሚመጥን ሐውልት በመቃብራቸው ስፍራ ለማቆምና አኩሪ ታሪካቸውን ትውልድ እንዲዘክረው በማሰብ በወቅቱ የኢፌዲሪ ፕሬዝደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ይሁንታቸውን የቸሩት አንድ ጊዜያዊ ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር።

የቀድሞ የሀገራችን ፕ/ት የነበሩት ነፍሰ ኄር መ/አ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በበላይነት በሚመሩት በዚህ ኮሚቴ ውስጥ፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማ/ር ፕሬዚደንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱ፣ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ዶ/ር ጥበበ የማነ ብርሃን፣ ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን፣ የኢትዮጵያ ታሪክና ቅርስ ተቆርቋሪ የነበረው አቶ ኃይለ መለኮት አግዘው፣ የታሪክና የቅርስ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞችና የጀነራል ጀጋማ ኬሎ ቤተሰቦችም በአባልነት ነበሩበት።

ታዲያ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ በአባልነትና በዋና ጸሐፊነት በነበረኝ ቆይታም እኚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጀግና፣ አርበኛ ቋሚ የታሪክ ማስታወሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በሐሳብና በሞራል፣ በእውቀትና በገንዘብ ይደግፋሉ የተባሉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ባለ ሀብቶችንና ምሁራንን በግሌና ከሌሎች የኮሚቴው አባላት ጋር በመሆን ለማግኘትና ለማነጋገር ሙከራ አድርገን ነበር።

ይሁን እንጂ እነዚህ ካገኘናቸውና ካነጋገርናቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ለኮሚቴው ፊትም ልብም ነሱት። ይህ ኮሚቴ በአጭሩ በአክራሪ ብሔርተኛ ኦሮሞዎች ዘንድ ቦታም ዋጋም ተነፍጎት ነበር። እንደውም አንዳንዶቹ ደፍረው እርሳቸው እኮ የኦሮሞ ሕዝብን የነፃነት ትግል ጥላሸት የቀቡ፣ እንደ ጀነራል ዋቆ ጉቱ ያሉትን የኦሮሞ ጀግኖችን የነፃነት ትግል በመቃወም ለነፍጠኛው ሥርዓት ያደሩ፣ የኦሮሞ ሕዝብን የካዱ ባንዳ ናቸው… ወዘተ የሚል ወቀሳን ጭምር የሰነዘሩ ነበሩ።

ከዚህም ባሻገር በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንደ ጀነራል ታደሰ ብሩ፣ ኮለኔል ዓለሙ ቂጤሳ፣ መ/አ ማሞ መዘምር እና ሌሎች በርካታ የኦሮሞ ልጆችን ለስቅላት ሞት፣ ለእስርና ለግዞት በዳረገው የሜጫና ቱለማ ማኅበር ምስረታ ምክንያትም ጀነራል ጃገማ ኬሎ የኦሮሞ ሕዝብን የካዱና ማኅበሩ እንዲፈርስ ትልቅ ሚናን የተጫወቱ ተደርገው ነው የሚቆጠሩት።

በጀነራል ጃጋማ ኬሎ ሞት ማግሥትም በአክራሪ ብሔርተኛ ኦሮሞዎች እና በኢትዮጵያ ነፃነት ብሎም በአፍሪካና በጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ተጋድሎ ታሪክ ምዕራፍ ውስጥ- የኦሮሞ ሕዝብ የከፈለው ግዙፍ መሥዋዕትነት- የኢትዮጵያዊነት፣ ከፍ ሲልም የአፍሪካዊነትና የሰው ልጆች ነፃነት ክብርና ኩራት ነው፤ በማለት በሚከራከሩ ኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎች መካከል በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ሲካኼድ የነበረውን ክርክር፣ ሙግት ያስታውሷል።

በመሠረቱ አሁንም ድረስ በአክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች ዘንድ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት፣ ለሕዝቦቿ ነፃነት ትልቅ መሥዋዕትነት የከፈሉ የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ጀግኖችን በኢትዮጵያ ከፍ ሲልም በአፍሪካ ሕዝቦች የነፃነት ትግል ታሪክ ማዕቀፍ ውስጥ ሰፋ አድርጎ የማየት፣ የመቀበል ችግር በስፋት አለ። ይህ የተንሸዋረረ የታሪክ ምልከታና ስሑት መረዳት አሁንም ድረስ አልተቀረፈም። በትልቁ የዚህ ሰለባ ከሆኑ የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች መካከል ደግሞ ጀግናው፣ አርበኛ፣ የጦር መሪ፣ ሌፍተናት ጀነራል ጀጋማ ኬሎ አንዱና ዋንኛው ናቸው።

የባሌ ገበሬዎችን ትግልና ዓመፅ የመራውን ጀነራል ዋቆ ጉቱን፣ በሜጫ ቱለማ ማኅበር ምስረታ ትልቅ ሚና የነበራቸውንና ደቡብ አፍሪካዊውን የፀረ-አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠት የሚታወቁትን በወቅቱ የኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ማሰልጠኛ አዛዥ ለነበሩት- ለጀነራል ታደሰ ብሩ ለመሳሰሉ የኦሮሞ ተወላጆች፣ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ቋሚ የታሪክ ማስታወሻ እንዲኖራቸው የሚከረከሩ አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች ተሳስተው እንኳን የጀግናውን ኢትዮጵያዊ አርበኛ፣ የጀነራል ጃጋማ ኬሎን ስምና ታሪክን ፈጽሞ ማንሳትም፣ ማስታወስም አይፈልጉም። በethino-nationalist የኦሮሞ ብሔርተኞች ታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድም ቢሆን እንደ እነ ጀነራል ጃጋማ ኬሎ ዓይነት ለሀገራቸው ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለሰው ልጆች ነፃነት ዋጋ የከፈሉ የኦሮሞ ጀግኖች የሚሰጣቸው ስፍራ ምንም ወይም ኢምንት ነው ማለት ይቻላል።

 

ይሁን እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በአንድነት በመሆን ለሀገራቸው ኢትዮጵያ አንድነት ለሕዝቦቿ ነፃነት የከፈሉት ግዙፍ መሥዋዕትነት- በአፍሪካውያንና በጥቁር ሕዝቦች የነፃት ተጋድሎ ታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ትልቅ ሰፍራ የሚሰጠው ነው። ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ድል ብሥራትን ካበሰረው በዐድዋ የጦር ግንባር በደማቸው ሕያው ታሪክን ከጻፉልን የኦሮሞ ፈረሰኞችና ጀግኖች ጀምሮ- የኦሮሚያ ምድር ካፈራቻቸው ከጀነራል ጀጋማ ኬሎ እስከ ኮለኔል አብዲሳ አጋ እና ጀነራል ታደሰ ብሩ ዓይነት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች- በአፍሪካ ከደቡብ አፍሪካ እስከ አውሮፓ ምድር- ሮም ኢጣሊያ በናኘው ጀግንነታቸውና የነፃነት ተጋድሎአቸው ታሪክ በታላቅ ክብር፣ ትውልድም ሁሌም በኩራት ይዘክራቸዋል።

 

በአክራሪ ብሔርተኛ ኦሮሞዎች ዘንድ ሆን ተብለው የተዘንጉትና ሥፍራ የተነፈጋቸው ኢትዮጵያዊው አርበኛና ጀግና፣ የጦር መሪ፣ ጀነራል ጃጋማ ኬሎ የፋሽስት ኢጣሊያን “የከፋፍለህ ግዛው” የዘረኝነት ፖሊሲው- ኢትዮጵያውያንን በዘርና በጎሳ ከፋፍለው ቅኝ ለመግዛት ያደረጉትን ሙከራ ያመከኑ፣ የኢትዮጵያን አንድነትና የሕዝቦቿን ነፃነት ፈጽመው ለድርድር ያላቀረቡ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ናቸው። የቢቢሲዋ ኤልዛቤት ገለጻን ልዋስና- “Ethiopian General Who Fought Fascism” ፋሺዝምን በጽናት፣ በታላቅ ጀግንነት የተፋለሙና የታገሉ እናት ኢትዮጵያ፣ አፍሪካ እና መላው ዓለም በክብር የሚያስታውሳቸው የሁልጊዜም ጀግናችን ናቸው- “የበጋው መብረቅ”፣ አፍሪካዊው የጦር ጀነራል/መሪ፣ ኢትዮጵያዊው ጀግና አርበኛ ሌፍተናት ጀነራል ጃጋማ ኬሎ!!

ሰላም!!

Filed in: Amharic