>

በክልል ምርጫ ጉዳይ ያለን አቋም! (አብረሃ ደስታ)

በክልል ምርጫ ጉዳይ ያለን አቋም!

አብረሃ ደስታ
አንዳንድ የህወሓት ሚድያዎች “ዓረናን ጨምሮ አራት የትግራይ ፓርቲዎች የምርጫ መራዘም ተቃውመው መግለጫ አወጡ” የሚል ዜና በመስራታቸው ምክንያት ዓረና ፓርቲ እንዲህ ዓይነት መግለጫ እንዳላወጣና የምርጫ መራዘም እንደሚደግፍ የፃፍኩ ግዜ አንዳንድ የህወሓት ሰዎች “ምርጫን አለመፈለግ የመመረጥና የመምረጥ መብትን በራስ ፍቃድ እንደመነፈግ ነው” የሚል መልእክት እያደረሱን ነው።
ምርጫ አንፈልግም አላልንም፤ ምርጫ እንፈልጋለን። በምርጫ የመሳተፍ እንዲሁም የመምረጥና የመመረጥ መብታችን እንዲከበር እንፈልጋለን። የመንግስትን ስልጣን ይዞ ሀገርንና ህዝብን ማስተዳደር ያለበት በህዝብ የተመረጠ አካል መሆን እንዳለበት እንገነዘባለን።
ታድያ ምን እያልን ነው?
(1) ምርጫ አሁን ግዜው አይደለም። የኮሮና ወረርሽኝ አደጋ ተደቅኖብናል። የወረርሽኝ ስጋት ባለበት ወቅት ምርጫ ማካሄድ የህዝብን ደሕንነት ለአደጋ ማጋለጥ ነው። ስለዚህ ምርጫ ወሳኝ ቢሆንም ከህዝብ የጤና ደሕንነት ስለማይበልጥ የኮሮና ስጋት እስኪያልፍ ድረስ ትንሽ እንታገስ ነው። ምርጫ ከጤና አይበልጥምና ወረርሽኑን እንከላከል። ምርጫ ከጤና በኋላ ይደርሳል። ህዝብ መምረጥ ሚችለው ጤናው ሲጠበቅ ነው።
(2) የመመረጥና የመምረጥ መብት የማይታለፍ ቢሆንም በዚሁ ቀውጢ ግዜ ግን ለግዜው ይቁይ። በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተገደበው መብት የምርጫ ብቻ ሳይሆን
ተቃቅፈን የመሳሳም መብት
ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት
የመሰብሰብ መብት
የመማርና የመስራት መብት
.
ብዙ መብቶች ተገድበዋል። ለምን? ህዝባችንና ራሳችንን ከኮሮና ወረርሽኝ ለመጠበቅ!
በክልላችን ለሦስት ወር የሚቆይ አስቸኳይ ግዜ የታወጀውኮ የወረርሽኝ አደጋ ስላለ ነው። ምርጫ ማካሄድ በምንችልበት ቁመና ላይ የምንገኝ ቢሆን ኖሮ አስቸኳይ ግዜ ማወጅ ለምን ያስፈልጋል?
በክልል ደረጃ የኮሮናን ወረርሽኝ ለመከላከል አስቸኳይ ግዜ ታውጆ የመንቀሳቀስ፣ የመስራት፣ የመማር፣ የመሰብሰብ ወዘተ መብቶች ታግደዋል። ምርጫ ይደረግ ከተባለኮ አስቸኳይ ግዜ አዋጁ ተነስቶ ፓርቲዎች እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው፣ ሰርተው፣ ህዝብ ሰብስበው ማስተማርና የምረጡኝ ቅስቀሳ ማካሄድ አለባቸው። ይሄ ሁኔታ የኮሮና ወረርሽኝን በበለጠ አያስፋፋውም? ለምርጫ ስንል ህዝባችን ለአደጋ እናጋልጥ? ትምህርቱ፣ መንቀሳቀሱ፣ መሰባሰቡ፣ ተቃቅፎ መሳሳሙ፣ ምርጫ ማካሄዱ ወዘተ ከኮሮና በኋላ አይደርስም? እኛ የህዝባችን የጤና ጉዳይ ነው ምናስቀድመው!
(3) ምርጫ እውነተኛ ፉክክር ያለበት፣ ሕጋዊና ገለልተኛ በሆነ አካል (የምርጫ ቦርድ) የሚፈፀም፣ ሁለም ዝግጅት የተጠናቀቀበት ወዘተ መሆን ይኖርበታል። አሁን በትግራይ ሐቀኛ ምርጫ ይደረግ ቢባል አደገኛ ወረርሽኝ ተከስቶ ህዝቡ በተቻለ መጠን ከቤት እንዳይወጣ በታወጀበት ወቅት እንዴት ነው ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሂደው እውነተኛ ፉክክር የሚታይበት ምርጫ ማድረግ ሚቻለው? ውድድሩ በየትኛው ሕጋዊ የምርጫ አስፈፃሚ አካል ነው ሚዳኘው? በወረርሽኙ ምክንያት የምርጫ ቁሳቁስ ከውጭ ሀገር ማስገባት እንዳልቻለ የምርጫ ቦርድ ገልፆልናል። አሁን ለትግራይ ምርጫ ማስፈፀምያ የሚሆን ቁሳቁስ ከየት እንዴት ሊገባ ነው?
በኛ እምነት ምርጫ ከወረርሽኙ በኋላ ይደርሳል። አሁን ሊያሳስበን የሚገባ ጉዳይ ምርጫ ሳይሆን ኮሮና ነው።
አይዛችሁ! በህይወት ከቆየን ምርጫ ማድረጋችን አይቀርም! ላሁኑ ግን ከምርጫ ይልቅ ሊያሳስበን የሚገባ የህዝባችን ጤና ነው። ከፖለቲካ ስልጣን የህዝብ ደሕንነት ይቀድማል!
Filed in: Amharic