>

ምናባዊ ጨዋታ (ሰማይ ቤት) ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው

ምናባዊ ጨዋታ(ሰማይ ቤት)

ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው
ጋሽ ሐዲስ አለማየሁ፦
“በቅርቡ የተቀላቀለን ጋሽ ውብሸት ነው። ጋሽ ውቤ የእንጀራ ጉዳይ ሆኖብህ ወደ ማስታወቂያ አዘነበልክ እንጂ ጥሩ የፊልም ባለሙያ ነበርክ። ርእሱን ረሳሁት እንጂ ቆንጆ ፊልም ራስህ ፅፈህ ፣ አዘጋጅተህ ተውነህ ነበር። ትልቅ ቦታ ሊደርስ የሚችል ተሰጥኦ ነበር። የእንጀራ ጉዳይ አጨናገፈው።”
ጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህን፦
“እውነት ነው። ለመሆኑ ጋሽ ስብሐት ምድር ላይ ሳላደርገው ይቆጨኛል የምትለው ነገር አለ?”
ጋሽ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፦
 “እኔ የተመኘኋትን አቅፌ፣ ያሰብኩትን ተናግሬ እንደልቤ ሆኜ ነው የኖርኩት። በእርግጥ ገንዘብ አልነበረኝም። ግን እንዲኖረኝም ተመኝቼ ስለማላውቅ አይቆጨኝም። ምን ይቆጭኃል ብትለኝ Roman ጋር ብዙ ግዜ አለማሳለፌ ነው። አንተስ ግን ጋሽ ፀጋዬ?”
ጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህን፦
“እኔ በተለይ በጥበቡ በኩል ነው የምብሰለሰለው። ግን አይቆጨኝም። የሚያድጉ ልጆች ተክቼያለሁ። ሁለቱ የስዩም ልጆች ታላቅ ገጣሚ ይሆናሉ። በትያትር በኩል ግን እንጃ። ጋሽ አባተ በዝግጅቱም የቲያትር ቤት አድባር ነበርክ። አንተም ብትሆን ጋሽ ስብሐት አለማየሁ ገላጋይ እና ዘነበ ወላ የጥበብ ልጆችህ ናቸው።”
ጋሽ ሰለሞን ደሬሳ፦
“በድርሰቱ ጌትነት እንየው በዝግጅቱ ደግሞ ማንያዘዋል እንደሻው ተተክተዋል”
ጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህን፦
“አንተ ደግሞ ጋሽ ሰሌ። ስጋ ቁጠር ብትባል ጣፊያ አንድ ትላለህ እንዴ። ማንያዘዋል እኮ እኔን ካልገመገምኩህ ያለ ደፋር እኮ ነው። ፑሽኪንን ማን ገመገመው?!”
ጋሽ በአሉ ግርማ፦
“ጋሽ ፀጋዬ አንተኮ እድለኛ ነህ። አንተንኮ እንገምግምህ ነው ያሉት። እኔ አለሁ አይደል እድለቢሱ “እንግደልህ” የተባልኩ። ድርሰትን፣ ባለቤቴን፣ ልጆቼን ሳልጠግባቸሁ የተለየሁ”
ጋሽ ብርሃኑ ዘርይሁን፦
 “በአሉ አንተምኮ እድለኛ ነህ። ቢያንስ ያረገዝከውን መፅሀፍ ወልደሃል። የሰዎችን ስሜት ኮርኩረሃል። አበሳጭተሃል። ቂም አስቋጥረሃል። እኔኮ ያረገዝኩትን መፅሀፍ ሳልወልድ ነው ያለፍኩት”
ጋሽ ገብረክርስቶስ ደስታ፦
“ለኔ በህይወቴ ሳላደርግ ቀረሁ የምለው የለም። ስሜቴን በስእልም በግጥምም ተንፍሽያለሁ። ታላላቅ ጓደኞቼ ነበራችሁኝ። ትንሽ ቅር የሚለኝ ከሃገሬ ወጥቼ መኖሬ ነው። የዚያ አምባገነን ስርአት ሰለባ ሆንኩ። ጋሽ አፈወርቅ አንተስ ምን ትላለህ”
ጋሽ አፈወርቅ ተክሌ፦
“እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ነው የሚባለው። በጥበቡ በኩል ሁሉን አሳክቻለሁ። ምናልባት ቅር የሚለኝ በስጋ የአብራኬን ክፋዮች ባለማየቴ ነው።”
ጋሽ ስብሐት፦
“በነገራችን ላይ ሎሬት በጋዜጠኝነት ህይወቴ ቃለመጠይቅ ካደረግኩላቸው ከያኒያን የእርስዎና የሐዲስ አለማየሁ ይገዝፍብኛል። እንደውም ለአለቃዬ በአሉ እኔ ዝነኛ ሰው ቃለመጠይቅ ማድረግ እፈራለሁ ብዬው እሱ ነው ያደፋፈረኝ። በግዜው መነን መጽሔት ላይ እየሰራሁ ነበር።”
ጋሽ አሰፋ ጎሳዬ፦
“ስለ ጋዜጠኝነት ከተነሳ አድማስን ሳስተዳድር ከጓደኛዬና ዋና አዘጋጁ ነብይ መኮንን አፍ የማይጠፋው ስም አሰፋ ጫቦ ነበር። ጋሽ አሴ በእውነቱ ታላቅ ስብእና የታደልክ ሰው ነህ። በአካል አግኝቶህ የማያውቅ ሰው ራሱ በፅሁፎችህ ትልቁን ልብህን ማየት ይቻለዋል። የጋሞ ባህል ደፋር እና ቀና አድርጎሃል”
ጋሽ ጥላሁን ገሠሠ፦
“ሁሉንም ተዉት። ሆድ ይፍጀው!”
Filed in: Amharic