>

ይድረስ ለዶ/ር አቢይ አህመድ (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

ይድረስ ለዶ/ር አቢይ አህመድ

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ሰላምህ ይብዛ ውድ ታናሽ ወንድሜ ዶ/ር አቢይ!

  1. አንድ ተራ ዜጋ ለአንድ ጠ/ሚኒስትር ጦማር መጻፍ የተመለደ እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ ቢለመድ ግን ምንም አይደለም፤ እንዲያውም መለመድ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም በጠ/ሚኒስትርና በተራ ዜጋ መካከል ያለው ዋና ልዩነት ጠ/ሚኒስትር መሆንና አለመሆን ነው፡፡ የተለዬ ቅባት የሚባል ነገር የለም፤ የሚገኙ አጋጣሚዎችን የመጠቀምና አጋዥ ሁኔታዎችን በቅጡ የመገልገል ነገርም ነው፡፡ ሥልጣን በሀገራችን ልዩ ግምት እየተሰጠው እላይ ያለ እንደ ፈጣሪ፣ እታች ያለ ደግሞ መሪው ራሱ እንደፈጠረው እየተቆጠረ እንጂ በመሠረቱ በአንዲት ሀገር ዜጎች መካከል የኃላፊነት ካልሆነ የዜግነትና የስብዕና ልዩነት ሊኖር ባልተገባ፡፡ ስለዚህ ይህን ጦማር ለማንበብ “ዕድሉ”ን ካገኘህ እየውማ ግዴለህም፡፡
  2. ውስጤ እየተረበሸ ከማርር መናገር የምፈልገውን ነገር  በግልጽ ልነግርህ ወደድሁ፡፡ ሰማኸኝ/አልሰማኸኝ የግል ጉዳይህ ነው፡፡ እርግጥ ነው በሥራ ብዛት እንደሌጦ ተወጥረህ የእያንዳንዱን ዜጋ ምክርና ተግሣፅ ትሰማለህ የሚል ጅልነት የለኝም፡፡ ያንተን ዕድል ሳስበው በአንድ ወገን ተፈልጎ የማይገኝ እጅግ ወርቃማ ሲሆን በሌላ ወገን በጎመን በጤና ፍርሀት-ወለድ የሀበሻ መፈክር ባፍንጫ እንዲውጣ ለ44ቱ ታቦት የሚሳሉለት ነው፡፡ ይህን ወረቀት ያዬ አንዱ ሹክ ቢልህ ደስ ይለኛል፤ ባታየውም ከኔ ይውጣ፡፡ ምልባት እነዳኒ ካዩት ቢጠቁሙህ ክፋት የለውም፡፡
  3. ሀገራችን መንግሥት አልባ የሆነች ትመስላለች፡፡ በአንተ ጊዜ ይህ መሆኑ ሊያሳስብህ ይገባል፡፡ ሁሉም እንዳፈተተው እየሆነ ነው፡፡ አንዱ የሚሠራው ለሌላው ግልጽ አይደለም፡፡ ጊዜው ዘመነ መሣፍንትም እየመሰለኝ እጨነቃለሁ፡፡ ትግራይ አገር ሆናለች፤ ኦሮሞ አገር ሆኗል፤ አንተ የየትኛው መንግሥት “ንጉሥ” እንደሆንክ ለማወቅ ተቸግረናል፡፡ ለምሣሌ ሰሞኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ የአቶ ለማ መገርሣ ንግግር ከላይ መጣ በተባለ ትዕዛዝ በሚዲያ ሳይተላለፍ ቀረ፡፡ ይህ አስቂኝ ነገር ነው፡፡ ሰውዬው እኮ የመከላከያ ሚኒስትር ናቸው – ማለቴ ነው! ይህ ዓይነቱ መደፋፈርና መናናቅ እየታዬ ነው፡፡ አንድ ባለሥልጣን እንደተፈለገ የሚከበር ወይ የሚዋረድ ከሆነ፣ አንዱ ሹም ከአንዱ ክልል ዜጎችን እያሳፈነ  ወይም ደብዛ የሚያጠፋ ከሆነ (ሰሞኑን የሀረር ባለሥልጣናት አንዲት ሴት የህግ ባለሙያ ከአዲስ አበባ አፍነው ከአንድ ወር በኋላ መልቀቃቸው የሚታወስ ነው) አዛዥ ናዛዡ ይጠፋና የሀገር አስተዳደር ውል አልባ ልቃቂት ይሆናል፡፡ አንድ የሥራ ኃላፊ የሥራ ኃላፊነቱና ግዴታው ሊታወቅና ተገቢው ክብር ሊሰጠው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ልክ እንደአፄዎቹና ኋላም እንደደርግና እንደወያኔ ዘመን ኃይለ ማርያም ደሳለኝን የመሰለ ጀንፈል “ጠ/ሚኒስትር” እየሾሙ በስልክ ማሾር ካለ የሀገር ጉዳይ የጨረባ ተዝካር ይሆናል፡፡ የሀገራችን አዝማሚያ በግልጽ የሚያሳየው ይህንን ነው፡፡ ለራስህ ስትል ዕወቅበት፡፡ አውቀህም ይሁን ሳታውቅ  ብዙ ነገሮች ከቁጥጥርህ ውጪ የሆኑ ይመስላሉ፡፡
  4. ሰዎችን ማሰርና ማሰቃየት አሁንም አልቆመም – አደግን ብለን ከማሰባችን የባሰብን ደናቁርት እየሆንን ነው፡፡ በማሰርና በመግደል “ፍላጎቴን እውን አደርጋለሁ”  ብሎ የሚያስብ መንግሥትና የመንግሥት ባለሥልጣን ባለበት ሀገር ፈሪዎችንና ፍርሀትን እያመረተ ሀገርን ያቆረቁዛል እንጂ ዕድገትና ብልጽግና የህልም ዓለም ምናባዊ ውጤቶች እንደሆኑ ይቀራሉ፡፡ አሁን እያየነው ያለው ነገር የአሣሪና ታሳሪ ለውጥ እንጂ ሂደቱና ድርጊቱ ከወያኔው ዘመን አልተለዬም፡፡ ቢለይ ኖሮ እኮ እኔና አንተ ይሄኔ “እንተዋወቅ” ነበር – ጥንጥዬና የተጋነነች ምሣሌ፡፡  አንዱን በዘሩ ምክንያት እንደልቡ ሲሆን ዝም ብሎ ማለፍ ሌላውን ምንም ሳያጠፋ እንዲሁ እንደሥጋት ምንጭ በመቁጠር ጭምር ማሰር ተገቢ አይደለም፡፡ የርስዎ መንግሥት ለአንዱ የእንጀራ እናት ለሌላው የእውነት እናት ሊሆን አይገባውም – (ውይ አንተንና እርስዎን አደበላለቅሁት ልበል? ይሁን – ዛሬ ያልተደበላለቀ ነገር ምን አለና)፡፡ ለምሣሌ የባልደራስ ሊቀ መንበርና የአብን ሰዎች ብዙውን ጊዜ በፖሊስ ራዳር ውስጥ ናቸው፤ በእስር ይንገላታሉ፤ በሀሰት ክስ ሣይቀር አሣራቸውን ይበላሉ፡፡ በሌላ ወገን ጃዋር የተባለው አሸባሪ እንደልቡ ሕዝብን ለዐመፅ ሲቀሰቅስ ማንም ዝምቡን እሽ አይለውም፤ ይህም የፈገግታ ምንጭ(ጬ) መሆኑን ሳልጠቁም ባልፍ እውነት ራሷ ትታዘበኛለች፡፡ ለምን? ጃዋር ምንድን ነው? ምንስ ስለሆነ? “ወንድማችን ጃዋር በጥሩ ሁኔታ ይገኛል” የሚል የክልል ፕሬዝደንት በአንድ በኩል፣ የፖለቲካ ፓርቲን ፕሬዝደንት የሚያስርና የሚያንገላታ ሞባይሉንም ቀምቶ ለሣምንታት እንዳሻው የሚበረብር ወንበዴ በሌላ በኩል – በአንዲት ሀገር ልጆች መካከል ይህን የመሰለ መድሎ ነውር ነው፤ ወንጀልም ነው፤ ንስሃ የሌለው ኃጢኣትም ነው፡፡ የፍትህን ዐይን አትደንቁሉ፡፡ Avoid double standards!  ዘመን ሲያልፍ ይህ ታሪክ ለቀጣይ ትውልድ ፍርድ የሚቀርብ በወንድማማች ሕዝቦች መሀል ጥቁር መጋረጃ የሚያስቀምጥ መጥፎ አካሄድ ነውና በአፋጣኝ ይቅር፡፡ ጃዋር ሣምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለቴ ሲበጠረቅ ማን ነካው? መጀመሪያ – “ከመስከረም 30 ቀን 2013 በኋላ ይህን መንግሥት በአፍንጫው እንደፋዋለን!” የሚል መልእክት ያዘለ ዛቻ ከቢጤው ልደቱ አያሌው ጋር ሆኖ እንደጣቃ ተቀደደ፡፡ ማንም ምንም አላለውም፡፡ ቀጠለና ለማስተባበል በሚመስል መልክ “በርግጥ እንዲህ ብለሃል ወይ?? ተብሎ በኦኤም ኤን ሲጠየቅ በሚያስገርም ሁኔታ “ሕዝብን ማነሳሳት የተካንበት ነው፤ ለዚያ ሁሉም ያውቅልናል፤ ብንፈልግ ማንም እንደማይከለክለን እናውቃለን፤ እነሱም ያውቃሉ፡፡ እነሱንም ወደ ሥልጣን ያመጣናቸው በዚሁ መልክ ነው፤ እኛ ግን አሁን ዐመፅ እየቀሰቀስን አይደለም…” በሚል ትምክህታዊ አሸባሪነቱ የቀደመውን ትዕቢቱን መልሶ ደገመው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን በልጆች የተሞላው መንግሥታችን፣ ከአንድ ጎሣ በተጠራሩ የአንድ ዘመን እኩያሞች የተዋቀረውና በዚያም ሳቢያ አዛዡና ታዛዡ በማይታወቅበት የሥራ ኃላፊነት ተዋረድም በጠፋበት ሁኔታ የሚገኘው “ፌዴራል መንግሥታችን” ትንፍሽ አላለም፡፡ ምንድን ነው ጉዱ? ታዛቢ የለም ነው? የሚያውቁብን የለም ነው? እንደፈልግነው ብንሆን ተቆጪ የለንም ነው? ለዚህ ያበቃችሁ ፈጣሪ እንኳን እንዴት ተዘነጋ?
  5. ለተወሰነ ነገድ የማድላት ነገር በመንግሥት ደረጃ በግልጽ ይታያል፡፡ በመንግሥት የዜና ዕወጃ ሰዓቶች ዜናዎችና ሀተታዎች ሲቀርቡ ልክ እንደወያኔው ዘመን ከአንድ ጎሣ የወጡ ሰዎች በአለቅነት ቀርበው ካልተናገሩ መንግሥት የማይፀና ይመስል የሚቀርበው አለቃ ሁሉ በስህተት ይሁን በድፍረት እስካሁን አልገባኝም ጉርሜሤና ፈይሣ ነው፡፡ ይህም አንዱ የፈገግታ ምንጭ(ጬ) ከሆነ ሰነበተ፡፡ ከአንድ የተማረና በሃይማኖት የለዘበ ዘመናዊ ሰው ይህ ዓይነቱ የደም አነፍናፊነት ውሻዊ ተፈጥሮ በፍጹም አይጠበቅም፡፡ የሥራ ምደባ ዘርንና ጎሣዊ ኮታን ሣይሆን ትምህርትንና ችሎታን ያማከለ መሆን ይገባዋል፡፡ እንዲህ የምለው “ተበደልን” የሚሉ ወገኖች ሌላ የበደል ዙር እንዳያመጡብን በመፍራት ነው፡፡ “ሜሪቶክራሲ” የሚባል ነገር አለ፤ ይህችን ጽንሰ ሃሳብ አንብባ(ቧ)ት፡፡ ሁሉም ለሚያልፍ ነገር ሸጥና ጎጥ ውስጥ መወተፍ ነውር ነው፡፡ ኅሊናም አለ፤ ፈጣሪም አለ፤ ትውልድም አለ፤ ዜጎችም አለን፡፡ ሁላችንም እንታዘባለን፡፡ እኛን መናቅ ራስንም መናቅ ነው፡፡
  6. አንበሣ ጠል መሆንህን እያየሁ ነው፡፡ ለምን? ነባር ነገሮችንና ተምሣሌቶችን በራስ ፍላጎት መለዋወጥ ደግ እንዳልሆነ ካንተ ከዶክተሩ የበለጠ ሊያውቅ የሚገባው አይኖርም፡፡ መለስ ዜናዊ ም እንዳንተው ጥሎበት አንበሣ አይወድም ነበር፡፡ አንተም ከንግግር ሥልት ባለፈ የስሜት ወራሽም ሆነሃል፡፡ አንበሣ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ነገሥታት ዓርማ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ በየዘመኑ መሪ በተለዋወጠ ቁጥር የሀገር ዓርማና ባንዲራ መለወጥ አለበት ማለት ነው? እስኪ አሜሪካንን ጨምሮ የሌሎች ሀገራትን ዓርማና ተምሣሌቶች ተመልከት፡፡ መለስ በዚህ ነባር ነገርን የመጥላትና የመደምሰስ ባሕርይው ብዙም የተጠቀመ አይመስለኝምና ሰውን ስማ፡፡ 
  7. ሰሞኑን ኮሮናን ምክንያት በማድረግ ያንተ አስተዳደር በአምልኮት ሥፍራዎች ላይ ቁጥጥሩን አጥብቋል፡፡ በፊት ጥሩ ክርስቲያን ትመስለኝ ነበር፡፡ የሃይማኖት ድንበር አጥበርብሮህ ያንዱን ከሌላኛው የምታስበልጥ አትመስለኝምም ነበር፡፡ አንድ የሀገር መሪ ከሃይማኖቶች በላይ መሆን አለበት፤ ከጎሣዎች በላይ መሆን አለበት፤ ከማናቸውም ሰው ሠራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ ልዩነቶች በላይ መሆን አለበት (ብዬ አምናለሁ)፡፡ በልዩነቶች የሚሳብ መሪ በፍትሃዊ መንገድ ማስተዳደር አይችልም፡፡ ለምሣሌ በዝምድና ከተሳበ ለልጁ ወይ ለእህቱ ሲል ፍርድን ሊያዛባ ነው ማለት ነው፡፡ ፍትሃዊ መሪ ግን ልጁ እንኳ የስቅላት ሞት ቢገባው እየመረረውም ቢሆን ያን ፍትህ መቀበል ይኖርበታል እንጂ መሪ ነኝ ብሎ ፍትኅን አያዛባም፡፡ ስለዚህ በገበያዎችና በሌሎች የሕዝብ መገናኛ ሥፍራዎች ሕዝብ እንደልቡ እየተንቀሳቀሰና “ቫይረሱን እያሰራጨ” አንተ ግን ቤተ ክርስቲያንን በተለይም ኦርቶዶክስን እምነቱን በማያከብሩና ምዕመናንን በሚያዋርዱ ወታደሮች የሙጥኝ እንዳልክ ቀናት ተቆጠሩ፡፡ ቁጥጥሩ ባይከፋም አድልዖው ግን ዜጎችን ብዙ እያስባለ ነውና ራስህንና መንግሥትዎን ይፈትሹ እባክዎን ውድ አቢይ፡፡
  8. ፖለቲካዊ ሤራንና ሸፍጥን ተው፡፡ ይህ ለማንም አይበጅም፡፡ እርግጥ ነው – የተወሰነ ዓላማና ግብ ሊያሳካ ይችላል፡፡ በቋሚነት ግን ጉዳት እንጂ  ጥቅም የለውም፡፡ ሸረኞች የማታ ማታ ተሸናፊ እንጂ አሸናፊ አይሆኑም- ራስህስ “መግደል መሸነፍ ነው” ትለን የለምን? የካርማ መዝብህን ( Karmatic Record) ያበላሽብህና ተመልሰህ ብትፈጠር እንኳን አሁን አምርረህ ከምትጠላቸው እንስሳት አንዱን ለምሣሌ እባብን ሆነህ ትፈጠርና አዳሜ አናት አናትህን እያለ ይቀጠቅጥሃል – እንደኔ ሳይሆን እንደ ቡድሂዝም እምነት ፍልስፍና፡፡ ስለዚህ የምታሳየው የዋህነት መልካም ሆኖ አንዳንዴ በተለይም የአማራውን ንቁ ፖለቲካዊ ተሣትፎ ለማደብዘዝ የምትጓዘውን ርቀት ስታዘብ ባንተ ውስጥ ብዙ ሰዉነቶችን እያየሁ አዝናለሁ፡፡ ባለሥልጣናቱን ሁሉ ስትፈልግ ሁሉንም ኦሮሞ አድርግ፤ ብትፈልግም ሁሉንም እስላምና ጴንጤ አድርግ፡፡ ግን ችሎታ የሌላቸውንና ሥራ የሚያበላሹትን እንዲሁም ሮጠው ያልጠገቡ ውሪዎችንና በልተው ያልረኩ ሆዳሞችን አትሹም – የሥልጣን ዕድሜህን አንተ ባላሰብከው መንገድ ያሳጥሩብሃልና፡፡ ጭቀንቴ ላንተም ነው፡፡ “የዳኛ ልል ያማታል፤ የምንትስ ልል ያፋታል” የሚለውን ብሂል ደግሞ አስታውስ ፡፡ ባለሥልጣኖችህ ከሞላ ጎደል ሁሉም በሚባል ደረጃ በሙስናና ዘረኝነት የበሰበሱ፣ በማይምነት የራሱ ናቸው፡፡

9 ምርጫው መተላለፉ ደግ ነው፡፡ የምርጫው መተላለፍ የውዴታ ሳይሆን የግዴታ ነው፡፡ በዚህ የወሸባ ወቅት ማንስ ወጥቶ ማንን ይመርጣል? ግን መራዘሙን የሚጠሉ ሰዎችን ወደ ጠበል ወይም ወደ ሀኪም ቤት ወስደህ ከተጣባቸው የሥልጣን በሽታ እንዲፈወሱ አድርግ፡፡ አለበለዚያ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ዕብደታቸው ዜጎችን እንዳያፋጅ ያሰጋል፡፡ የሥልጣን ፍቅር መድኃኒት የለውም፡፡

  1. በሃይማኖት ስም ራሳቸው ቀውሰው ማኅበረሰቡን እያቀወሱ ያሉ ወፈፌዎችን አደብ አስገዛ፡፡ ሁሉን አንተ እንድትፈጽም ደግሞ አይጠበቅብህም፡፡ ሁነኛ ሰው ምረጥና መድብ፡፡ ይህን ነገር እየተከታተለ ፈር የሚያሲዝ ለብቻው አንድ ቢሮ አቋቁም፡፡ ቀላል ነው፡፡ ለምሣሌ ይቺ ቀድሞ ሞዴል ነበረች የሚሏት እህተ ዲያቢሎስ (እህተ ማርያም ብላ ራሷን የምትጠራዋ ወፈፌ) ብዙ የዋሆችን ገደል እየከተተች ናት፡፡ አንዱን የባላገር ጀለንፎ ንጉሥ ትሆናለህ ብላው እርሱም እውነት መስሎት እየተጃጃለ ብታየው አንተም ትስቃለህ – ያንተ እናት ትንቢት እንኳን መንገዱ የቀና አይመስልም እንጂ የተሳካ ይመስላል፤ (ክብርት እናትህ ያለችህን ብትልም እንኳን በዘመነ “ዴሞክራሲ” በዚያ መልክ ራስህን ባትገልጽ በበኩሌ ደስተኛ ነበርኩ – የኛን ሰው ታውቀው የለ? ስንት አቃቂር አወጡብህ መሰለህ!)፡፡ ያ ጅል ግን የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን አቋርጦ በየሚዲያው ሲሞላፈጥ ብታየው ለርሱም ታዝናለህ፤ ወያኔዎች በገረፍ ገረፍ አሰልጥነው እንደላኩልን(ብን)ም ይወራል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሞኞቾችና እስራኤል ዳንሳን እንዲሁም አጥማቂና ፈዋሽ ነን የሚሉ ሃሳይ መሲሆችንና ታምራት ገለታን የመሰሉ አባይ ጠንቋይ ቀፋዮችን እየተከታተለ መስመር የሚያሲዝ አንድ መንግሥታዊ ተቋም መሥርት፡፡ ከዚያም ብዙ ሰዎች ከውዥንብርና ከባዕድ አምልኮት ይድናሉ፡፡ አንተም ቆምኩለት ለምትለው ሃይማኖት ለትዝብት በሚዳርግህ መልኩ ብዙ አትሟሟትለት፡፡ ምክንያቱም አንተ የሁሉም ሀብት እንጂ፣ አንተ የሁሉም ዜጎች ንብረት እንጂ… የዚህ ወይም የዚያ ተቋም ብቸኛ አገልጋይና አንጡራ ጥሪት አይደለህም፡፡ አንድ መሪ በአእምሮውና በዕውቀቱ፣ በጥበብና በብስለቱ ቢቻል ከሁሉም አሊያም ከብዙዎቹ ዜጎች መብለጥ አለበት፤ ለዚህም ነው “መሪ” የሚል ወፍራም የማዕረግ ቅጥያ ማግኘቱ፡፡ ስለሆነም ለዚህ ወይ ለዚያ ሃይማኖት ማድላት የለብህም፡፡ እንደገናም ሁሉንም ለማስደሰት ብለህ ማኅሌት መቆም ወይም ሶላት መስገድ አለዚያም ስብከትና መዝሙር ማዳመጥና ማስደመጥ አይጠበቅበህም፡፡ በዚህች ምድር ፍጹም እውነት የሚባል አለመኖሩን ደግሞ ላንተ አልነግርህም ወንድሜ፤ ብዙ ነገሮች ምናልባትም ሁሉም ነገሮች የአንጻራዊነት ህግ ተገዢ ናቸው፡፡  ሁሉም እንዲወድህ የሁሉንም መብት በእኩል ማክበር እንጂ ከዚህ የተለዬ ነገር ማድረግ አይኖርብህም፡፡ የሁሉም ሰው መሆን ይቻላል፤ ሁሉንም ማስደሰት ግን ይከብዳል፡፡ አየህ – ለምሣሌ አንድ ሰው አሳዝኖህ አሥር ሽህ ብር ብትሰጠው ሊቆጣህ ይችላል፤ ያሳዘነህ ምን ሆኖ እንደሆነ ማወቅ ይቀድማል ለማለት  ነው፡፡ ባጠፋሁ ይቅርታ …. እግዜር ካንተ ጋር ይሁን፤ ብርታቱንም ይስጥህ፡፡

 

ma74085@gmail.com

Filed in: Amharic