>

የመለስ አጓጉል ቱሩፋቶች...!!! (አሰፋ ሀይሉ)

የመለስ አጓጉል ቱሩፋቶች…!!!

አሰፋ ሀይሉ
አምናለሁ፡፡ የሰው ልጅ መልዓክ ሆኖ አልተፈጠረም፡፡ የሰው ልጅ የተባለ ሁሉ ክፉም በጎም ጎን አለው፡፡ መለስም ከዚህ የተፈጥሮና ፍጡራን ሎጂክ ውጭ አይደለም፡፡ መለስ እንደ መሪ ሲታወስ – እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ – ጥሩም እኩይም ጎን ይኖረዋል፡፡ ስለ መለስ ጥሩ ጎኖች – በዚሁ ፌስቡክ ላይ ብዙዎች ብዙ መልካም ቱሩፋቱን ሲያዥጎደጉዱለት ተመለከትኩ፡፡ በጎውን ጎን መርጠው ማንሳታቸው መሠለኝ፡፡ ምንም ተቃውሞ የለኝም፡፡ ነገር ግን በምሉዕነት አምናለሁ፡፡ የሰው ታሪክ ከበጎውም ከእኩዩም አቅጣጫ ታይቶ ምሉዕ ተደርጎ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ በመጨረሻ ክፉውንም በጎውንም አይቶ ስለ ሰውየው መፍረድ አንድም የታሪክ፣ አንድም የህዝብ፣ አንድም ደግሞ የፈጣሪ ተግባር ይሆናል፡፡ የእኛ ተግባር ሰውየውን ምሉዕ አድርጎ ብርታቱን ከነደካማ ጎኑ ማቅረብ ነው፡፡
እንዳልኩት ከሰሞኑ ብዙ የፌስቡክ ወዳጆቼ የመለስን በጎ ቱሩፋቶችና ተክለ ሰብዕና ግሩም አድርገው ስለዘከሩት ስለዚያ የምለው የለኝም፡፡ አንድም አንድን ሰው በፈለጋቸው ዓይነት መነፅር መመልከት፣ እና ምልከታቸውን ለታሪክ ጽፈው ማኖር መብታቸው ነው፡፡ ምናልባት በፍራቻ ተሰንገው ያደረጉት ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም የክፉ ቀን ወዳጆቻቸውን ላለማስከፋት ሊሆንም ይችላል፡፡ ምናልባትም ሙትን ላለመውቀስ አድርገውትም ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም የምስል ግንባታ ሥራቸውን ተግተው እየከወኑ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያታቸውም ሆነ ሞቲቫቸው ለእኔ ዋና ጉዳዬ አይደለም፡፡ ዋና ጉዳዬ እየቀረበ ያለውን የመለስ ምስል ምሉዕ ይሆን ዘንድ – ተመጣጣኝ የሆኑ አጓጉል ሰብዕናዎቹንና ሌጋሲዎቹን በአንክሮ መዘከር ነው፡፡ ምናልባት ወደፊት የታሪክ አጥኚዎች በዚህ ወቅት ስለ መለስ ዜናዊ ሰዎች ምን ዓይነት አስተያየት አሳድረው እንደነበረ ከማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሊያመሳክሩ ቢሹ – ግንጥሉን መልካሙን ቅዱሱን መለስ ብቻ ሳይሆን – እኩዩን መለስም ያዩና የተመለከቱ ሰዎች እንዳሉም ጭምር እንዳይረሱት – ቢያንስ ለታሪክ ሃቅ በማለት – የመለስን አጓጉል ቱሩፋቶች – እንደታዩኝና ብዙዎችም ሃሳቤን እንደሚጋሩኝ አድርጌ – እንደሚከተለው ዘርዝሬያቸዋለሁ፡፡
በቅድሚያ ግን በተለይ ከሞቱ በኋላ የመለስ መታወቂያ እየሆነ ስለመጣ አንድ የመለስ ገጽታ ወይም ስብዕና ላንሳ፡፡ እርሱም የመለስ ጀግንነት ነው፡፡ ብዙዎች መለስን ጀግና ነው ይሉታል፡፡ እንግዲህ ይሆን ይሆናል፡፡ ቢያንስ ነፍጥ አንስቶ የተዋጋ ነፍጠኛ (ባለ ነፍጥ) ነበርና ይሁንለት የመገዳደል እና ለመሞት የመቁረጥ ጀግንነቱ፡፡ ግን ይሄንንም ቢሆን የማይቀበሉት ብዙ የትግል አጋሮቹ አሁንም በህይወት አሉ፡፡ አቶ ስዬ አብርሃ አንዱ ናቸው፡፡ አሁን ነገሮችን ለማለዘብ ላይደግሙት ቢችሉም በአንድ ወቅት ግን ስለ መለስ ሲጠየቁ – ጀግናው ማን እንደሆነ እርሱን ራሱ ብትጠይቁት አይዋሽም፣ ጀግንነት አንሶን አይደለም ወደ እስርቤት የተወረወርነው፣ ለብዙ መርሆዎች ተገዝተን ነው – ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ በአውስትራሊያ የሚኖሩት አቶ ገብረመድህን አርአያ በበኩላቸው – መለስ ዜናዊ ኦፕሬሽን ምራ ተብሎ ታጋይ ጓዶቹን አስፈጅቶ እግሬ አውጭኝ ብሎ ሰው በሩጫም በበረራም ይደርስበታል ተብሎ በማይታሰብ ርቀት ላይ አምልጦ ተገኝቷል – ብለው በአንድ ወቅት እየማሉ እየተገዘቱ በፍርሃቱ ሲያስቁን ነበር፡፡ ቃላቸውን ይድገሙት አይድገሙት የኔ ጉዳይ ባይሆንም ቅሉ የአስመራው አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ደግሞ ሌላው ስለዚሁ የፈሪነት ባህርይ ተመሳሳይ ምስክርነትን የሰጡ እና አሁንም በሕይወት ያሉ ሰው ናቸው፡፡ ከዚህ በላይ ብዙ ልል አልፈልግም፡፡ ብቻ ‹‹ጀግና.. ጀግና…›› እያልን ሰውን ስንገልጽ – ይህንንም ገጽታ አንርሳው ለማለት ያክል ብቻ ነው፡፡
በበኩሌ የመለስን የጦርሜዳ ጀግንነት ለትግል አጋሮቹና ለታሪክ ፍርዱን ትቼ ማተኮር የምፈልገው መለስ በዘመኑ በእኩይነት ስለጀገነባቸው ብዙ ተነግረው በማያልቁ ጀግንነቶቹ ላይ ነው፡፡ አሁንም ግን ቀደም ብዬ ያልኩትን ልድገመው፡፡ መለስ ዜናዊ በሌሎች ነገሮች ሲመዘን ለብዙዎች ጀግና ሆኖ ተገኝቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ያን ብዙዎች ከሰሞኑ ጭምር ብዙ ብለውለታል፡፡ ያ የእኔ የትኩረት አቅጣጫ አይደለም፡፡ አሁን በቀጥታ የማወሳው መለስ የጀገነባቸውን እኩያን ትሩፋቶቹ ላይ ነውና፡፡
1ኛ/ የዩኒቨርሲቲን የተከበረ ቅጽር የደፈረ ጀግና
መለስ ገና ከበረሃ ትግል ወጥቶ በአዲሳባ የሚገኘውን የምኒልክን ቤተመንግሥት እንደያዘ ሮጦ የሄደው ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደነበረ ብዙዎቻችን የምናውቀው ነው፡፡ ምናልባት በእነ ዋለልኝ ዘመን በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የለውጥ መፈክር በሚጮህበት ዘመን ከዩኒቨርሲቲ የሸፈተ ሰው ስለነበረ – አሁንም – በአበባየሆሽ ጊዜ የደነቆረች፣ ሁልጊዜ ዘፈኑ ሁሉ አበባየሆሽ ይመስላታል እንደሚባለው – መለስም ከዩኒቨርሲቲ የጠበቀው የድሮውን የእርሱን ዘመን በዘር ትያቄ የሰከሩ የዋለልኝ ምርኮኛ ወጣቶች ነበር እና በግራና በቀኝ አበባና ዘንባባ እየበተኑ እንደ ጀግናቸው የሚቀበሉት መስሎት ይመስለኛል እንዲያ ሰፍ ያለው፡፡
 መለስ ግን በተለይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጠበቀው ቀርቶ በወጉ ታገልኩ ለሚለው የጀግንነት ሥራ አሌ ብሎ ጆሮውን የሚሰጠው ተማሪም ምሁርም አጣ፡፡ ጭራሽ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ጋሻው የኤርትራን መገንጠል፣ ሻዕቢያንና ወያኔን እና የአሜሪካን ጣልቃገብነት ተቃውመው በአደባባይ ጮኹ፡፡
እና መለስ በዚያ ባልጠበቀው የዩኒቨርሲቲ ምላሽ እጅጉን የተበሳጨ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ማንም የኢትዮጵያ መሪ አድርጎት የማያውቀውን – ሀገሪቱ አለኝ የምትለውን አንጋፋ የአካዳሚክ ተቋም – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ታጣፊ ክላሽ ባነገቡ የአርሶ አደር ሠራዊቶች በመውረር – በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋና አፈና አካሄደአ፡፡ ብሎም ኢትዮጵያ ለዘመን አምጣ ያፈራቻቸውን 40 ዕውቅ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን – ብዙ ፕሮፌሰሮችን – ብቃት የላችሁም እያለ – በድፍረትም በድድብናም ጀግኖ – ከዩኒቨርሲቲ በአንዴ አባረራቸው! ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቤተመንግሥታቸውን ለዩኒቨርሲቲ መማሪያ እንዲሆን የሰጡ መሪ ነበሩ፡፡ ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም የራሱን የፖለቲካ ት/ቤት በመኢሶኖች ተደግፎ በዩኒቨርሲቲው ያቋቁም፣ የካድሬ ምሁራንን ያስጠጋ፣ እና ሌላውን ያንጓጥጥ እንጂ – እንዲህ ዓይነት ዓይን ያወጣ የመሃይም ተግባር አልፈጸመም፡፡ እና መለስ ዜናዊ – በዚያ ወራዳ ተግባሩ – የመጀመሪያውም – ምናልባትም የመጨረሻውም – ዩኒቨርሲቲን የደፈረ ጀግና ሆነ!
2ኛ/ ድንቁርናን ሀገራዊ ፖሊሲ ያደረገ ጀግና
ለማንኛውም የሙያ መስክ የራሱ የሰለጠኑ እና ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች አሉት፡፡ አንድን ሙያዊ ዕውቀት የሚያስፈልገው ተቋም መምራት ያለበትም በሙያው አንጋፋ ደረጃ ላይ የደረሰ የሙያው ሰው እንደሆነ ካላበድን በቀር ምንም የሚያጠያይቅ ነገር አይደለም፡፡ መለስ ዜናዊ ግን ያደረገው የዚህን ተቃራኒ ነበረ፡፡ ደናቁርት የሀገሪቱን ማናቸውንም ተቋም መምራት እንደሚችሉ – በተግባር ታማኝ ሎሌዎቹን በየተቋማቱ እንደራሴ አድርጎ በመሾም የገለጸ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሪ ነው መለስ፡፡ ኢትዮጵያዊ ከተባለ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙዎች – የትግል ጓዶቹ ሳይቀር – ኢትዮጵያዊነቱን ደጋግመው በጥያቄ ምልክት ውስጥ አስገብተው እኛም እንድናስገባው አሳስበውናልና፡፡ እና መለስ ዜናዊ በገነት ዘውዴ አልነበረም ድንቁርናን ሀገራዊ ፖሊሲ መሆኑን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበሰረው፡፡ የእርሷ ስም የገነነው ለትምህርት ሚኒስትርነት የታጨች በመሆኗ ነበረ፡፡
የትምህርት ሽፍታ የትምህርትን ሚኒስቴር የሚያህል የሀገሪቱን የጥበብ ተቋም እንዲመራ ሲደረግ – እና መማር አስፈላጊ መስፈርት አለመሆኑ በመለስ አፍ በአደባባይ እና በከፍተኛ ድፍረት ሲታወጅ – እና ገበሬም ቢሆን የኢህአዴግን ፖሊሲ እስካስፈጸመ ድረስ የትምህርት ሚኒስትር እናደርገዋለን ተብሎ ሲለፈፍ – ያኔ ነው – ድንቁርና የኢህአዴጓ ኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሀገራዊ ፖሊሲ መሆኑ በግልጽ የተረጋገጠው፡፡ ወይም የተወሰኑ የሚጠራጠሩ ሰዎች ጥርጣሬያቸው የተገፈፈላቸው፡፡ ይሄ ሃገራዊ የድንቁርና ፖሊሲ ቀጥሎ – በመጨረሻ የወያኔ/ብአዴን ካድሬው ተፈራ ዋልዋ – የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ ተቋም መሥራችና መሪ ተደርጎ ተደመደመ፡፡ አይ እፍረት! አይ ውርደት! እንዴት የፊዚክስን፣ የስፔስ ሳይንስን ሀ እና ፐ ለይቶ የማያውቅ ሰው የአንድ ሀገር የስፔስ ሳይንስ መሪና ተንታኝ ይሆናል? የአሁኑ የኢህአዴግ ተረኛ መሪ አብይ አህመድ ራሱ ያንኑ የድንቁርና ሌጋሲ ተከትሎ – በአደባባይ በቲቪ በቀረበ ዝግጅት ሚኒስትሮቹን ሰብስቦ – ማንም ሰው የትኛውም ቦታ ተመድቦ ከተቋም ተቋም እየተቀያየረ በከፍተኛ ኃላፊነት ማገልገል ይችላል – እያለ ሲደሰኩር ነበር፡፡ ከመንፈስ አባቱ ከመለስ ዜናዊ ያገኘውን ሀገራዊ የድንቁርና ፖሊሲ እያስቀጠለ መሆኑን – ለሚከታተሉት የወያኔ አለቆቹ እያረጋገጠላቸው መሰለኝ፡፡ እንጂ ሌላ በምን ሎጂክ ይገለጻል ይሄ? ለማንኛውም ከብዙ በጥቂቱ – መለስ ዜናዊ – በዚህና በሌሎች ሺህ ዓይነት መሰል ድርጊቶቹ – ድንቁርናን ሀገራዊ ፖሊሲ ያደረገ ጀግና መሆኑ ፈጽሞ የማይካድ እና በተግባር የተገለጠ እና የቀጠለ ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ነው!
3ኛ/ ቤተክርስትያንን የደፈረ ጀግና
መለስ ዜናዊ ቤተክርስትያንን መድፈር የጀመረው የምኒልክን ቤተመንግሥት ከወያኔ ጭፍሮቹ ጋር ከተረከበ በኋላ አይደለም፡፡ ከ1983 እጅግ ቀደም ብሎ ነው፡፡ ለዚህ ብዙ ማስረጃ መጥቀስ ሳያስፈልገኝ የወያኔውን የቀድሞ ታጋይ የዶ/ር አረጋዊ በርሄን የዶክትሬት ጥናት ጽሑፍ ብቻ መጥቀሱ በቂ ነው፡፡ አረጋዊ በርሄ – በወያኔ አፍላ ዘመን ጀምሮ – የቤተክርስትያንን የምንኩስና ገዳማትና የተከበሩ ቤተመቅደሶች ሳይቀር – በወያኔ ካድሬ ደቀመዝሙሮች የመሙላት ሥራ እንዴት በዘመቻ መልክ እንደተሰራ፣ እንዴት ህወሃት ፀረ-ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀገራዊ የትግል እንቅስቃሴ እንዳደረገ፣ እንዴት አድርጎ በ70ዎቹ ብዙዎቹን የትግራይ ቤተክርስትያናት ለህወሃት ባደሩ ቀሳውስት እንዳጥለቀለቃቸው፣ እንዴት አድርጎ ሃሳዊ የእስልምና አስፋፊ፣ እና መናፍቃዊ የክርስትና አቆርቋዥ አብዮታዊ አቋም እንደያዘ በሚገባ ስም እና ቦታ ጭምር እየጠቀሱ አስቀምጠውልናል፡፡ ለዚህ የታሪክ ሀቅ እማኝነታቸው እኚህ ሰው በታሪክ ተገቢ ስፍራ ላይ ሲመሰገኑ እንደሚኖሩ በበኩሌ ጥርጥር የለኝም፡፡
የሆነ ሆኖ ወያኔ አዲስ አበባ ስትገባ፣ መሪዋ መለስ ዜናዊ ቤተክርስትያንን ለመጀመሪያ ጊዜ የደፈረው ‹‹ወዳጅ›› መስሎ ነው፡፡ የደርግ መንግሥት ከቤተ ክርስትያንና ከፓርላማ አጠገብ በመሆኑ ምክንያት ነው በሚል የፀጥታ ምክንያት ግንብ ገንብቶ ያጠረውን የቅድሥት ሥላሴ ቤተክርስትያን መግቢያ ቅጽር – መለስ ዜናዊ እንደ በርሊን ግንብ በማፈራረስ ጀመረ ቤተክርስትያንን መድፈር፡፡ ብዙዎች አጨበጨቡለት፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም የዘጋውን ቤተክርስትያን መለስ ዜናዊ ከፈተው፡፡ ፖለቲካውን መታ፡፡ ግን ወዲያው ደርግን ደግፈዋል – የኢትዮጵያን አንድነት ሰብከዋል ብሎ ጥርስ የነከሰባቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ብቸኛ ህጋዊ ጳጳስ – አዋርዶ፣ ዘርጥጦና አዋክቦ ከሀገር አባረራቸው፡፡ ጳጳስ በሕይወት እያለ ሌላ ጳጳስ መሾም በቤተክርስትያኒቱ ለዘመናት የቆየ በፍጹም የማይደፈር ቀኖና ነበረ፡፡ ቀኖና የማያውቀው፣ እግዜርም የሌለው መለስ መጣና – አቡና መርቆርዮስ በሕይወት እያሉ – ከአድዋ የአክሱም ወጬጌ ያደረጋቸውን የወያኔ ዶክተር አምጥቶ ጳጳስ አድርጎ ቀብቶ ሾማቸው፡፡ ቤልጂያኖችንና ኔዘርላነዶችን ሳይቀር በጉልበት ሰራተኝነትና በአናጢነት ከአውሮፓ ድረስ አስመጥቶ – የኢዮቤልዩን ቤተመንግሥት የሚስተካከል የጳጳስ ቤተመንግሥት ሠራላቸው፡፡ እና ቤተክርስትያንን በቀደመ የህወሃት ትግል መስመር የካድሬ መፈንጫ አደረጋት፡፡ በዓለም የታወቀው – እና በህገመንግሥቱ የሰፈረው – የሐይማኖትና የመንግሥት መለያየት መርህ – በወያኔው መሪ መለስ ዜናዊ – በጠራራ ፀሐይ ተጣሰ፡፡ መንግሥትንና ሐይማኖትን የሚለየው ግንብ ተፍረከረከ፡፡ ለበጎ ቢሆን ጥሩ፡፡ ለክፋት፡፡ እና ቤተክርስትያኒቱን ለወያኔ/ኢህአዴግ ለማሳደር፡፡ በጥቅም የተሳሰሩ ሎሌዎችን ለማርመስመስ፡፡ እና ፈሪሃ እግዜርን ከቤተመቅደሶቿ ለማጥፋት፡፡ እና ስያሜው ላደረጋቸው ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው አጽራረ ቤተክርስትያን ድርጊቶች ቢያንስ እንጂ ፈጽሞ አይበዛበትምና አሁንም እንለዋለን – መለስን – ቤተክርስትያንን የደፈረ መሪ!
4ኛ/ የኢትዮጵያን ህዝብ አንጡረ ሃብቶች ለመዝባሪዎች አሳልፎ የሰጠ ጀግና
በመለስ ዜናዊ የሀገር አስተዳደር ዘመን ብዙ ከሥርዓቱ ጋር በጥቅም የተሻረኩ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ሀገሪቱን እንደተራበ ጥጃ ሙልጭ አድርገው አልበዋታል፡፡ ከሼክ መሀመድ አልአሙዲ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የመንገድ ተቋራጮች፣ ከቻይናና አሜሪካ የማዕድን አውጪዎች ጀምሮ፣ እስከ አረብ ሃገራርና ሩቅ ምስራቅ ኢንቬስተሮች ድረስ – የመለስ መንግሥት የሀገሪቱን የከበሩ ማዕድናት፣ የከበሩ ድንጋዮች፣ ወርቅና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ምርት ሊሰጡና ሕዝቡን ሊያገለግሉ፣ ሊመግቡ፣ ሊያለብሱ፣ ኑሮውን ሊያሻሽሉ ይችሉ የነበሩትን ብዙ ብዙ የልማት አውታሮች – በጥቅም ለተሻረኩ የወያኔ ጋሻጃግሬዎቹና ከሥርዓቱ ጋር እጅና ጓንት ሆነው ለተሻረኩ የውጭ ባለሀብቶች በመስጠት – የቻለውን ያህል የሀገሪቱን ሕዝብ አንጡረ ሃብት – ለግል ጥቅም ህይወታቸውን ለሰጡ የሥርዓቱ ሆዳም ሎሌዎችና ለሀገር አቋራጭ ብዝበዛ ለተሰማሩ የውጭ ነጋዴዎች አንድም ሳይቀር አከፋፍሎ ሕዝቡን የበዪ ተመልካች አድርጎት ኖሯል፡፡
እንዴት ከገበሬ መሀል ነው የወጣሁት፣ አርሶ አደሩ ነው መሠረቴ የሚል፣ ኮሚኒስታዊ ርዕዮተዓለም ውስጤ ነው የሚል ቡድን – እንዴት እንዲህ ያለ ጭካኔን በድሃው ህዝብ ላይ ያሳድራል? እንዴት ከደሃው ህዝብ ጉሮሮ ላይ፣ እና ከቀጣይም ትውልዶች ጉሮሮ ላይ እየነጠቀ – አብጠው ሊፈነዱ ለደረሱ አጋሰስ ባለሀብቶች የሀገሪቱን ማዕድናትና የተፈጥሮ ሀብቶች ሙልጭ አድርጎ ያዘርፋል፣ እና አብሮ በዝርፊያ ላይ ይሰማራል? ይሄን ማወቅ የሚችለው አንድዬና መለስ ዜናዊ ብቻ ነው፡፡ በግሌ እንኳ በዓይኔ በብረቱ አይቼ ከማውቀውና ከነማስረጃዎቹ ዘርዝሬ መጥቀስ ከምችለው ብጠቅስ – ከጎንደር ላይ ነጥቆ – ምዕራባዊ ትግራይ ብሎ በሰየመው በረሃ ሳይቀር – ሀገር ምድሩን ለጥቂት ውጭ ላኪ የህወሃት ተሻራኪ ኢንቬስተሮች አከፋፍሎ ሰጥቶ – ድሃው የትግራይ ሕዝብ – ሌላ ቀርቶ ታጋይ የነበሩና ቤተሰቦቻቸውን በበረሃ አርሰው፣ ፍየል አርብተው ለማብላት የሚፍጨረጨሩ ምስኪን ድሆችን ደም እንባ እያስለቀሰ – እንዴት የህሊና ሰላም አግኝቶ ሥልጣንን የሙጥኝ ብሎ መኖር እንደሚችል ላሰበው እጅግ የሚገርም ነው፡፡ ሌላ ሌላው – አማራውና ኦሮሞው፣ ጋምቤላው፣ አፋሩ ቤኒሻንጉሉ ላይ ያደረሰው መከራና ሙልጭ ያለ የአንጡረሃብት ቅሚያና ዝርፊያማ ምኑ ይነገራል? ራሱን የቻለ ትልቅ መጽሐፍ ይወጣዋል! እንዴት ደሃውን ወገንኩ የሚል መሪ – በመሐል አዲሳባ ተበድረው ተለቅተው የሚኖሩ ድሆችን ከቤታቸው አፈናቅሎ በትኖ – የሀብታም መዝናኛ ያስገነባል? ዓይን ያወጣ አረመኔነት ካልሆነ በቀር ምን ይሉታል ይሄን? ኢትዮጵያዊነቱን ቢጠራጠሩ እኮ ወደው አይመስለኝም! እንዲህ ያለ እልል ያለ ህዝብን ራቁቱን በድህነት አስቀርቶ የመዘበረ – እና ለዚያም ምንም የህሊና ተጠያቂነት የማይሰማው – የምዝበራ ጀግና ነበር መለስ!
5ኛ/ በኢትዮጵያ 50ሺኅ ወጣት ደም ላይ የቀለደ ጀግና
የባድመን የእርሻ መሬት ኤርትራ ወረረችብኝ በማለት በተጀመረው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከሁለቱም ወገን ያለቀውን ወጣት ቁጥር ብዙ ዓለማቀፍ ታዛቢዎች – 70ሺህ ያደርሱታል፡፡ 70 ሺህ ያደርሱትና – ዘ ሴንስለስ ዎር ብለው ይጠሩታል! ትርጉም የማይሰጥ ጦርነት – ለከንቱ የፈሰሰ ደም – እያሉ፡፡ ለምን እንዲህ ሊሉት ቻሉ? ምክንያቱም ሥፍራዋ ያ ሁሉ ደም ሊፈስላት የምትገባ መሬት አልነበረችም በማለት፡፡ ምክንያቱም ምንም ዓይነት ፋይዳ ለህዝባቸው የምታመጣ ሥፍራ አይደለችም በማለት፡፡ እና የጦርነቱን ውጤት በማየት፡፡ ሲጀመር – የኢትዮጵያ ህዝብ ለዓመታት የደማለትን የኤርትራን ክፍለ ሀገር በሙሉ ከነባህሩና ከነደሴቶቹ – ያለ አንድም የይገባኛል ጥያቄ – ለሻዕቢያ እያጨበጨበ የሰጠ እንደ መለስ ያለ ፀረ-ኢትዮጵያ መሪ – እንዴት ባለ መርህ ቢመራ እና ምንስ ህልም ቢታየው ነው – ቁራሽ መሬት ሻዕቢያ ወሰደችብን ብሎ – ወደ ጦርነት እንግባ ሲባል – አሜን ብሎ ተቀብሎ – ቁራሽ መሬት ለማስመለስ የኢትዮጵያውያንን ደም ለመገበር ፊት መሪ ሆኖ የተሰለፈው? ማንም የሚያውቅ የለም መልሱን፡፡ መለስ በግሉ የኤርትራን ጦርነት ተቃውሞ እንደነበረ – ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በጻፉት መጽሐፋቸው ገልጠውልናል፡፡ ይሁንና አምነን እንቀበል ይባል፡፡ ነገር ግን ጦርነቱን አላምንበትም ያለ ሰው – ሥልጣኑን ለቅቆ – ከዚህ ቀደም ለምን የባህር በር አጣን ላሉ ኢትዮጵያውያን እንደመለሰው – መንገዳችሁን ጨርቅ ያድርግላችሁ፣ እኛ በበኩላችን ጦርነት መርሮናል፣ ሰልችቶናልና ከዚህ በኋላ ጠብመንጃ አንስተን አንዋጋም – ብሎ አርፎ መቀመጥ ነበር፡፡
ነገር ግን ይህን ካደረገ የሞተላት የተጋደለላት ሥልጣን ከእጁ ልትወጣ ነው፡፡ ስለዚህ በማዕከላዊነት ሰበብ – የጋራ ውሳኔውን ተቀብያለሁ ብሎ – ጦር ግንባር ድረስ ሄዶ ጦሩን በመቀስቀስ – እና ጦርነቱ ሲለኮስ – ፍጥነት! ፍጥነት! ፍጥነት! ባለ በሌለ ኃይል ፍጥነት! አሁንም ፍጥነት! እያለ ያን ሁሉ ኢትዮጵያዊ ወጣት የሻዕቢያ ፈንጂ ማምከኛ አድርጎ ሲያበቃ – በመጨረሻ አምላኬ አሜሪካ ተመለስ አለችኝ ብሎ – በደሙና ወደር በሌለው መስዋዕትነት አሸንፎ ጠላትን ወደ ማሳደድ የገባውን የኢትዮጵያን ጦር – ያለምንም ምክንያት ደሙን በበረሃ እንደፈሰሰ መና አስቀርቶ – ቀኝ ኋላ ዙር! የሚል ትዕዛዝ የሰጠ – በኢትዮጵያውያን ደም የቀለደ ደም-አይጠግቤ ሰው ነበረ መለስ ዜናዊ፡፡ በነገራችን ላይ ከፆረና ግንባር የመጡ የቅርብ ዘመዶች ነበሩኝ፡፡ ሲነግሩኝ – በመለስ ወደመጣችሁበት ተመለሱ ሲባል – በሥፍራው የሆነው በእውነቱ እጅግ ያሳዝናል፡፡ የመለስን ትዕዛዝ አንቀበልም ያሉ መኮንኖችና ወታደሮች ነበሩ፡፡ በእንባ ስቅስቅ ብለው የተራጩ ወታደሮች ነበሩ፡፡ ተመለስ-አልመለስም በሚል እርስ በእርስ የተተኳሶሱና የተፋጁ ነበሩ፡፡ በባድመ፣ ሽራሮ፣ ዛላምበሳ፣ ቡሬ፣ እና በሌሎችም በርካታ አውደ ግምባሮች የሆነው ከጾረናው የማይተናነስ እንደነበረ ብዙዎች በሀዘን ያወሱታል፡፡ ያን በከንቱ የፈሰሰ የወገን ደም የተቃወሙ እና ለምን ብለው የጠየቁ ኢትዮጵያውያን ለእስር፣ ለርሸናና ለስንብት የተዳረጉም ነበሩ፡፡
እና መለስ ያን ሁሉ ሀገሬን ያለ ኢትዮጵያዊ ወጣት፣ ያን ሁሉ ቃል የገባለት የመለዮ ግዴታ ይዞት የዘመተ ኢትዮጵያዊ ሠራዊት ሁሉ ደሙን በከንቱ አፍስሶ – እርሱ ባቋራጭ ሄዶ – ከኢሳያስ ጋር አልጄርስ ላይ ደም የፈሰሰለትን መሬት በሰላም አስረክቦ መጣ!! የዚያን ሁሉ 50 ሺህ ኢትዮጵያውያን ደም በከንቱ አፍስሶ መሬቱን አስለቅቆ ፈርሞ ይግባኝ ለሌለው ችሎት አስረከበ፡፡ እና ደግሞ ይግባኝ የሌለው ውሳኔ ሲወሰንበት – ዳግም የኢትዮጵያውያንን ደም ለማፍሰስ – በተለያየ ሰበብ አስባብ አሁንም መሬቱን አላስረክብም ብሎ የሙጥኝ! እንዴ? ምን ዓይነት ደም-ጥማት ነው ግን ይሄ?!! በዚህ ብቻ ቢያበቃም እኮ ጥሩ ነው! እስካሁን የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው የወያኔው የቀድሞ ታጋይ ስዩም መስፍን ራሱ በቀጥታ በግሉ ትዕዛዝ የኢትዮጵያን ሕዝብ ባድመ ለእኛ ተፈርዶልናል ብሎ በውሸት ዜና ያስጨፈረ ለማስመሰል – መለስ ዜናዊ እጁን እንደ ጲላጦስ ከደሙ አጥቦ – ሁሉንም ነገር በስዩም መስፍን ላይ አላክኮበት ቀረ፡፡ ይኸው እስከዛሬም – ስዩም መስፍን ኢትዮጵያውያንን በውሸት አስጨፈረ የሚል እንጂ – በመለስ መሪነትና ትዕዛዝ – የኢትዮጵያ ሕዝብ በከንቱ የገበረው ደም ሳያንስ – በከንቱ እና በውሸት ሲያስጨፍረው ከረመ – የሚል ሰው አይሰማም! እውን ይህ ሰው ግን – እውን ኢትዮጵያዊ ነበር? እነርሱ እንደሚሉት… ትግራዋይስ ነበር? አላውቅም! I don’t know! ጦርነትን ደግሶ ያለፈ መሪ – በኢትዮጵያ 50ሺኅ ወጣት ደም ላይ የቀለደ ጀግና ግን እለዋለሁ – በድፍረት! ድፍረት ከሆነብኝም ይሁንብኝ! አሁንም ደግሜ እለዋለሁ!
(…/ ይቀጥላል)
Filed in: Amharic