>

በኢትዮጵያ ‹‹ሕገመንግሥታዊ›› ሥርዓት.. እውን መንግሥትና ሐይማኖት ተለያይተዋል? ( አሰፋ ሀይሉ)

በኢትዮጵያ ‹‹ሕገመንግሥታዊ›› ሥርዓት.. እውን መንግሥትና ሐይማኖት ተለያይተዋል? 

አሰፋ ሀይሉ
 
* እውን የዳኝነት ነጻነትስ አለ? ወይስ ምን?
 
ጽሑፌ ሦስት ግልጽና አጭር ዒላማዎች ላይ ያተኮረ ነው፡-
 
1ኛ/ በወያኔ-ኢህአዴጓ ኢትዮጵያ በሃሳብም በተግባርም መንግሥት እና ሐይማኖት እንዳልተለያዩ ለማሳየት፣
 
2ኛ/ የወያኔ-ኢህአዴግ ‹‹ሕገመንግሥት›› የሐይማኖታዊ ዳኝነትን መንግሥታዊ ተቋማዊ ቅርጽ እንደሰጠውና ኢ-ተገቢነቱን ለማሳየትና፣
 
3ኛ/ በወያኔ-ኢህአዴጓ ኢትዮጵያ የዳኝነት ነፃነት በሃሳብም በተግባርም እንደሌለ ለማሳየት ነው፡፡ 
_________________
1ኛ/ በወያኔ-ኢህአዴጓ ኢትዮጵያ በሃሳብም በተግባርም መንግሥት እና ሐይማኖት እንዳልተለያ
የወያኔ-ኢህአዴግ ህገመንግሥት ተብዬ – በአንቀጽ 11 ላይ ‹‹መንግሥት እና ሐይማኖት›› ተለያይተዋል – በማለት ያውጃል፡፡ ወይም ይደሰኩራል፡፡ መንግሥት የሚያፀድቀው ወይም በመንግሥት መመሪያ የሚተገበር ሐይማኖት እንደሌለም ያሰፍራል፡፡ ከዚያም አልፎ መንግሥት በሐይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ እንደማይገባና፣ ሐይማኖትም በመንግሥት ጉዳዮች ጣልቃ እንደማይገባ ይገልጻል፡፡ ይህ ፍፁም ኩሸት መሆኑን ብዙም ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገኝ በዚያው በህገመንግሥት ተብዬው ላይ ስላለ እጠቅሰዋለሁ፡፡ ይሄው ሕገመንግሥት ይሄንኑ ባለበት አፉ – ዝቅ ብሎ ቃሉን ይሽረውና በአንቀጽ 78 (በንዑስ አንቀጽ 5) ላይ ‹‹ሐይማኖታዊ ፍርድ ቤቶች በዚህ ህገመንግሥት መሠረት እውቅና አግኝተው ይደራጃሉ››!
እንደዚህ እንደኛ ሀገር ህገመንግሥት ተብዬ በሳቅ ፍርስ የሚያደርግ ህገመንግሥት በዓለም ላይ ተፈልጎ የሚገኝ አይመስለኝም! ከመንታ ምላሶቹ በአንዱ – መንግሥት ከሐይማኖት ጋር ተለያይቷል፣ መንግሥት በሐይማኖት ጣልቃ አይገባም ይልሃል፡፡ በመንታው ምላሱ ደግሞ – የሐይማኖታዊ ፍርድቤት በህገመንግሥቱ እውቅና ተሰጥቶታል፣ በመንግሥት ይደራጃል ይልሃል! ምን ዓይነት ቀልድ ነው ይሄ? – አላውቀውም! ዋናው ዓላማዬ መንግሥትና ሐይማኖት እንዳልተፋቱ – እንዲያውም እንደ አዲስ እንደተጋቡ – ለማሳየት ነውና ወሬዬን በዚሁ ቀጨሁት!
2ኛ/ የወያኔ-ኢህአዴግ ‹‹ሕገመንግሥት›› የሐይማኖታዊ ዳኝነትን መንግሥታዊ ተቋማዊ ቅርጽ እንደሰጠውና ኢ-ተገቢነቱ
ከላይ እንዳቀረብኩት – የወያኔ-ኢህአዴግ ሕገመንግሥት ተብዬ ሐይማኖታዊ ዳኝነትን መንግሥታዊ ቅርጽ ሰጥቶ ለማደራጀት ቃልኪዳን የተገባበት ሰነድ ነው! ይህን – ከሕገመንግሥት ተብዬው ወጣ ብሎ የሚያስተውል ሰው – ታዲያ – የወያኔ-ኢህአዴግ ካድሬዎች (ከአውራው ከመለስ ጀምሮ) ቀንና ሌሊት ሲያዜሙት የማይጠግቡትን በንጉሡ ዘመን – ሐይማኖት የመንግሥት ዕውቅና ተሰጥቶት በህገመንግሥት ተቀመጠ እያሉ ቡራከረዩ ማለታቸውን ምን አመጣው? – ብሎ መገረሙ አይቀርም፡፡ እርግጥ ነው – የወታደራዊው መንግሥት ያወጣው – የኢህዲሪ ህገመንግሥት – መንግሥትና ሐይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን በሃሳብም የደነገገ በተግባርም የገለጸ መንግሥት ነበረ፡፡ የወያኔ-ኢህአዴግ ህገመንግሥት ግን ሐይማኖትና መንግስት ተለያይቷል እያለ መንግሥታዊ የሐይማኖት ዳኝነት ተቋም ህገመንግሥታዊ ዕውቅና ሰጥቶ አደራጃለሁ ብሎ ተነሳ፡፡
የመለስ ዜናዊ የወያኔ ኢህአዴግ መንግሥት ከንጉሡ መንግሥት የሚለየው – በመንግሥት ዕውቅና ሰጥቶ ባደራጀው የሐይማኖት ተቋም አይነት ብቻ ነው፡፡ ቀኃሥ የኦርቶዶክስን ቤተክርስትያን ጳጳስ ንጉሡን ካልቀቡ ንግሥናው አይፀድቅም የሚል ህገመንግሥት አውጀዋል፡፡ ግን ሐይማኖትን መንግሥታዊ ተቋም አድርገው ዳኝነት ሥራ ውስጥ እንዲገባ አላደራጁትም፡፡ ደርግም ይሄንን አላደረገም፡፡ መለስ ዜናዊ ግን ይሄን ሊያደርግ ተነሳ፡፡ እና የጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት የሚባል – የመንግሥት የእስልምና ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ ምድር ህጋዊም ህገመንግሥታዊም እውቅና ሰጥቶ አቋቋመ፡፡ መንግሥት ከሐይማኖት በተለየበት ሀገር – እንዴት መንግሥት ሐይማኖታዊ ፍርድ ቤት ያቋቁማል? የኢትዮጵያ መንግሥት ሴኪዩላር – ማለትም ዓለማዊ – መንግሥት ነው? ወይስ ሃይማኖታዊ? – መልሱን የሚያውቀው ህገመንግሥቱን የጻፈውና ያስፃፈው የወያኔ-ኢህአዴጉ ቁንጮ መለስ ዜናዊ ብቻ ይመስለኛል!
መለስ ዜናዊ – በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ውስጥ ከዓለማዊው እና ለሁሉም በገለልተኝነት ከሚሠራው መደበኛ የዳኝነት አካል በደባልነት – መንግሥታዊ የሸሪዓ ፍርድ ቤት ማቋቋሙ ብቻ እኮ አይደለም የሚገርመው! የሚገርመው ብዙ ነው፡፡ በበኩሌ እጅግ ከሚገርሙኝ ነገሮች መካከል አንዱ – ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሕዝብ ላይ ከሚሰበሰብ ታክስ ላይ እየተመዠረጠ – በየዓመቱ ለሸሪዓ ፍርድ ቤት የሚመደበው በሚሊዮን የሚቆጠር መንግሥታዊ ባጀት ነው!
ሌላ ሌላውን ትቼ – በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣው የፌዴራል መንግሥቱ ዓመታዊ ባጀት ላይ የ2 ተከታታይ ዓመት የባጀት ምደባዎችን በምሳሌነት ልጥቀስ፡፡ በእነዚህ ማንም ሰው አራት ኪሎ ብርሃንና ሰላም መደብር ሄዶ ገዝቶ ሊያመሳክረው የሚችላቸው የመንግሥት ባጀት ታትሞ ከወጣባቸው የነጋሪት አዋጆች መካከል – የምርጫውን ግርግር ተከትሎ በነበረው የ1999 ዓመተ ምኅረቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት ዓመታዊ ባጀት ውስጥ – ለፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት የተመደበው ባጀት ብር 1,569,300 (አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ስድሳ ዘጠኝ ሺህ ሶስት መቶ ብር) ነበረ፡፡ በተከታዩ ዓመት በ2000 ዓመተ ምህረት ላይ ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት ለሐይማኖታዊው የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት የመደበው ዓመታዊ በጀት በእጥፍ ገደማ አድጎ ብር 2,756,100 (ሁለት ሚሊየን ሰባት መቶ ሃምሳ ስድስት ሺህ አንድ መቶ ብር) ያሳያል፡፡ ሌላ ሌላውን አልገባበትም፡፡ ጉዳዩን ለሚያጠና ተመራማሪ እንዲጨነቅበት እተወዋለሁ!
ይሄ ማለት ምን ማለት ነው? በመለስ ዜናዊዋ ኢትዮጵያ ከቀኃሥ ዘመነ መንግሥት ወዲህ የተደረገው ለውጥ – ካርታውን በውዞ – አንዱን ሐይማኖት በሌላው መተካት ብቻ አይደለም – ለአንድ ሐይማኖታዊ ተቋም የህገመንግሥት ዕውቅና መስጠት ብቻ አይደለም – በመንግሥት ማደራጀት ብቻም አይደለም – በመንግሥት ባጀት እየተመደበ የእስልምና ሐይማኖት የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች እንዲንቀሳቀሱ ተደርገዋል ነው!  – እና በመለስ ዜናዊዋ የኢህአዴጓ ኢትዮጵያ – መንግሥትና ሐይማኖት ተለያይተዋል? ሌሎችስ ሐይማኖቶች በዳኝነት ሥራ ውስጥ ጣልቃ ገብተው ሃይማኖታዊ የዳኝነት አካል እንዲያቋቁሙ ይፈቀድላቸዋል ወይ? ኢትዮጵያ ውስጥስ መንግሥት የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን የሚያቋቁመው በምን ምክንያት ነው? ኢትዮጵያ እንደ ሣዑዲ አረቢያ እስልምና የመንግሥት ሐይማኖት የተደረገባት አረባዊት ሀገር ነች ወይ? የኦፔክ (የነዳጅ ላኪ ሀገራትስ አባል ነን ወይ?).. ሀሀሀሀሀሀ…!!! ከዚህ በላይ አልሄድበትም፡፡ እዚሁ ላይ ተቆጥቤ ምሳሌዬን በሰነዘርኳቸው ጥያቄዎቼ እቋጨዋለሁ፡፡
____________________
3ኛ/  በወያኔ-ኢህአዴጓ ኢትዮጵያ የዳኝነት ነፃነት በሃሳብም በተግባርም እንደሌለ
የዳኝነት ነጻነት በይስሙላ ደረጃ – በኢትዮጵያ የወያኔ-ኢህአዴግ ህገመንግሥት ተብዬው በአንቀጽ 78 ላይ ተደንግጎ እናገኛለን፡፡ ሁሌ የሚገርመኝ የዚህ አንቀጽ ርዕሱ ነው፡፡ ርዕሱ ‹‹የዳኝነት ነፃነት›› ነዋ የሚለው፡፡ እና በሳቅ ያፈነዳኛል፡፡ የዳኝነት ነፃነት በሌለበት ሃገር – ርዕስ ሆኖ ገጽ ማባከኑ – በእርግጥ ያበሽቃል እንጂ አያስቅም፡፡ ግን አንዳንዴ ካልሳቅክበት ሁሌ አርረህ ተቃጥለህ አትዘልቀውምና ትስቃለህ፡፡ ‹‹መሣቁን ይስቃል ልቤ መች አረፈ – ልቤ ነው በጣሙን እጅግ ያኮረፈ›› እንዲል ጋሽ ጥላሁን ገሠሠ፡፡ በአንዳንድ የታወቁ አምባገነን ሀገሮች ህገመንግሥቶች ላይ – የዳኝነት ነፃነት ቢያንስ ለስሙ – በሚገርም ዓይነት አማላይ መልኩ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ቢያንስ ለማትተገብረው ነገር ምናለ አሳምረው ብትጽፈው? – ብለው ይመስለኛል፡፡ በኛ ሀገር የዳኝነት አካሉ ነጻ እንደሆነ በሚጠቅሰው በዚያው ህገመንግሥት ተብዬ ላይ – የዳኝነት አካሉ – በአስፈጻሚው አካል – ማለትም ስማቸው መጠቀስ ብቻ በቀረው በጠቅላይ ሚኒስትሩ (ማለት በጓድ ታጋይ መለስ ዜናዊ) – ቁጥጥር ሥር እንደዋለ እዚያው በዚያው ትገነዘባለህ፡፡
የዳኝነት ነፃነት ብዙ መስፈርቶች አሉት፡፡ ሌሎች ሌሎቹን በተግባር ዓለም ‹‹የካንጋሮ ፍርድቤቶች›› እያለ በታዛዥ ፍርድ ቤቶቻችን ላይ የዘበተባቸውን ፌዝና ትቼ – ዘፋኞች ‹‹ዳኛውም ዝንጀሮ መፋረጃው ገደል፣ እምን ላይ ተሁኖ ይነገራል በደል›› እያለ የተቀኙትን ሁሉ ትቼ – እስቲ እጅግ ዋና ዋና የሚባሉትን መለኪያዎች ላንሳና መለኪያዎቹ አንጻር የኛን ሀገር ፍ/ቤቶች (ወይም የዳኝነቱን አካል) ነፃነት አስመልክቼ ጥቂት ምጥን ቃላትን ልወርውር፡፡ የዳኝነት ነፃነት ስንል ስለየትኛው የዳኝነት ነፃነት እያወራን እንደሆነ ለይተን ማወቅ አለብን፡፡ ለምሳሌ የዳኝነት ነጻነት የሚከተሉትን የያዘ ነው፡-
• መዋቅራዊ ነጻነት፣
• የውሳኔ ነጻነት፣
• የአሠራር ነፃነት፣
• የበጀት ነፃነት፣
• የዳኞች የኢኮኖሚ ነፃነት፣ እና
• ውጫዊ (ከሌላ አጥቂና አሸማቃቂ) ነጻነት፡፡
መዋቅራዊ ነፃነትን በተመለከተ – የኢትዮጵያ የዳኝነት አካል ሙሉ በሙሉ በወያኔ-ኢህአዴግ ቁጥጥር ሥር እንዲውል ተደርጎ የተቀረጸ መዋቅር ነው ያለው፡፡ በህገመንግሥት ተብዬው ላይ የየፍርድ ቤቱን የፌዴራል ዳኞችንና፣ የጠቅላይ፣ የከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶችን ፕሬዚደንቶች ለመሾም – ምን መደረግ አለበት? ለፓርላማው ቀርበው ሹመታቸው መጽደቅ አለበት፡፡ ፓርላማው በማን የተሞላ ነው? አሁን በ100 ፐርሰንቱ ወያኔ-ኢህአዴግ፡፡ በፊት ደግሞ በ95 ፐርሰንቱ ወያኔ-ኢህአዴግ አባላት የተሞላ ፓርላማ! ያ ፓርላማ የዳኞቹንና የፍርድ ቤቶቹን ፕሬዚደንቶችና ምክትል ፕሬዚደንት ሹመት ያፀድቃል፡፡ ነገር ግን ዳኞቹን ለፓርላማው ለሹመት ማቅረብ የሚችለው ማነው? – ያን ማድረግ የሚችለው አንድ ሰው ነው፡፡ እርሱም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ይባላል! ስሙም አቶ መለስ ዜናዊ! (አሁን ደግሞ ህጋዊ የአደራ ወራሾቹ!)፡፡ ዳኞች በመለስ አቅራቢነት – ለወያኔ-ኢህአዴጉ 100 ፐርሰንት ፓርላማ ይቀርቡና – ይሾማሉ – ህገመንግሥቱን ይዘው እየማሉ! የዳኝነት አካሉማ የመዋቅራዊ ነጻነት አለው! ከዚህ በላይ ነፃነት ከየት ይምጣልህ? ሀሀሀሀሀ!!!!
ቆይ ቆይ ይሄ ብቻ እኮ አይደለም! ለመለስ ዜናዊ (ለጠቅላይ ሚኒስትሩ) የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኞቹን መልምሎ የሚያቀርብለት አካል ማነው? ያ ዳኞችን ለክቡርነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ (በፓርላማ አቅርበው እንዲያሾሙና እንዲያሽሩ) የሚያቀርብላቸው አካል ደግሞ – ‹‹የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ›› በመባል የሚታወቅ ተቋም ነው፡፡ ታዲያማ – የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 24/1988 ዓ.ም፣ ላይ የዚህ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ 9 አባላት እንዳሉት ይነግርሃል፡፡ እና 9ኙ አባላት ማን ማን ቢሆኑ ጥሩ ነው?
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመርጦ በፓርላማው የተሾመው የጠቅላይ ፍርድቤቱ ፕሬዚደንትና ምክትል ፕሬዚደንቱ (2 አባል በልልኝ)፡፡ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመርጦ በፓርላማ የተሾመው የከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፕሬዚደንቶች (2 አባል በልልኝ)፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ከፓርላማው አባላት መካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወደደውን መርጦ የሚሾማቸው ሶስት የፓርላማ አባላት (3 አባል በልልኝ)፡፡ እስካሁን 7 አባላት ሞልተዋል፡፡ 2 አባላት ቀሩ፡፡ 2ቱን አባላት ደግሞ – አሁንም በጠ/ሚኒስትሩ የተመረጡት የጠቅ/ፍቤት ፕሬዚደንት በከፍተኛና መጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤቶች ካሉ ዳኞች መካከል – ሁለት ሲኒየር ዳኞችን ይመርጣሉ (2 አባል በልልኝ)፡፡ በቃ በድምሩ 9 አባላት ሞሉኮ!! እነዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ 9 አሻንጉሊቶች ናቸው – ዳኞችን ለወያኔ-ኢህአዴጉ ጠቅላይ ሚኒስትር እያቀረቡ የሚያሾሙት፣ የሚያሽሩት፣ ከስራ የሚያሰናብቱት፣ ወዘተ፡፡  እንግዲህ ዳኞችን የሚያስተዳድረው ተቋም፣ ደንብና ዲሲፕሊን የሚያወጣው፣ የዲሲፕሊን ቅጣት የሚሰጠውና እንዲሰናበቱ የሚያደርገው አካል – ይሄ የእነ መለስ መጫወቻ የሆነ አካል ነው፡፡
በነገራችን ላይ ለይስሙላ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን በበላይነት ይመራል የሚባልለት – ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ – ለምሳሌ በሆነ ያገሪቱ ክፍል ቅርንጫፍ ፍርድ ቤቶችን መክፈት ያስፈልገኛል ቢል መክፈት አይችልም፡፡ ይሄንን ማድረግ የሚችለው ፓርላማው ነው፡፡ ይታይህ! የፍርድ ቤት ቅርንጫፍን መከፈትና አለመከፈት ለመወሰን – ፓርላማ ሲወስን! እንዲህም አድርጎ ነፃነት የለ! ሌላ ቀርቶ ህገመንግሥቱን ለመተርጎም ያልተፈቀደለት ፍርድ ቤት ነው – የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት፡፡ በኢትዮጵያ ህገመንግሥቱን በተመለከተ ክርክር ሲነሳ የሚወስኑት – ከየክልሉ የተላኩ – የብሄር ፓርቲ ተወካዮች ናቸው! ከፍርድ ቤት በላይ ህገመንግሥቱን የሚያውቁት እነሱ ናቸው! (በእርግጥም – ስታስበው – የፖለቲካ ሰነድ ነው ብቻ ሳይሆን  – የአንድ አምባገነን ፓርቲ የፖለቲካ ሰነድ ነው እየተባለ በብዙዎች የሚተችን ህገመንግስት – ከራሳቸው በቀር ማን የበለጠ ይተረጉመዋል? እና ያገሩን ሰርዶ፣ ባገሩ በሬ! ማለት ይሄኔ አይደል? ሀሀሀሀ!!!
/ወደ ቁምነገሩማ ከገባን – ያኔ በ1985 ላይ እነ መለስ ህገመንግሥቱን መተርጎም ያለበት ሕዝብ ነው ፍርድቤት አይደለም በሚል – የህገመንግስት አርቃቂውን ሃሳብ ሽረው – ህገመንግስትን የመተርጎምን ስልጣን ለፌዴሬሽን ምክርቤት የብሄሮች ተወካዮች መስጠታቸውን በተመለከተ በወቅቱ በህግ አማካሪነት በአርቃቂ ኮሚሽኑ ተሳትፋ የነበረችው የዛሬዋ የጠቅላይ ፍርድቤቷ አዲስ ተሿሚ ፕሬዚደንት – ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ – በአፍሪካን ሎው ጆርናል (በአፍሪካ የህግ መጽሔት) ላይ – በወቅቱ ወያኔ-ኢህአዴግን ሳትፈራ ታሪካዊ እማኝነቷንና የሰላ ሙያዊ ትችቷን አሳትማ ነበረ! ምን ዋጋ አለው? አፈር መስኮት የለው!? ከፖለቲካና ከፖለቲከኞች ጋር የተነካካ ጭንቅላት – የሆነ ብሎኑን ማላላቱ አይቀርም! አትንካ – አትነካካ – አለዚያ ዋጋ አይኖርህም!/ እንግዲህ ስለ ፍርድቤቶች ተቋማዊ ነጻነት ይሄን ያህል ካልኩኝ ጊዜና ቦታ ስለማይበቃን አንድ የመጨረሻ መለኪያ ነጥብ አንስቼ ይብቃኝ፡፡
የበጀት ነጻነት አንዱ የዳኝነት ነጻነት ማሳያ ነው፡፡ ለህልውናው ለሚያስፈልገው የገንዘብና የካፒታል ባጀት – በአስፈጻሚው አካል – ማለትም በጠቅላይ ሚኒስትሩና በካቢኔያቸው ላይ ሲበዛ ጥገኛ የሆነ የዳኝነት አካል – ነጻ ነው ሊባል አይችልም፡፡ የሰው ኃይሉንና ስራውን በአግባቡና በነፃነት ለማከናወን የሚያስችለው – ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ለመቅጠርና ለማሰልጠን የሚያስችለው – ከመንግሥት ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ ለመገዳደር የሚያስችለው – የኢኮኖሚ አቅም የሌለው የዳኝነት አካል – በጠቅላይ ሚኒስትሩ የበጀግ ኩርኩም ሥር መውደቁ አይቀርም! በአንድ ኮሚኒስት አምባገነን የወያኔ-ኢህአዴግ ፓርቲ ቁጥጥር ሥር በዋለ ፓርላማ – በጀቱን እየተመጸወተ፣ ዳኞቹን እያሾመና እየተሻሩበት፣ ቅርንጫፍ ልክፈት ወይ? እያለ እያስፈቀደ፣ ይሄ የህገመንግሥት አንቀጽ አልገባኝም ምን ለማለት ፈልጋችሁ ነው? እያለ እግራቸው ሥር ወድቆ ትርጉም እየጠየቀ የሚንቀሳቀስ የዳኝነት ተቋም – በጤነኛ አዕምሮ ነፃ ሊሆን ይችላልም ተብሎ ከቶውኑም የሚታሰብ ጉዳይ አይደለም! የኢትዮጵያ የዳኝነት አካል – ባለፉት የመለስ ዜናዊ የወያኔ-ኢህአዴግ የአገዛዝ ዓመታት ሁሉ – እስካሁንም ድረስ – በሃሳብ ብቻም ሳይሆን በተግባርም ነፃ ሆኖ አያውቅም!
በነገራችን ላይ – በአጋጣሚ ሆኖ – እኔ በግሌም ካደረግኩት ብዙ ጊዜ የፈጀ ጥናት ሌላ – ሌሎችም በርካታ የህግ ባለሙያዎችና የውጭ ሀገር ምሁራን ሳይቀር በሀገራችን የፍርድ ቤት ነፃነት ጉዳይ ላይ የሠሯቸው ብዙ ብዙ የጥናት ውጤቶች ስላሉ – እነዚያን ፈልጎ ማንበብ – እኔ የምናገራቸውን ነገሮች እውነታነት የሚጠራጠር ካለ – ከመጠራጠር ለመዳን ሁነኛው መፍትሄ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የኢትዮጵያ የዳኝነት አካል – በበጀት ነፃነት በኩል – በምን ያክል ደረጃ የአስፈጻሚው አካል ጥገኛ ብቻ ሳይሆን – መቀለጃ ሆኖ እንደኖረ ለማወቅ የሚሻ ሰው – በቀላሉ – የነጋሪት ጋዜጣ ገዝቶ የየዓመቱን የፌዴራልና የክልል ባጀቶች ድልድል የሚናገሩትን የጥቂት ዓመታት ቁጥሮችን ማየት ይችላል!
የሚገርመው ነገር – በኢትዮጵያችን – ያውም ፍርድ ቤቶች በቅጣትና በሌሎች የቀረጥና የቴምብር ሰበቦች – ከ10 ሚሊየን ብር ያላነሰ ገቢ በየዓመቱ እያስገቡ (በእርግጥ ሱቆች ስላልሆኑ ይሄን እንደ ንግድ ትርፍ አትመልከቱብኝና!) – እንደዚያም ሆኖ – ለምሳሌ በ1995 ዓመተ ምህረት የሀገሪቱ አጠቃላይ በጀት የሀገሪቱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተመደበላቸው በጀት 14 ሚሊየን የማይሞላ (13.3 ሚሊየን ብር ገደማ) ነው፡፡ በ1990 ዓመተ ምህረት ላይ 11.8 ሚሊየን ብር፡፡ በ1991 ዓመተ ምህረት 14.4 ሚሊየን ብር፡፡ በ1993 ዓመተ ምህረት 13.7 ሚሊየን ብር፡፡ በ1994 ዓመተ ምህረት 17.8 ሚሊየን ብር፡፡
በሚሊኒየሙ ዋዜማ የተመደበለት የ2000 ዓመተ ምህረት የአጠቃላይ የፍርድ ቤቶች ባጀት 40 ሚሊየን ደርሶ እጅግ ከፍ ያለ ጣራውን ነክቶ ነበር፡፡ ከዚያ 40 ሚሊየን ብር ውስጥ 10 ሚሊየኑ ለሸሪዓ ፍርድ ቤቶችና – በአዲሳባ መስቀል ፍላወርን እልፍ ብሎ አጎና ሲኒማ አካባቢ የመኖሪያ ህንጻና መማሪያ ክፍሎች ተሰርቶላቸው እዚያው እየኖሩ ለአንድ ዓመት ሥልጠና እንዲያገኙ ከየክልሉ ለመጡ ሠልጣኝ ዳኞች በጀት ተደርጎ የተከፋፈለ ነው!
እንግዲህ የኢትዮጵያ የፍርድ ቤቶች ባጀት – ከአንድ አነስተኛ ፒ ኤል ሲ ወይም የግል የንግድ ድርጅት የገንዘብ ካፒታል ራሱ ያነሰ ዓመታዊ ባጀት ነበረ!! የመለስ ዜናዊ መንግሥት ለፍርድ ቤት 13 እና 14 ሚሊየን ብር የዓመት በጀት ነው ብሎ እያስመደበ – (እየቀለደ ልበለው እንጂ!) – በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ለመከላከያ ሠራዊት እየተባለ የሚመደበው አማካይ ዓመታዊ ባጀት 3,000,000,000 ብር (ማለትም ሶስት ቢሊየን ብር ነበረ! ) – ልብ በሉልኝ ‹‹ሚሊየን›› አይደለም – ‹‹ቢሊየን›› ነው – 3 ቢሊየን ብር በያመቱ! ይሄ እንግዲህ የመለስ የቀድሞ ታማኝ የወያኔ ታጋዮችና ጋሻጃግሬዎቻቸው የሚቀራመቱት – ጄነራል ኦዲተር ራሱ የማያውቀው – በየዓመቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየተገፈፈ ሲበተን የኖረ ገንዘብ ነው!! የደህንነቱን ባጀት፣ ለፍትህ እየተባለ ያን ክሰሱ፣ ያን እሰሩ ለሚባሉት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስር ላለው የፍትህ ሚኒስቴር ከሳሽና አሳሪ ፈቺ ተቋም የሚበተነውን ባጀት አትጠይቁኝ፡፡ አሁንም እየተበተነ ነው!
ይሄን ሰማይ ጠቀስ ባጀት አይታችሁ ዝቅ ስትሉ – ታዲያ የኢትዮጵያ የዳኝነት አካል ዓመታዊ በጀት – ከማን ባጀት ጋር ሊወዳደር ይችላል ካላችሁኝ አፌን ሞልቼ እነግራችኋለሁ!!! የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዳኝነት አካሉ ባጀት ሊወዳደር የሚችለው – ከቤተመንግሥቱ ባጀት ጋር ብቻ ነው! ለመለስ ቤተመንግሥት የሚመደበው ዓመታዊ ባጀት – ለአጠቃላይ የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች ከሚመደበው ዓመታዊ በጀት ጋር ተስተካካይ ነው፡፡ አንዳንዴ በ2 ወይም በ3 ሚሊየኖች ያንሳል!
ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ የሚባል ጠፍቶ አይደለም፡፡ በቃ መድበን ብቻ ነው ትርፉ፡፡ ለውጥ የለውም! ተንፍሶ ለታሪክና ለትውልድ ለማቆየት ካልሆነ በቀር – ትርፍ የለውም! አንድ ከወያኔ-ኢህአዴግ ጋር የተሻረከ መንታፊ – የ50 ሚሊየን ብር ህንጻ በቀላሉ በሚያስገነባባት ሀገር – ለኢትዮጵያ የዳኝነት አካል ያን ያህል ገንዘብ የ3 እና የ4 ዓመት ባጀቱ ነው! ዳኝነትን፣ የዳኝነትን የበጀት ነጻነት – እነ መለስ ዜናዊና የአደራ ወራሾቻቸው የቀለዱበት እንደዚህ ነው!
እንግዲህ ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል፡፡ ሶስቱን ነጥቦቼን አትርሱብኝ አደራ – ብዬ አበቃለሁ፡፡ በመለስ ዜናዊዋ – በወያኔ-ኢህአዴጓ ኢትዮጵያ ሥርዓት ውስጥ – መንግሥትና ሐይማኖት ፈጽሞ አልተለያዩም፡፡ እንዲያውም ‹‹ሕገመንግሥት›› ተብዬው ወደ አንድ ወገን የተንሸዋረረ ሐይማኖታዊ የዳኝነት ሥልጣንን መንግሥታዊ ተቋማዊ ቅርጽ ሰጥቶታል፡፡ በወያኔ-ኢህአዴጓ ኢትዮጵያ የዳኝነት ነፃነት በሃሳብም በተግባርም የለም፡፡ እውነቱ ይኸው ነው፡፡ አበቃሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን አለሁሽ ይበላት!
ፈጣሪ ይታረቀን!
እናት ኢትዮጵያ በአይበገሬ ልጆቿ ፀንታ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic