>

ፕሮፌሰር አንድሪያስና “የኦሮሞ ጥያቄ” (ዳንኤል ደምሴ)

ፕሮፌሰር አንድሪያስና “የኦሮሞ ጥያቄ”

ዳንኤል ደምሴ

 

“እልህ ምላጭ ያስውጣል” 

ድንቅ አባባል ነው። በተለይ በአሁኑ ወቅት በርካታ የጠሚ እብይ አስተዳደር ተቃዋሚዎች በንዴት ምላጭ ስለመዋጣቸው እየታዘብን ነው።
የአብይ አስተዳደር ምላጭ ካስዋጣቸው ሰዎች አንዱ ጃዋር መሀመድ ነው። ጃዋር ከነቆሻሻ አስተሳሰቡ የተነከረበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለ3 አመታት ያከማቸውን የዝና እና የተቀባይነት ካባ ከላዩ ላይ ገፎ እርቃኑን እስቀርቶታል። በተለይ 86 ንፁሃን ዜጎች በተጨፈጨፉበት አረመኒያዊ ክስተትና ኦፌኮ ባደረጋቸው ህዝባዊ ውይይቶች የተንፀባረቁት ጃዋር – ወለድ ፋሽስታዊ ቅስቀሳዎች የሰውየው የፖለቲካ ጉዞ ከጅምሩ ቅርቃር ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። በዚህም ምክኒያት ትኩረት ያስገኙልኛል ያላቸውን ማናቸውንም ነገር በደመነብስ መነካካቱን ተያይዞታል።
የማያርፈው የጃዋር እጅ ዛሬ ዕድሜ ልኩን ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ሆኖ የኖረውንና ያወዛጋቢ ስብዕና ባለቤት የሆኑትን ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴን ጎትቶ እዚህ ፌስቡክ ላይ አምጥቷቸዋል። የኦሮሞ ጠበቃ ነኝ የሚለው ጃዋር ለመሆኑ ፕሮፌሰሩን ያውቃቸዋል?
ህዳር ወር አካባቢ 1996 ዓም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሞ ተማሪዎችና በመንግስት መካከል ውጥረት ነገሰ። የኦሮሞ ተማሪዎችም ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጋር መወያየት እንደሚፈልጉ በመግለፃቸው የወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር አንድሪያስ ከተማሪዎቹ ጋር በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ አዳራሽ ስብሰባ ተቀመጡ። ይሁንና ስብሰባው በብጥብጥ ተቋረጠ። በመቀጠል የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የጋበዛቸውን እንግዶች 6 ኪሎ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በልደት አዳራሽ ሰብስቦ የኦሮሞ ባህል ፌስቲቫል ለማካሄድ ሲሞክር በኩርፊያ ውስጥ ያሉት ተማሪዎች ወደ አዳራሹ በመግባት ረብሻ በማስነሳታቸው ፌስቲቫሉ ተቋረጠ ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግርግርም የልደት አዳራሽና ኬነዲ ላይብረሪ ላይ ጉዳት ደረሰ። ፕሮፌሰር አንድርያስም የኦሮሞ ተማሪዎችን የሚሰድብበትን ቃል ሲያፈላልግ ሰነበተ። በመጨረሻም በሚዘገንን ሁኔታ “Mindless Vandalism” ሲል የገለፀበትን መግለጫ ኬኔዲ ላይብረሪ በር ላይ ለጠፈው።
ፖሊስም ረብሻውን ይመራሉ የሚላቸውን ልጆች መብራት እያጠፋ ጨለማን ተገን አድርጎ ከየዶርማቸው መልቀሙን ተያያዘው። በዚህ የተበሳጩ ከ300 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችም ከመንግስት ጋር አብረዋል ያሏቸውን ፕሮፌሰሩን ለመቃወም በፕሬዚደንቱ ፅ/ቤት ፊት ለፊት (ራስ መኮንን አዳራሽ) ተሰባሰቡ። ፕሮፌሰር አንድርያስም ፖሊስ ጠርተው ተማሪዎችን አሳፈሱ። በማግስቱም በፐሮፌሰሩ ፊርማ ከ300 በላይ ተማሪዎች ተባረሩ። በሚያሳዝን ሁኔታ 1993 ላይ ታግደው የነበሩ ተማሪዎች አሁንም በድጋሚ ተባረዋል።
በወቅቱ የተባረሩት ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ከሄዱ መንግስት ሊያስራቸው ይችላል ብሎ የሰጋው የሜጫና ቱለማ ማህበር ተማሪዎቹ አዲስ አበባ እንዲቀመጡ ወሰነ ይህንንም ለማሳካትም በጀት መደበ።
በዚህ ስጋት የገባው መንግስት አሁንም ከፕሮፌሰሩ ጋር በመተባበር በዩኒቨርስቲው ዋናው ግቢ(6ኪሎ) በተማሪዎች መኝታ ህንፃ TV Room ውስጥ በተቀነባበረ ሁኔታ ቦምብ በማፈንዳት ሜጫ ቱለማ ማህበርንና ተማሪዎቹን በመክሰስ ዶክመንተሪ ተሰራ። የሜጫ ቱለማ አመራሮችም ዘብጥያ ወረዱ ማህበሩም ተዘጋ።
እንግዲህ ጃዋር በኦሮሞ ላይ ይህን ያህል በደል የፈፀሙትን ፕሮፌሰር አንድርያስን ንግግር ተጠቅሞ ነው ለኦሮሞ ጥቅም መንግስትን ለመታገል የሞከረው።
በነገራችን ላይ ሻዕቢያ በ1983 ኢትዮጵያውያንን ንብረታቸውን ነጥቆና አንገላቶ ሲያባርር የአጣሪ ኮሚቴ አባል የነበሩት ፕሮፌሰር አንድርያስ “ስለሻዕቢያ የተባለው ሁሉ ውሸት ነው። ኢትዮጶያውያን ከኤርትራ በእንክብካቤና በሰላም ነው የወጡት” ማለታቸው እስከዛሬ እያስወገዛቸው ያለ ጉዳይ ሲሆን ከቅርብ አመታት በፊት የሸገር ቅዳሜ እንግዳ አድርጋ ያቀረበቻቸው ማዕዛ ብሩ ጉዳዩን አንስታ “ህዝብ ተቀይሞዎታልና ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ይቅርታ ይጠይቃሉ ወይ?” ስትላቸው “ምንም ያጠፋሁት፣ የሚቆጨኝም፣ ይቅርታ የምጠይቅበትም ጉዳይ የለኝም” ብለዋል።
ፕሮፌሰር አንድርያስ ሲበዛ አጫሺና የአልኮል ሱሰኛ ሲሆኑ በዩኒቨርሲቲው በመምህረነት “Legal History“ እና “Moral Philosophy” ኮርሶችን በሚሰጡበት ወቅት እንኳ ክፍል ውስጥ ከማጨስ የማይመለሱ ናቸው። ሌላው ቀርቶ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ሳይቀር ቢሯቸው ውስጥ እግራቸውን ጠረጴዛ ላይ ሰቅለው የሚያጨሱ ሲሆን በአንድ ወቅትም ይሄው ድረጊታቸው በኢንተርቪው ላይ ለህዝብ ተላልፏል። አልኮል ከማብዛታቸው የተነሳ ጭንቅላታቸው በመጎዳቱ ግማሽ አካላቸው ሽባ እንደሆነም ይታወቃል።
ለማንኛውም የነጃዋር የፖለቲካ ጉዞ መደናበሩን አጠናክሮ ቀጥሏል።
Filed in: Amharic