>

በሀገራችን ዓበይት ወቅታዊ ጉደዮች ዙሪያ ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኀበር ምከር ቤት የተሰጠ መግለጫ

በሀገራችን ዓበይት ወቅታዊ ጉደዮች ዙሪያ ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኀበር ምከር ቤት የተሰጠ መግለጫ

እናት ኢትዮጵያ የቆመችበት ምሰሶ፣ የተሳሰረችበት ማገር እና ወጋግራም ሆነ ክዳኗ የተገነባው በልጆቿና ከአራቱም ማዕዘናት እየተጠራሩ ባፈሰሱት ደም እና በከሰከሱት አጥነት ነው፡፡ ሀገራችን የአፍሪካ መመኪያና የዜጎቹ መኩሪያ ለመሆን የበቃችው አያሌ መስዋዕትነት ተከፍሎ ነው፡፡ ትውልድ ይህን አኩሪ ታሪክ የመጠበቅ አደራ ተረክቧል፡፡

የአባቶችና የእናቶችን አደራ የማይወጣ ትውልድ የዘመን ባለዕዳ ከመሆን ባሻገር ህይወቱ ከጐስቁልና ሊላቀቅ አይችልም የተደላደለ ኑሮ ለመኖር ሀገር የተመቻቸ ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ ሰላምን ስለፈለጉት ብቻ አይቀዳጁትም፡፡ የጋራ መግባባት ከሌለ ሰላም አይሰፍንም፡፡ ውስጣዊ ሁኔታዎች የተረጋጉና በጠንካራ መግባባት ላይ የታነፁ ቢሆኑ እንኳ ውጫዊ ባህርያት በቀና ሀዲድ ላይ ካልተሽከረከሩ በአንድ እጅ ማጨብጨብ እንደማይቻል ሁሉ የተሟላ ሰላምና ደህንነትም መቀዳጀት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ 

ኢትዮጵያ አያሌ ወራሪዎችን መክታ ነፃነቷን አስከብራ የመኖር ምስጢር ሌላ ሳይሆን ሕዝባዊ አንድነቷ በማይናወጥ መሠረት ላይ የተወቀረ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ በቅኝ ገዥዎች መዳፍ ወድቀን የዛሬው ኩሩ ታሪካችንን አስጠብቀን አሁን ላለንበት ደረጃ እንዳበቃነው ሁሉ ዛሬም ይህን ቅርስ አስጠብቀን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡ የምንከተለው ሶሺዮ ኢኮኖሚክ ስርዓት ዲሞክራሲያዊ የመሆኑ ያህል የሃሳብ፣ የርዕዮተ ዓለምና የአመለካከት ልዩነት መኖሩ ይደገፋል፡፡ ይህ መብት ግን ሀገራዊ አንድነትና ሠላምን ባስጠበቀ ገደብ ይጓዝ ዘንድ ግዴታ ነው፡፡ ሰላምና ሀገራዊ አንድነትን በዝቅታ ማዬት አይቻልም፡፡ ሁሉም በሀገር ነውና፡፡ ጐጆን አፍርሶ በፀሐይ እየተቃጠሉ፣ በብርድ እየተንገረገቡ፣ መጠለያ አጥቶ ለምክክር መቀመጥ አይቻልም፡፡ በሀገራችን ሊካሄድ ታስቦ የነበረውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያራምዱት የተለያዬ አቋም ሳቢያ ሰላማችንና ሀገራዊ ደህንነታችንን ለአፍታም ቢሆን ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚያስገባ ክፍተት እንዳይፈጠር የጥ/ኢ/ጀ/አ/ማ ሁሉም ወገኖች በተረጋጋና ማስተዋል በተሞላው አኳኋን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ይመክራል፡፡ መሪዎቻችንን እናከብር ዘንድ ያደግንበት ኢትዮጵያዊ ባህልና ጨዋነት ብቻ ሳይሆን ሕግና ሞራል ያስገድደናል፡፡ በመከባበር ተደማምጠን ለጋራ መፍትሔ እንሰለፍ ዘንድ እምነቶቻችንም ሆኑ ከመቃብር በላይ ሁሌም አደራ የሚለን የአባቶቻችን ድምፅ ይጠራናል፡፡ ተመርጦ በሥልጣን ወንበር መቀመጥም ሆነ ልጅ ወልዶ ማሳደግ ወይም በሠላም ኖሮ በክብር መቀብር የሚቻለው ሀገር ሠላም ሲሆን ነው፡፡ 

የሕዳሴው ግድብን በተመለከተ ፋይዳው ለኢትዮጵያ የልማት ጉዳይ ብቻ አይደለም የዓባይ ግድብ የዲኘሎማሲ፣ የህልውና፣ የኢኰኖሚና የተጋድሎ ታሪካችን አንድ አካል ተደርጐ የሚታይ አውራ ርዕሰ ነገር ነው፡፡ በውስጡ ዶጋሊ፣ ዓድዋ፣ መተማ፣ ማይጨው፣ካራማራ፣ ወልወልና የሌሎች የአርበኝነት ትንቅንቆች ምስጢራት አሉበት፡፡ የዓባይ ግድብን ዳር ማድረስ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ማስከበር ነው፡፡ የዓባይ ግድብን በጅምር ማቋረጥ የትውልድ ሽንፈት ብቻ ሳይሆን የዜግነት የሞት ሞት ነው፡፡ ዓባይን ለስልጣን ሆነ ለአፍቅሮ ነዋይ ጥማት ለባዕዳን በገፀ በረከትነት የሚያቀብል ዜጋ ወይም ቡድን እርሱ በእያንዳንዳችን አንገት ካራ ያኖረ አውራ ጣላት ስለሆነ በምህረት የሚታለፍ አይደለም፡፡

በመሆኑም ከልማት ባሻገር ብዙ ሰምና ወርቅ ያዘለውን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዳር ለማድረስ እንዲቻል መላው ኢትዮጵያ በገንዘቡ፣ በአዕምሮው፣ በጉልበቱና አስፈላጊ ከሆነም ጊዜው በሚጠይቀው ረገድ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል እንዲዘጋጅ የጥ/ኢ/ጀ/አ/ማ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ኮቪድ 19ን በተመለከተ በዓለም ዙሪያ ያስከተለው ቀውስ ከቃላት በላይ ነው፡፡ ዓለምን አልፈው ሕዋን ለመቆጣጠር ችለናል የሚሉት ኃያላን ሀገራት ሳይቀሩ በደረጃ ኢኰኖሚና በተራቀቀ ሥልጣኔ ላይ ያሉት እንኳን ሊቋቋሙት ባለመቻላቸው የተነሳ የሰው ልጅ ህይወት እንደ ቅጠል በመርገፍ ላይ ይገኛል፡፡ እኛ ባለን ደካማ ምጣኔ ሀብት፣ በውል ባልዘመነ የሕክምና መዋቅር፣ ባልደረጀ ሞያተኛና ግንዛቤን ለመተግበር ዝግጅነቱ ባልጐለመሰ ህብረተሰብ ሃሳብ ውስጥ እየኖርን ኮሮና ቫይረስ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ለመቋቋም እንደምንቸገር ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡     

ለጊዜው በእጃችን ያለው መፍትሄ መንግሥትና የጤና ሞያተኞች የሚያስተላልፏቸውን የጥንቃቄ መመሪያዎችን በትኩረት ተቀብሎ መተግበር ብቻ ነው፡፡ የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ በሄደ ቁጥር የሚያስከትላቸው ማኀበራዊ ቀውሶች ከትንበያ የከፋ ስለሚሆኑ ዜጐች ሁሉ ይህን ከፍተኛ አደጋ ለመከላከል የመንግስትን አመራርና የጤና ባለሞያተኞች ምክር ተቀብሎ እንዲተገብር እንመክርለን፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር የምንሳሳላት ሀገርና የምወደው ሕዝብ ለዚህ አስከፊ በሽታ በስፋት ሊዳረግ ስለሚችል የሚቻለንን ሁሉ በጥነቃቄ እንድናከናውን የጥ/ኢ/ጀ/አ/ማ አደራውን ያስተላልፋል፡፡

ሠላምና የሀገር ደኀንነት ጉዳይ በምንም መለኪያ ለድርድር የማይቀርቡ፣ በምንም መስፈርት ለማነፃፀሪያ የማይታሰቡ የህልውናችን መሠረቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም በምርጫ ረገድም ሆነ በሌሎች የፖሊሲ ጉዳዮች ያገባናል የሚሉ አካላት ሁሉ ከመንግስት ጋር በሚነጋገሩባቸው ርዕሶች ሁሉ ትናትና፣ ሀገራዊ ኃላፊነት፣ የትውልድ አደራን ከምንም በላይ ውጫዊና ውስጣዊ ጂኦ ፖለቲካውን በጥንቃቄ ግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ ይከናወን ዘንድ ማኀበራችን አጥብቆ ይመክራል፡፡ ከዚህ አካሄድ ባፈነገጠ መልኩ የሚካሄዱ ሥርዓት የለሽ አቀራረቦች የሚነቀፉ ብቻ ሳይሆን በአያሌ መስዋዕትነት የተገነባችውን የሀገራችንን ህልውና ለአደጋ የሚያጋልጡ ስለሆነ በጥብቅ የሚወገዙ ናቸው፡፡ 

ስለሆነም ተግባራቶቻችን ሁሉ በብስለት፣ በመግባባት፣ ሰጥቶ በመቀበል፣ በአስተውሎትና በመቻቻል ይከናወኑ ዘንድ የጥ/ኢ/ጀ/አ/ማ ከልቡ ይመክራል፡፡

ፈጣሪ እናት ሀገራችንንና ሕዝቧን ይባርክ

የጥ/ኢ/ጀ/አ/ማ የሥራ አመራር ምክር ቤት

ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም

Filed in: Amharic