አሰፋ ሃይሉ
* 14 ግኝቶቹን ዘርዝሮ ያቀረበው የአሜሪካ የምርመራ ውጤት የዶ/ር ቴድሮስን ንዝህላልነትና ለፖለቲካዊ ፍጆታ ሲባል ዓለምን ለከፋ አደጋ በሚያጋልጥ አኳኋን ለቻይና ዘብ መቆም አረጋግጧል፣ አሜሪካ ለ WHO የ30 ቀናት የአሠራር ማሻሻያ ቀነ-ገደብ አስቀምጣለች፣ ያ ካልሆነ አሜሪካ የገንዘብ ልገሳ ክልከላውን በቋሚነት ትሠርዛለች፣ ከ WHO አባልነቷም ልትወጣ ትችላለች – ብለዋል ፕ/ት ትራምፕ በዛሬው ዕለት ይፋ በሆነው ኦፌሴላዊ ደብዳቤያቸው!
14ቱን ነጥቦች ዘርዝሮ የያዘው ሙሉ ደብዳቤው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ክቡርነትዎ
ለዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ
የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር-ጀነራል
ጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ!
የዓለም ጤና ድርጅት ለኮቪድ-19 የሰጠውን እርባና የለሽ ምላሽ በተመለከተ የእኔ አስተዳደር ተገቢውን ምርመራ እስከሚያከናውን ድረስ አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የምታዋጣውን ገንዘብ በመጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳገድኩት ይታወቃል፡፡ የተከናወነው ይህ ምርመራ እኔ ባለፈው ወር ያነሳኋቸው ብዙዎቹ አሳሳቢ ስጋቶች ልክ መሆናቸውን ያረጋገጠ ከመሆኑም በላይ የዓለም ጤና ድርጅት በተገቢው መልኩ ምላሽ ሊሰጥባቸው ይገቡ የነበሩ ሌሎች ጉዳዮችንም አመልክቷል፤ ከእነዚህም መካከል በተለይ የዓለም ጤና ድርጅት አስደንጋጭ በሆነ ደረጃ ከሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና ተፅዕኖ ራሱን ነፃ አድርጎ አለመገኘቱን ያመለከተበት አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ በተደረገው ምርመራ መሠረት በአሁን ወቅት የሚከተሉትን ልናውቅ ችለናል፡-
• የዓለም ጤና ድርጅት ከህዳር ወር 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ገደማ ጀምሮ፣ እንዲያውም ከዚያም ቀደም ብሎ፣ ከዉሃን ግዛት የቫይረሱን ሥርጭት የሚያሳዩ – ከላንሴት ሜዲካል ጆርናል የቀረበውን ጨምሮ – ዋጋ የሚሰጣቸው ሪፖርቶች ቢደርሱትም ወጥነት ባለው መልኩ ሪፖርቶቹን ንቆ ትቷቸዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት የቻይና መንግሥት ከሚሰጣቸው ኦፊሻል መግለጫዎች ጋር የሚጣረሱ ዋጋ የሚሰጣቸው ሪፖርቶች ሲደርሱት – ሌላ ቀርቶ ከራሷ ከዉሃን ካሉ ምንጮች የተላኩለት ጭምር ሲደርሱት – ሪፖርቶቹን በተመለከተ የራሱን ገለልተኛ ምርመራ ማከናወን ተስኖታል፡፡
• ታህሣሥ 20፣ 2012 ዓ.ም. ከመድረሱ በፊት ቤጂንግ የሚገኘው የዓለም ጤና ድርጅት ጽሕፈት ቤት ‹‹ከፍ ያለ የጤና ጉዳይ›› መከሰቱን ያውቅ ነበር፡፡ በታህሣሥ 16 እና በታህሣሥ 20 መካከል – የቻይና ሚዲያ ከዉሃን ከሚላኩ የጀኖም ምርመራ የሚያደርጉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ካምፓኒዎች ከዉሃን ከሚላኩላቸው የህሙማን ናሙናዎች በመነሳት በዉሃን አዲስ ቫይረስ ስለመከሰቱ መረጃ እንደተገኘ በቻይና ሚዲያ ተገልጾ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ በዚሁ ጊዜ ውስጥ፣ በሁቤይ አውራጃ ሆስፒታል በቻይናና ምዕራባውያን የተቀናጀ ህክምና ማዕከል ይሰሩ የነበሩት፣ ዶክተር ዣንግ ዢሺያን፣ አዲስ ዓይነት የኮሮና ቫይረስ በዓይነቱ አዲስ የሆነን በሽታ በመቀስቀስ በወቅቱ በግምት ወደ 180 የሚደርሱ ህሙማንን ተጠቂ ያደረገ ስለመሆኑ ለቻይና የጤና ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡
• በቀጣዩ ቀን፣ የታይዋን ባለሥልጣናት ከሰው-ወደ-ሰው የሚተላለፍ አዲስ ቫይረስ መከሰቱን የሚጠቁም መረጃ ለዓለም ጤና ድርጅት አስተላልፈዋል፡፡ እንዲህም ሆኖ፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ ምናልባትም ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል፣ የደረሰውን ይህን አንገብጋቢነት ያለው መረጃ አንዱንም ለተቀረው ዓለም አለማጋራትን መርጧል፡፡
• የየዓለም ጤና ደንቦች የሚደነግጉት ሀገራት የሰውን ጤና ለአደጋ የሚያጋልጡ ድንገተኛ ነገሮች ሲከሰቱ በ24 ሰዓታት ውስት ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው ነው፡፡ ነገር ግን በዉሃን የተከሰቱትን ምንጫቸው ያልታወቀና ቁጥራቸው የበዛ የሳንባ ምች ህመሞች በተመለከተ ምንም እንኳ ቻይና ከቀናት ወይም ከሳምንታት በፊት የምታውቀው ቢሆንም እስከ ታህሣሥ 21፣ 2012 ዓ.ም. ድረስ ይፋ አላደረገችም፡፡
• የሻንጋዩ የሕዝብ ጤና ክሊኒክ ማዕከሉ ዶ/ር ዣንግ ዮንግዠን እንደተናገሩት፣ የቫይረሱን ጄኖም ሲክወንስ በምርመራ እንደደረሰበት ለቻይና ባለሥልጣናት በታህሣሥ 26 ቀን 2012 ዓ.ም፣ አሳውቀዋል፡፡ ነገር ግን ዶክተሩ ራሳቸው ከስድስት ቀናት በኋላ፣ በጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም. መረጃውን በድረገጽ ላይ እስኪለቁት ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ ከማንም ወገን የተሰጠ ምንም መረጃ አልነበረም፡፡ በቀጣዩ ቀን የቻይና ባለሥልጣናት ‹‹የማስተካከያ እርምጃ›› በማለት የዶክተሩን ላቦራቶሪ አሽገውታል፡፡ ራሱ የዓለም ጤና ድርጅት እንዳመነው፣ የዶክተር ዣንግ መረጃውን ይፋ ማድረግ ከፍተኛ የሆነ ‹‹የግልጽነት›› ተግባር ነበረ፡፡ ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት ስለ ዶ/ር ዣንግ ላብራቶር መዘጋትም ሆነ እርሱ ከስድስት ቀናት በፊት ለቻይና ባለሥልጣኖች አዲስ ዓይነት ቫይረስን የሚያሳየውን ግኝቱን ይፋ ስለማድረጉ የቀረበውን ሃተታ በተመለከተ ስለሁለቱም ጉዳዮች የመረጠው አስገራሚ ዝምታን ነው፡፡
• የዓለም ጤና ድርጅት የጎላ ስህተት የተስተዋለባቸውና ወደ ተሳሳተ መንገድ ሊመሩ የሚችሉ መግለጫዎችን በተደጋጋሚ ሲሰጥ ቆይቷል፡-
o በጥር 5 ቀን 2012 ዓ.ም. የዓለም ጤና ድርጅት በራሱ አነሳሽነት በሰጠው መግለጫ – አሁን ፉርሽ መሆኑ የተረጋገጠውን የወቅቱን ኮሮና ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ አይችልም የሚለውን የቻይና መግለጫ ተቀብሎ በማስተጋባት – ‹‹የቻይና ባለሥልጣናት ባደረጓቸው ቅድመ ምርመራዎች በዉሃን፣ ቻይና የተገኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ (2019-nCov) ከሰው-ወደ-ሰው ስለመተላለፉ ምንም የተጨበጠ ማስረጃ አላገኙም›› በማለት የቻይናውን መግለጫ በማረጋገጥ ተግባር ተሰማርቶ ነበረ፡፡ ይህን የሚያደርገው ደግሞ ከዉሃን የሚወጡ በግልጽ ተጻራሪ ይዘት የነበራቸው ሪፖርቶች ሳንሱር እየተደረጉ መግለጫ እየተሰጠባቸው እንደሆነም እየታወቀ ነው፡፡
o በጥር 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ላይ ደግሞ፣ የኮሮና ቫይረስ በሽታ ለስመቀስቀሱ ለዓለም እንዳያስታውቁ ፕሬዚደንት ዢ ዢንፒንግ እርስዎን በቀጥታ በማግኘት ግፊት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ እርስዎም ለዚህ ጫና እጅ በመስጠት በማግስቱ በዓለም ፊት ቀርበው ኮሮና ቫይረስ ዓለማቀፍ ትኩረትን የሚሻ ድንገተኛ ሕዝባዊ የጤና አደጋን አልደቀነም በማለት መግለጫ ሊሰጡ ችለዋል፡፡ ይሄን ካሉ ከሳምንት በኋላ ደግሞ – በጥር 21 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ እርስዎ ከሰጡት መግለጫ ጋር የሚቃረኑ እጅግ ብዙ መረጃዎች ሲመጡብዎት ቃልዎን ለመቀየር ተገደዱ፡፡
o በጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ እርስዎ ፕሬዚደንት ዢ ዢንፒንግን በቤጂንግ ካገኙዋቸው በኋላ፣ የቻይና መንግሥት የኮሮና ቫይረስን በተመለከተ ስላሳየው ‹‹ግልጽነት›› የቻይና መንግሥትን በማመስገን ቻይና ከዚህ በበፊት ታይቶ የማያውቅ ‹‹አዲስ የበሽታን መዛመት መቆጣጠሪያ ስታንዳርድ›› ክብረ ወሰንን አስመዝግባለች በማለት እና ይህን በማድረጓም ቻይና ለቀሪው ዓለም ‹‹ጊዜን አትርፋለታለች (ገዝታለታለች)›› በማለት መግለጫ ሰጡ፡፡ በመግለጫዎት ግን ቻይና በተመሣሣይ ጊዜ ስለ ቫይረሱ የተናገሩ በርካታ ዶክተሮችን ፀጥ በማሰኘትና የቻይና ተቋሞች ስለቫይረሱ መረጃዎችን ይፋ እንዳያደርጉ ክልከላ እያደረገች እንዳለች ለአፍታ እንኳ ለመጥቀስ አልፈለጉም፡፡
• ሌላ ቀርቶ እርስዎ ስንት ዘግይተውም ቢሆን በጥር 21 ቀን 2012 ዓ.ም. የተቀሰቀሰውን በሽታ ዓለማቀፉን ማኅበረሰብ ሊያሳስበው የሚገባ ድንገተኛ ሕዝባዊ የጤና ጠንቅ ነው በማለት መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንኳ፣ ቻይና በተገቢው ፍጥነት ከዓለማቀፍ የህክምና ባለሙያዎች የተውጣጣውን የዓለም ጤና ድርጅት የመርማሪዎች ቡድን ወደ ሀገሯ እንድታስገባ ጫና ባለማድረግዎ የተነሣ፣ ይህ አስፈላጊ ቡድን ከእርስዎ መግለጫ በኋላ ሁለት ሳምንት ጠብቆ በመጨረሻ በየካቲት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ወደ ቻይና መግባት እስኪፈቀድለት ድረስ መጠባበቅ ግድ ሆኖበታል፡፡ እንዲያም እንኳ ዘግይቶ ገብቶ የህክምና ምርመራ ቡድኑ የቆይታ ጊዜ ሊጠናቀቅ ባሉት የመጨረሻ ቀናት እስኪፈቀድለት ድረስ የቡድኑ አባላት ወደ ዉሃን እንዳይገቡ ተከልክለው ቆይተዋል፡፡ ይባስ ብሎ ቻይና በዓለማቀፉ የህክምና ቡድን ውስጥ የተካተቱን ሁለት አሜሪካውያን አባላት ወደ ዉሃን እንዳይገቡብኝ ብላ ነጥላ ስታስቀራቸው – የዓለም ጤና ድርጅት የሰጠው ምላሽ በዝምታ ተሸብቦ መመልከትን ነበር፡፡
• በተጨማሪም እርስዎ ቻይና በሀገር ውስጥ ጉዞዎቿ ላይ የጣለቻቸውን ጥብቅ ገደቦች አስመልክተው ታላቅ ሙገሳን ለቻይና ሲያቀርቡ፣ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ግን እኔ የአሜሪካን ድንበር ከቻይና ለሚመጡ ሰዎች ዝግ ማድረጌን፣ ወይም የጉዞ ገደቤን፣ ተግባራዊ ሳደርግ ድርጊቱን ሲቃወሙት ተደምጠዋል፡፡ የእኔ የጉዞ ገደብ በሥራ ላይ ያዋልኩት የእርስዎን ፍላጎት ወደጎን በመተው ነበረ፡፡ ይህ የእርስዎ የፖለቲካ ጌም ተጫዋችነትዎ አደገኛ ገዳይነት ነበረው፣ ምክንያቱም በእርስዎ አስተያየት ላይ እምነታቸውን በመጣል፣ ሌሎች መንግሥታት፣ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ሊያድንላቸው ይችል የነበረውን ከቻይና እና ወደ ቻይና የሚደረጉ ጉዞዎችን የማገዱን ተግባር ለማዘግየት ተዳርገዋልና፡፡ በሚገርም ሁኔታ በጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ደሞ፣ የቀድሞውን አቋምዎን በማደስ፣ ቻይና ዓለምን ከቫይረሱ ለመከላከል ታላቅ ሥራ እየሠራች ነው እና እየተጣሉባት ያሉት የጉዞ ማዕቀቦች ‹‹ከሚያስገኙት ጥቅም ይልቅ እያደረሱ ያሉት ጉዳት ይበልጣል›› የሚል አስተያየት ሰጡ፡፡ ነገር ግን እርስዎ ያን እያሉ ባሉበት ሰዓት ዓለም ደግሞ የተገነዘበው ነገር – የቻይና ባለሥልጣናት ዉሃንን ከማንኛውም ጉዞ ዝግ እንድትሆን ከማድረጋቸው በፊት ቁጥራቸው ከ5 ሚሊየን በላይ የሚደርሱ ሰዎችን አስቀድመው ከከተማዋ እንዲወጡ ፈቅደውላቸው እንደነበረ ነው፣ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ደግሞ ወደ ተለያዩ ዓለማቀፍ የጉዞ መዳረሻዎች የሚንቀሳቀሱ ነበሩ፡፡
• ከጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ቻይና ሀገራት የጣሉባትን የጉዞ ገደቦች እንዲያነሱላት በመወትወት ጠንካራ ግፊት እያደረገች ነበረ፡፡ ይህም የቻይና ዓለማቀፍ ግፊት የማሳደር ዘመቻ በእርስዎ የተቃና ድጋፍ የታገዘ እንደነበረ ለመረዳት እርስዎ በዚያው ዕለት ለዓለም ሁሉ የቫይረሱን ሥርጭት አስመልክቶ የተናገሩት፡- ቫይረሱ ከቻይና ወጥቶ ወደተቀረው ዓለም ለመሠራጨት ያለው ዕድል ‹‹ዝቅተኛ እና አዝጋሚ›› መሆኑንና ‹‹ከቻይና ውጪ ባለ በየትኛውም ዓለም በዚህ ቫይረስ የመያዝ ዕድሉ በጣም የመነመነ ነው›› በማለት የሰጧቸው የቻይናዎቹን ዘመቻ የሚያጠናክሩ ንግግሮች ይገኙበታል፡፡
• በየካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ላይ፣ የዓለም ጤና ድርጅት – የቫይረሱን የጎንዮሽ ሥርጭት አስመልክቶ በትክክል ከሆነው በታች በማቃለል የተሰራጨውን ኦፊሴላዊ የቻይና መግለጫ ጠቅሶ በማስተጋባት፣ ለዓለም እየነገረ የነበረው መረጃ፡- ‹‹COVID-19 የኢንፍሉዌንዛን ያህል እንኳ ከሰው ሰው የመጋባት አቅም እንደሌለው›› እንዲሁም ከኢንፍሉዌንዛ በተለየ ሁኔታ ይህ ቫይረስ ‹‹ቫይረሱ በውስጣቸው ቢኖርም ገና ወደ ህመም ባልተቀየረባቸው ሰዎች አማካይነት ወደ ሌላ ሰው የመተላለፍ ዕድል እንደሌለው›› የሚናገር መረጃ ነበረ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ይህን እያለ አብሮ ይጠቅስ የነበረው ከቻይና የወጣ ማስረጃ ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ውስጥ ‹‹የበሽታውን ምልክት የማያሳዩት አንድ ፐርሰንት ብቻ የሚሆኑት መሆናቸውንና፣ ሌላው (99 ፐርሰንቱ) ቫይረሱ ያለበት ሰው በአንድና በሁለት ቀናት ውስጥ የበሽታው ምልክቶች እንደሚታይበት›› ነበረ፡፡ ብዙ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ከጃፓን፣ ከደቡብ ኮሪያና ከሌሎች የዓለም ሥፍራዎች የተገኙ መረጃዎችን በመጥቀስ እነዚህን የተነገሩትን ድምዳሜዎች በጥያቄ ምልክት ውስጥ ከትተው ሲሞግቱ ነበረ፡፡ አሁን ግን በግልጽ እንደታወቀው – እነዚያ ከቻይና ይወጡ የነበሩትና በዓለም ጤና ድርጅት መልሰው ለዓለም ይስተጋቡ የነበሩት መረጃዎች ሁሉ – በተጋነነ ሁኔታ የተዛቡ መረጃዎች ነበሩ፡፡
• በመጨረሻ እርስዎ ቫይረሱ ወረርሽኝ ነው በማለት ባወጁበት በመጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ላይ፣ ቫይረሱ ከ4,000 ሰዎች በላይ ሕይወትን ቀጥፏል፣ እንዲሁም ቁጥራቸው ከ100,000 በላይ የሚደርሱ እና በዓለም ዙሪያ በ114 ሀገሮች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በቫይረሱ ተቀስፈዋል፡፡
• በሚያዝያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ በርካታ የአፍሪካ አምባሳደሮች በጉዋንግዙና በሌሎች የቻይና ከተሞች ከቫይረሱ ጋር ግንኙነት አላችሁ በተባሉ አፍሪካውያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን አድሏዊ አያያዝ አስመልክተው ለቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽፈዋል፡፡ የቻይና ባለሥልጣናት በእነዚህ ሀገራት ዜጎች ላይ በኃይል ወደ መለያ ጣቢያዎች የማጎር፣ የማፈናቀል፣ እና አገልግሎት ለመስጠት እምቢተኝነት ድርጊቶችን ያካተተ ዘመቻ እያካሄዱባቸው እንደሆነ እርስዎም ያውቃሉ፡፡ እነዚህን በዘረኝነት ላይ ተመሥርተው እየተከናወኑ ያሉ አድሏዊ ተግባራት በተመለከተም አንድም አስተያየት አልሰጡም፡፡ ነገር ግን እርስዎ፣ በሌላ በኩል፣ ታይዋን እርስዎ ወረርሽኙን በተመለከተ በአግባቡ አልያዙትም ያለቻቸውን በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ስሞታዎች ግን ሲቀርብልዎት መሠረተ ቢስ በሆነ መንገድ ‹‹ዘረኝነት›› ነው በማለት ገልጸውታል፡፡
• ይህ ቀውስ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የዓለም ጤና ድርጅት የቻይናን ‹‹ግልጽነት›› እያነሳ ለማወደስ በተደጋጋሚ ሲተጋ ተስተውሏል፡፡ ምንም እንኳ ቻይና በየትኛውም ምክንያት ብትመሰገን በግልጽነት ግን ልትነሳ የማትችል መሆኗ ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ እርስዎም ግን በተደጋጋሚ የእነዚህን አመስጋኞች ተርታ ተቀላቅለው ተገኝተዋል፡፡ ለአብነት ለመጥቀስ ቻይና በታሕሣሥ መጨረሻ ገደማ፣ የቫይረሱ ናሙናዎች እንዲወድሙ ትዕዛዝ በመስጠት፣ ወሳኝ የሆነን መረጃ ዓለም ሊያገኘው እንዳይችል አድርጋለች፡፡ አሁን ላይ ሆነን ራሱ ቻይና ትክክለኛውን መረጃ በሰዓቱ ለመስጠት፣ የቫይረስ ናሙናዎችንና ልየታዎችን፣ እና ስለ ቫይረሱና ስለ ቫይረሱ አነሳስ መሠረታዊ የሆኑ መረጃዎችን ሳትደብቅ ለመስጠት እምቢተኝነቷን በማሳየት የዓለማቀፉን የጤና ደንቦች በማንኳሰስ ላይ ትገኛለች፡፡ እስከዚህች እስካሁኗ ቀን ድረስ ቻይና ዓለማቀፍ ሳይንቲስቶችንና ተያያዥ እንቅስቃሴዎቻቸውን በመከልከል፣ እና ኃላፊነት የጎደላቸውን ጅምላ ውንጀላዎችን በመሰንዘር፣ እና የራሷ ኤክስፐርቶች ይፋ የሚያደርጓቸውን መረጃዎች በጽኑ በመቆጣጠር ላይ መሰማራቷን የቀጠለች ሀገር ነች፡፡
• የዓለም ጤና ድርጅት – እስካሁን ቻይና አላስገባም ያለችውን ገለልተኛ የመርማሪዎች ቡድን ወደ ሀገሯ ገብቶ የቫይረሱን አነሳስ በተመለከተ ምርመራዎችን እንዲያደርግ እንድትፈቅድ በይፋ ጥሪ እንዲያቀርብ – ሌላ ቀርቶ የራሱ የድርጅቱ የአስቸኳይ ጊዜ ኮሚቴ አቋሙን ቢያሳውቀውም – ይህን ይፋዊ ጥሪ ለቻይና ማቅረብ ተስኖታል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ይህን ለማድረግ አለመቻሉ፣ በአሁኑ የዓለም ጤና ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ‹‹የኮቪድ-19 ምላሽ››ን በተመለከተ ድርጅቱ ቀውሱን ለመመከት ነገሮችን ስላስኬደበትና ምላሽ ሰለሰጠባቸው ሁኔታዎች በገለልተኛ እና ነፃ አካል ሁሉን አቀፍ ክለሳ እንዲከናወን በማለት፣ አባል ሀገራቱ በዩናይትድ ስቴትስ የቀረበውን ጥሪ የሚደግፍ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያስተላልፉ አድርጓቸዋል፡፡ ይኸው ውሳኔም የበሽታውን መነሻ ምክንያቶች በተሻለ መንገድ ለማወቅ እንዲቻል በቫይረሱ መነሻ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ የሚጠይቅ እንደሆነ ይታወሳል፡፡
ከእነዚህ ሁሉ ውድቀቶች በላይ ነገሮችን ያከፋብን ነገር ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት ካደረገው በላይ በጣም የተሻለ ማድረግ ይችል እንደነበረ ማወቃችን ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ የዓለም ጤና ድርጅት በሌላ ዳይሬክተር ጄነራል በሚመራ ጊዜ፣ ምን ያህል ለዓለም የማበርከት አቅም እንዳለው አሳይቷል፡፡ በ1995 ዓ.ም. ላይ፣ የሳርስን /Severe Acute Respiratory Syndrome (SARS)/ በቻይና መቀስቀስ ተክትሎ – በወቅቱ ዳይሬክተር ጄነራል የነበሩት ሃርለም ብራንድትላንድ – የዓለም ጤና ድርጅት በ55 ዓመታት የጉዞ ምክር አገልግሎቱ ዓይቶት የማያውቀውን ዓይነት የማያወላዳ ቁርጠኛ ምክር በይፋ በመግለጽ – ማንኛውም በሽታው ወደተቀሰቀሰበት ወደ ደቡባዊ ቻይና እና ከዚያ በመነሳት የሚደረግ ማናቸውም ጉዞ አደጋ ያንዣበበበት እንደሆነ አሳወቁ፡፡ ወይዘሮዋ ይህን ሲያውጁ ደግሞ ቻይና በተለመደው የታወቀችበት መንገድ መረጃ ያወጡ ሰዎችን በማሰርና ሚዲያውን ሳንሱር በማድረግ ስለ በሽታው መቀስቀስ ለመሸፋፈን መሞከሯ የዓለምን ጤና ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው በማለት በይፋ የሰላ ትችታቸውን ከመሰንዘር ወደ ኋላ አላሉም ነበር፡፡ እርስዎም ያንን የዶክተር ብራንድትላንድን አርአያ ተከትለው ቢሆን ኖሮ፣ ብዙ ሕይወቶችን ማትረፍ በተቻለ ነበር፡፡
ለተከሰተው ወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠት በእርስዎ እና በድርጅትዎ አማካይነት የተወሰዱት የተሳሳቱ እርምጃዎች ዓለምን እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ እንዳስከፈሏት ግልጽ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ለዓለም የጤና ድርጅት ያለው ብቸኛ የሚበጅ መንገድ በተግባር ራሱን ከቻይና ነፃ ማድረጉን ማስመስከር ከቻለ ብቻ ነው፡፡ የእኔ አስተዳደር እንዴት ባለ መልኩ ድርጅቱ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል እየመከረበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ፈጣን ድርጊት ይፈለጋል፡፡ የምናባክነው ጊዜ የለንም፡፡ ለዚህ ነው እንደ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ይህን የማሳወቅ ግዴታ ያለብኝ፡- በቀጣዮቹ 30 ቀናት ውስጥ የዓለም ጤና ድርጅት ራሱን ለአብይ መሠረታዊ መሻሻሎች ካላበቃ አሁን ለጊዜው ያገድኩትን ዩናይትድ ስቴትስ ለዓለም ባንክ የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ቋሚ ውሳኔ እንዲሆን ለማድረግ፣ እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ አባል ሆነን የመቀጠላችንንም ጉዳይ ዳግም ለማጤን እገደዳለሁ፡፡ ከአሜሪካ ታክስ ከፋዮች ላይ ሰብስቤ ያገኘሁትን ዶላር፣ አሁን ባለበት ሁኔታ፣ በግልጽ ለአሜሪካ ጥቅሞች አስተዋፅዖ እንደሌለው እያሳየ ያለን ተቋም በገንዘብ ለመደገፍ እያዋልኩት መጓዝን አልፈቅድም፡፡
ከትህትና ጋር
/የማይነበብ የዶናልድ ትራምፕ ጥቁር ፊርማ አርፎበታል/