>

ነብይ ጋዳፊ ! (አሌክስ አብርሃም) 

ነብይ ጋዳፊ !

(አሌክስ አብርሃም)
 
* ነብዩ ‹‹….ለዚህ ዓለም ቁሳቁስና ብርቅርቅ ኑሮ አትጓጉ …እኛኮ ይሄ ምድር ድንኳናችን ነው በድንኳን ነው የምንኖረው… በድንኳን !  …ድንኳን ናት ይች ዓለም …ዘላለማዊቱን ቤታችንን መንግስተ ሰማይን  እናስብ ›› ሲል  መንግስተ ሰማይን ሳይሆን  <<ሰይጣን መንፈሴን ጠልፎ>>  የጋዳፊን ድንኳን አሳሰበኝ 
 
‹‹ወገኖቸ ›› አለ በቲቪ የማየው ነብይ …በኮሮና ምክንያት ከመኖሪያ ቤቱ ሳሎን ነበር ስብከቱንና ትንቢቱን  የሚያስተላልፈው …ግምቱ ሁለት መቶ ሽ ብር የሚገመት ሶፋ ላይ ካለአምሳ  ሽ ብር የማይቀመስ ሙሉ ልብሱን ገጥግጦ ተቀምጦ አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር የሚሸጥ ወርቃማ መፅሃፍ ቅዱሱን  የመቶ  ሽህ ብር ጠረጴዘ ላይ ከፊቱ ገልጦ   ‹‹ወገኖቸ ›› አለ … አርፌ ስብከቱን ከመስማት ይልቅ አይኔ እጅግ የተንቆጠቆጠውን የነብዩን ቤት መቃኘት ጀመረ…
ከኋላው በትንሹ  ግማሽ ሚሊየን ብር  የፈሰሰበት  የጅብሰምና እምነበረድ ስራ ቤቱን አስውቦት ይታያል …ራቅ ብሎ  በወርቃማ  የድጋፍ ብረት የታጠረ የእምነበረድ  ደረጃ ስለሚታይ ቤቱ ፎቅ እንዳለው ያስታውቃል (መቸስ ደረጃው ወደምንግስተ ሰማይ አይወስድ) በቀኝ በኩል ለኳስ አፍቃሪዎች ‹‹በዚህስ ኳስ ማየት ነበር ›› የሚያስብል በኢንች ሳይሆን በክንድ የሚገመት ቲቪ ግድግዳውን ሸፍኖታል …ትንሽ ራቅ ብሎ ከዳር እስከዳር የተዘረጋው መጋራጃ መቶ ሽዎች የፈሰሱበት የዱባይ እቃ ለመሆኑ አፍ አውጥቶ ይናገራል…ይሄን ሁሉ አይቸ ስመለስ  ‹‹ ወገኖቸ ›› አለ ነብዩ ….
‹‹….ለዚህ ዓለም ቁሳቁስና ብርቅርቅ ኑሮ አትጓጉ …እኛኮ ይሄ ምድር ድንኳናችን ነው በድንኳን ነው የምንኖረው… በድንኳን ! በተለይ አገልጋዮች አርዓያ እንሁን… በመጠን ኑረን የእንግድነት ዘመናችንን ለጌታ ሰጥተን እንለፍ …ድንኳን ናት ይች ዓለም …ዘላለማዊቱን ቤታችንን መንግስተ ሰማይን  እናስብ ›› ሲል  መንግስተ ሰማይን ሳይሆን  <<ሰይጣን መንፈሴን ጠልፎ>>  የጋዳፊን ድንኳን አሳሰበኝ !
የሊቢያው መሪ መአመር ጋዳ (ፊታሪክ ይቅለላቸውና)  በሄዱበት ተጭኖ የሚከተላቸው ድንኳን ነበር … እሳቸውም ከፖለቲካው አረፍ ሲሉ ወይም ሲደብራቸው  እንደዚህ ነብይ ስለድንኳን ኑሮ ለዓለም ህዝብ ይሰብኩ ነበር …‹‹ህዝቤ በበረሃ በሚኖርበት ድንኳን እንጅ እንደአሜሪካ ፕሬዝደንቶች  በየሄድኩበት  በተንፈላሰሰ ሆቴል አላርፍም… ለዚች ዓለም ኑሮ ኬሬዳሽ ›› ይሉ ነበር …
ድንኳናቸው ውስጥ ጎራ ሲባል ግን ከፓሪስ ቆነጃጅት እስከአረብ አገር ደናግላን የሚንፈላሰሱበት ምቹ አረቢያን መጅሊስ ከነወርቅ ክፈፉ …ግጥግጥ ብሎ ይታያል …የድንኳኑ መወጠሪያ ዘለበት ሳይቀር እንደሙሴ ዘመን የቃልኪዳን ታቦቱ ማደሪያ ድንኳን ከንፁህ ወርቅ የተሰራ ነበር ! የሻይ ማቅረቢያዎቹም እንደዛው …ድንኳኑ ከሙሉ ቆነጃጅት ባለሙያዎቹ ጋር  የማሳጅ ክፍል ሁሉ ነበረው !ባለኮከብ ሆቴል ባለቤቶች ራሱ ድንኳኑ ውስጥ ለመኖር ይመኙ ነበር ! እና ይሄ ነብይ ዝም ብሎ ስሙ ነብይ ጋዳፊ መሰለኝ …የግዚያብሔር ሰው ነብይ ጋዳፊ !
‹‹ወገኖቸ   ስሙኝ ››  አለ ….እኔ ወገኑ በደርግ ጊዜ  እናቴ ባሰፋችው ጣቃ በተሸፈነ አሮጌ ሶፋ ላይ ተቀምጨ በ14 ኢንች ቴሌቪዥን በረከቱን እካፈላለሁ ! በርግጥ ሁለተኛ ድግሪየን  ይዠ በአንድ ኮሌጅ አስተማሪ ብሆንም ዓለማዊ እውቀት ከማካፈል የግዜርን ቃል ማካፈል በረከት እንዳለው እንዲሁ ከነብዩ አኗኗር ተሰብኪያለሁ !
  ነብዩ ‹‹እስቲ ነብይ መሆን የምትፈልጉ እጃችሁን አውጡ ›› ሲል ሪሞት የያዝኩበት ቀኝ እጀን እንደሮኬት ሽቅብ ተኮስኩት…እጀን ሳወጣ  የኬሻ ኮርኒሳችንን በሪሞቱ ጫፍ  ስለነካሁት አቧራና ጥላሸት ተራገፈብኝ !ጥላሸቴን ሳራግፍ ነብይነቱ ለትንሽ አለፈኝ ! ነብዩ እኔን ያየ ይመስል ‹‹የእግዚአብሔር ጥሪ የሚያልፋችሁ ሲጣራ  በሌላ ጉዳይ ስለምትንጎዳጎዱ ነው …ወገኖቸ  ስትጠሩ መረባችሁን ጥላችሁ ከነአቧራችሁ ተከተሉት እሱ ያራግፍላችኋል …ከነሸክማችሁ ኑ እሱ ሸክማችሁን ቀሊል ያደርገዋል ›› አለ !
    ነብዩ ለሁለተኛ ጊዜ ‹‹እስቲ ብትሉት ብትሉት ብር አልያዝላችሁ ያለ …ከወር ወር የማይደርስላችሁ  በስራችሁ ስኬት የምትፈልጉ እጃችሁን አውጡ››  ሲል መንግስትን ጨምሮ መቶ ሚሊየን የኢትዮጵያ ህዝብ  ሳይቀድመኝ ፈጥኘ  እጀን ዘረጋሁ …ከመጀመሪያ ስህተቴ በመማር እጀን ወደላይ ሳይሆን ፊት ለፊት ወደቲቪው ነበር  የዘረጋሁት … ለተመለከተኝ ሰው በረከት የምካፈል ሳይሆን የናዚን ወታደራዊ ሰላምታ የምሰጥ ነበር የምመስለው ! ከማድጋዋ ዘይት እንዳያቋርጥ ነብዩ እንደባረካት ሴት እናተም ከዚች ሰዓት ጀምሮ ከኪሳችሁ ብር አይነጥፍም አለ ! ውጤቱን ከወር በኋላ አሳውቃለሁ ! ላመነ የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝም ከወር ወር ይደርሳል! አሜን !
ነብዩ ትንቢት መናገር ጀመረ ‹‹ በዚህ በሰሜን በኩል አማራ ክልልን አልፎ ኤርትራ ሳይደርስ …ጌታ ሰዎች ለምርጫ ደፋ ቀና ሲሉ ያሳየኛል …ቀዳዳ ያለው ኮሮጆ ተሸክመው ነው የሚያሳየኝ ….ጌታ እንዲህ ይላል ሃሳባችሁን ምርጫ ቦርድ አልደገፈውምና በፊቴ ሃጢያት ሁኗል ተመለሱ ኮሮጇችሁንም መልሱ እምቢ ካላችሁ ግን መቸስ ምን ይደረጋል ህገመንግስቱ ላይ ትርጓሜ ይሰጥ ከማለት በስተቀር ›› አለ ! ይሄማ የብልፅግና  መንፈስ ነው አልኩና ወዲያው ንስሃ ገባሁ !
መጨረሻ ላይ ነብዩ ክርስቶስን ከመስበክ በተረፈው አንድ ሰዓት  ሚስቱን ሰበከ … ካሁን ካሁን ታማልዳለች ሊል ነው እንዴ እስከምል  ነበር ሚስቱን  የሰቀላት !  ‹‹ጌታ የባረካት… ትሁት …ቆንጆ… የልጆቸ እናት…ቸር…የተራቡትን ይምታበላ…የታረዙትን የምታለብስ …ካለቀሱት ጋር የምታለቅስ …አንዴ ፆም ከያዘች ፌዴራል ፖሊስ መጥቶ በግድ ካላስፈታት የማትፈታ  ጉልበቷ ከመንበርከክ ብዛት የታመመ …ለአገሯ ማቅ ለብሳ  ትቢያ ነስንሳ የምትፀልይ …እውነት እላችኋለሁ ልብሷን ሁሉ ለድሆች ሰጥታ ቁም ሳጥናችን ወስጥ  ፒጃማና የዋና ልብስ ብቻ ነው የተረፋት … እስቲ ባርኳት …ካሜራው ሚስቱ ላይ አረፈ …
   በእውቋ ዲዛየነር ቲቲ ሃበሻ የተሰራ  የመቶ ሃምሳ ሽህ ብር  ያበሻ ቀሚስ …በተረከዘ ረጅም የጣሊያን ጫማ የለበሰች …እንዲሁም ሰላሳ ሽህ ብር የሚያወጣ ዊግ እንደአክሊል የደፋች ፊቷ በምቾት ሊፈነዳ የደረሰ የጌታ ሰው ብቅ አለች …እጇ ላይ ያለውን የወርቅ ብራዝሌት አንገቷ ላይ የጠለቀችውን የወርቅ ሃብል ጆሮዋ ላይ ያንጠለጠለችውን የወርቅ የጆሮ ጌጥ እና እግሯ ላይ ያሰረችውን የወርቅ አልቦ ስመለከት …ጌታ ካሜራ ማኑንን  እንደ ሐዋሪያው  ቅዱስ  ፊሊጶስ ነጥቆ ሻኪሶ የወርቅ ጉድጓድ ውስጥ የጣለው ነበር የመሰለኝ !
ሞልቀቅ ባለ ድምጽ ‹‹ወገኖቸ …›› ስትል ‹‹ አይ ….ወገንሽን እዛ እነቢዮንሴና ሻኪራ ጋር ፈልጊ ብየ በብስጭት ቲቪየን ዘጋኋት ! 14 ኢንች ቲቪየ ድርግም ስትል የምትጣቀስ ነበር የምትመስለው ! ትክዝ ብየ እንዲህ አልኩ ‹‹ጌታ ሆይ በቃልም በኑሮም ወገናችን የሆነ ሰባኪ ስጥን ››

https://www.facebook.com/363902217152782/posts/1348948891981438/

Filed in: Amharic