>
5:21 pm - Thursday July 21, 9678

የማይሚዶ ጦርነት...!!!!  (ኢዮብ ዘለቀ)

የማይሚዶ ጦርነት…!!!!

 ኢዮብ ዘለቀ 

* ማስታወሻነቱ ከዛሬ 32 ዓመት በፊት  ግንቦት 14 ቀን 1980 ዓ.ም ማይ ሚዶ ላይ ላለቁት የኢትዮጲያ አየር ወልድ አባላት
 
እንደ መንደርደሪያ
ዘመኑ 1951 ዓ.ም ፤ ሀገሪቷ ካላት መደበኛ ሠራዊት በተጨማሪም የተለያዩ አስቸጋሪ ግዳጆች በብቃት መወጣት የሚችል ልዮ የአየር ወለድ ሀይል ማቋቋም በማስፈለጉ ከፖሊስ ሠራዊት ክቡር ዘበኛ እና ጦር ሠራዊት  የተመለመሉ 13 አባላቶች  በሻለቃ ዮሓንስ መሪነት ወደ እስራኤል ለልዮ የአየር ወለድ ሥልጠና ተላኩ፤ ከ ሰልጣኛቹ ውስጥም ዘጠኙ ስልጠናቸውን በከፍተኛ ደረጃ አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
ከ ሁለት አመት በሁዋላም ከሠራዊቱ የተመለመሉ ሌሎች አባላት ወደ እስራዔል ተልከው ተመሳሳይ የአየር ወለድ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጔል፤ ለአየር ወለድ ይሰጠው የነበረው  ስልጠና በውጭ ብቻ መሰጠት የለበትም ከሚል እሳቤ በመነሳትም  በሀገር ውስጥ ስልጠናዎችንም እንዲያገኙ ተደርጔል ።
ይህ ሀይል  የሀገሪቱ ተወርዋሪ ሀይል በመሆን  በተለያዮ ቦታዎች ተልኮ ግዳጁን በብቃት በመወጣት ከፍተኛ የሆነ ዝናን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጎናጸፍ ችሏል ።
በ 1967 ቱ መፈንቅለ መንግስት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከስልጣን ሲወገዱ በወቅቱ ስልጣን የያዘው ሀይል በመጀመርያው አካባቢ ከዚህ የአየር ወለድ ሀይል ጋር መልካም የሆነ ግንኑነት ነበረው ኃላ ላይ ግን በወቅቱ  ከደርግ ጋር በከፍተኛ ሁኔታ ይፋለሙ ከነበሩት ኢህአፓ ጋር ትስስር አለው የሚል ጥርጣሬ በመፈጠሩ  እስከ መፍረሰ የደረሰበት አጋጣሚም ተፈጥሮ ነበር ።
ይህንንም ክስተት  ብ/ጄ ተስፋዬ ኃ/ማሪያም የጦር ሜዳ ውሎ በሚለው መጽሀፋቸው በወቅቱ የተፈጠረውን እንደሚከተለው ያብራራሉ
” ከ 1968 ዓ.ም ጀምሮ ደርግ የአየር ወለድን ጦር በጥርጣሬ አይን ይመለከተው ጀመር ፤ ከተቃራኒ ቡድኖች በተለይ በተለይ ( ኢህአፓ ) ጋር እየወገነ ነው የሚል ስጋት አደረበትና በ 1970 ዓ.ም በአስቸኳይ ፈርሶ በየክፍሉ እንዲበተኑ ሞያተኛቹ ሁሉ በተራ ተዋጊነት ተመድበው እንዲሰሩ ተወሰነ “
በዚህ  ሁኔታ ግን ብዙም መዝለቅ አልተቻለም በወቅቱ አገሪቱ ከነበረችበት ውስብስብ ችግሮች አንጻር የአየር ወለድ ክፍለ ጦር አስፈላጊነት እየጎላ መጣ፤  በ 1973 ዓ.ም አንድ የአየር ወለድ ብርጌድንም  ለማሰልጠን እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ፤ 2600 ወጣቶችም ተመለመሉ በአዋሳና በደብረዘይትም የተግባርና የቲዎሪ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ተደረገ ፤ የብርጌዷ  አባላትም በመጋቢት  ወር 1975 ዓም ስልጠናቸውን አጠናቀው ተመረቁ ፤ ብርጌዷም  አምሰተኛ የአየር ወለድ ብርጌድ የሚል መጠሪያንም አገኘች ።
ከዚህ በኃላ ተከታታይ ስልጠናዋች ለአዳዲስ የአየር ወለድ ምልምሎችም መስጠት ተጀመረ ፤ የአየር ወለድ ሀይልም  እስከ ክፍለ ጦር ደረጃ የተዋቀረበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር። በዚህ ደረጃ ብቅ ካሉት ውስጥ  የ 102 ኛው የአየር ወለድ ክፍለ ጦር ተጠቃሽ ነው።
የ 102 ኛው የአየር ወለድ  ክፍለ ጦር የተለያዩ  ግዳጆችን  በመፈጸም አኩሪ ታሪክን ለማስመዝገብ የቻለ የጠንካራ አገር ወዳድ ኢትዮጲያውያኖች ስብስብ ነው ፤ በከባድ ግዳጆች ላይ በመሰማራት ደማቅ ታሪክንም ጽፏል  ፤ ለአብነት ያህል…..
 በ ዘመቻ ባህረ ነጋሽ ምእራፍ አንድ ፦
♦ ነሐሴ 18 ቀን 1977 ዓ.ም ከ 17 ኛው ሜካናይዝድ ብርጌድ ጋር በመሆን በሰነዘረው ማጥቃት ሻዕቢያን ደምስሶ ባሬንቱን ነጻ አውጥቷል
♦ ከ ነሐሴ 18 በሁዋላ ባሉት ተከታታይ ቀናት እስከ ነሐሴ 24 ቀን 1977 ዓ.ም ድረስ ሐይኮታብ ፣ተሰነይንና አሊ ጊደርን ሰብደራትንና ጋሎጅን በአጠቃላይ የጋሻንና ሰቲት አውራጃ ከተሞችና ሰፋፊ እርሻዋችን በሙሉ  ነጻ አውጥተዋል  ።
የማይሚዶው  ጦርነት እና በ 102 ኛው የአየር ወለድ ክፍለ ጦር ላይ  የደረሰው አሳዛኝ እልቂት 
በግንቦት ወር 1980 ዓ.ም የ 102 ኛው የአየር ወለድ ክፍለ ጦር ከረን ጦር ግንባር በአንድ  ምሥጢራዊ   ግዳጀ ላይ ለመሰማራት በተጠንቀቅ ይጠባበቅ ነበር ፤ ሆኖም ግን እጅግ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከ ሁለተኛው  አብዮታዊ ስራዊት ወደ ሌላ ግንባር እንዲንቀሳቀስ መልእክት ይደርሰዋል ። ጦሩም ግንቦት 7 ቀን 1980 ዓ.ም ከ ከረን ግንባር ተነስቶ በሽኢብ እንዲሰባሰቡ ተደረገ፤  አዲሱ  እቅድ ወደ ማይሚዶ በመንቀሳቀስ ጠላትን ከጀርባው ማጥቃት የሚል ነበር ።
ከዘመቻው መጀመር አስቀድሞ ጦሩን በማማከር  የሚሰራው ሩሲያዊ ጀነራል እና ሌሎች ወታደራዊ መኮንኖች ማለትም  ፣ ሜጀር ጄነራል አምሃ ደስታ ፣ ሜጀር ጀነራል ሃይሉ ገ/ ሚካኤል ብ/ጄነራል ተስፋዬ ትርፌ  ሩሲያውን  ሰው አጅበው  ለሠራዊቱ አዛዥ ብርጋዲየር ጀነራል ተመስገን ገመቹ የመጨረሻ የስራ መመሪያ ለመስጠት  በስፍራው ተገኝተው ነበር  ፤ በዚህ ወቅት የ አየር ወለድ የ ክፍለጦሩ  አዛዥ ብ/ጄ ተመስገን ገመቹ ”   ዘመቻው የችኮላ ነው ፤አንድ ጊዜ ቆም ብለን ልናስብበት ይገባል፤ ኃላ እንዳንጸጸት ፤ የግንቦት   ወር የማይሚዶ የአየር ሁኔታ በህይወት ለመቆየት እጅግ ፈታኝ ነው፤ የሙቀት መጠኑ ከ 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ  በላይ የሚሆንበት ወቅት ነው፤  በዛ ላይ በቂ የውሃና የስንቅ ዝግጅት አልተደረገም፤ የተሰጠን ካርታ ወቅታዊ አይደለም  እናም በዚህ ሁኔታዎች ውስጥ እጅግ ወጣት የሆኑ የሰራዊቱ አባላት ለምን እናስፈጃለን”  ሲሉ ስሜታዊ የሆነ ንግግር ተናገሩ …ሆኖም ግን ሰሚ አላገኙም  ፤ የአካባቢውን ሁኔታ ጠንቅቀው የሚያውቁት የ ሰራዊቱ አዛዥችም የሩሲያውን አማካሪ ከመደገፍ ውጭ ለ ብ/ጄነራል ተመሰገን  ከጎናቸው ሊቆሙ አልቻሉም ።የሩሲያው ሰውም ጀነራል ተመስገን ገመቹን” ወደ ኃላ ብታፈገፍግ አንገትህን እንቆርጠዋለን” ብለው ዝተው ወደ ሂሊኮፕተራቸው አመሩ አብረዋቸው  የመጡት ጀነራሎችም ተከትሏቸው ፤ ከጀነራል ተመስገን ገመቹ ጎን በመሆን የተሟገተ አንድም ስው አልነበረም ።
ሜጀር ጀነራል መርዳሣ ሌሊሳ በአንድ ወቅት ከአንድ የራዲዮ ጣቢያ ጋር  ባደጉት ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት  ጁነራል ተመስገን የሚመራው ጦር ማጥቃት ከመጀመሩ አንድ ቀን ቀድም ብሎ በአንዲት ግራር   ጥላ ስር ቁጭ ብለን አውርተን ነበር፤ ፈጽሞ ከዚህ ውጊያ በ ህይወት  እንደማይወጣ ያውቀው ነበር፤  የሆነ  ደብዳቤም ለቤተሰቤ ስጥልኝ ብሎ  እንደስጣቸውም  ተናግረዋል /ይህቺ ደብዳቤ  ከቤተሰብ ደርሳ ከሆነ ልጃቸው አሌክስ ይነገረን ይሆናል ።/
በ ወቅቱ ምንም  አይነት አማራጭ ያልነበራቸው   የ 102 ኛው የአየር ወለድ ክፍለ ጦር አባላት ከሻቢያ ሀይሎች ጋር ጦርነት ገጠሙ ፤ በወቅቱ በዚያች ስፍራ ምን እንደተፈጠረ ሜጀር ጀነራል መርዳሣ ሊሊሴ የኢትዮጲያዊነት ትውስታ በተሰኘው መጽሀፋቸው በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ  እንደሚከተው ያስቀምጡታል …
” ከጅምሩ የተቀበለው ግዳጅ የጎመዘዘውና ላቀረበውም ጥያቄ በተሰጠው ደንታቢስነት ምላሽ የተበሳጨው ጄ/ ተመስገን አማራጭ አልነበረውምና የሩሲያውን አማካሪ ጀነራል ትእዛዝ ለመፈጸም ጦሩን ይዞ ተንቀሳቀሰ ፤ ያለ አንዳች አጋዥ ሀይል የአየር ወለድ ብርጌዶች ብቻቸውን ግንቦት 13 ቀን ከሻዕቢያ ጋር ውጊያ ገጠሙ ።  …….የአየር ወለድ ጦር አባላት ያንን ሁሉ የሚያኮራና በወኔ የተሞላ ወታደራዊ ግስጋሴ ሲያደርጉ ውሃና ቀለብ አልነበራቸውም ነበር ፤ በዚያ ላይ ሰን ስትሮክ /Sun Stroke / ወታደሮችን እየፈጀ ነበር ።”
በዚህች ወሳኝ የፍልሚያ ሜዳ ላይ ከጠላት እየተኮካሰ ከሚወድቀው በላይ በውሃ ጥም የሚሞተው በዛ፤ በተደጋሚሚ የድረሱልን ጥሪ ለማድረግ   የሬድዮ ግንኙነት ለማድርግ ቢሞከርም አልተጫለም ራሱን  የሚያጠፋው ሰራዊትም ቁጥር በዛ
ከተደጋሚ ሙከራ በሁውላ ደብረ ዘይት ከሚገኘው ቀሪ ክፍል ጋር መገናኘት ስለተቻለ ብ/ ጀነራል ተመስገን ገመቹ የሚከተውን መልእክት ለ ጄነራል ደምሴ ቡልቶ አስተላለፋ
 ” በማእረግ የጀነራል ማእረግ ደርሻለሁ በእድሜም ቢሆን ገፍቻለሁ ፤ ለኔ ሳይሆን ለዚህ ታዳጊ ጦር ስትል መርኪያ ሳይሆን ከንፈር ማርጠቢያ ውሃ ላክልኝ “
ሆኖም ግን ምላሹ አሁንም የዘገየ ነበር ሻዕቢያም  ማጥቃቷን  ጀመረች የክፍለ ጦሩ አዛዥ ጄነራል ተመስገን ገመቹ በጦርነቱ ላይ ቆሰሉ ፤ በጠላት እጅ ላለመውደቅ የእራሳቸውን ሽጉጥ ጠጥተው ሞቱ።
በዚህ ውጊያ አብዛኛው  የአየር ወለድ አባላት በውሃ ጥም አልቀዋል ።
ክብር  ለኢትዮጵያ   ሠራዊት !!!!
Filed in: Amharic