>
5:33 pm - Saturday December 5, 9846

መንጌ - የኢትዮጵያን ሴቶች የምሩን ያከበረ ጀግና!!! (አሰፋ ሀይሉ)

መንጌ – የኢትዮጵያን ሴቶች የምሩን ያከበረ ጀግና!!!

አሰፋ ሀይሉ 
 
መንጌ – ከጎኑ መጽሐፍ ከእጇ ካልተለያት ባለቤቱ ከውባንቺ ቢሻው – እና በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ፣ እንዲሸነሸኑና እንዲጠላሉ ካልተደረጉት የያኔዎቹ ክብርት ብርቅዬ ኢትዮጵያጵያውያን ሴቶች ጋር – የተነሳው ፎቶ ነው! እንግዲህ – የያኔው ክቡር የኢህዲሪ ፕሬዚደንት ሌተና ኮ/ል ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም – ዓለማቀፉን የሴቶች ቀን በቤተመንግሥት – እንዲህ ያከብሩት ነበር!
 
ብዙ ጊዜ ስለ ሴቶች እኩልነት ጥናቶች ሲቀርቡ፣ ሲነገር፣ ሲዘከር – የመንጌ ስም ሲዘለል አያለሁ፡፡ እና ይገርመኛል በጣም፡፡ ስለ ሴቶች ‹‹ኢምፓወርመንት›› – ሴቶች በማኅበረሰባችን የሚገባቸውን ሚና እንዲያገኙ አበክሮ የሰራውን መንጌን ሳታነሳ እንዴት ስለ ሴቶች ለተለያዩ ሚናዎች መብቃት ታሪክ ማውራት ትችላለህ? መንጌን አትውደደው፡፡ ግን እውነት የሆነውን ታሪኩን ለምን ታልፈዋለህ? 
 
ከመንጌ ዘመን ሴቶች ጥቂቶቹን እናንሳ፡፡ በሳንቲሞቻችን ላይ የነበሩ የነገሥታቱን ቤተሰቦች ምስሎች ሁሉ በጭቁን የሀገር ልጆች ምስል እንዲተካ ሲወሰን – በገንዘቦቹና ሳንቲሞቹ ላይ – የሴቶችም የወንዶችም ምስሎች እንዲወጡ የመንጌ ፅኑ አቋም ነበረ፡፡ ምናልባት በወቅቱ የሳንቲሞቹን ንድፎች የሰሩት የጥበብ ሰዎች አሁንም በሕይወት ስላሉ – ይሄን እውነት ቢጠየቁ የሚክዱት አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም የስሙኒዋ ሴት ትገርመኝ ነበር – አብዮቱ ከወንድ እኩል በሴትም እየተመራ የምታሳይ – የወቅቱን የመንጌን የሴቶች እኩልነት አስተሳሰብ ቀርፃ የያዘች – እና እስካሁንም ያለች ሳንቲም ነችና! በነገራችን ላይ – በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ያለ ሴቶች የነቃ ተሳትፎ አብዮቱ ግቡን አይመታም!›› የሚል ሀገርአቀፍ ታዋቂነትን ያገኘ መፈክር ከአፅናፍ አፅናፍ የተስተጋባው በመንጌ ጊዜ ነው፡፡ 
 
ደግሞ በመፈክር ብቻም አልቀረም! እውነትም በኢትዮጵያ ታሪክ ሴቶች በዘርፈ ብዙ መስኮች ከፍተኛውን የነቃ ተሳትፏቸውን ያሳዩት በመንጌ ዘመን ነበር፡፡ የፋይናንስ ምሁሯን የአ.ኢ.ሴ.ማ.ዋን ሊቀመንበር እነ ወይዘሮ ጥሩወርቅን የሚያስታውስ – ሴቶች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዴት ያለ ቆራጥ ሚና ይጫወቱ እንደነበረ አበክሮ ያስታውሳል፡፡ ‹‹የቆራጡ መሪ ፍሬው ጎመራ›› ዘፋኟ ሻለቃ ውብሻው ስለሺ ከዚያ ዘመን ቆራጥ ሴቶች አትረሳኝም፡፡ በስቱድዮ ውስጥ ወደ ከፍታ እየዘለለች ‹‹ሎሚ.. ፅባ.. አብዮታዊት ኢትዮጵያ…›› እያለች ትዘፍን የነበረች ስሟ አሁን የተዘነጋኝ ቆራጥና አስደማሚ የትግርኛ ዘፋኝ፡፡ ወደ ኤርትራ የቅስቀሳ ዘፈን ለማቅረብ ሰትጓዝ ሻዕቢያ እርጉዝ እያለች በላውንቸር ተኩሶ ከሌሎች 16 ሙዚቀኞች ጋር የገደላት (እና በሕይወት እያለች በግልም የማውቃት!) የሐረሯ የምሥራቅ ዕዝ ኦርኬስትራ መለሎ ሙዘቀኛ ንግሥት አበበ፡፡ ብዙ ብዙ በለዛቸውና በተሰጥዖዋቸው፣ በቆራጥነታቸው ልዩ ተወዳጅነትን ያተረፉ፣ ትኩስ ደም የተላበሱ አይረሴ ሴቶች በብሔራዊ ደረጃ ታዋቂ ሆነው ብቅ ያሉበት ዘመን ነበረ – የመንጌ ጊዜ! 
 
እና መንጌ በእውነትም – ሴቶችን ከወንዶች እኩል ከፍ እንዲሉ፣ በሀገር ደረጃ ታላቅ ሚናን እንዲጫወቱ፣ ከፍ ያለ አስተዋፅዖ ያደረገ መሪ ነበር ቢባል ማንም የማይክደው ሃቅ ነው! ስለ መንጌ ዘመን ሳነሳ – በበኩሌ በ70ዎቹ መጨረሻ ገደማ – ልደታ ሰፈር ጎረቤታችን የነበሩትን እትዬ እታገኝን አልረሳቸውም፡፡ እትዬ እታገኝ የሁለት ወንዶች ልጆች እናትና አብዮት ጠባቂ ነበሩ፡፡ ቆፍጣና! እሳቸው እያሉ ማን የዚያችን ሰፈር ደኖች ንክች ሊያደርግ?! እሳቸው እያሉ ማን ወንድ ደፍሮ ሚስቱን ሊነካ!? ማን ሌባ ያን ሰፈር ሊረግጥ?! እትዬ እታገኝ እንደ አብዮት ጠባቂ ብቻ ሳይሆን እንደ እናት ደግሞ ብዙ ወጣቶችን ከብሔራዊ ምልመላ አስጥለዋልም ይባላል! እንደ እትዬ እታገኝ ያሉ ብዙ ብዙ የዘመኑን ቆራጥ ሴቶች በዘመኑ እግሬን ባሳረፍኩባቸው ስፍራዎች ሁሉ አውቃለሁ፡፡ እና እነዚያ ዓይነቶቹን ቆራጥ ወይዛዝርት ሴቶች በየቤቱ፣ በየሀገሩ፣ በየመንደሩ፣ በመላዋ ኢትዮጵያ ያበቀለ – የሴቶች እኩልነት ሃዋርያ ነበር መንጌ! 
 
ምን ይህ ብቻ? ለመጀመሪያ ጊዜ የትምህርት ሚኒስቴር በሚያሳትማቸው የመማሪያ መጽሐፎች ላይ የየብሔረሰቡን ሴቶች ምስል ተካትቶ እንዲወጣ ያደረገ ሰው ነበረ መንጌ፡፡ የዛሬን አያድርገውና ዛሬ የዚህ የጎሳ አፓርታይድ ዋና መገለጫ የሆኑት የሐረር አደሬዎች – ያኔ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መንግሥቱ ኃይለማርያም ነበረ – የአደሬ ሴትን በመማሪያ መጽሐፍ ላይ ፎቶዋ እንዲወጣ እና ብዙሃኑ ዜጋ ስለሀገሩ ብሔሮች እንዲያውቅ ያደረገው፡፡ የሴቶች ዕደ ጥበብ ሥራዎች በየሀገሩ በሙዝየም እንዲቀመጡና ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች እንዲታዩ፣ እንዲተዋወቁ፣ እና ሴቶቹን እንዲበረታቱ ያደረገ – የሴቶች ተንከባካቢ ነበረ መንጌ! ኧረ ብዙ ነው! ስንቱ ወተርቶ ያልቃል? 
 
(በነገራችን ላይ የመንጌን ወሳኝ ተግባር ስናገር – በ60ዎቹ ላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የተሰማሩ እንደ እነ ኢህአፓና መኤሶን ያሉ ድርጅቶችም – የኢትዮጵያን ሴቶች ከፍ ወዳለ ሀገራዊ ሚና በማብቃት በኩል አበርክቶት ማንኳሰሴ እንዳልሆነ ልብ ይባልልኝ!) 
 
በመጨረሻም – የሴቶች አክባሪውን የታላቋ ኢትዮጵያ የመጨረሻ መሪ – ቆራጡን መንጌን – ክፉም በጎም ቢያደርግ – ፈጣሪ እንዲህ እንዲህ ዓይነቶቹን ተወርተው የማያልቁ በጎ በረከቶቹን ቆጥሮ – ከዚህም በላይ ረዥም ዕድሜን ጨምሮ እንዲሰጠው ተመኘሁለት! 
Filed in: Amharic