>

ህገ ወጡ ግንቦት 20...!!! (ተስፋዬ ሀይለማርያም)

ህገ ወጡ ግንቦት 20…!!!

ተስፋዬ ሀይለማርያም

ጠ/ሚር ዶ/ር አብይ ለግንቦት 20 የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፍከው ለማን ነው? መቼም ለእኔና ለወዳጆቼ አይደለም። መልዕክቱ በህወሃት እንዳይወልዱ የማምከኛ መርፌ ለተወጉት የአማራ ተወላጆች አይደለም። በአርባ ጉጉ ለታረዱ ወገኖችም አይመስለኝም። መልዕክቱ በኢሬቻ በዓል ለሞቱ የኦሮሞ ልጆች ቤተሰቦችም ሊሆን አይችልም። መልዕክቱ በጋምቤላ በወያኔ ለተጨፈጨፉ ወገኖችም አይመስለኘኝም።
መቼም “ክልል እንሁን” ብለው ለጠየቁና በመትረየስ ለተረሸኑ  የደቡብ ህዝቦችም አይሆንም። መልዕክቱ ህወሃት ለሚያሰቃያቸው ሃቀኛ የትግራይ ተወላጆች አይደለም። መልዕክቱ በወያኔ እሥር ቤቶች ለተገደሉ፣ ለተገረፉና ለተኮላሹ አይሆንም። መልዕክቱ ኢትዮጵያን ጠብቀው ላቆዩ የቀድሞ ሠራዊት አባላት አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሬ እንኳን ደስ አላችሁ ያልከው ማንን ነው?
ለማንኛውም ግንቦት 20 ህገ ወጥ በዓል ነው። ለምን ማለት ጥሩ ነው። በኢትዮጵያ የሚከበሩ ሁሉም ህዝባዊ በዓላት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቀው በአዋጅ የተደነገጉ ናቸው። ከግንቦት 20 በስተቀር።
ግንቦት 20 ሥልጣን በተሰጠው አካል እንደ ህዝባዊ በዓል ተቆጥሮ በአዋጅ ዕውቅና ያልተሰጠውና በተለምዶ የቀን መቁጠሪያ (calendar) ላይ by default  እንደ በዓል የሚቆጠር የ”ዕረፍት” ቀን ነው።
በጣም የሚገርመው ከግንቦት 20 ይልቅ  መስከረም 2 ቀን ህጋዊ የህዝብ በዓል መሆኑ ነው። ምክንያቱም መስከረም 2 የአብዮት በዓል እንዲሆን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀና በአዋጅ የተደነገገ ህዝባዊ በዓል ነው። መስከረም 2 እስከ ዛሬ ድረስ በአዋጅ አልተሻረም፣ ግንቦት 20 ደግሞ እስከ ዛሬ ድረስ በአዋጅ አልጸደቀም። ስለዚህ ግንቦት 20 ማንም ሊያከብረው የማይገባ ህገ ወጥ በዓል ነው።
 “ግንቦት 20 ደርግ የወደቀበት” ….
ሌለው ሁሌ የሚገርመኝ ካላንደር ላይ ግንቦት 20 ለምን እንደሚከበር ሲዘግብ  “ግንቦት 20 ደርግ የወደቀበት” እያለ ነው። ይህ የሚያሳየው የበዓሉ ባለቤቶችን የዞረ አስተሳሰብ ነው።  አስቡት እስቲ! እንዴት የአንድ ነገር መውደቅ እንደ በዓል ይቆጠራል?
“ደርግ የወደቀበት” ብሎ ከማክበር ይልቅ “ኢህአዴግ ያሸነፈበት” ብሎ ማክበር ለእስክስታውም ይመቻል። ሰዎቹ በደርግ መውደቅ እንጂ በእነሱ ማሸነፍ እስከ ዛሬ ድረስ እርግጠኞች አይደሉም
 
ግንቦት 20  ዘረኞች የነገሱባት….
የበርካቶች ተስፋ የጨለመበት፣ ከሐገር አልፎ አሕጉርንና አለምን ያስደመሙ የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊት የተበተነባት፣ ምሁራን የተገፉበት ፣ ለሐገርና ለወገን የሚተቅሙ የተገደሉባት የተሰደዱባትና ዘረኞችና አናሳ የአፓርታይድ ስርዓት አራማጆች ስልጣን በጠበንጃ የጨበጡባት እለት ናት።ሕወሓት/ኢሕአዴግ ስማቸውን እየቀያየሩ በሕዝብ አናት ላይ የሚዘፍኑባት አገር የተፈጠረችው በዛሬው እለት ነው።
ዛሬ ላይ ቆመን የምናያቸው ሐገርን ለማተራመስ አመጽ የሚሰብኩ፣ ፖለቲካውን በዘር የሚለኩ፣ ቢሮክራሲውን በጎጥና በብሔር የሞሉ፣ ቅድሚያ ለዜጎች ሳይሆን ለዘር የሚሰጡ፣ አደርባዮች፣ የአፓርታይድ አራማጆች፣ የሚናገሩትና የሚያደርጉት የተለያየ የሆኑ ባለስልጣኖች። አስመሳዮችና በወሬ የሚደልሉ ታሪክ አጥፊዎች፣ የፖለቲካ ደላሎችና የ አዞ እንባ አፍሳሾች፣ ያዘኑ መስለው ሕዝብን የካዱ ውርጃዎች የግንቦት ሃያ ፍሬዎች ትሩፋቶች ናቸው። አሁንም አብረውን አሉ።
 
ግንቦት 20  በጨለማ ጉም ተሸፈንበት…
 
 አገርና ህዝብ ጥቁር የሃዘን ልብስ ለበሱ:: ሲጠሏት እና ታሪኳን እና ህዝቧን ሲያዋርዱን ሲያንቋሽሹ በነበሩት ወያኔ ህወሃት ለእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ተዳረገች:: ዘረኛው እና ጎጠኛው ወያኔ ህወሃት በመለስ ዜናዊ የሚመራው የማፍያ ፋሺስት ግልገል እና ግብረ አበሮቹ ጸረ ሀገር እና ጸረ ህዝብ የሆኑትን ለዘመናት የተከበረው የምኒሊክ ቤተ መንግስት ተቆጣጥረው የግልገል ፋሺስቶች መንደላቀቂያ ሆነ:: እነሱም ስልጣን እንደጨበጡ ኤርትራን አስገንጥለው የቀይ ባህር ንግስት የነበረችው ኢትዮጵያ ወደብ ወይም የባህር በርዋን አጥታ አንገትዋ የተቆረጠ ዝግ አገር አደረጉዋት::
ወያኔ ህወሃት ከደደቢት ይዞት የመጣውን ህገ ደንቡን የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አደረገው:: ኢትዮጵያን በዘር ፣ በቋንቋ እና በሃይማኖት ከፋፍሎ የህዝቡን አንድነት እና ኢትዮጵያዊነት አጠፋዋለሁ ብሎ ያመጣውን የዘረኝነት ህጉን በኢትዮጵያ ዘረጋ::
አሮጌ የአምባገነኖች ስልቻ በአዲስ የአምባገነኖች ስልቻ የተተካበት። ወታደራዊው ደርግ ሲሞት ወንበዴው ደርግ የተወለደባት ቀን ግንቦት ሐያ። ትልቅ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ኪሳራ በሀገር ላይ ያደረሱ ሐገሪቱን ካለባሕር በር ያስቀሩ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ስልጣኑን የተቆናጠጡበት እለት ግንቦት 20።
Filed in: Amharic