>
5:18 pm - Tuesday June 15, 5210

ዘረኝነት (መስፍን አረጋ )

ዘረኝነት

መስፍን አረጋ 


የራሱን ንጹህ ጥብቆ፣ ራሱ ጥሎ አውልቆ

የሰው ቆሻሻ አጥልቆ፣ ተበክሎ ተጨመላልቆ፣

ሰው ተጸይፎት ርቆ፣ ሲሳለቅበት በሽቆ፣

ዙሮ እንባ ፈንጥቆ፣ እያለቀሰ ተነፋርቆ

ተናቅኩኝ ይላል ተንሰቅስቆ፣ ራሱን በራሱ አስንቆ፡፡

 

ዘረኝነት የሌላ የምንም ሳይሆን ራስንና የራስን የማክበር ወይም ያለማክበር ውጤት ነው፡፡  በራስህ ተማመን፣ ራስህን አክብር፣ በማንነትህና በምንነትህ ኩራ፣ የራስህን ውደድ፣ ጠንክረህ ሥራ፣ ሳይወዱ በግዳቸው ያከብሩሃል፡፡ 

 ውዴታ ቸሬታ፣ ከበሬታ ግዴታ ነው፡፡  ሰውን እንዲያከብር እንጅ እንዲወድ ማስገደድ አይቻልም፡፡  ማስገደድ ይቅርና ማስተማርም አይቻልም፡፡  

እኔ እበልጥሃለሁ በማለት ሊርቅህ የሚሸሽን ሰው፣ እኩል ነን እያልከ ብትከተለው በበለጠ ፍጥነት ይሸሽሃል፡፡  እኔ እበልጠሃለሁ ብለህ በተቃራኒ አቅጣጫ ከሄድክ ግን ቢያንስ ባለበት ይቆማል፡፡  የመለማመጥ ትርፉ መከራን ማርዘም፣ ፍዳን ማብዛት፣ አበሳን ማባስ ብቻ ነው፡፡  የሚጠላን ሲለማመጡት በጥላቻው ላይ ንቀት ይጨምርበትና ይበልጥ ይጠላል፣ የሚጠላን ሲጠሉት ግን ጥላቸው በከበሬታ ይለዝባል፡፡  

ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የመጀመርያው ያሜሪቃ ‹‹ጥቁር›› ፊምበር (president) ባራክ ኦባማ ነው፡፡  አቦማ ለሚወዱት ጥቁሮችና ተራማጅ ነጮች (progressive whites) በተለይም ደግሞ ግራፈናኞች (leftists) ከሚያስበው በላይ ለሚጠሉት ዘረኛ ነጮች በመጨነቅ ሲለማመጣቸው፣ ዘረኞቹ ለሱ ያላቸው ከበሬታ እየቀነሰ፣ ይበልጥ እየናቁትና ንቀታቸውም ጥላቻቸውን ይበልጥ በማጠንከር እያመረረው ሄደ፡፡  እሱም ከሁለት ያጣ ጎመን ሆነ፡፡  ዘረኛ ነጮቹ እንደሚጠሉት፣ እሱም ይውጣላችሁ ቢላቸው ኖሮ ፣ ባይወዱትም ስለማይንቁት ከበሬታቸው ጥላቻቸውን ባለዘበው ነበር፡፡  

ኦባማን ዘረኞቹ ነጮች የሚጠሉት በድርጊቱ ሳይሆን በሱነቱ ስለሆነ፣ ምንም ቢያደርግላቸው ዐመድ አፋሽ እንደሚሆን እሱም ራሱ በትክክል የተረዳው አይመስለኝም፡፡   

ጥቁር አሜሪቃውያን ደግሞ የተቀደሰ አመለካከት ቢሆንም የሰውን ደመነፍሳዊ ባሕሪ የሚጻረር በመሆኑ ምክኒያት መቸም ሊተገበር የማይችለውን የማርቲን ሉተርን ኢተግባራዊ ምናባዊ ተምኔት (impractical imaginary utopia) ከማቀንቀን ይልቅ በማልኮልም ኤክስ መንገድ በሙሉ ልብ ቢሄዱ ኖሮ፣ ዘረኛ ነጭ ሳይወድ በግዱ እንዲያከብራቸው ባስገደዱት ነበር፡፡  ለማናቸውም ድርጊት አጸፋውን የሚመልሱት በማልኮልም ኤክስ መንገድ መሆኑን ዘረኛውን ነጭ በደንብ እንዲገነዘብ ካደረጉት፣ እኩይ ድርጊት ሊፈጽምባቸው ከመነሳሳቱ በፊት እየፈራና እየተባ፣ እያንገራገረና እየተንጰረጰረ፣ እየራደና እየተርበደበደ ሺ ጊዜ ያስብና ያሰላስል፣ ያወጣና ያወርድ ነበር፡፡  እድሜና ጾታ ሳይለይ በሁሉም አቅጣጫ፣ በሁሉም ቦታና፣ በሁሉም ጊዜ በገፍ የሚግታቸውን ግፍ ባስቸኳይ ያቆም ነበር፡፡

ያሜሪቃ ጽሑፋዊ ሕግ (written law) እና ተግባራዊ ሕግ  (applied law) ገማዘንጋዊ ተቃራኒ (diametrically opposite) ወይም ደግሞ ሐራምባና ቆቦ (እንጦጦና የረር) መሆናቸው መዘንጋት አያስፈልግም፡፡  ሕጉ በጽሑፍ መላዕካዊ ቢመስልም በተግባር ግን ሰይጣናዊ ነው (በተለይም ደግሞ ጥቁሮችን በተመለከተ)፡፡  ድሃው ጥቁር ጀሪ ዊሊያምስ (Jerry Dewayne Williams) አንድ ኩርማን (one slice) ፒዛ በቀልድ መልክ ቢነጥቅ እድሜ ልክ የሚፈርድ፣ ሐብታሙ ነጭ ኢታን ኮች (Ethan Couch) ሰክሮ በመንዳት አራት ሰወችን ገድሎ አስራ አንድ ሰወችን ሲያቆስል ግን ሃብትሳክ (affluenza) በሚል የፉገራ ሰበብ በማስጠንቀቂያ የሚያልፍ ሕግ ነው፡፡  

ያሜሪቃ ውጀወች (police) ማናቸውንም ዓይነት ወንጀል በጥቁሮች ላይ ፈጽመው በጽሑፋዊው ሕግ (written) ተከሰው ፍርድቤት ቢቀርቡ፣ በተግባራዊው ሕግ (applied law) ግን በነጭ ማይሞች የሚሞላው ጁሪ (jury) አወድሶና አሞግሶ በነጻ እንደሚያሰናብታቸው አሳምረው ያውቃሉ፡፡  ለወንጀላቸው የሚያገኙት ‹‹ቅጣት››፣ እየተከፈሉ ረፍት እንዲወስዱ መደረግ፣ በከፍተኛ ካሳ ከሥራ መሰናበት፣ በመገናኛ ብዙሃን እየቀረቡና መጻሕፍትን እየጻፉ ታዋቂና ሐብታም መሆን ነው፡፡  

የጊወርጊስ ፍሎይድ (George Floyd) ገዳይ ዴሬክ ቻውቪን (Derek Chauvin) እጁን ኪሱ ውስጥ ከቶ፣ መነጽሩን ግንባሩ ላይ ጥሎ፣ ደረቱን ነፍቶ በኩራት መንፈስና በተረጋጋ ስሜት ፎኪናውን (ፎቶ መኪናውን፣ camera) ፈት ለፊት እያየ ወንጀሉን የፈጸመው፣ ጥቁሮችን በተመለከተ የበለጠ ጭራቅ ሲሆን የበለጠ እንደሚደነቅና የበለጠ እንደሚያተርፍበት ስለሚያውቅ ነው፡፡   የዴሪክ ቻውቪን የእስር ፎቶ (mugshot) አለመለቀቁ ክብሩ እንዳይነካ የመጠንቀቅ ይመስላል፡፡  የዋስትና መብቱ 5መቶ ሺ ዶላር ብቻ መሆኑ ደግሞ ዋስትና እንዲያገኝ የታቀደለት ያስመስላል፡፡ 

ወደኛ ወደጦቢያውያን ስንመለስ ደግሞ ራሳችንን በራሳችን ስለናቅን፣ ነጮች ቢንቁንና ቢጠየፉን ሊገርመን አይገባም፣ ባለቤቱ ያቀለለውን ዐሞሌ ገዥ አይቀበለውምና፡፡  የሚከተሉትን ጥያቄወች ራሳችንን እንጠይቅ፡፡

  • እስከመቸ ነው የነጭን የውበት ብያኔ (definition) ተቀብለን ነጭን የቁንጅና ተምሳሌት በማድረግ፣ በነጭ ፀጉር፣ ከንፈር … ለመዋብ የምንሞክረው፣ ሞናሊዛየ ነሽ እያልን የምንሟዘዘው?  ውበት እንደ ውሃ ነው፣ መልክም ሆነ ቅርጽ የለውም፡፡  ወንጌላዊው ዮሐንስ በመጀመርያ ቃል ነበር፣ ቃልም … እንዳለው ውብ ነኝ የሚል ውብ ይባላል፡፡ 

ታሪክ ስለሆነ በኡደት የሚሖስ

ጊዜውን ጠብቆ የሱ ተራ ሲደርስ

ወደላይ የወጣ ወደታች ሊመለስ

በታች የነበረ በላይ ሁኖ ሊነግሥ

ሕገ ተፈጥሮ ነው መቸም የማይጣስ፡፡

 

ሚዛን ለመጠበቅ እድገት ለማካካስ

ያነሰ ሲተልቅ የተለቀ እንደሚያንስ

ምሳሌወች ናቸው አውሮጳ ጦቢያ ፋርስ፡፡ 

 

አንዱን እያነሳ ሌላውን በመጣል

ታሪከ ያለማቆም ኡደቱን ሲቀጥል፣

ወርተራው ደርሶለት የሚሆነው ከላይ

ውበትን በይኖ በዕይታው መሳይ፣

የሱን ነገር ሁሉ ያደርግና ሰናይ

የታቹን ይለዋል ሁለመናው እኩይ፡፡

በሌላ አነጋገር የውበት ብያኔ

ሳይሆን ቋሚ ትርጉም የዘላለም ቅኔ

እያንጸባረቀ የወቅቱን ስልጣኔ

የሚለዋወጥ ነው በእስስት አስተኔ፡፡ 

 

  • እስከመቸ ነው አብሔር (God)፣ ወልደሔር (Son of God)፣ እመወልድ (Mother of God) እና መላዕክት ነጭ ነን ብለው ራሳቸው ባንደበታቸው የነገሩን ይመስል በነጭ (ባለማችን ላይ ይህ ነው የማይባል የሰው ዘር ጭፍጨፋና የተፈጥሮ ውድመት ባደረሰ ዳቢሎሳዊ ፍጡር) ለሚመሰሉ ስዕሎች ተንበርክከን የምንጸልየው?

ጦቢያ ስለሆነ ቀዳሚ የሰው ዘር

ሰውን በአምሳሉ መፍጠሩን ሲናገር

ጌታ ማለቱ ነው ነኝ እንደሱ ጥቁር፡፡

ስለዚህም ሰይጣን የጌታ ባላንጣ

በተቃራኒ መልክ ይሆናል የነጣ፡፡

ለፈረንጅ ስዕል የሚሰግድ አበሻ

ተዋርዶ አዋራጅ የረከሰ ውሻ፡፡

 

መስፍን አረጋ 

mesfin.arega@gmail.com

                   

Filed in: Amharic