>

መቼም ሆነ የትም ስለ ቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዝም አልልም!!! (በቀለ ገብረየሱስ)

መቼም ሆነ የትም ስለ ቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዝም አልልም!!!

በቀለ ገብረየሱስ

ዝም የማልለው በምክኒያት ነው! ዝም የማልለው እንደ ቁራ መጮህ ስለምወድ ሳይሆን እኔም ከሰለባዎቹ አንዱ በመሆኔና እስካሁን ያልፈነዳ በውስጤ እየተንተከተከ የሚያቃጥለኝ እሳተገሞራ ስላለ ነው! ዝም የማልለው ቆስቋሽና ቆንጣጭ እውነት በውስጤ ስላለ ነው።
እኔ ሁሌም ዝም እንዳልል የሚከለክለኝና የህሊና እረፍት የሚነሳኝ የበደላቸውን፣ የንቀታቸውንና የትእቢታቸውን ጣሪያ የሚያሳየው መለስ እና ስዬ ስለ ሠራዊታችን የተናገሩት ፀያፍ ቃል ነው። በቦምብና በጥይት የቆሰልነው ድኗል ያልዳነውና እያመረቀዘ የሚጠዘጥዘን በነሱ ጋጠወጥ ቃላት የቆሰለው አይምሯችን ነው።
          መንግስቱ ኃ/ማሪያምን የጎዱ መስሏቸው በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት ተሰብስበው የሚያድጉበትን ህፃናት አምባ ዘግቶ ህፃናቱን እንደበተነው፣ ከሶመሌ፣ ከሻአቢያ ከወያኔና ከሁሉም ፀረ ኢትዮጵያ ሀይሎች ጋር ሲፋለም እጁን እግሩን፣አይኑን አጥቶ በደብረ ዘይት ጀግኖች አንባ የተጠለሉትን የአካል ጉዳተኞች ለመበተን ሲመጡ ፣ ይሄኮ የግለሰብ ሳይሆን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሁኖ በጀግንነት ሲዋጋ አካሉን ያጣ ኢትዮጵያዊ ነው ለምን ይሄን ያክል በጥላቻ ተሞልታችሁ እንደዚህ ያለ ታሪክ ይቅር የማይለው ውሳኔ ትወስናላችሁ ሲባሉ፣ እየቀለዱ ” እናንተ ጀግና ከተባላችሁ እናንተን እንዲህ ያደረገው ምን ሊባል ነው” ነው ያሉት። ይሄ የምፀት ድምፅ መቼም ከህሊናዬ አይጠፋም። ሲጀመር እነሱ ፈሪዎች እንጂ ጀግኖች አይደሉም ፣ጀግና አዛኝና ሩህሩህ ነው እንጂ ጨካኝ አይደለም።
በመጨረሻ በለስ ቀንቷቸው አሸናፊ ቢሆኑም ሻአቢያም ሆነ ወያኔ ፈሪዎች ናቸው፣ ፣ ይሄን የምለው ደግሞ ሁለቱንም በተለያየ ጊዜና ቦታ በመድፍ ርቀት ተቀምጬ ሳይሆን በቦንብ ርቀትና በጨበጣ ውጊያ ፊት ለፊት ተገናኝተን ተያየተን ስለምናውቅ ነው።
ደርግን ለመጣል ተራሮችን ያጠቀጠው ትውልድና ጦርነትን መዋጋት ብቻ ሳይሆን መስራት እንችላለን የሚሉት አመራሮቻቸው ባድሜና ፆረና ላይ ሻቢያ ሲገርፋቸው ለምን ቂጣቸውን ገልበው ሸሹ? ለምንስ ትናንት ንቀው የበተኑትን ሰራዊት አድነን ብለው ተማፀኑ፣ ያ የበተኑት ሰራዊት አይደለም እንዴ ከጉድ ያወጣቸው? እንዴትስ ተራራን ያንቀጠቀጠና ጦርነት መስራት የሚችል ትውልድና አመራር ሶስት ወር ባልሞላ ህዝባዊ አመፅ ድንጋይና ጩኸት ፈርቶ ከቤተመንግስት ሸሽቶ በመቀሌ ምሽጉ ይገባል? ስለዚህ ፈሪዎች ናቸው የምለውም በምክኒያት ነው።
@ ለመሆኑ ያ የቀድሞ ሠራዊት ሀጢያቱ ምንድነው? ኢትዮጵያ ሀገሬ ካንቺ በፊት እኔ ልቅደም ብሎ ላብና ደሙን ስላፈሰሰ? አጥንቱን ሰለከሰከሰ? ውድ ህይወቱን በፈቃደኝነት ስለሰጠ? የሀገሪቱን ሉአላዊ የየብስ የአየርና የባህር ክልል ስላስከበረ?ቤቱን ሚስትና ልጆቹን፣ ወዳጅ ዘመዶቹን ለአመታት ተለይቶ በየጠረፉ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ድንጋይ ተንተርሶ ስለተኛ? ወይስ ከተበተነ በሁዋላ እንኳን አንዳዶች በዛገ ቢላዋ እያስፈራሩ ግለሰብና ድርጅት ሲዘርፉ ዝናር ሙሉ ክክ የመሰለ ጥይት ከ ፒኬኤም መትረየስ ጋር እንደታጠቀ ቁራሽ እንጀራ መለመኑ?በወቅቱ ምንም ማድረግ እየቻለ ላለማድረግ ቁራሽ እንጀራ መለመኑ የታነፀበትን ጠንካራ ወታደራዊ ዲሲፕሊ የሚያሳይ እንጂ በድክመት ሊታይ አይገባውም ነበር።
ተዋግተው ሀገር ያስገነጠሉትና ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍሎ የሚያፈራርስ ፓሊሲ ቀርፀው የመጡ ወንጀለኞች ደልቷቸው እየተንደላቀቁ ለሀገሩ ዋጋ የከፈለው ባለውለታ ግን በሀገሩ ጉዳይ እንደባይታወር ተቆጥሮ በማንኛውም የፓለቲካን ማህበራዊ ጉዳይ እንዳይሳተፍ ተወስኖበት በሀገር ውስጥና በስደት ተበትኖ መከራውን እንዲያይ ሲደረግ ” ፍትህ ሀገርሽ የትነው?” አያስብልም?
ግፈኛው ወያኔ ከተባረረ በሁዋላ መንበረ ስልጣኑን የተቆናጠጠው ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚሰብከው የዶክተር አቢይ መንግስት ከመጣም በሁዋላ ለዚያ ሰራዊት እውቅና አለመስጠቱና ይቅርታ አለመጠየቁ ሲታይ እኛው በኛው በህጋዊ መንገድ ተደራጅተን በሰላማዊ መንገድ ካልተሟገትን ማንም ስለኛ መብት ሊከራከርልን ወይም በችሮታ ሊሰጠን አይችልም፣ መብታችንን ለማስከበር መደራጀት ለነገ የሚባል ነገር አልደለም።
ፈጣሪ ረጅም እድሜና ጤና በህይወት ላሉ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ይስጥልን፣
እግዚአብሄር ሀገራችንንና ህዝቧን ይባርክ።
Filed in: Amharic