>

አመፅ!! (በእውቀቱ ስዩም)

አመፅ!!

(በእውቀቱ ስዩም)
 


በለው! በለው! ዛሬ ታሪክ ተሰራ! ከተማውን ባንድ እግሩ አቆምነው!!
 
“ሽጉጥ መትረይሱን አንግቶታል
ያ ጥቁር ግስላ ደም ሽቶታል” 
 
የሚለውን  የአለማየሁ እሼቴን ዘፈን በአለማየሁ ፋንታ ድምፅ እያንጎራጎርሁ  ከቤቴ ወጣሁ   ፤ ፓርኩ ላይ ስደርስ አንዲት ደርባባ ኤሽያዊት ሰልፈኛ  ተዋወቅሁ፤   
 ከኢትዮጵያ እንደሆንኩ ስነግራት  አይኗ በደስታና ባድናቆት ብዛት   ተጨፈነ ፤ባጠቃላይ ፊቷ  ግንባር ሆነ ፤ 
 
“ እኔ ከደቡብ ኮርያ ነኝ  “ 
 
“ አያቴ   ስለ አገርሽ  ብዙ ይነግረኝ ነበር ፤  በነገርሽ ላይ አያቴ  እናንተ አገር ዘምተው ከነበሩት  ዘማቾች አንዱ ነው ”  ብየ ቀደድኩ፤
 
“የምርህን ነው?”
 
“ አያቴ ይሙት”
 
‘ ኦ ማይ ጋድ ! “ ልትጠመጠምብኝ  እጆቿን ዘርግታ ስትንደረደር ገለል አልኩ፤  ከፊት ለፊቷ ከቆመው ዘንባባ ላይ ተጠመጠመች፤
 
“  ዛሬ በተቃውሞ ላይ ለመሳተፍ መወሰንህ  ያያትህን ጀግንነት  መውረስህን ያሳያል”  አለችኝ::
 
“ነው ብለሽ ነው?” አልኩና እየተሽኮረመምሁ   ወደ ለበሰቺው ቁምጣ ተመለከትኩ:: 
 
  እሷ በቁምጣ  እኔ በቁጣ ተሞልተን መራመድ ጀመርን!! የኦሃዮን ወንዝ የሚያሻግረውን ብጫ ድልድይ አልፈን ዳውንታውን የሚያስገባ አውራ ጎዳና ላይ ስንደርስ የተቆጣው ሰልፈኛ ቁጥር  እየጨመረ ሄደ ፤ ጥቁር፤  ነጭ፤ ላቲኖ ኤሽያ የቀረ የለም፤ ዳውንታውን ስንደርስ የቤት መዝጊያ የሚያካክል የመስታወት ጋሻ የያዙ ፖሊሶች ተሰልፈው ጠበቁን  ፤ ካጠገባቸው ፤ አድማ በታኝ መኪና ፤ ብረት  ለበስ መኪና ፤ ታንክ እና  ያየር መቃወሚያ  ሳይቀር ያየሁ መስሎኛል፤ ሰልፉ በሰላም እየተካሄደ እያለ አንድ የተረገመ ጎረምሳ ጋዝ የተሞላ  የሄኒከን  የቢራ ጠርሙስ  ወደ ፕሊሶች ወረወረ!  (ሄኒከን ቢራ የሚቀጥለውን ፅሁፌን ስፖንሰር  እንደሚያደርግ  ተስፋ አደርጋለሁ )፤
 
 ወድያው  ከፊት ያለው  ፖሊስ  ሰልፈኛውን የፕላስቲክ ጥይት ተኩሶ ጠነበሰው  ’፤ አየሩ በስጋትና በቁጣ ተሞላ፤፤  ji young ( የኮሪያይቱ ስም ነው)  መፈክሯን  አንከርፍፋ  አይን አይኔን ታየኛለች፤ 
 
“  ጥግሽን ይዘሽ ጠብቂኝ “ አልኩና  ጃኬቴን አውልቄ አቀበልኳት  
 
“በጨበጣ ልትገጥማቸው ባልሆነ” አለችኝ ባድናቆት ጮሃ ::
 
“ በጨበጣ  ካልሆነማ በርቀት በፕላስቲክ ጥይት ለቅመው ይጨርሱናል”  ስል መለስኩላት፤ 
 
“   ስማኝ ሃኒ “ አለችኝ “  በጣም ከተጠጋኻቸው  pepper spray  ይረጩሀል አለቺኝ”
 
“ አታስቢ !  በርበሬ ስታጠን ስላደግሁ ችግር የለም፤ “
 
 ወደ ፖሊሶች መራመድ ጀመርኩ፤ ተቃዋሚው ሰልፈኛ ፀጥ  አለ!  ፖሊሶች አይናቸውን ማመን አልቻሉም፤ ቶሎ ብለው አንድ ቁና  ጭስ ለቀቁብኝ፤  በልጅነቴ፤ የጎረቤታችን ጠላ ሻጭ  ሴትዮ የጠላ ቂጣ ሲጋግሩ ያለ ፍላጎታችን ጭስ ሲያካፍሉን ስለኖሩ አይኔ ለምዶታል ፤  እንዲያውም  ቤት ውስጥ መለስተኛ ጭስ ከሌለ አይኔ በቅጡ አያይልኝም፤ 
 
ፖሊሶች ሁለተኛ ዙር ጭስ  ለቀቁብኝ ፤ ይሄኛው ጭስ  አፕል ፍሌቨር እንዳለው ልብ አልኩ!
 
 ከፊት ለፊት ከቆመው ፖሊስ ልደርስ ሁለት ጫማ ሲቀረኝ ስልኬን አውጥቼ ፎቶ አነሳሁት፤
 
ከጥቂት ደቂቃ በሁዋላ ወደ ነበርኩበት ተመልሼ  ስቆም::
 
“  ለመሆኑ አያትህ  ኮርያ የዘመቱት በምን ዘርፍ ነበር ?” አለቺን ጂ ያንግ ! 
 
“ በጋዜጠኝነት”
Filed in: Amharic