>

እባካችሁ -  ወርዳችሁ አታውርዱን፤ ተዋርዳችሁ አታዋርዱን!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

እባካችሁ –  ወርዳችሁ አታውርዱን፤ ተዋርዳችሁ አታዋርዱን!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

“በአንድ ቀን ተከብቢያለው በማለት 86 ዜጎች ሲገደሉ አምነስቲ የት ነበር? ስለነሱስ እንዴት አይዘግብም? ዜጎች አይደሉም? ኢትዮጲያውያን አይደሉም? ” 
ጌታቸው ባልቻ  – የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ 
ጌታው እርሶስ የት ነበሩ? እርሶ እና ጓደኞችዎት አገሪቱን የምታስተዳድሩት ሰዎች የማንን ጎፈሬ እያበጠራችሁ ነበር? በዚህ ጉዳይ ላይ አምነስቲ አልዘገበም እንጂ ቢዘግብ ምን ብሎ ሪፖርት ያቀርብ እንደነበር ያውቃሉ? የኢትዮጵያ መንግስት አንድ ጃዋር የሚባል የኦሮሞ ፖለቲከኛ ግብረ አበሮቹን አነሳስቶ 86 ንጹሃን ዜጎችን በጠራራ ጸሃይ ሲያስገድል መንግስት ጥቃቱን አላስቆመም፤ ያም አልበቃ ብሎት ጥቃት ፈጻሚዎቹን በሕግ ተጠያቂ አላደረገም፣ ያም አልበቃ ብሎት ጠቅላዩ የሚመሩት ቡድን ከከተማ ከተማ እየዞረ አይዟችሁ እናንተንስ ማን ነክቷችው፣ ጃዋርንስ ማን አባቱ ደፍሮት እያሉ አጥቂውን ኃይል ያጽናኑ ነበር። ያም አልበቃ ብሏቸው ጠቅላዩ ከአስርቀን በላይ ተኝተው ነው በጉዳዩ ላይ የተወጫበረ መግለጫ የሰጡት ይል ነበር። ይህ የመንግስት አድራጎት ከፍተኛ የመብት ጥሰት ነው። ለሞቱትም ሰዎች ይሁን ለደረሰው የመብት ጥሰት መንግስት ጥቃቱን ባለማስቆም እና የዜጎችንመብት እንዳይጣስ የመከላከል ሕገ መንግስታዊ እና አለማቀፋዊ ግዴታውን አልተወጣም።  86ቱን ዜጎች የገደሉ እና ግድያውን ከዳር ቆመው የተመለከቱ የመንግስት አካላት ለፍርድ ይቅረቡ ብሎ ነው መግለጫ ቢያወጣ እንኳ ሊናገር የሚችለው።
እባካችው የመንግስት ኃላፊዎች ተዋርዳችሁ አገሪቷንም ለአዋራጅ አሳልፋችሁ አትስጧት። አታዋርዷት። ተዋርዳችሁ ሕዝቡንም አታዋርዱት። ይች አገር በእነማን እጅ ነው ያለችው አታስብሉ። በተጠያቂነት ደረጃ ለ86 ሰዎች ሕይወት መጥፋት በጃዋር፣ ድርጊቱን በቀጥታ በፈጸሙት ሰዎች እና ድርጊቱን እንደ ድራማ ዳር ቁጭ በለው በተመለከቱት በእርሶ እና በመሰል ባለስልጣናት መካከል ልዩነት የለም። ጠያቂ ሲኖር ሁላችሁም እንደየ ድርሻችሁ ትጠየቁበታላችሁ። እንዲህ ብሎ በአደባባይ፤ ሊያውም ለሚዲያ መግለጫ መስጠት ግን ነውር ነው።
Filed in: Amharic