>

ጥቋቁሮቹ ግሥሎች!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ጥቋቁሮቹ ግሥሎች!!!

አሰፋ ሀይሉ

* «ሽጉጥ መትረየሱን አንግቶታል፤
ያ ጥቁር ግሥላ ደም-ሽቶታል!!
* … ‹‹ግሥላ›› ባገራችን ጀግኖች ደመ-ቁጡነቱን እየተነሣ — እንደ አራስ ነብር — የሚያሞገስ፣ የሚሸለልበት፣ የሚፎከርበት፣ የሚቅቅራራበት ሣተናና አይበገሬ (እና አስፈሪ) ቁጡ አውሬ ነው! በተለምዶም ‹‹እንደ ግሥላ እላዩ ላይ ተከመረበት!!›› ይባላል!
በቅርቡ ራሱ በአድዋ ድል መታሰቢያ ላይ አለማየሁ እሸቴ ከወጣቶች መሃል ገብቶ በስሜት እየተወዛወዘ ‹‹ያ ጥቁር ግስላ.. ደም ሸቶታል..፤ ሽጉጥ መትረየሱን አንግቶታል….!!!›› እያለ ሲያስነካው አሁንም ከ60ዎቹ የእኩልነት ትግል የተወለደ የአፍሪካዊነት አይበገሬ መንፈሱ እንደጋመ መሆኑ ግርም ይላል፡፡ እኔም እንግዲህ… እኒህን የአሜሪካ የ60ዎቹና የ70ዎቹ የሰብዓዊ መብት አርበኞች… «ብላክ ፓንተርስ»ን – ‹‹ጥቋቁር ግስሎች›› ብዬ ጠራሁና ልዘክራቸው ጀመርኩ፡፡
እነዚህ አይበገሬ ጥቋቁር ግሥሎች… ነፃነት እንደመንግሥተ ሠማያት በራቀባት… እንደክፉ እንጀራ እናት ፍዳቸውን በምታበላቸው… በዚያች የ60ዎቿ ነጣ ያለች የአሜሪካ ምድር… ታላቅ የ‹‹እኩልነት›› ራዕያቸውን ሠንቀው በታላቅ ሰብዓዊ ወኔ ብቅ ያሉ – የነፃነት አርበኞች ናቸው — «ብላክ ፓንተርስ» — ጥቋቁር ግሥሎች!!! የያኔዋ የአሜሪካ የነፃነት ሃውልት – ጥቋቁር ቀለም ያላቸውን ሰዎች በሙሉ ዓይኖቿ የማታይ… በከፍታ ላይ የተሰቀለች.. የማትበላ እንጀራ.. የማይደረስባት ተስፋ ነበረችና.. ጥቁሮች በቀለማቸው ልዩነት የተነሣ — በተለይ በፀጥታ ኃይሎች — የሚደርስባቸው ሥቃይ፣ እንግልትና፣ ሞት ከፍተኛ ቁጣና ንዴትን ቀሰቀሰባቸው!!!!
በዚያው በ60ዎቹ ውስጥ — በአንዱ ሆድ የባሰው ቀን ላይ — በአሜሪካ ሣንፍራንሲስኮ ከተማ — ማቲው ጆንሰን የተባለ የ21 ዓመት ጥቁር አሜሪካዊ ወጣት… በፖሊሶች እጅ በሠላም ከወጣበት ቤቱ — ለከፍተኛ ሥቃይና ድብደባ ከተዳረገ በኋላ፣ በፖሊሶች በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ አለፈች!!! የዚያን ዕለት ሣንፍራንሲስኮ ባንድ እግር ቆመች ብቻ ሳይሆን ‹‹ኮሶ ጠጣች!›› ማለት ይቀላል!!! እገሌ ከእገሌ ሳይባል — ያን የግፍ ዜና ያዩ ጥቁር አሜሪካውያን ሁሉ — በነቂስ ግልብጥ ብለው የሣንፍራንሲስኮ ጎዳናዎችን… አውሎነፋስ እንዳመጣው ጎርፍ… በአፍታ አጥቀለቀለቁት!!! በዚያች ዕለት የነደደችው ቁጣ ያረፈችበት ነገር ሁሉ — አንድም ሣይቀር ሥብርብሩ ወጣ!! ያን ኃይል — እንደ አውሎንፋስ ጎርፍ — መሸሽ እንጂ ለማስቆም መሞከር የማይታሰብ ነበርና!!!
ያቺው የማቲውን አሣዝኝ ሞትና… የሣንፍራንሲስኮ ነዋሪዎችን ነዲድ ቁጣ ያስተናገደች ዕለት — የ«ብላክ ፓንተርስ»ን — ‹‹ጥቋቁር ግሥሎች››ንም ወለደች!!! በዚያች ዕለት በቁጣ ከሚጎርፈው ሕዝብ መሃል ሆነው.. አንድ የተለየ ነገር የተመለከቱ የሚሪየም ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ሁለት ጥቁር አሜሪካውያን ወጣቶች ነበሩ፡- ሁዌይ ኒውተን እና ቦቢ ሲል!!! ሁዌይ እና ሲል ያ ለጥቁሮች ፊቷን ባዞረችው… በዛኔዋ የአሜሪካ ምድር… ድንገት ብልጭ ያለው ያ የጥቁር ሕዝቦች እሣተ ገሞራዊ ኃይል — ለሁዌይ እና ቦቢ ሲል ድንገት እንደመብረቅ ብርሃን በመሠለች ድንገተኛ ብልጭታ.. አንድ ታላቅ ራዕይ ፈነጠቀላቸው፡-
ይህ ሁሉ ጥቁር ሕዝብ የእኩልነት መብቱ እስከሚከበርባት… እስከዚያች ከድሬድ ስኮት… ከፕሌሲ… ከእነ ማርከስ ጋርቬይ ትንቢት ዘመን ጀምራ… ስትናፈቅ የቆየችው ያቺ የእኩልነትና የነፃነት ቀን እስከትመጣ ድረስ… ጥቁሮች ያላቸው ተስፋ አንድና አንድ መሆኑን፡፡ ያም የራሳቸውን ሰብዓዊ መብት — በአንድነታቸው፣ በኃይላቸው፣ በብርታታቸው፣ ተሰባስበው፣ ተነሥተው፣ የራሳቸውን ነፃነት በራሳቸው በጥቁሮች ማስጠበቅ!!!!
እናም ለዚያ መልስ ይሆን ዘንድ «ብላክ ፓንተርስ» — ጥቋቁር ግሥሎች የተሰኘው ማህበር በምድረ አሜሪካ የጥቁሮች መብት አስጠባቂ ተቋም ሆኖ በእውን ተከሰተ!!!
የብላክ ፓንተርስ የመጀመሪያው ስልት (ኢኒሻል ስትራቴጂ) በመንገድ ላይ በነጻነት ወዳሻቸው የመንቀሳቀስ መብታቸውን ተጠቅመው ጥቁሮችን ይደበድባሉ ብለው የሚጠረጥሯቸውን የፖሊስ መኪኖች ከኋላ ከኋላ እየተከተሉ መሄድ ነበር — ፊሽካ በእጃቸው ይዘው፡፡ ልክ ፖሊሶቹ የሆነ ቤት ሲገቡ ይነፋሉ — ከዚያ የሚነፋውን ገምቱት እንግዲህ፡፡ ቀጠሉና ብላክ ፓንተርስ ሕጋዊ ፍቃድ ያለው የተመዘገበ መሣሪያ የያዙ አባሎቻቸውን ቢሮዋቸውን እንዲጠብቁ በበራቸው ላይ ማቆም ጀመሩ፡፡ ለምን ታጠቅክ? መብቴ ነው፤ ፍቃድ አለው መሣሪያዬ! ብቻ ነበር መልሳቸው፡፡
እና ሲቆይ… እነዚያ አለማየሁ እሸቴ… ሽጉጥ መትረየሱን አንግቦታል የሚልላቸው… የታጠቁ ጥቁሮች በአሜሪካ ከተሞች ሁሉ የጥቁሮችን መብት ለማስጠበቅ… ይንቀሳቀሱ ጀመር፡፡ ይሄ እንግዲህ በወቅቱ ህግ ክልክልነት አልነበረውም፡፡ አስፈሪነቱ ግን ግልጽ ነበር፡፡ ለምን? የታጠቁ ብዙሃን የከተማ አብዮት ሊቀሰቅሱና የነጮቹን መንግስት ሊገዳደሩት ነዋ!!! የያኔው የኤፍ ቢ አይ ዳይሬክተር – የሁዋላ መሪ – እድጋር ኸርበርት ሁቨር – ጥቁር ግስሎቹን ‹‹የመንግሥታችን ቁጥር አንድ አደገኛ ጠላቶች›› ብሎ መጥራቱ ብቻ ይበቃናል መሠል፡፡
እነዚህ ጥቁር ግስሎች — ነፃነታችንን ለማስከበር እስከሆነ ድረስ ማንኛውንም መንገድ እንጠቀማለን — የሚል ፅንፍ የያዘ ግን ቆራጥም የሆነ አቋም ያራምድ በነበረውና (ስለሆነም በተተኮሰበት ጥይት በሰው እጅ በተገደለው) – በማልኮም ኤክስ ክፉኛ የሚመሰጡ ነበሩ፡፡ እና የማልኮልም ኤክስ ሙት ዓመት ሲከበር አንድ ታላቅ የጥቁሮች ኮንፈረንስ ተዘጋጀ፡፡ የማልኮልም ኤክስ ሚስት የነበረችው ቤቲ ሻቫዝ ደግሞ በዚያ ኮንፈረንስ ላይ ተገኝታ ንግግር ለማሰማት… ከሣንፍራንሲስኮ አየር መንገድ ተነሥታ ትጓዛለች፡፡ እና ብላክ ፓንተርስ ምን ቢያደርጉ ጥሩ ነው— የማልኮልም ኤክስ ኮንፈረንስ ተሣታፊ የሰማዕት ሚስት ሽኝት!!! እና በርካታ ቁጥር ያላቸው የብላክ ፓንተርስ የታጠቁ ጥቁሮች በሠልፍ.. የፓንተርስን አርማ ለብሰው… ቤቲ ሻባዝን አጅበው – የሰልፍ ጉዞ ወደ ሣንፍራንሲስኮ አየር ማረፊያ!!! ጉድ ተባለ!!
የአሜሪካ መንግስትም ‹‹ይህች ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም›› ሳይል አልቀረም መሠለኝ፡፡ የምን መሠለኝ?!! አለ እንጂ – ያለምንም ማንገራገር — የዚያኑ ሰሞን አዲስ አዋጅ ተደነገገ!! በከተማ ውስጥ የጦር መሣሪያ አንግቦ መገኘት በወንጀል ዘብጥያ ያስገባል የሚል!! እናም ከ1966 እስከ 1982 የቆየው… ታላቁ፣ ረዥሙና አሣዛኙም… የብላክ ፓንተርስ ጥቁር ግስሎች እና በእነ ኩክሉክስ ክላን (ኬኬኬ) ተፅዕኖ ወደቀ እየተባለ ሲታማ የነበረው… የአሜሪካ የምርመራ ቢሮ የኤፍ ቢ አይ… ሁለት አስርቴ ዓመታትን ያስቆጠረ ታላቁ ትንቅንቅ በዚህ መልኩ ተጀመረ!!!
በነገራችን ላይ ጥቁር ግስሎች ጭቆናን በነውጥ ለመጋፈጥ ብቻ አልነበረም ትጋታቸው፡- ድህነት የወደቀባቸው ህፃናትን እየሰበሰቡ ያበላሉ፣ ይንከባከባሉ፣ ትምህርት ያስተምራሉ፡፡ ችግረኞች የሚረዱበትን ትልቅ 68 ከተሞችን ያዳረሰ ብሔራዊ ዕድር መስርተው አባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን ይረዳሉ፡፡ በጥቁር መንደሮች ሁሉ በዝቅተኛ ዋጋ እና በነፃ በመቶ ሺህዎች የሚደርሱ ጥቁሮች የሚታከሙባቸውን የጤና ጣቢያዎች በየግዛቱ ያቋቁማሉ፡፡ መጻሕፍትን ይሸጡና ገቢውን ለትግል አላማ ያውላሉ፡፡ በጥቁሮች ላይ የሚፈጸሙ የድብደባ፣ ግድያ፣ እስራትና ሌሎች መብት ጥሰቶች ነቅተው ይከታተላሉ፣ ያጋልጣሉ፡፡ ጥቁሮች እንደ ነጮች መብታቸው ተከብሮ በእኩልነት የሚኖሩባትን አሜሪካ በትግላቸው ለማምጣት… የማርቲን ሉተርን ሕልም አሁኑኑ ለመተርጎም ብለው… ሌት ተቀን ይሰራሉ፡፡ ጥቁር ግስሎች – ‹‹ብላክ ፓንተርስ›› እንግዲህ እኚህ ነበሩ፡፡
መቼም እነ ኦባማ ባንድ ጀምበር ለፕሬዚደንትነት አልበቁምና እኒህን ማየቱ ጥቂትም ቢሆን አንዳች አብነት አይጠፋውም..፡፡ ለሌላ ጊዜ ተከታዮቹን አንዳንድ ክስተቶች የምንመለስበት ሆኖ… ለዛሬው ግን እነዚያ የአሜሪካ ጥቁር ግስሎች “ዋት ዊ ዎንት ናው?” ‹‹አሁን የምንፈልገው ምንድነው?›› በምትለው ቀይዋ ሕትመታቸው ያወጧቸውን ‹‹አስርቱ ፍላጎቶች›› (አስርቱ ትዕዛዛት የሚሏቸውም አሉ!) ብንመለከት አይከፋም፡፡ የጥቁር ግስሎቹ አስርቱ ትዕዛዛት እነዚህ ነበሩ፡-
አንደኛ፡- እኛ ነፃነት እንፈልጋለን፡፡ የጥቁሮችን ዕጣ-ፈንታ ራሳችን ለመወሰን ደግሞ ሕጋዊ የሆነ ሥልጣን እንፈልጋለን፡፡
ሁለተኛ፡- እኛ ሕዝባችን በሙሉ በወዙ የሚያድርበት ሥራ እንዲኖረው እንፈልጋለን፡፡
ሦስተኛ፡- እኛ በጥቁር ማህበረሰባችን ላይ በካፒታሊዝም የሚደርስብን ዝርፊያ እንዲያበቃ እንፈልጋለን፡፡
አራተኛ፡- እኛ ማንኛውም ክብር ላለው ሰብዓዊ ፍጡር ሊኖረው የሚገባውን ዓይነት መኖሪያ ቤት እንፈልጋለን፡፡
አምስተኛ፡- እኛ የዚህን የዘመኑን የአሜሪካ ማህበረሰብ እውነተኛ አኗኗር የሚያጋልጥ፣ እውነተኛ ታሪካችንን የሚናገር፣ እና ባሁኑ  ዘመናችን ልንፈጽመው ስለሚገባን ሚና የሚነግረን ትክክለኛና እውነተኛ ትምህርት እንዲተገበር እንፈልጋለን፡፡
ስድስተኛ፡- እኛ ሁሉም ጥቁሮች ከውትድርና ግልጋሎት ነፃ እንዲደረጉ እንፈልጋን፡፡
ሰባተኛ፡- እኛ በጥቁር ሕዝቦቻችን ላይ ፖሊስ እየፈጸመ ያለው ጭካኔ የተሞላበት ማሰቃየትና ግድያ በአስቸኳይ እንዲቆምልን  እንፈልጋለን፡፡
ስምንተኛ፡- እኛ በፌዴራል፣ በወረዳ፣ በከተማ እስርቤቶችና ጣቢያዎች ታጉረው የሚገኙ ጥቁሮች ሁሉ ነፃነት እንዲያገኙ እንፈልጋለን፡፡
ዘጠነኛ፡- እኛ በሕገ መንግሥቱ እንደሠፈረው ጥቁሮች ተከሰው በሚቀርቡበት ሸንጎዎች ሁሉ ከራሳቸው ከጥቁሮች ማህበረሰብ በመጡ  በራሳችን ዳኞችና በራሳችን ታዛቢዎች እንዲዳኙልን እንፈልጋለን፡፡
አስረኛ፡- እኛ መሬት እንፈልጋለን፤ ዳቦ (እንጀራ!) እንፈልጋለን፡፡ መጠለያ ቤት እንፈልጋለን፡፡ ትምህርት እንፈልጋለን፡፡ ልብስ  እንፈልጋለን፡፡ ፍትህ እንፈልጋለን፡፡ እና ሠላምም እንፈልጋለን፡፡
እንግዲህ የጥቁር ግሥሎቹ — የብላክ ፓንተርስ — አስርቱ ፍላጎቶች – አስርቱ ጥያቄዎች – ወይም አስርቱ ትዕዛዛት እነዚህ ነበሩ፡፡ እነዚህን ትዕዛዛት ግን… ያኔ በዚያን ወቅት እነዚህን ሁሉ በተነፈጉት ጥቁሮች ቦታ ሆናችሁ እንጂ… አሁን ላይ ሆናችሁ ግን አታስቡት፡- የያኔውን ብሶት፣ የተመለሱና ያልተመለሱ ጥያቄዎቻቸውንና ያሳለፉትን ጎዳና… እና አሁንን ለማየት እንችል ዘንድ!!!!
ለዛሬው አበቃሁ፡፡ በአለማየሁ እሸቴ የብላክ ፓንተርስ ዘፈን፡-
«ሽጉጥ መትረየሱን አንግቶታል፤
ያ ጥቁር ግሥላ ደም-ሽቶታል!!
«… ጥቁር እንደአራዊት የሚቆጠርበት፤
ምንድነው ምክንያቱ ብሎ በማለቱ በግፍ ተሰቀለ፤
ያ አፍሪካዊ ጀግና እንዴት ሆኖ ዋለ!!
«ሽጉጥ መትረየሱን አንግቶታል፤
ያ ጥቁር ግሥላ ደም-ሽቶታል!!»
/የአለማየሁ እሸቴን፤ «ያ ጥቁር ግሥላ ደም ሸቶታል» ቪዲዮ ለማየት፡-
Filed in: Amharic