>

ተመስገን ደሳለኝ እና አሥርቱ የሙያ ትዕዛዛቱ!!! [ክፍል አንድ] (ለሰገጤ አይመከረም)  

ተመስገን ደሳለኝ እና አሥርቱ የሙያ ትዕዛዛቱ!!!

 (ለሰገጤ አይመከረም)

  ክፍል አንድ

ከሰሞኑ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የዞረው ሾተላይ፣ ትንቅንቅ በዝቶበት በኖረው የኢትዮጵያ ነጻው ፕሬስ ታሪክ ውስጥ ግዝፈት የሚነሳ ሚና ያለውን ሙያተኛ፣ ዋጋውን ማቅለል ባይቻለውም ጥቂት የዋህ ወንድሞችን በአሉባልታ ሊያጨናብር ሲሞክር አስተውለናል፡፡ እናም በአምደኝነት እና በዋና አዘጋጅነት አብሮ እንደሰራ ወንድም፤ ስለ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን የማውቀውን እመሰክራለሁ፡፡
ዛሬ ላይ በደረስኩባቸው አቋሞቼ የማልስማማባቸው ነጥቦች ቢኖሩም፣ ከተመስገን ቅድመ እስርም ሆነ በድኀረ እስራቱ አብሮ እንደሰራ ሰው፣ አሥርቱ የሙያ ትዕዛዛቱን እንዲህ ገልጫቸዋለሁ፡-
1)  ሚዲያን የትግል መሳሪያ ማድረግ፤
ትሕነግ/ኢህአዴግ፣ ያኔ የድኀረ-ኮምኒዝም አስገዳጅ ሁነቶች ተጭኖት በ1984ዓ.ም ባጸደቀው የነጻ ፕሬስ አዋጅ ማግስት ቁጥራቸው የበዛ የነጻው ፕሬስ ውጤቶች ገበያውን መቀላቀል ቢችሉም የፕሬሱ ጉዞ በሞት ሸለቆ ውስጥ የመጓዝ ያህል ፈታኝ ነበር፡፡ ሚዲያውን የትግል ሜዳ ለማድረግ የሞከሩ ሁሉ እስራት አልያም ስደት ዕጣ ክፍላቸው ነበር፡፡ ቀዳሚውን ዕጣ ያነሳው ተመስገን፣ በቅድመም ሆነ ድኀረ እስራት ጊዜው ሚዲያውን የትግል መሳሪያ አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡ መንፈሳዊ መልዕክት ካለው ነገር የሚነሳ ቢሆንም ‹‹የፈራ ይመለስ››፤ ዛሬም ድረስ የትግል መርሁ አስኳል ሆኖ ዘልቋል፡፡ ግፈኞችን የማሸነፊያ ብቸኛው መንገድ የፍርሃት ሰንሰለትን በጣጥሶ መጣል ስለመሆኑ በነቢብም በገቢርም አስመስክሯል፡፡ እንደዛሬው ታጋይ በጎጥ ውክልና ይዋጣልን ሳይበል፣ ያኔ በበላዔሰቦቹ ዘመን የግፉዓን ልሳን ሆኖ በመገኘቱ ከፕ/ር መስፍን እስከ ከፕ/ር ዓለማየሁ ገብረማርያም፣ ከቡልቻ ደመቅሳ እስከ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም፣ ከኦባንግ ሜቶ እስከ አሰገደ ገ/ሥላሴ፣ …ድረስ ያሉ ህሩያን፤ ሚዲያን ለአደባባይ ምክንያተኝነትና ሞጋች ወጣቶች መፍጠሪያነት በትጋት ስለመጠቀሙ መስክረውለታል፡፡
2)  ለደም አልባ አብዩት መታመን፤
ሌኒን ‹‹የአብዩት መከሰቻ ወቅትና ግሥጋሴ መተንበይ አይቻልም፡፡ የራሱ በሆኑ ከሞላ ጎደል ምስጥራዊ ሕግጋት የሚመራ ነውና›› በሚል ያምናል፡፡ በአንጻሩ ተመስገን ከዚህ ሃቲት በሚቃረን መልኩ አብዩትን በቀጠሮ ለማዋለድ፣ አብዩቱንም ያለ ደም የሚከወን ‹‹የሕዳሴ አብዩት›› ማድረግ ይቻላል ብሎ ተከታታይ ጽሁፎችን አስነብቦናል፡፡ የተመስገን መነሻ 2006 ላይ በኢትዮጵያ የነበሩ ‹አብዮታዊ ሁኔታዎች› ወደ አውዳሚ ግጭት ከማደጋቸው በፊት የሰላማዊ ትግላችን ግብዓት ማድረግ አለብን የሚል ነበር፡፡ በተለይም የአረቡ ዓለም የጸደይ አብዮት ሂደት (ያኔ እንዲህ አጓጉል አልሆነም ነበር) ለአገር ቤቱ መነቃቃት ሊሆነን ይገባል በሚል መነሻ፤ ‹ጠመንጃ አናነሳም፤አደባባዩን ግን እንቆጣጠረዋን› በማለት የጄን ሻርፕን የሠላማዊ ትግል አስተምህሮት አብዝቶ ሰብኳል፡፡ በዚህ አቀራረቡ ‹‹ደም ካልፈሰሰ ሥርየት የለም›› ከሚሉት ወገን ጋር እንደማይሰለፍ አሳይቷል፡፡ ተመስገን በብዕሩ ‹ይህ ትውልድ በባርነት ከሚኖር በደም አልባ የህዳሴ አብዮት ለራሱም ሆነ ለቀጣዩ ትውልድ ነጻነትን ማውረስ ይችላል› የሚል ሙግት ነበረው፡፡ አብዩታዊ ዴሞክራሲን ለመድፈቅ፣ የራሱ ቀለም ያለውን የአብዩታዊ የጋዜጠኝነት ኀልዩትን ከትግል ጓዶቹ ጋር ሆኖ አሳይቷል፡፡ የቀለም አብዩት ናፍቆቱና የሕዳሴ አብዩት አተገባበሩ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ አኳያ ተጨባጭ ተቃርኖ ቢኖርበትም፣ እንዳለውም አደባባዩ ለወጣቶቹ አልራቀቸውም ነበር፡፡ ከደም አልባ አብዩት ውጭ ኢትዮጵያን እንደ አገር ማቆየት እንደማይቻል ካመነ ውሎ አድሯል። የሚዲያው ቅኝትም ይሄው ነው።
3)  የሃሳብ ነጻነትን ማክበር፤
የዴሞክራሲ አዕማድ ተደርገው ከሚወሰዱት ፍሬ ነገሮች አንዱ፤ ‹የተለያየ አመለካከት እና ሀሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብትን ማስተናገድ ነው›፡፡ ዛሬ ‹ሊበሪታንያን› (Liberitanian) የመንግሥት ሥርዓት ባላቸው አገራት ‹‹ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እስከ ማበሳጨት›› በሚደርስ ተለጣጭ ባህሪ ሲሰራበት ይታያል፡፡ ስለየትኛውም ነገር ያለ ገደብ የራስ አመለካከትንና ነጻ ሃሳብን ማሰራጨት የሚፈቅደውን ሥርዓት ፣ እንድንቀበለው ወደ መድረኩ የተገፋ ቢሆንም፣ የላቀ ነጻ ሃሳብ መድረክ ሊሆኑ በሚገባቸው የግል ሚዲያዎች ላይ ተተግባሪነቱ እምብዛም ነው፡፡ በተለይም ከብሔር ውግንና፣ ከፖለቲካ አተያይና ዝንባሌ፣…ወዘተ አኳያ ሚዲያ ላይ ያሉ ሰዎች (ባለቤቶች) የነጻ-ሃሳብ ቀበኞች ሆነው ይታያሉ፡፡ ታሪክና ሃይማኖት ነክ ጉዳዩችን በነጻነት ከማስተናገድ አኳያ፣ የብሉይ ባህሪያትን የሚዋረሱት ማህበራዊ ዕይታዎቻችን ፈታኝ በመሆናቸው በዚህ ዙሪያ ያለን ጉዳይ አክብሮ የሃሳብ ነጻነትን የማስተናገድ ዝግጁነት ይጎድላል፡፡ የታሪክ ጥናት ተመራቂው ተመስገን ደሳለኝ፣ ለዘመናዊት ኢትዮጵያ የታሪክ መሃንዲስ ለሆኑት  ነገሥታት አዎንታዊ አረዳድ ያለው ቢሆንም፤ በእርሱ ሚዲያ አጼ ቴዎድሮስን እና አጼ ምኒልክን የሚያብጠለጥሉ አልፎም የሚያራክሱ ጽሁፎች እንዲስተናገዱ፣ በነገሥታቱ ታሪክ ላይ ጸሐፍት ያለ ገደብ እንዲሟገቱበት ማድረግ ችሏል፡፡
በዚህ ረገድ በቁመትና በዝና የመጨረሻውን ጃንሆይ መስሎ የሚታየው በዕውቀቱ ሥዩም አጼ ቴዎድሮስን እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ዳግማዊ ግራኝ…›› አይነት አቀራረብ፣ የታሪክ ሙግት ሲያቀርብ አፍቃሪ ቴዎድሮስ የሆነው ተመስገን የክርክር መድረኩን ከማስፋት በቀር እቀባ ለማድረግ ግላዊ ዝንባሌው አልተጫነውም፡፡ ሁነቱ የሃሳብ ነጻነትን ከማክበር እንጅ ከገበያ ፍላጎት የሚመነጭ እንዳልነበር የዚያን ዘመን የፍትሕ ጋዜጣ ፖለቲካዊ የይዘት አቀራረብና የህትመት ብዛት የሚያስታውስ ሰው ይመሰክራል፡፡ (30 ሺህ ኮፒ ድረስ የሚታተም ሳምንታዊ የግል ጋዜጣ ወደ ፊት ካልመጣ በስተቀር የያኔዋ “ፍትሕ” ብቸኛ ባለታሪክ ሆና ትቀጥላለች)
4)  ለቀደመ የትግል መርህ መታመን፤
ተመስገን ደሳለኝ የዘውጋዊ ብሔርተኝነት መናፍቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከልቡ የተቀበለ እና ታሪካዊ ይዘቷን ያከበረ፤ የኢትዮጵያን ብርቅየነት (Exceptionalism) በብዕሩ ሲመሰክር የኖረ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ይህ የትላንትም ሆነ የዛሬ አቋሙ ነው፡፡ አንድ ሰው ብሔርተኛ ሲሆን በዜግነቱ ላይ ጥያቄ እያነሳ ነው፡፡ የአርነት ጉዞው የራሴ ከሚለው ነጠላ ማንነት ጋር እንጅ ህብራዊት ኢትዮጵያ ጋር አይደለም፡፡ (በቅንፍ ውስጥ የኔን የተለየ ሃሳብ ላክል፤ የአማራ ብሔርተኝነት በበዛ በደልና ምሬት እንደተቀሰቀሰ ሀቅ ነው ይህ ማለት ግን ‹ዓርነት› ምርጫው ይሁን ማለት አይደለም፤ ከኦነጋውያንም ሆነ ከትሕነጋውያን ሊለይ ይገባል ስል ከዚህ አውድ በመነጨም ጭምር ነው፤ተመስገን ደጋግሞ ‹ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ ተቀይረህብኛል› ሲለኝ፣ ‹‹ትግል በቅራኔ ዕድገት ልክ ምርጫው ይወሰናል›› ብየ መመለሴን አስታውሳለሁ) ተመስገን የህትመት ሚዲያውን ከተቀላቀለበት ከ 2001 ጀምሮ ላለፉት 12 ዓመታት የኢትዮጵያን ብርቅየነት በብዕሩ ሲመሰክርና ለጋራ ነጻነት ጥሪ ሲያቀርብ ኑሯል፡፡ የደረሰበትን እስራትም ሆነ እንግልት የተረጎመው ከሥርዓቱ ጨቋኝ ባህሪ የተነሳ እንጅ ከእርሱ ዘውጋዊ ማንነት ጋር አያይዞ አይደለም፡፡ ይህ የራሱ አረዳድ ነው። የቅራኔ ዕድገቱ በትግል ስልቱ ላይ ለውጥ  አላመጣም፡፡ ይህ ቋሚ ባህሪው  ከአርፋጅም ሆነ ከሰንባች ብሄርተኛው ጋር በሃሳብ ሲያላትመው ቢቆይም ለቀደመው የትግሉ መርህ እንደታመነ ዛሬም ድረስ ዘልቋል፡፡
5)  የተሻጋሪ ሐሳብ ባለቤትነት፤
ከተመስገን ብዕር በተደጋጋሚ የሚወጡ ቃላት፡- ነጻነት፣ ፍትሕ፣ እኩልነት፣… የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ቃላት የሚሸከሟቸው ፖለቲካዊ ትርጉሞች በአውድ በአውዱ ሊታዩ የሚችሉ ናቸው፡፡ ገዥ-ሐሳባቸው ግን የሥርዓቱ መገለጫ ‹ከተቋማት ግንባታ ይልቅ የግለሰብ አምልኮ ይጫነዋል›› የሚል ተጠየቅ በማንሳት፤ የመንግሥትነት ግንባታ በመሪዎች ‹እኔነት› ወድቀት እንደገጠመው፣ ለዚህም መውጫ መንገዱ የተቋማት ግንባታ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሞግቷል፡፡ ይህ ከመለስ ዜናዊ እስከ ዐቢይ አህመድ ድረስ የዘለቀ ሙግቱ ነው፡፡ በይበልጥ ‹‹የመለስ አምልኮ›› የሚለው መጽሐፉ የተሻጋሪ ሐሳብ ባለቤትነቱን ያስረግጥለታል፡፡ ያኔም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ የፖለቲካና የዴሞክራሲ ተቋማት መኻን ነች የሚል ሙግት  አለው፡፡ መለስን በሞገተበት መለኪያ ዐቢይ ላይም ብዕሩን መዝዟል፡፡ ገና በጥዋቱ ‹‹የዐቢይ መንገድ…›› በማለት ለውጡን ተቋማዊ መሠረት እንዲይዝ ማድረግ የግድ ስለመሆኑ አሳስቧል፡፡ ሳሞራን በተቸበት ብዕሩ ብርሃኑ ጁላንም አላስተረፈውም። ተመስገን እንደዛ ነው፤ የሚቆምለት የፍትሕ ጥያቄ እንጅ የግለሰብ ፍላጎት የለም። ፍትሕ ደግሞ የሕዝብ ነች!
(ይቀጥላል)
Filed in: Amharic