>

የብርሐነ መስቀል አበበ ሰኚ ነገር. . .  (አቻምየለህ ታምሩ)

የብርሐነ መስቀል አበበ ሰኚ ነገር. . . 

አቻምየለህ ታምሩ
አቶ ብርሐነ መስቀል አበበ ሰኚ   የሚባለው ሰውዬ ከሹመቱ ከተወገደ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ዛሬ ባሰማው ሙሾ አምነስቲ ኢንተርናሽናል  ወለጋና ጉጂ ውስጥ  ተፈጸመ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያወጣውን ዘገባ [ሪፖርት አለልሁም] <<በካፒታልዝም ስም የጭሰኛውን ስርዓት መልሰው በሕዝባችን ላይ ሊጭኑ የሚቋምጡት አሃዳዊያን>> ያላቸው  ኃይሎች የፈጸሙት አድርጎ አቅርቦታል። አቶ ብርሐነ መስቀል ሙሾውን  የጠቀለለው ወለጋና ጉጂ  ኦነግ እያደረገ ስላለው ሽብር  <<ከዚህ በኋላ  አንድ ቋንቋ ብቻ የሚናገር የኢትዮጵያ መንግስት የአማራ ክልል መንግስት ይሆን እንደሆን እንጂ፣ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መንግስት አይሆንም።>> በማለት ባቀረበው <<የመፍትሔ ሀሳብ>> ነው።
የአምነስቲው ዘገባ የሚሸፍነው ብርሐነ መስቀል አበበ ሰኚ ተደምሮ አገር ቤት ከገባበት ቀን ጀምሮ በቆንስልነት ተሹሞ ወደ አሜሪካን የመጣበትንና በቆንስልነት የነበረበትን ጊዜ ነው። ብርሐነ መስቀል አበበ ሰኚ በዚህ ከዐቢይ አሕመድ ጋር ተደምሮ ሽር ብትን ይል በነበረበት ጊዜ  ኦሮምያ በሚባለው ክልል  በተለይም  ወለጋ ውስጥ ይካሄድ የነበረውን ጦርነት ይገልጠው የነበረው <<ጌታቸው አስፋ በኦሮሞ ስም ያደራጃቸው  ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች  በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የከፈቱት  የውክልና ጦርነት>> ፤ << በሕወሓት የሚታገዝ የኦሮሞ ካባ የለበሰ ጸረ ኦሮሞ አጀንዳ [አራማጆች] >> ፤ <<[የኦሮሞ ካባ የለበሱ]  ጃንጃዊዶች  ሽብር>>  ሲል  የገለጻቸው፤  ወለጋ ውስጥ  ኦሮሞን  አሸበሩ ያላቸውና  መንግሥት ትዕግስቱ አብቅቶ እርምጃ ሊወስድባቸው ይገባል እያለ ይመክር የነበረው ኦነግ ሸኔዎችን ነው።
ባጭሩ አምነስቲ ወለጋ ውስጥ  የኃይል እርምጃ ተወስዷል ብሎ ዘገባ የሰራው ብርሐነ መስቀል አበበ ሰኚ ሹም በነበረበት ወቅት ጃንጃዊድ፤  <<ጌታቸው አስፋ በኦሮሞ ስም ያደራጃቸው  ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች  በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የከፈቱት  የውክልና ጦርነት>> ፤ << በሕወሓት የሚታገዝ የኦሮሞ ካባ የለበሰ ጸረ ኦሮሞ አጀንዳ [አራማጆች] >> ብሎ የጠራቸው ሸኔዎች  በኦሮሞ ሕዝብ ላይ  ፈጸሙት ብሎ ይነግረን የነበረውን የሽብር ተግባር ነው።
በሌላ አነጋገር አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዘገባው ወለጋ ውስጥ በአግዛዙ ተፈጸመ ብሎ የዘረዘረው የኃይል እርምጃ ብርሐነ መስቀል አበበ ሰኚ ተደምሮ ሹም በነበረበት ወቅት የዐቢይ አሕመድ አግዛዝ  በሸኔ ላይ እንዲወስድ ይመክረው የነበረውን እርምጃ ነው።
 ይታያችሁ እንግዲህ!  አምነስቲ  በዘገባው ከአንድ ዓመት በፊት በወለጋ  በአግዛዙ ኃይሎች ተወሰደ ያለውን የኃይል እርምጃ ብርሐነ መስቀል አበበ ሰኚ <<በካፒታልዝም ስም የጭሰኛውን ስርዓት መልሰው በሕዝባችን ላይ ሊጭኑ የሚቋምጡት አሃዳዊያን>> የፈጠሩት አድርጎ  ዛሬ በጻፈው ሙሾ ያቀረበው እሱ ራሱ በመካከላቸው በተፈጠረ የጥቅም ግጭት ከቆንስልነቱ  ከመነሳቱ በፊት የዐቢይ አሕመድ አግዛዝ ወለጋ ላይ በመሸገው ኦነግ ሸኔ ላይ እንዲወስድ  ያሳስበውን የነበረውን የኃይል እርምጃ ነው።
የኦሮሞ ብሔርተኞች ፖለቲካቸው ከአማራ ወይም  አሐዳውያን ብለው ከፈረጁት የኅብረተሰብ ክፍል ጥላቻ ውጭ ሌላ ሀሳብ ስለሌበት ትናንትና ሹምና ተደማሪ ሳሉ በእነሱ ምክርና ተማጸኖ የኦሮሞ መንግሥት ነው በሚሉት አግዛዝ  ወለጋ ውስጥ ወሰደው የተባለውን የኃይል እርምጃ ብቻ ሳይሆን  ምግብ ሲበሉ ትን የሚላቸውን ሁሉ አማራ  ያደረሰባቸው አድርገው ካላቀረቡት ፖለቲካ የሰሩና ቆመው የሚሄዱ አይመስላቸውም። ለዚህም ነበር  የአሞራ ስጋዎቹ የኦሮሞ ብሔርተኞች ፖለቲካ  ሁልጊዜ የጥንብ አንሳ ፖለቲካ ያልነው።
አቶ ብርሐነ መስቀል አበበ ሰኚ  በሙሾው  ያነሳው ሌላው ነገር <<ከዚህ በኋላ  አንድ ቋንቋ ብቻ የሚናገር የኢትዮጵያ መንግስት የአማራ ክልል መንግስት ይሆን እንደሆን እንጂ፣ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መንግስት አይሆንም።>> ሲል  የጻፈው ጉዳይ ነው።  ይገርማል! የኦሮሞ ብሔርተኞች ግብዞች  ስለሆኑ አማራውን የሚከሱበት የአንድ ቋንቋ ፖለቲካ የኦሮሞ ብሔርተኞች የራሳቸው ገመና እንደሆነ እንኳ አያውቁም። ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ  አንድ ቋንቋ ብቻ የሚናገር መንግሥት  ወይም ክልል ያለው እነሱ እንደሚሉት የአማራ በሚባለው ክልል  ውስጥ ሳይሆን ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ ነው። የአማራ በሚባለው ክልል ውስጥ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ አዊኛ፣ ሕምጥኛ፣ ቅማንትኛና አርጎብኛ የስራ ቋንቋዎች ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ቋንቋዎች የስራ  ቋንቋዎች በተደረጉበት የአማራ በተባለው ክልል ውስጥ የሚኖሩት የእነዚህ  ቋንቋዎች ተናጋሪዎች ነገዶች ሁሉ የራሳቸው ፓርላማ ያላቸው፣ <<ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ>>፣ ለማንነታቸው እውቅና የተሰጣቸው፣ በቋንቋቸው የሚማሩ፣ የሚዳኙና የሚሰሩናቸው። በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር አማራ፣ በሚሊዮኖች፣ በመቶ ሺዎችና በአስር ሺዎች የሚቆጠር ጉራጌ፣ አርጎባ፣ ትግሬ፣ ዝይ፣ ዳዋሮ፣ ጌዲዮ፣ ሐድያ፣ ካፊቾ፣ ከምባታ፣ ኮንሶ፣ ማኦ፣ ሲዳማ፣ ሲልጢ፣ ሶማሌ፣ ዎላይታ፣ የም፣ ወዘተ  በሚኖሩበት ክልል ውስጥ አንድ ቋንቋ ማለትም ኦሮምኛ ብቻ የሚነገርበትና ሌላው እንዳይሰራበት በሕግ የተከለከለበት፤ ከኦሮሞ በስተቀር ማንነቱ የታወቀና ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር አንድም የኢትዮጵያ <<ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ>> የሌለበት ክልል ቢኖር ኦሮምያ ክልል የሚባለው ነው።
በዐይኑ ላይ ያለውን የራሱን ጉድፍ የአማራ ቆሻሻ የሚያደርገው ብርሐነ መስቀል አበበ ሰኚ ግን በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር አማራ፣ በሚሊዮኖች፣ በመቶ ሺዎችና በአስር ሺዎች የሚቆጠር ጉራጌ፣ አርጎባ፣ ትግሬ፣ ዝይ፣ ዳዋሮ፣ ጌዲዮ፣ ሐድያ፣ ካፊቾ፣ ከምባታ፣ ኮንሶ፣ ማኦ፣ ሲዳማ፣ ሲልጢ፣ ሶማሌ፣ ዎላይታ፣ የም፣ ወዘተ  በሚኖሩበት ክልል ውስጥ አንድ  ቋንቋ ማለትም ኦሮምኛ ብቻ የሚነገርበትን፤ ከኦሮሞ ውጭ ላንድም <<ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ>> እውቅና ሳይሰጥ፣ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ሳይፈቅዱና  እስከ ቀበሌ ድረስ አንድ አይነትና ልሙጥ የሆነ አሕዳዊ አገዛዝ የዘረጋውን ኦሮምያ የሚባለውን ክልል ታቅፎ ስድስት ቋንቋዎች የስራ ቋንቋዎች የሆኑበትን፣ ስድስቱንም ቋንቋዎች የሚናገሩት ነገዶች ሁሉ የራሳቸው ፓርላማ ኖሯቸው ፣ <<ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ>>፣ ለማንነታቸው እውቅና ተሰጥቷቸው፣ በቋንቋቸው እየተማሩ፣ እየተዳኙና እየሰሩ የሚኖሩበትን የአማራ የሚባለውን ክልል በአንድ ቋንቋ ብቻ ተናጋሪነት ሲከስ አይሰቀጥጠውም።
ከታች የተያያዙት ስክሪንሾቶች አቶ ብርሐነ መስቀል አበበ ሰኚ ዛሬ <<በካፒታልዝም ስም የጭሰኛውን ስርዓት መልሰው በሕዝባችን ላይ ሊጭኑ የሚቋምጡት አሃዳዊያን>> እንደተፈጸመ አድርጎ ያቀረበውና አምነስቲ የዘገበውን የኃይል እርምጃ  << ጌታቸው አስፋ በኦሮሞ ስም ያደራጃቸው ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች>> ፤ << በሕወሓት የሚታገዝ የኦሮሞ ካባ የለበሰ ጸረ ኦሮሞ. . . >> ፤ <<ጃንጃዊድ>>  ወዘተ.. . እያለ በጠራው  ኦነግ ሸኔ እንደተወሰደ የመሰከረባቸውና የዐቢይ አሕመድ አግዛዝ  ትዕግስቱ አብቅቶ በሸኔ ላይ ን የኃይል እርምጃ እንዲሰወድ የተማጸነባቸው የፈስቡክ ፖስቶቹ ናቸው።
Filed in: Amharic