>

እነ ማን ነበሩ??? አሁንስ ማን ናቸው??? (ገብረመድህን አርአያ - ፐርዝ፤ አውስትራሊያ)

እነ ማን ነበሩ??? አሁንስ ማን ናቸው???

ገብረመድህን አርአያ
ፐርዝ፤ አውስትራሊያ

…. ጥቂት ስለ ጽሁፉ እንደ መግቢያ፡- ከዚህ በታች የቀረበው ጽሑፍ – ከ3 ገጽ ያነሰ ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ የህወሓት ነባር ታጋይና አመራርም የነበሩት አይተ ገብረመድህን አርአያ ከጥቂት ዓመታት በፊት ‹‹እነ ማን ነበሩ? አሁንስ ማን ናቸው?›› በሚል ርዕስ ከጻፉት ጽሑፍ የመጀመሪያዎቹ 3 ገጾች ላይ ተወስዶ እንዳለ የቀረበ ነው! የሚናገሩት የበረሃ ጉድ በግርምትም በድንጋጤም አፍን አስይዞ ያስቀራል፡፡ ግርም ይላል በጣም፡፡
በእርግጥ አቶ ገብረመድህን አርአያ የእውነትና የሀቅ ሰው ሆነው ለብዙ ዓመታት በቆራጥነት ህወሓትን በሃሳብ የሞገቱ አስገራሚ ፅናትን የተላበሱ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በሚሰጧቸው ቃለመጠይቆችና በጽሑፎቻቸውም ላይ ከፍ ያለ ጥላቻን የተሞሉ እና የራሳቸውን `ሳይድ` ብቻ ያገናዘቡ አቋሞችን በህወሓት ላይ ሲያንፀባርቁ ይታያሉ፡፡
እና – ይሄስ በዚህ ጽሑፍ ያሰፈሩት ቃላቸው ምን ያህል በገለልተኝነት የተጻፈ፣ ምን ያህልስ ያልተበረዘ-ያልተከለሰ ሀቅ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ለታሪክ እና ለእውነት ትቼ – የእኚህን አባት የእውነት ቃል ያልሰማ፣ ያላየ፣ ያላነበበ ካለ – ራሱ አይቶ እንዲፈርድ በማሰብ – በተለይ – ሶሻሊስቷ ህወሓት በሐይማኖቶች ላይ በተግባር ያራመደችውን የቆየ የዕምነት ተቀናቃኝነት ፖሊሲ በተመለከተ – ገብረመድህን አርአያ ያሰፈሩትን የእምነት ቃል እንዳለ አቅርቤዋለሁ!
ብዙዎቻችን እንኳን ህይወታችንን ሰጥተን አምነንበት ተሰልፈንበት የነበረን ታሪክ ይቅርና በአለፍ ገደም እንኳ የተገኘንበትን ታሪክ ምን ያህል እያቆለጳጰስን እንደምናወሳው ራሳችንን ስናስብ – የነበሩበትንና ያሳለፉትን ሕይወት ኮንነው ሃቁን ለትውልድ ለመናገር ታላቅ የመንፈስ ወኔን ለተላበሱት ለእኚህ ጸሐፊ ልባዊ አድናቆት ለማሳደር እንገደዳለን፡፡ በዚህ ዓይን ጸሐፊውን እያደነቅኩና እያመሰገንኩ – ፍርዱን ለታሪክ ሀቅ ትቼ – ለፌስቡክ አንባብያን ወዳጆቼ – መልካም ንባብን እየተመኘሁ ተለየሁ! ጽሁፉ ብዙ አይደለም፡፡  |||||||
“ይህ ጽሑፍ ትኩረት የሚሰጠው በትግል በረሃ በነበርንበት ወቅት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት.) በክርስትና እና በእስልምና ሃይማኖቶች ላይ ሲከተል የነበረውን አቋሙን ተቀብሮ ከነበረበት ጉድጓድ አውጥቼ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እነማን ናቸው የሚለውን
ታሪካቸውን እና የተፈጸመውን ጸረ-እምነት ግፍ በአጭሩ ለማሳወቅ ነው።
“ህ.ወ.ሓ.ት. ገና ሲፈጠርና ተ.ሓ.ህ.ት. ተብሎ እንደተመሰረተ ሙልጭ ያለ ጸረ-ዲሞክራሲ ድርጅት ነው። በጸረ-ኢትዮጵያነትና በጸረ-ሕዝብነት የተሰማራ ቅጥረኛ ድርጅት መሆኑን ብዙ ጊዜ በጽሑፍና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ህዝብ ተናግሬአለሁ። የአሁኑ
ጽሑፌ ህ.ወ.ሓ.ት. በሃይማኖት ላይ ሲከተለው የነበረውን ፖሊሲ ገና ከመጀመሪያ ትግሉ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የነበረውን ጸረ-ሃይማኖት ተግባራቱን የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልጽ አውቆታል። እኔ ደግሞ የራሴን ልበል።
“በ1969 መጀመሪያ ጀምሮ “ወይን” በሚለው የድርጅቱ ልሳን መጽሔት ላይ በተደጋጋሚ “የክርስትና ሃይማኖትና አማራው” በሚል ርእስ ተጽፎ የሚወጣው ጽሑፍ፣ “የክርስትና ሃይማኖት የአማራው ዋና መሳሪያና የግዛቱን ህልውና ማስጠበቂያ ነው፣ በመሆኑም የትግላችን ጠላት አማራውና መሳሪያው የተዋህዶ ክርስትና ስለሆኑ አብረው እንዲጠፉ ማድረግ አለብን” እያለ ያትት ነበር። ይህንን መጽሔት በሰፊው ለታጋዩና ለአባላቱ በማሰራጨት ሰፊ ቅስቀሳ አካሂዶበታል።
“በነሐሴ 1969 “ወይን” መጽሔት አማርኛ ቋንቋም አብሮ መጥፋት እንዳለበት ሃተታ ይዞ ወጥቷል። “ወይን” መጽሔት ከ1969 ጀምሮ በተከታታይ የሚያወጣው ጽሑፍ በህ.ወ.ሓ.ት. ፕሮግራም ላይ የተቀመጡ የረጅም ጊዜ እቅድ በመተንተን እና በማብራራት ለታጋዩ ለውይይት በማቅረብ ሲያብራራ፣ “ኢትዮጵያ ወይም ሞት” ብሎ የሚናገረውን አማራ ማጥፋት ከሱም ጋር አብሮ የሚቀበረው አማርኛ ቋንቋ ይሆናል ይላል።
” “ወይን” የምትለውን መጽሔት የሚያዘጋጁት ከፍተኛ የአመራር አባላት በፕሮፓጋንዳ ቢሮ ሆነው ለዚሁ ተግባር የተዘጋጁ ጽሑፎችን በስፋት የሚያሰራጩት፣ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሃየና መለስ ዜናዊ ነበሩ። እነዚህ ሶስቱ የህ.ወ.ሓ.ት. አመራር አባላት እብዶችና በጸረ-
ሃይማኖት፣ ጸረ-አማራ ባህሪያቸውና አቋማቸው በሰላማዊው ህብረተሰብና ታግዩም ጭምር በግልጽ የሚታወቁ ናቸው።
“የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ የሚመራውም በነዚህ ሶስት እብድ አመራሮች ነበር። ከዚህ በመነሳት መስከረም 1970 በጸረ-ሃይማኖት፣ በተለይም በተዋህዶ ኦርቶዶክስ ላይ ቅስቀሳውን በስፋት ለማካሄድ በማሰብ፣ ሕዝብ ያሳምናሉ ተብለው የሚታመንባቸውን ታጋዮች መርጠው እገላ ወረዳ መሬቶ ተብላ በምትጠራ ቁሽት ውስጥ ተሰብስበው ቦታ ተዘጋጅቶ ከላይ በተጠቀሱት ሶስቱ አመራር ሴሚናር ተዘጋጀ። በሴሚናሩ ላይ የሚከተሉት ታጋዮች ተካፍለው ነበር፤
“1. መርሳ ረዳ          |||||||  9. ጉእሽ ጓእዳን
2. ሃለቃ ፀጋይ በርሄ   |||||||  10. ቢተው በላይ
3. ቴዎድሮስ ሃጎስ      |||||||  11. ሃድሽ ገዛኸኝ
4. አባይ ወልዱ         |||||||  12. ሮማን ገ/ሥላሴ
5. ሃዳስ ዓለሙ         |||||||  13. አፈራ ተክለሃይማኖት
6. ኃ/ሥላሴ ገ/ኪዳን   |||||||  14. ወልደገብርኤል ሞደርን
7. ሃሪያ ሰባጋድስ       |||||||  15. አዲስዓለም ባሌማ
8. ቅዱሳን ነጋ
“ከላይ የተጠቀሱት ታጋዮች በተካሄደው ሴሚናር በጸረ-ክርስትና እና በጸረ-እስልምና አስተሳሰብ በሶስት ቀን ውስጥ ተጠምቀው ጨረሱ። እንደጨረሱም በሶስት ሪጅን ተመደቡ፤ አመዳደባቸውም፤ ሪጅን-1 መርሳ ረዳ፤ ሪጅን-2 ሃለቃ ጸጋይ በርሄ፤ ሪጅን-3 አዲስዓለም ባሌማ በሃላፊነት እንዲመሩት ተመረጡ። ቀሪዎቹም በእነዚህ የበላይ ተጠሪዎች ስር ተደለደሉ።
ሪጅን 1 
መርሳ ረዳ ተጠሪ
1-ጉእሽ ጓእዳድ
2-አባይ ወልዱ
3-ኃ/ሥላሴ ገ/ኪዳን
4-ሃርያ ሰባገድል
ሪጅን 2
ጸጋይ በርሄ ተጠሪ
1-ቅዱሳን ነጋ
2-ሃዳስ ዓለሙ
3-ቢተው በላይ
4-ሃድሽ ገዛኸኝ
5-ሮማን ገብረሥላሴ
ሪጅን 3
አዲስዓለም ባሌማ ተጠሪ
1-ቴዎድሮስ ሃጎስ
2-ወ/ገብርኤል ሞደርን
3-አፈራ ተ/ሃይማኖት
“በዚህ መልክ ተደራጅተው በየሪጅኑ ተሰማሩ። ድጋፍ ሰጪ የሕዝብ ግንኙነት ካድሬዎችም በየድርጅቱ በስፋት ተሰማሩ። እነዚህም በተጠናከረ ሃይል ጸረ-ክርስትና፣ ጸረ-አማራ፣ ጸረ-እስልምና ቅስቀሳቸውን ቀጠሉበት። በተዋህዶ ክርስትና ላይ ሙሉ ሃይላቸውን በመጠቀም በስፋት ጸረ-ክርስትና ቅስቀሳውን በተከታታይ እሁድና ሌሎች በዓላት እንዳይከበሩና የሥራ ቀን መሆናቸውን በማወጅ በህብረተሰቡ ላይ ካባድ ተጽእኖ አሳደሩበት።
ቀሳውስትና ዲያቆናት በማንኛውም በዓላት ቤተ ክርስቲያን ከፍተው ሲቀድሱ ቢገኙ ከባድ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስጠነቀቁ። አልፎ አልፎ ተቃውሞ ይገጥማቸው ስለነበር በበላይ አመራሩ ለእነ ስብሃት ነጋ ምን እናድርግ እያሉ ሪፖርት ያቀርቡ ነበር። ከአመራሩ የተሰጠው ምላሽ፣ ማንም ያንገራገረ ቄስ፣ ባህታዊ፣ ዲያቆን ወይም ሌላ እዛው ባለበት በሕዝቡ ፊት ግደሉት የሚል መመሪያ ተሰጣቸው።
“በዚህ መሰረት አድዋ አውራጃ እንዳባጻህማ ወረዳ የሚገኘው እንዳሥላሴ ተብሎ የሚታወቀው ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን መሪ አባ ሃይለሥላሴ የሚባሉ ቄስ፣ “ሃይማኖታችንን አታርክሱት፣ የተቀደሰ ሃይማኖት ነው” ብለው ስላሉ በቦታው የነበረ ጸጋይ በርሄ የሚባል ታጋይ በያዘው አጭር ጓንዴ ተኩሶ ጭንቅላታቸው ላይ በመምታት በሕዝብ ፊት ገደላቸው። ቀሪው ምእመናን ተደናግጦና በርግጎ ተበታተነ። ሃለቃ ጸጋይ በርሄ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የነበረውን ንብረትና ሃብት ጠራርጎ ወሰደው።
“በተመሳሳይ፣ ዛና ወረዳ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን መሪ የነበሩት አባ ቄስ አርአያ ከአንድ የ90 ዓመት አዛውንት ባህታዊ ጋር ሆነው፣ “እባካችሁ ሃይማኖታችንን አታርክሱብን” በማለታቸው ከቢተው በላይ ጋር ተደራቢ ሆኖ የሄድው አርከበ እቁባይ ሁለቱን ንጹሃን ዜጎች በሕዝቡ ፊት ገደላቸው።
“በስብሃት ነጋ፤ አባይ ፀሃየና መለስ ዜናዊ የሚመራው ጸረ-ክርስትና ሃይማኖት ከላይ የተጠቀሱትን 15 ታጋዮች የተግባሩ ፋጻሚዎች በማድረግ በርካታ ቤተ ክርስቲያናትን አቃጥለዋል። ከአድዋ፣ አክሱምና ተምቤን አውራጃዎች ብዙ ቀሳውስትና ባህታውያን እንዲሁም ዲያቆናት ሌሊትና ቀን እየታፈኑ ተውስደው የውሃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል።
“የእስልምና ሃይማኖትን በተመለከተ፤ እስልምና ተከታይ ኢትዮጵያውያን ጸሎት ለመድረግ በሚሰበሰቡበት ጊዜ እየጠበቁ ጸረ-እስልምና ሰበካዎችን ለማራመድ በየመንገዱ ቅዱሱን ነብዩ መሃመድን እና ቅዱስ ቁርአንን ማብጠልጠልና ማራከስ በጀመሩበት ወቅት፤ ከሪጅን 1-3 በሚገኘው የእስልምና ተከታይ ሰፊ ተቃውሞ ገጠማቸው። በተለይ በሪጅን 3 አፋሮች የእስልምና ተከታዮች ስለሆኑ ጸረ-ወያኔ ተቃውሞ በማሰማት ለእምነታችን እንሞታለን፤ እንዋደቃለን በማለት ከፍተኛ ተቃውሞ አሰሙ። በሪጅኑ የተመደቡትን የህ.ወ.ሓ.ት. አባላት ተከታትለው በማደን ገደሏቸው። ከተገደሉት መካከል፣ ትእግስት አሰፋ፣ የኋላሸት ገ/መድህን (አላሚን)፣ ፀሃየ አብርሃ፣ ወዘተ ይገኙበታል።
“የዚህ አይነቱን ተመሳሳይ እጣ በታጋዮች ላይ በተደጋጋሚ አድርሰዋል። የህ.ወ.ሓ.ት. አመራር ስለሁኔታው ሲጠየቅ እስከ አሁን ድረስ ድርጊቱን በመካድ “በጦርነት ሞቱ” እያለ ይዋሻል። በጦርነት ሳይሆን ነቢዩ መሃመድን በማንቋሸሻቸውና ቅዱስ ቁርአንን በማቃጠላቸው በአፋር ሕዝብ የተገደሉ ናቸው። ቀሪዎቹ ማለትም አዲስዓለም ባሌማ፣ ቴዎድሮስ ሃጎስና አፈራ ተክለሃይማኖት ጨለማን ተገን በማድረግ ሸሽተው በዱር በገደል ሲያመልጡ ተሰባብረውና ገርጥተው ባንድ ወር ጊዜ አጋሜ አውራጃ ሶቦያ ደርሰው ሕይወታቸውን አዳኑ። በዚህ ምክንያት ህ.ወ.ሓ.ት. እስከ 1976 ድረስ አፋር ውስጥ መግባት ስለፈራ እንቅስቃሴውን አቆመ።
“በዚህ ወቅት በርካታ ቅዱስ ቁርአን እና መጽሐፍ ቅዱስ በህ.ወ.ሓ.ት. የተዘረፈ ንብረት ማጠራቀሚያ ውስጥ ታጉረው ለእሳት ማቀጣጠያ ይደረጉ እንደነበር በርካታ በጊዜው የነበሩ ታጋዮች የሚናገሩት የነበረ ሃቅ ነው።
“የእስልምና ታከታዩ ኢትዮጵያዊ በወያኔ ህ.ወ.ሓ.ት. የተጀመረውን ጸረ-እስልምና እንቅስቃሴ በሶስቱ ሪጅን የሚኖረው አማኝ ከፍተኛ ተቃውሞ በማስነሳት በአንድነት ቆመ። ወይ ወያኔ ይጨርሰን አለበለዚያ እኛ እንጨርሳችኋለን እንጂ በሃይማኖታችን አትገቡብንም
በማለት የህ.ወ.ሓ.ትን አመራር ጉሮሮ ያዙት። የወያኔ አመራር በሁኔታው ተደናገጠ። በገጠርም ሆነ በከተማ የሚኖረው ሕዝብ ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙት የአመራር አባላት የሆኑት ስብሃት ነጋ፣ መለስ ዜናዊና አባይ ፀሃየ መሆናቸውን በማወቁ እነዚህ ግለሰቦች በፍርሃቻ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አቆሙ፣ ከተንቀሳቀሱም በታጋይ እየታጀቡ ሆነ።
“በዚህ ጊዜ ወያኔ በኢ.ዲ.ዩና በኢ.ህ.አ.ፓ. የተወረረበት ወቅት ስለነበረ የአመራሩ የትግል ስሜት መሬት የወረደበት ጊዜ ነበር። ከዚህ በመነሳት ለጸረ-ሃይማኖት ተግባር ለተመደቡት ታጋዮች አስቸኳይ ትእዛዝ በማስተላለፍ ጸረ-እስልምና እንቀቃሴአቸውን እንዲያቆሙ፣ ጸረ-ክርስትና ሃይማኖት ሥራቸውን ግን እንዲቀጥሉበት ታዘዙ። ጸረ-ክርስትናው ቀጠለ። በህ.ወ.ሓ.ት. ነፃ መሬት የሚኖሩት የእስልምና ሃይማኖት እህቶቻን እና ወንድሞቻችን ከዛች ቀን ጀምሮ ለወያኔ መታዘዛቸውን አቆሙ። ክርስቲያኑ ወገን የህ.ወ.ሓ.ት. ንብረት አመላላሽ እየሆነ ሲያገለግል የእስልምና ተከታዮች ኢትዮጵያውያን ግን ሳይደፈሩ ተፈርተው ለዓመታት ቆዩ።
“የካቲት 1971 የህ.ወ.ሓ.ት. 1ኛው ጉባኤ በተካሄደበት ጊዜ የተመረጠው አመራር ማለትም፤ የድርጅቱ ሊቀ መንበር ስብሃት ነጋ፣ የፕሮፓጋንዳው ሃላፊዎች መለስ ዜናዊን እና አባይ ፀሃየን መረጠ። እነዚህ ሶስቱ ጸረ-ሕዝብ አመራሮች ሃይላቸውን እና ጉልበታቸውን
በማጠናከር ድርጅቱ ያወጣውን በርካታ አዳዲስ ፖሊሲ ግንባር ቀደም በማድረግ በሥራ ላይ ማዋል ጀመሩ። እነሱም፣ የተዋህዶ ክርስትና ሃይማኖት የአማራው መሳሪያና መገልገያ ስለሆነ፣ እግዚአብሄር የሚባል ነገርም ስለሌለ፣ ከአሁን ጀምረን ከነፃ መሬታችን ጠራርገን ማጥፋት አለብን። ለወደፊትም የሃገራችን የትግራይ መንግሥት ሲቋቋም ሕዝባችን ከማንኛውም አጉል እምነቶች ነፃ የሆነ ሃገር እንመሰርታለን በማለት የህ.ወ.ሓ.ት. አመራር ወሰነ።
“ከላይ የተጠቀሰው እንዳለ ሆኖ፣ በአዲስ ጉልበትና አዲስ ጸረ-ተዋህዶ ክርስትናን ማዳከሚያ ፖሊሲ ተጠናክሮ ወጣ። በተግባር ከተፈጸሙት መካከል፣
“1ኛ. በህ.ወ.ሓ.ት. ነፃ መሬት የሚገኙት አብያተክርስትያናት ያላቸውን ሃብትና ንብረት በሙሉ ለህ.ወ.ሓ.ት. እንዲያስረክቡ ታዘዘ፣
“2ኛ. ቄሶች ቆባቸውን እና ጥምጥማቸውን አውልቀው በመጣል የህ.ወ.ሓ.ት. “ወየንቲ” (ሚሊሻ ማለት ነው) እንዲሆኑ ተወሰነ፤ በተግባርም ታየ። ቄሶች የህ.ወ.ሓ.ት. ምንሽር፤ ጓንዴ፤ አልቤን እየተሸከሙ የህ.ወ.ሓ.ትን ነፃ መሬት ጠባቂ ሆኑ።
“3ኛ. በህ.ወ.ሓ.ት. ነፃ መሬት የሚገኙ ዲያቆናት ትዳር የመሰረተ ትዳሩን አፍርሶ ከነሚስቱ ወደ ትግል ሜዳ እንዲቀላቀሉ፣ ትዳር የሌለው ደግሞ በቀጥታ ወደ ትግሉ እንዲገባ ተብሎ ተወሰነ። ብዙ ትዳር ፈርሶ በውዴታም በግዴታም የህ.ወ.ሓ.ት. ታጋይ ተደረጉ።
“ወላጆች ጧሪ አልባ ሆነው ቀሩ። አብያተ ክርስቲያናት ካለ ቀዳሽና አገልጋይ ክፍት ሆነው ቀሩ። አብያተ ክርስቲያናት በዘራፊው የህ.ወ.ሓ.ት. ማፊያ ቡድን ተዘረፉ። በወያኔ አመራር የተዘረፈው ጥንታዊና ታሪካዊ መጽሐፍት፤ ውድና ብርቅ ጥንታዊ ታሪካዊ ንብረቶች ሲዘረፉ፣ በርካታ የግእዝ የብራና መጽሐፍትና ቅዱሳን መጽሀፍት ተቃጠሉ።
“ይህንን ጸረ-ሃይማኖት ድርጊትና የማውደም ሥራ እንዲከናወን በተለያዩ ጊዜያት ትእዛዝና አመራር የሰጡት፤ ስብሃት ነጋ፣ መለስ ዜናዊና አባይ ፀሃየ ነበሩ። በተባባሪነት ተጨማሪ እርዳታ የሚያደርጉት ደግሞ፣ አርከበ እቁባይ፣ ኤርትራዊው ጻድቃን ገብረተንሳይ፣ አውአሎም ወልዱ፣ ዘርአይ አስገዶም፤ ስየ አብርሃ፣ ስዩም መስፍን ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ናቸው። እነዚህ የአመራር አባላት የነመለስ፣ አባይና ስብሃት ታማኝና አገልጋይ አሽከሮች በመሆን ሕዝበ እስላሙን እና ክርስቲያኑን ሲያቃጥሉ የታዩ ናቸው። ብዙ አብያተ ክርስቲያናትንም በማቃጠል አውድመዋል፡፡
“ይህ በዚህ አይነት እየቀጠለ ባለበት ጉዞ፣ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ በውድም በግድም የለቀቁ ቄሶችና ዲያቆናት የካድሬ ሴሚናር ለሳምንታት ለመስጠት የሚከተሉት “መሪሕ ባእታ” ካድሬዎች ተመረጡ፤
“1. ሙሉጌታ ጫልቱ      |||||||  6. ጎበዛይ ወ/አረጋይ
2. ዘርአይ አስገዶም        ||||||  7. አባይ ወልዱ
3. መርሳ ረዳ               ||||||  8. ቅዱሳን ነጋ
4. አክሊሉ ደንበአርቃይ  |||||||  9. ግደይ በርሄ
5. ገብረኪዳን ደስታ      |||||||  10. ቢተው በላይ
“እነዚህ ካድሬዎች በሪጅን 1 እና 2 በመመደብ በተለያዩ ቦታዎች በመሰማራት ቀሳውስትና ዲያቆናትን ከ1973 መጀመሪያ አንስቶ ለስድስት ወራት በመዘዋወር የማርክሲስም ሌኒኒዝም ትምህርት በማስተማር በክለው ጸረ-ክርስትና ሃይማኖት አደረጓቸው። በሚመረቁበት ጊዜ በእነ ኢያሱ በርሄ የሚመራው የባህል ቡድን በበዓሉ ላይ በመገኘት ቀሳውስቱ እስክስታውን (ስእሲኢት) አወረዱት፣ አምላክን አወገዙት፣ “ክርስትና ሃይማኖት ከአማራው ጋር አብሮ ይደመሰሳል” እያሉ በየስብሰባው መክፈቻ መፈክራቸው አደረጉት።
“4ኛ. በህ.ወ.ሓ.ት. ነፃ መሬት የሚከተሉት በአዋጅ ታግደው ነበር። በሕዝብ ግንኙነት በኩል ተፈጻሚ እንዲሆኑም ትእዛዝ ተሰጥቶባቸው ነበር፣ እነሱም
“4.1|||||||   በህ.ወ.ሓ.ት. ነፃ መሬት ሠርግ ታገደ
“4.2|||||||   ተስካር (ተዝካር) እና የሞት ፍትሃት ታገደ
“4.3|||||||   አዲስ ለሚወለዱ ሕፃናት ክርስትና እና ጥምቀት ታገደ
“4.4|||||||   በየወሩ በመሰባሰብ ጸበል ፀዲቅ ማድረግ ታገደ
“4.5|||||||   በህ.ወ.ሓ.ት. ነፃ መሬት በየትኛውም ቦታ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በየዓመቱ የሚያካሂዱት በዓላት ታገዱ።
“ከላይ የተጠቀሱትን የህ.ወ.ሓ.ት ትእዛዝ የጣሰ እንደ ጸረ-ህ.ወ.ሓ.ት ተቆጥሮ ሃለዋ ወያነ 06 (“ባዶ ስድስት”) ገብቶ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰድበታል። ሃብት ንበርቱ ለህ.ወ.ሓ.ት ገቢ ይደረጋል። የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ታጋዮችም ይህንን ተግባራዊ አደርገውታል። ስለሆነም ሕዝብ በሃሰት እየተከሰሰ ሃለዋ ወያነ በመግባት የስንቱ ሕይወት በከንቱ ጠፍቷል። ንብረታቸው ተወርሶ እናትና ልጆቿ ለክፉ መከራ ተጋልጠዋል። አብያተ ክርስቲያናት ገንዘባቸውና ሃብት ንብረታቸው ተዘርፏል። ይህ በ1969 የተጀመረው ድርጊት ህ.ወ.ሓ.ት እስከ መጨረሻው ቀጥሎበት ፖሊሲውን በተግባር አውሎታል።__”
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic