>
5:13 pm - Friday April 19, 1297

የጣና ዳር ቁማርተኞች...!!! (ሀብታሙ አያሌው)

የጣና ዳር ቁማርተኞች…!!!

 
ሀብታሙ አያሌው
እውነትም የደጃዝማች በላይ ዘለቀ እርግማን ትውልድ እየተሻገረ ተከትሎናል።  “ኢትዮጵያዬ እውነት በድዬሽ ከሆነ ወንድ አይብቀልብሽ ”  ብሎ በግፍ ገመድ ነፍሱ በህቅታ አለፈች።  የወንዶች መስፈሪያ ቁናው አባኮስትር ነፍሱ በቀላያት ጥሪ ተማርካ እነ መይሳውን ናፍቃ ስትበር እርግማኑ ከኛው ጋር ቀረና እግር ይዘን የማንራመድ ስንኩል ሆነን ቀረን።
ይህው የእርግማኑ ቃል እውን ሆኖ ጀግና እንደ ሸክላ እየተሰበረ  ምንደኛ እና ሰላቱው መሪ ሆኖ የጀግኖቹን አሻራ የታሪካቸውን እልፍኝ  ማስበርበርን እንደ ጀብዱ ቆጥሮ ይፎክርበታል።
የጉድ አገር
=======
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ የአረም ማስወገጃ ማሽኖችን በሀገር ውስጥ  በማስመረት  መስከረም ላይ የማሽን ኦፕሬተሮች አሰልጥኖ ማሰማራቱ የአደባባይ ዜና ነበር።  የመልካም ዜናውን እወጃ ተከትሎ የእምቦጭ አረም ከታዘለበት ከጣና ትከሻ ላይ እየተጎተተ ሲወድቅ  ጣና እፎይታ አግኝቶ ሲተነፍስ አይናችን አይቶ ልባችን አረፈ።  ቁማርተኞቹ ጫወታቸውን ጣና ዳር ያደርጋሉ ብሎ የገመተ አንድስ  እንኳ አልነበረም።
ጣናን ለመታደግ  ዘምተው የነበሩት ወጣቶች ከቴክኒክና ሙያ  ተቋቋም ተመርቀው  ለዚሁ ስራ ብቁ እንዲሆኑ ተብሎ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ  ለወራት ያህል በቂ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርገው ነበር፡፡
ወደ ተግባር በገቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ  በቀን ከ800 ሜትር ኪዩቭ በላይ  የእምቦጭ አረምን ከጣና ላይ እየመነገሉ  በጭነት  መኪና ጓጉዘው በማራቅ  በእሳት ወደ አመድነት በመቀየር  ይቀይሩት ጀመር።
ይህ ግን በጣና ዳር ቁማርተኞች አልተወደደም።  አዲስ አበባ ለኢሬቻ ድምቀት ሰው ሰራሽ ሐይቅ ለመገንባት ከ2.5 ቢሊየን ብር በላይ ሲፈስ  ባህርዳር ላይ የአባይ እስትንፋስ የታሪክ ማህደር  ጣና  ወደ የብስነት እንዲቀየር አይታከም ተውት  ጣና ቃትቶ ይሙት ተብሎ ተፈርዶበታል።
ትዕዛዙ እንዲህ የሚል ነበር  . . .
“የእምቦጭ አረም  ለሌላ አገልግሎት ይፈለጋል፤ ሌላ ትዕዛዝ እስኪመጣ  እምቦጭን ከጣና ላይ ማጥፋቱ ይቁም”
የሰለጠኑት ተማሪዎች እንዲበተኑ ተደረገ።  እምቦጭ መስፋፋቱን ቀጠለ፤ በዚህ አላበቃም  ተመራማሪ ነን የሚሉ አካላት አረሙን ከጣና ወስደው  ለምርምር በሚል አብይ ዳርቻ ላይ ዘሩት ወራቶች ነጎዱ ተመራማሪ ነን ያሉት የውሃ ሽታ ሆኑ የእምቦጭ አረም ከጣና ተሻግሮ አባይን ሰንጎ ለመያዝ ጥድፊያውን ቀጥሏል።
በእርግጥ  ቢሊየን ብሮች ፈስሰው ሰው ሰራሽ ሐይቅ በሚሰራባት አገር ጣና በቁማርተኞች ወደ የብስነት እንዲቀየር ብንተወው ታሪክ ይቅር ይለናል ??
ለመሆኑ የአማራ ክልል ህዝብ አዴፓ (አማራ ብልፅግና) ፓርቲን የሚታገሰው እስከመቼ እንደሆነ ፤ የትዕግስት ድንበሩ ሲያልፍ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ተስኗችኋልን ??
የአዴፓ  አመራሮች አንድ ነገር ልንገራችሁ  አለሁ ባይ አጥተው ላደጋ የተጋለጡት የደብረ ሮሐ  የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሳይፈርሱ ፤  ጣና  እንዲህ ታምሞ ታሞ ትንፋሹ ተቋርጦ የብስ ሳይሆን  የአማራ ህዝብ ፈጥኖ እናንተን ወደ ታሪክነት ለመቀየር  ለማይቀረው የመጨረሻ አብዬት መነሳቱ አይቀሬ እየሆነ ነው።  የመጨረሻውን እድል  ብትጠቀሙበት የሚበጅ ይመስለኛል።
ግልባጭ
======
Ato Temesgen Tiruneh – ተመስገን ጥሩነህ
Amhara Communications
Amhara Prosperity Party /APP/
Amhara Mass media Agency
Asrat Media house
Bahir Dar university
Filed in: Amharic