>

"የሙሉቀን መለሰ ትዝታዎች!!!" (በዕውቀቱ ሥዩም)

“የሙሉቀን መለሰ ትዝታዎች!!!”

በዕውቀቱ ሥዩም

ከብላቴናነቴ ጀምሮ ሙሉቀን መለሰን ስወደው ኑርያለሁ። አስቴር አወቀ፣ ኤፍሬም፣ ሙሉቀን እና አበበ ተካ በዜማ ባያጣፍጡት ኖሮ የጉብዝና ወራቴ ምንኛ እጅ እጅ ይል ነበር…!
“ስለምትመኘው ነገር ተጠንቀቅ አንድ ቀን ልታገኘው ትችላለህና” ይላል ጠቢብ…!
ታድያ አንድ ቀን ራሴን ሙሉቀን መለሰ ቤት አገኘሁት። በርግጥ ያገኘሁት በልጅነቴ የማልመውን ሙሉቀንን አልነበረም፤ ሙሉቀን የወጣትነት ሥራውን ሲኮንን ነበር የደረስኩበት።
“የዘፈን ምንጭ ሰይጣን ነው” ይላል
(ነገሩ እንዲህ ከሆነ፤ የኢትዮጵያ ባህል ሚኒስትር ሰይጣን ላገራችን ኪነጥበብ ያደረገውን አስተዋጽኦ አስታውሶ ቢሸልመው ደስ ይለኛል…ሰይጣን አይሸለምም ያለው ማነው?)
ሙሌ የተራኪነት ተሰጥኦ አለው፡፡ ስለአማርኛ ዘፈን ታሪክ ሲነሣ ጠንከር ያለ ትንታኔ ያቀርባል፣ ለጊዜውም ቢሆን ዘፈን የሰይጣን መሆኑን ይረሳና በግሉ ስላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይተርካል።
በርግጥ የታዋቂ ዘፋኞችን ችሎታ ያጣጥላል። አንዱን ስሙን የማልጠቀሰውን ዘፋኝ ሣነሳበት…
“እሱ እንዲያውም መዝፈን አይደለም ዘፈን እንዲያዳምጥ እንኳ ሊፈቀድለት አይገባም” አለኝ🤭 በተለይ ጥላሁን ገሠሠን ተችቶ አያባራም…
”እሱ እኮ የጉልበት ዘፋኝ ነው” ይለዋል።
ነገሩን ማስ ማስ ሳደርገው ከጥላሁን ገሠሠ ጋር ያለው ግኑኝነት የፉክክር ብጤ ይመስላል። አልፈርድበት “ሁለት አንበሶች ባንድ ዋሻ ውስጥ አይኖሩም ” ይላል ጎርኪ።
“…ትዝ አለኝ እኔም 5ኛ ክፍል ደርሻለሁ!”
በቅርቡ ሙሌ፤ “ናፍቆት ኢትዮጵያ” ከተባለ መጽሄት ጋር ዘለግ ያለ ቃለ-መጠይቅ አድርጓል።
ከምልልሱ ውስጥ ይቺን በፈገግታ ቀንጭቤ ልሰናበት…
ናፍቆት:- ለመሆኑ እስከ ስንተኛ ክፍል ተምረሃል?
ሙሉቀን፡- ረሳሁት እስከ ሦስተኛ ክፍል የተማርኩ ይመስለኛል።
ናፍቆት፡- ድምፃዊው ጥላሁን ገሠሠ በሁለት ክፍል ይበልጥሃላ!
ሙሉቀን፡- እሱ እዚያ ደርሷል እንዴ?
ናፍቆት:– አዎ፣ የምናውቀው እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ መማሩን ነው ….
ሙሉቀን፡- እንዲያውም አሁን ትዝ አለኝ አምስተኛ ክፍል ድረስ ነው የተማርኩት…🤭🤣🤣
(ቀንጭቤው ነው እንጂ ረጅም ነበር)
 “ሀገሬ አትናፍቀኝም” 
የቀድሞው  እውቅ ዘፋኝ የአሁኑ ዘማሪ ሙሉቀን መለሰ ሰሞኑን በሰጠው ቃለ-ምልልስ ኢትዮጵያ አትናፍቀኝም በማለቱ  መስመሩን ለቀቅ ያደረገ  ዘለፋና ትችት እያስተናገደ ነው። ሙሉቀን “ሀገርህ ትናፍቅሃለች ወይ?” የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት ሰንደቅ ዓላማ ጠምጥሞ “እምዬ ሀገሬ”እያለ ማልቀስ የሚያቅተው አይመስለኝም። ያን ቢያደርግ ቢያንስ አሁን እየደረሰበት ያለው ዘለፋ ላይደርስበት እንደሚችልም አይጠፋውም። ሆኖም የሽንገላ ቃል ከማዥጎድጎድ ይልቅ እውነተኛ ስሜቱን ሳይዋሽ መናገርን መረጠ። በበኩሌ  ስሜቱን ሳያድበሰብስ  በግልጽ በመናገሩ አድንቄዋለሁ።
ሌላው “አትናፍቀኝም” ሲል ብዙ ምክንያት ሊኖረው እንደሚችል መገመትም ይቻላል።  በቀላሉ ሀገሬ -ንጹሀን- በግፈኛ ባለጊዜዎች የሚገደሉባት፣ህግ የሌለባት፣ ድሆች የሚያለቅሱባት፣ ወጣቶች ሥራ በማጣት በአጉል ሡሶች የጠፉባት…ምድር  እስከሆነች ድረስ ልትናፍቀኝ አትችልም እያለ ሊሆን ይችላል። ዞሮ ዞሮ ምክንያቱም ምንም ሆነ ምን  ሀገሬ አትናፍቀኝም በማለቱ ልንዘልፈው የምንችልበት ምንም ዐይነት የሞራል መሰረት የለንም።
እኛ እንናፍቃታለን ለምንላት ሀገራችን ግዴታችንን የምንወጣውና ፍቅራችንን የምናሳዬው በተግባርና በሥራ እንጂ ከኛ የተለዬ ሃሳብ የሰጡትን በመዝለፍ አይደለም።  አንድ የሀገር ባለውለታ  እኛ የማንወደውን አስተያዬት በመስጠቱ  ውለታው ሁሉ በዜሮ ተባዝቶ  በጤንነት መታወክ ሳቢያ ባጋጠመው ችግር ላይ መሳለቅ እጅግ ያሳዝናል፣ ያሳፍራልም።
ወንድማችን ሙሉቀን መለሰ፣ እግዚአብሔር ምህረቱን ያወርድልህ ዘንድ ጸሎታችን ነው።
Filed in: Amharic