>

ሽምግልና በኢትዮጵያ !!   (ዘመድኩን በቀለ) 

ሽምግልና በኢትዮጵያ !! 

 ዘመድኩን በቀለ 

ለመርዞ፣ ለኢትዮጵያ ካንሰሯ ለአጅሪት ህወሓት ለአሮጊቷ ጁቬ ሽምግልና መላኩን በሰማሁ ጊዜ….  
•••
ሽምግልና በኢትዮጵያ እጅግ የተከበረ ቅዱስ ተግባር ነበር። በሁሉ የሚወደድ በሁሉም የሚከበር፣ በሁሉም የሚፈራም ራሱን የቻለ አንድ ሃይማኖታዊ ክፍል የሆነ ግዙፍ ተቋምም ነበር። ከምር እጅግ ልዩ ነበር ሽምግልና በኢትዮጵያ። መንገድ የሚለቀቅለት፣ ከተቀመጥክበት ተነስተህ ለጥ ብለህ እጅ የምትነሳው ነበር የኢትዮጵያ ሽምግልና።
•••
በኢትዮጵያ ሽማግሌ የሆነ ሰው እና ለሽምግልና የደረሰ ሰው ክብሩ ከቅዱሳን ክብር እንደ አንዱም የሚቆጠር ፀጋም እንዳለው ባለ ዕድል ነበር። ሽምግልና በኢትዮጵያ የቅድስና ያህል ክብር ያለው ነበር። ሰው የአባቱን ገዳይ በፍፁም ይቅርታ ከልቡ፣ ከአንጀቱ፣ ከኩላሊቱ፣ ከሆዱ ይቅር ብሎ ያለ ቅሬታ የሚታረቀው በኢትዮጵያውያን የሽምግልና ተግባር ብቻ ነበር። ይሄ እንግዲህ ነበር ነው።
•••
የኢትዮጵያ ሽምግልና በካህናት የሚመራ፣ ተጣዮቹ ሀገረ ገዢ ከሆኑ፣ ከፍ ባለ ፖለቲካዊ ጉዳይ የተጣሉ ከሆኑ፣ ብዙ ህዝብ የሚያነካኩ፣ የሀገር ንብረት የሚያስወድሙ ከሆኑም ሽምግልናው ከበድ ይል ነበር። ለዚህ ዓይነቱ ሽምግልና ታቦቱን ከመንበሩ፣ ካህናቱ፣ ዲያቆናቱን ከየደብሩ፣ ባህታዊ መነኮሳቱን ከየገዳማቱ ይዞ መውጣትም ግድ ይልም ነበር። ሽፍታ ከሆነም ለማስታረቅ የካህን መስቀል በቂው ነበር። እናም ድሮ ሽምግልና በኢትዮጵያ የተከበረ ነበር።
•••
ለባልና ሚስት ፀብ እንኳ ዘው ተብሎ ወደ ፍርድ ቤት አይኬድም ነበር። መጀመሪያ ሽማግሌ ይግባበት ይባላል። ሽማግሌ ይየው ይባል ነበር። የንስሀ አባት ይግባበት፣  ካህኑ መስቀል ይዘው፣ በሰፈሩ አንቱ የተባሉ አረጋውያን አበው ሽማግሌዎችም ተመርጠው ተሰይመው በዚህ መልኩ ነበር መጀመሪያ የባልና የሚስት ጠብ እንኳ ለመፍታት የሚሞከረው። ከሽማግሌ ያለፈ ነገር ብቻ ነበር ወደ ፍርድ ቤት የሚያመራው። ይሄ እንግዲህ ድሮ ነው።
•••
አይደለም ለጠብ፣ ለክርክር ለትዳር ሽማግሌ የሚያስፈልገው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። አንቱ የተባሉ ሽማግሌ መርጠህ፣ የተከበሩ፣ በተግባራቸው የሚወደዱ፣ ባለ ሁለት ጠጉር ሽማግሌዎች ሰይመህ የምታገባት ሴት ቤት ልከህ ነው ሚስት እንኳ የምታገባው በኢትዮጵያውያን የሽማግሌዎች ይሁንታ ነው። ነውረኛ ከሆንክ ለአንተ ሽማግሌ።ሆኖ የሚሄድልህ አታገኝም። ለነውረኛ ሽማግሌ የሚሆን፣ መዋረድ የሚፈልግ የለም። ለነውረኛ ሽማግሌ መሆን መዋረድ ነው። ድሮ ሽማግሌ የገባበት ነገር ሁሉ ያማረ የተወደደ ነበር የሚሆው። ድሮ በኢትዮጵያ።
•••
ይሄ ባህል በሁሉም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛት የነበረ የተቀደሰ ባህል ነበር። በኦሮሞም፣ በሱማሌም፣ በአፋርም፣ በደቡብም የነበረ ባህል ነበር። ዐማራና ትግሬም ባህሉ ነበር። ሽምግልና ክቡር የተከበረ ነበር። አዎ የተከበረ ነበር። አላየህም የጋሞ ሽማግሌዎች ተንበርክከው የተቆጣ ህዝባቸውን ሲያበርዱ፣ ሲያረጋጉ። ለዚህ ነገር ሽምግልና ይግባበት፣ ኧረ ሽማግሌ እንላክ፣ ሽማግሌ ልኬበት እኮ ነበር፣ ሽማግሌ ላክበት፣ ሽማግሌ እንላክ እንዴ? ሽማግሌ ሆናችሁ ሂዱልኝ። በሽምግልና የሚፈታ እኮ ነው። ኧረ የሽማግሌ ያለህ? ጨምሩበት። ሽማግሌ በኢትዮጵያ እንዲህ የተከበረ ቅዱስ ተግባር ነበር።
•••
ሰይጣኗ፣ የሰይጣን ዲቃላዋ፣ የሰይጣን ቁራጯ፣ ዕጣ አውጥታ የራሷን ታጋዮች የሰው የወንድሞቿን ሥጋ አርዳ በመብላት በቁሟ ልቡሳነ ሥጋ አጋንንት ሆና በኢትዮጵያ መንበር ላይ የተቀመጠችው ህወሓት የተባለች ነቀርሳ ርግምን የሆነች ተንከሲስ ስልጣን ከያዘች በኋላ ግን የሽምግልና ወጉ ፈረሰ። ክብሩም ተዋረደ። በዘመነ ህውሐት በፈንጂ፣ በድማሚት ከተናዱ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ዋነኛው የኢትዮጵያ ቅዱሱ የሽምግልና ተግባር ነበር።  የኢትዮጵያ ሙሉ ቅድስናዋ የሆነው ጎደፈው በዘመነ ህወሓት ነበር።
•••
የኢትዮጵያን ቅዱስ፣ ክቡር የሽምግልናን አሴት አጎደፈችው፣ አረከሰችውም። ሽምግልና ክብሩን እንዲያጣ፣ ሽማግሌ እንዳይታመን፣ እንዲናቅ ሆን ብላ ሥራዬ ብላ፣ ይሁነኝ ብላ በአቋም ሠራችበት። ሃይማኖት ስለሌላት፣ ማቴሪያሊስት፣ የአልባንያ ኮሚኒስት ስለሆነች ሃይማኖትንም፣ ሃይማኖተኞችንም አዋርዳ መሳቂያ መሳላቂያ አደረገቻቸው። በዘመነ ህውሓት የኢትዮጵያ ሽምግልና ተናቀ፣ ተዋረደ። ተጠላም።
•••
ህወሓት መጀመሪያ ያደረገችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ካህናትን ማረድ ነበር። በትግራይ ከእሁድ ዕለተ ሰንበት ቅዳሴ በኋላ ዐውደ ምህረት ላይ ቆመው ተአምረ ማርያም የሚያነቡ አረጋውያን ካህናትን በህዝቡ ሁሉ ፊት በጥይት በመረሸን ነበር ሽማግሌንና ሽማግሌ ካህናትን ማጥፋት የጀመረችው። ይህቺ አረመኔ። የተረገመች።
•••
በመቀጠል ትግሬን በመብላት የፈረጠመችው ህወሓት መላ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረች በኋላ በተለይ በወልቃይትና በጠገዴ፣ በራያ፣ በመላ ኢትዮጵያም ታሪክ አዋቂ ሽማግሌዎችን፣ አረጋውያን የሰፈር አድባር የሆኑ ሽማግሌዎችን እየመረጠች ነበር አርዳ የጨረሰችው። በተለይ ዐማራን ፈጀችው። ኦሮሞንም እንዲሁ አረደችው።
•••
ጦርነት ገጥማ ያንገረገሯትን፣ ወጥረው ተወግተው ምላሽ የሰጧትን የዐማራ፣ የኦሮሞ፣ የአፋርና የሱማሌ ኢትዮጵያውያን ተቀቃዋሚዎቿንም በሙሉ በማታምንበት፣ ይሁነኝ ብላ በዕቅድ እንዲረክስ ባደረገችው የተከበረው ኢትዮጵያዊው የሽምግልና መንገድ በመሄድ፣ ካህን፣ ሼክ፣ ታቦትና መስቀል በመላክ ነበር ተቃዋሚዎቿን ያንበረከከችው።
•••
የሚያሳዝነው ነገር በሽምግልና፣ በአማላጅነት ወደ ሰላማዊ ኑሮ የተመለሱ፣ የካህን መስቀልና ታቦት አምነው፣ የሀገር ሽማግሌም አምነው ከማኅበረሰቡ የተቀላቀሉ፣ ነፍጣቸውን የጣሉ ጀግኖችን አንዳንዱን ዕለቱን፣ ሌሎችን ደግሞ አውላ፣ አሳድራ፣ ገድላቸዋለች። በዚህም ምክንያት ሽምግልናን እንዲረክስ አድርጋለች። እንዲናቅ አድርጋለች። እንዲያውም በሰሜን ጎንደር የነበሩ ታጋይ ፋኖዎች ቢመራቸው ጊዜ ለሟቹ ሊቀጳጳስ ለብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ “ ሁለተኛ ሽምግልና ብላችሁ ብትመጡ እናንተ ላይ ነው የምንተኩሰው በማለት እስኪመልሷቸው ድረስ ነበር ያስመረቻቸው። ሃይማኖት አልባዋ ህወሓት ሃይማኖተኛውን ህዝብ ተጫወተችበት። በመጨረሻ እነ ደብረ ጽዮን፣ ስብሃት፣ ስዩምና ዓባይ ፀሐዮ ካባ ደርበው፣ ጋቢ ለብሰው አክሱም ጽዮን ስላያችኋቸው አትሸወዱ። አረመኔዎች ናቸው።
•••
በረከታቸው ይደርብንና ብፁዕነታቸው አቡነ ኤልሳዕም በመጨረሻ ወያኔን አፈር ከደቼ ያበላውን ዐመጽ እንዲያስቆሙ፣ ለፋኖዎቹ ታቦትም ቢሆን ተሸክመው እንዲያረጋጉ ሲጠየቁ “ አላደርገውም። እኛ እናንተን አምነን በረሃ ወርደን፣ ስንቱን ጀግና በመስቀል ገዝተን ካስገባነው በኋላ ገደላችሁት፣ አሰራችሁት፣ ደበደባችሁት፣ በጉልበት ያቃቷችሁን በእኛ የግዝት ቃል ካመጣንላችሁ በኋላ ረሽናችሁ ጨረሳችሁ። እናም ሁለተኛ አልሄድም በማለታቸው ነው የጎንደሩ አብዮት ጎምርቶ ህወሓትን ከመላ ኢትዮጵያ ጠራርጎ መቀሌ የወሸቃት። ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ከዚያ ወዲህ ታመሙ። አረፉም። በረከታቸው ይደርብን።
•••
በ1997 የቅንጅት አመራሮችን ያደነዘዘችው በሽምግልና ሰበብ ነው። አይሁዳዊውን ፕሮፌሰር ይስሀቅን፣ ጠፍጥፋ የሠራችውን ፓስተር ዳንኤልን፣ የዋሁን ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ጨምራ ቅንጅቶችን በነጭ ወረቀት ላይ አስፈርማ የሠራቻቸውን ጉድ ሁላችንም የምናስታውሰው ነገር ነው። ህወሓት የኢትዮጵያን ሽማግሌና የሽምግልና ተግባር
ያዋረደች አዋራጅ ናት ናት። መድኃኔዓለም አባቴ ያዋርዳት። የሽምግልና ያለህም ያሰኛት። ለህወሓት ፍርድ እንጂ ሽምግልና አያስፈልጋትም። ህዝቡ ኢትዮጵያዊ ነው።ህወሓት ግን የሰይጣን ድቃይ ሰይጣን ናት። ህወሓት ሽማግሌ አያስፈልጋትም። ቂሊንጦ። አሜን።
•••
በኦሮሞም ዘንድ ልክ እንደ ዐማራው ሁሉ በህወሓት ሽምግልና ስም ተታሎ የተረሸነውን ዜጋ ቤት ይቁጠረው። በዐማራ በድኑን ብአዴንን፣ በኦሮሚያ ሙትቻውን ሆድ አደር ኦሆዴድን እንደ ኮንዶም በመጠቀም ስንቱን የኦሮሞ ጀግና በሽምግልና ሰበብ ጠርታ ስታበቃ በገበያ መሃል እንደሰቀለችው፣ በጥይትም እንደ ደበደበችው ሃገር ምስክር ነው። እናም ህወሓት ክፉ ናት። እኔ እስክሞት ድረስ ነፍሴ አምርራ ትጠላታለች። ቅድስት ሀገሬን በብዙ መልኩ ያረከሰቸ ርኩስ ስለሆነች ነፍሴ አጥብቃ ትፀየፋታለች። ለዚህም ነው የተከበረው የኦሮሞ የሽምግልና ባሕል አሁን ላይ እንዲህ ረክሶ የሚታየው። ኦነግና ኦህዴድ ስንቴ በሬ አርደው በሽማግሌ ፊት ታረቁ? ስንቴ ደም ጠጡ፣ ደም ተቀቡ፣ በአንድ ቅል ወተት ጠጡ፣ ለምለም ቄጤማ ቆርጠው ተመራረቁ? ግን ሽምግልናን ህወሓት ስላረከሰችው አልተሳካም። አይሳካምም። ህወሓት ካልተቀበረች የኢትዮጵያ የሽምግልና ክብር አይመለስም። ያው እየተባላህ ትኖራለህ። የኦነግ ሸኔ የኦሮሞን አባት ሱሪ አስወልቆ እንደሴት ይደፍራል ይልሃል የOBN ዘገባ። ይሄ ሁሉ ጭካኔ እኮ የመርዟ የህወሓት ውርስ ነው።
•••
አሁን ህወሓት አዚሟ ተገፏል። አስማቷ ሁሉ ከሽፏል። ክላሽ የታጠቀ ባዶ ሆዱን የሚንጠራወዝ አቅመቢስ ወታደርና ከኢትዮጵያ መንግሥት ግምጃ ቤት የዘረፈችው ክላሽና ቦንብ የታጠቀ የራበው ሚኒሻ ብቻ ነው ያላት። ዋናዋን ህወሓት ኤድስ፣ ስኳር፣ ሪህና ቂጥኝ፣ ጨብጥ አድቅቋታል። አብዛኛዎቹ የህወሓት ጎምቱዎች የጠሉት፣ ያረከሱት የሽምግልና ዘመን ላይ ደርሰዋል። ደርሰው ግን ቀሪ ዘመናቸውን በሰቀቀን እንደ ቀበሮ በመቀሌ ዋሻ እንዲኖሩ ነው ታቦተ ጽዮን የፈረደችባቸው። ዳይፐራቸውን መቀየሪያ ጊዜ እስኪያጡ ድረስ ነው ተደብቀው ያሉት። መጨረሻችሁን ያሳየኝ። እንደ ሳዳም፣ እንደ ጋዳፊ አድርጎ ያሳየኝ። እናንት የሀገር ነቀርሳዎች። ይንቀላችሁ።
•••
እኔ ሽምግልናን ባልጠላም ለህወሓት ግን ሽምግልና አያስፈልጋትም ባይ ነኝ። ለህወሓት የሚያስፈልጋት ጧ ነበር። ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ማስወገድ። ልክ እንደ ጀርመን ናዚ በሕግ ስሟን መደመሰስ። ስሟን ያነሳ፣ መታሰቢያዋን ያወሳ ሁሉ ውግዝ ከመ አርዮስ ርኩስ ከመ ዲያብሎስ ብሎ ማውገዝ ነበር።  እንዲያ ነበር ነበር ለህወሓት አሮጌ ጅብ የሚያስፈልገው። ይሄ ደግሞ በራሱ በትግራይ ህዝብ የሚፈጸም ተግባር ነው። ህወሓትን ገድሎ፣ ቆፍሮ የሚቀብራት ራሱ የትግራይ ህዝብ ነው። የሚበላው የሚያጣ፣ የተራበ ህዝብ መሪዎቹን ይበላል አይደል ያለው ራሱ ተርቦ ራሱን ሳይበላ በፊት። አይ ዶክተር መረራ። ነፍስ ይማር።
•••
አንድ ነገር ግን ልብ ማለት ያስፈልጋል። መቐለ ለሄዱት ለሽማግሌዎቹም ቢነገራቸው የምለውና የምሰጣቸው አንድ ምክረ ሃሳብም አለኝ። ሽምግልናው ይቀጥል፣ የሽምግልናው ውጤት ግን መሆን አለበት የምለው ከተቻለ ብዙ ጥፋትና ውድመት ሳይከሰት አጅሬ ሰይጤ ህወሓት ራሷን በራሷ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ እንድታጠፋ ቢያግባቧት ጥሩ ነው ባይ ነኝ። ራሷን በራሷ እንድታስወግድ ቢመክሯት ጥሩ ነው። እኔ ከሞትክ ሰርዶ አይብቀል ማለቷን እንድታቆም ቢደረግም መልካም ነው። ህወሓት ካንሰር ናት፣ ዲያብሎስን በጭካኔና በተንኮል የምትበልጥ አረመኔ ናት። ዲያብሎስ ህወሓትን የሚበልጣት በዕድሜ ብቻ ነው። በሌላው ትቦንሰዋለች። ህወሓት መቼም ዳግም በዳይፐር እየተግማማች ኢትዮጵያን አትገዛም። አከተመ።
•••
ሌሎች የትግራይ ልጆችን ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ማምጣት ነው የሚያስፈልገው። የታቦተ ጽዮንን ልጆች ማምጣት ነው የሚያስፈልገው እንጂ ህወሓትን መለማመጥ አስፈላጊ አይደለም።
•••
በሌላ በኩል ይሄ የትግራይ ሽምግልና ሌላም ነገር ያሳየናል። ዘርፈህም ሆነ ሠርተህ በገንዘብ፣ በኢኮኖሚ፣ በጠብመንጃ ከፈረጠምክ ጡት ቆርጠህም፣ ጥፍር ነቅለህም፣ ወንድም ሴትም ደፍረህም፣ መርከብ አውሮጵላን ሰርቀህም፣ ህዝብን ዜጎችን ረሽነህም ቢሆን አቅም ካለህ ትከበራለህ። ለመከበር ደግሞ ጉልበት ወሳኝ ነው ማለት ነው። ዐማራ ያጣው ይሄንን ነው። የሚያሳዝነኝም ለዚያ ነው። እንዲያ ባይሆን ኖሮ ዐማራ ላይ ገሌው ኢዜማ እንኳ ባልተንበጫበጨ ነበር። ልደቱ ሽምግልና ነው የሚሻለው ሲል ባንዳ የሚል፣ ብልጽግና አዎሽምግልና ነው የሚሻለን ሲል ጀግና የሚለው በቀቀኑ የበሬዉ ቆለ* ይወድቅልኛል ብሎ ከዐቢይ ስር የሚያቶሰቱሰው ኢዜማ እንኳን ባልቀለደበት ነበር። ታዲያ መሬው እንደ ህወሓት አውሮጵላን ሙሉ ሽማግሌ እንዲላክብህ ከፈለክ፦
• የጎጥ አክቲቪስትነትህን ተው።
• ጎጃም ሸዋ፣ ወሎ ጎንደር መባባልህን ተው።
• ኢትዮጵያን መዳረሻህ አድርገህ አንድ ዐማራ ላይ ወጥረህ ሥራ።
• ድግስና ሆድ አያንበርክክህ።
• ቀሚስ ባየህበት አትደፋ። ለሀጭህን አታዝረክርክ።
• ብር እንደ አሞሌ ጨው መላስ አትውደድ።
• ቅድሚያ ለማንነትህ ትጋ። ለእሱም ሥራ።
• አትመቀኝ፣ አትልከስከስ፣ አትወረድ፣ አትለያይ፣ አንድ ሁን። የውስጥ ችግርህን ይዘህ ወደ ፌስቡክ አትንጦልጦል። እልህህን በልክ አድርግ። ለምስኪኑ ገበሬ አባትህ እዘን። አንተ አውሮጳ አሜሪካ ስላለህ ያን ምስኪን አታስወጋው፣ አታስንቀው፣ አትከፋፍለው። በእውቀት በጥበብ ተመራ። እንደ አባቶችህ ሃይማኖተኛ ሁን። ጥገኛ፣ ፈሪ፣ ገሌ፣ ተለማማጭ አትሁን። እንደ ወንድ ቆፍጠን በል። ቀበቶህን አጥብቅ። አትንሿከክ፣ ሾካካ የቡና ላይ ሃሜተኛ አትምሰል። ያዝ ለቅቅ፣ አገም ጠቀም አትሁን። ተጠራራ፣ ምከር። ወስን። ያኔ አውሮጵላን ሙሉ ሽማግሌ ይላክልሃል። እንደ ህወሓት በመግለጫ ብቻ እያስፈራራህም ተከብረህ ትኖራለህ። ህወሓት ግንዱን መቁረጥ የቀረው ዛፍ ማለት ነው። እንደዚያ ነው።
•••
እኔ የምለው ቄስና መስቀል፣ የሀገር ሽማግሌ ተልኮበት በስምምነት በዕርቅ የተመለሰው መቶ አለቃ ማስረሻ የሚባለው የጎዣም ዐማራን ብአዴን ከምን አደረሰችው? አይ ሽምግልና !!
•••
ለማንኛውም ኢትዮጵያ ምንም አትሆንም። ህወሓትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ጠላቶች በሙሉ ግን ምንም የሚሆኑበት ጊዜ ብዙም ሩቅ አይደለም። ከጥቂት መንገራገጭ በኋላ ሁሉም ነገር ይስተካከላል። ኢትዮጵያ ትነሣለች። ጠላቶቿ አፈር ከደቼ ይልሳሉ። ይኸው ነው።
•••
ሻሎም !  ሰላም  !
ሰኔ 9/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።
Filed in: Amharic