>
5:23 pm - Thursday February 2, 2023

ጃዋር በትዊተር ገጹ ሲጠበቅ የነበረን ጉድ አጋለጠ!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ጃዋር በትዊተር ገጹ ሲጠበቅ የነበረን ጉድ አጋለጠ!!!

አሰፋ ሀይሉ

(…እስኪ ረጋ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ! መቶ ሃያ ሚሊየን ኢትዮጵያውያን… ወደ ምን እየገባን ነው? ወደ ሀገር አልባነት ወይስ…)
«የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል» በሚል አቅጣጫን ጠቋሚ በሆነ ቃል – ከ50 በላይ ብሄሮችን (ጎሳዎችን፣ ነገዶችን ወይም የዘውጌ ስብስቦችን) በአንድ ላይ ጨፍልቆ – የደቡብ ክልል የሚባል በዓለም ታሪክ ላይም በኢትዮጵያ ታሪክ ላይም ተሰምቶ የማይታወቅ የአቦሰጡኝ ክልል የፈጠረው የወያኔ-ኢህአዴግ ህገመንግሥት – በመጪው ጥቂት ጊዜያት ውስጥ – የክልል እንሁን ጥያቄ በሚያቀርቡ እና ቁጥራቸው ከ15- 20 በሚደርሱ ‹‹ብሔሮች›› ህጋዊ ጥያቄ የተነሣ – ከባድ ፈተና ውስጥ እንደሚገባና – “ህገመንግሥቱ” የግድ የእነዚህን ህጋዊ ብሔሮች ህጋዊ መብት ለማስተናገድ ሲባል እንደሚሻሻል – ይህም ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሚነሱ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ጋር ሲደማመር – የሀገሪቱን ክልሎች ቁጥር አሁን ካሉት ክልሎች በላይ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሻቅበው በዚሁ በፌስቡክ ገጽ በጥልቅ ጥናት ላይ ከተመሰረተ አንድ የሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ጠቋሚ ትንተና ላይ ተቀንጭቦ መቅረቡ ይታወሳል፡፡
ይህም ሂደት ከቀጠለ – የወደፊቱን የወያኔ ክልሎች ሽንሸና (የክልሎች ‹‹አሩሳይዜሽን›› ወይም ‹‹ባልካናይዜሽን››) በብዛትና በጥራት የምናይበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ለማወቅ የግድ ነቢይ መሆን አይጠይቅም፡፡
የወያኔ-ኢህአዴግ ህገመንግሥት አስጠባቂ ባለአደራዎቹ ስማቸውን ብልጽግና በሚል ስም ቀይረው ቢመጡም ያላቸው አማራጭ – ወይ እነዚህን ህጋዊ የክልልነት ጥያቄዎች በተከመደው ስልታቸው በጉልበት ለማፈን መሞከር ነው – አሊያ ደግሞ በህጋዊ መንገድ መብትን አክብረው ክልልነትን በሰልፍ ተሰድሮ ለሚጠብቀው ወፈሰማይ የሀገሪቱ ጎሳዎች ማደል ነው! ጉልበት መጠቀሙ – በአንድ ጊዜ 50 እና 60 አውደ ግንባሮችን በመፍጠር – የእስስቱን የወያኔ-ኢህአዴግ ህገመንግሥት ባለአደራዎች ዕድሜ ባጭር ይቀጨዋል! መብትን ለጠያቂዎቹ ማጎናፀፍ ደግሞ በአደራ የተቀበሉትን ህገመንግሥታዊ ሥርዓትና የፓርቲ አሰላለፍ እንዳልነበር አድርጎ የልጆች መጫወቻ ደብተር ወይም የጨረባ ተዝካር ያደርገዋል – ተብሎ ይገመታል!
ስለዚህ አሁን በሥልጣን ኮርቻ ላይ ተንጠላጥሎ ያለው እስስቱ የወያኔ ባለአደራ መንግሥት ያለው አማራጭ – በኮሮናም አሳቦ፣ በሌላም ምድራዊም ሰማያዊም ሰበብ አመካኝቶ – ጊዜ መግዛት ብቻ ነው፡፡ ወይ ጉልበት እስኪያወጣ – ወይ አጢኖ ትርፍና ኪሳራውን አሰላስሎ ጥያቄዎቹን ለመቀበልና ለመበወዝ ጊዜን አጥብቆ ይሻል፡፡ ጊዜ በአንዳች ተዓምር ለዓመታት ለተብሰከሰኩት ጥያቄዎች ከሰማይ መልሥ ይዞ ይወርድና ይመልሰው ይመስል!
ዛሬ የኦሮሞው አክራሪ እስላም መሪ ጃዋር ሲራጅ መሀመድ በትዊተር ገጹ በማስረጃ አስደግፎ ይፋ ያደረገው መረጃ – በደቡብ ክልል ምክርቤት በሚባለው ‹‹የክልል ፓርላማ›› ውስጥ ያሉት 38 የወላይታ ብሔር ተወካዮች – ራሱን የቻለ የወላይታ ክልል እንዲመሠረት እስስቱ የወያኔ ወራሽ መንግሥት ካልፈቀደልን – ከፓርላማ አባልነታችን ራሳችንን እናገላለን የሚል ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡
ጃዋር ሲራጅ መሀመድ ይሄንን ማስጠንቀቂያ – ልክ እውነት ከዛሬ ጀምሮ በገዛ ፈቃዳችን ከደቡብ ክልል ምክርቤት ለቅቀናል ያሉ በማስመሰል ትንሽ ቸኩሎም፣ አጋኖም ቢያቀርበውም – እውነታው ግን – እነዚህ ሰዎች – ራሱን የቻለ የወላይታ ክልል ካልተሰጣቸው – የዛቱትን ማድረግ ብቻም ሳይሆን – አካባቢውን ከሆነው በላይ የትርምስ ቀጣና ማድረጋቸው አይቀርም!!
ሲዳማ የተባለው ብሔር ተመሳሳይ የክልልነት ጥያቄ አቅርቦ በሂደት ላይ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ኮሮና መጣና እነ እስስቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀው ምንም ዓይነት ምርጫ እንዳይደረግ ወሰኑ እንጂ – የሲዳማው ጥያቄ ያለቀለት ጥያቄ ነበር፡፡ አሁን ወላይታ ተከትሏል፡፡ ይሄም ምንም ገጭ-ረጭ የሌለበት – እና ግልጽ መልስ የሚያሻው – ግልጽ ጥያቄ ነው፡፡
ይሄ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጎሳና በዘር፣ በቋንቋና በጎጥ ለመሸንሸንና የአንድን ሀገር ህዝብ እንደዜጋ አንድ እንዳይሆን በአናሳ ጎጠኞች የተፈበረከ የኢፌዲሪ ህገመንግሥት የተባለ አጥፍቶ ጠፊ ሰነድ የሀገሪቱ የበላይ ህግ ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ – ገና ከ40 በላይ ክልሎችን ማየታችን አይቀርም!
ያ ብቻ አይደለም ችግሩ – ህገመንግሥቱ ለዓመታት አስከፊ የጥላቻ ዘረኝነትንና የእርስ በእርስ ጠብን ሲዘራበት የቆየውን የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስበርስ ሳያባላና ደም ሳያፋስስ እንዲህ በቀላሉ ጦሱን ጥምቡሳሱን ይዞ የሚቀደድ ሰነድ አይመስልም በዚህ አኳኋኑ!
መፍራት ያንን ነው! አሁን ጦሩን በመያዝና በማባበል በማዕከላዊ ሥልጣን ኮርቻ ላይ የተፈናጠጠው እስስታዊ ኃይል – ህገመንግሥቱን ጠባቂና የደም አደራ ተረካቢ ነኝ ባይ መሆኑ ሳይዘነጋ – ህገመንግሥቱ ሀገሪቱን በመሸንሸን እስኪጠናቀቅ፣ አሊያም ሀገሪቱን አኪልዳማ በማድረግ ሳይጠፋ በፊት – የሚያደርሰውን ሀገራዊ ትርምስና ፍርጃ – አንድዬ ብቻ ይመልሰው ማለት ነው፡፡
ይህን በህገመንግሥቱ የቆረበ እስስት ሃይል የሚገዳደርም – በጎጠኞች ከተሰመረለት የጎጥ መስመር ወጥቶ ስለ አጠቃላይ ሀገር አዲስ ትልም ይዞ ህዝብን የሚያደራጅ አካል በጠፋበት በአሁኑ ሰዓት – ዕለት ዕለት እየሆነ ያለው ነገር – እጅግ አስጊ እየሆነ መምጣቱን – ዓይኑን ያልጨፈነና ማገናዘብ የሚችል ሰው ሁሉ የሚረዳው ጉዳይ ነው፡፡ ኮሮናን አሳብቦ ሀገሪቱን በጦሩ ጉልበት አስገብራለሁ ብሎ የተነሳው እስስታዊ ኃይልም ሆነ – አሁን ተቃዋሚና ጠብ-ደጋሽ ሆኖ የቀረበው የአስከፊው ሥርዓት ዋነኛ ጠንሳሾችና ወጣኞች – ሀገሪቱን ወደምን እያንደረደሯት እንዳሉ አስተዋይ የሆነ ዜጋ ሁሉ ጠንቅቆ ሊገነዘብና ለሚሆነው ነገር ዝግጁ ሆኖ መጠባበቅ ያለበት አሳሳቢ ጊዜ ላይ ነን፡፡
ወይ የሀገሪቱን የጎሣ ሥርዓት እንደ ሀገር እና እንደ ዜጋ ለመለወጥ መንቀሳቀስ አሊያም – የሚሆነውን በሩቅም በመሐልም ሆኖ መመልከት የወቅቱ መፍትሄ የሌለው አማራጭ ሆኗል፡፡ በጥቂት ጽንፈኛ ሃይሎች ወከባና ቁጥጥር ሥር በዋለ ሀገራዊ የፖለቲካ አውድ ላይ – ዝም ያለው አብዛኛው ህዝብ – ‹‹ዘ ሳይለንት ማጆሪቲ›› – እለት እለት የሚቀያየረውን እስስታዊ ፖለቲካችንን – እና እስስታዊ መንግሥታችንን – እና እስስታዊ ተለዋዋጭ ሀገራዊ ትኩሳት – ዳር ቆሞ በዝምታ መመልከቱን የመረጠ ይመስላል!
እንግዲህ – ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቃታል ብለን እናምናለንና… የሰዎች እና የዜጎች ቁርጠኛ ዘላቂ መፍትሄ ከምድራችን ማህፀን እስኪወጣ ድረስ… በዚህ አስከፊ ወቅት … ፈጣሪ ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ ዘንድ ከልብ ከመመኘት በቀር ማድረግ የምንችለው አንዳች ነገር የለም!
ይህ የገዛ ሀገራቸውን መጻዒ ዕታ ፈንታ በዝምታ የሚመለከቱ አቅመቢስ ኢትዮጵያውያን የቁጭት ድምጽ ነው፡፡
This is the solemn cry of the helpless, the exhausted, the puzzled, the politically marginalized silent majority of Ethiopians!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic