>
5:16 pm - Tuesday May 24, 4935

....እንግዲህስ ብሞትም....!!!" (ያሬድ ሹመቴ)

….እንግዲህስ ብሞትም….!!!”

ያሬድ ሹመቴ


በቀድመ የድል ታሪክህ ኮርተህ ጠላትህን ከመናቅህ በፊት ይህንን አንንብ። በዓድዋ ድል ዘመቻ ወቅት ታላቁ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በክተት አዋጃቸው ላይ “… እንግዲህስ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞም እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም። አሁንም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም…” የሚል ሀሳብ አንጓ ሆኖ እናገኘዋለን።

*     *        *

* ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ስለምን በአዋጁ ላይ ይህንን ሀሳብ ተጠቀሙ? ብለን ስንጠይቅ ይህንን መልስ እናገኛለን።

* የኢትዮጵያ አንድነት መስራቹ ጀግናው አፄ ቴውድሮስ በመጨረሻው የህይወታቸው ዘመን በመቅደላ ከናፔር ጦር ጋር ተፋጠው በመጨረሻም ዋና የሚሏቸውን ቀኝ እጃቸውን (ፊታውራሪ ገብርዬን) ካጡ በኋላ “እጄን ለነጭ አሳልፌ ሰጥቼ፣ ሀገሬን አላዋርዳትም” በማለት ራሳቸውን በአንድ ጥይት ማጥፋታቸውን በማሰብ።

* ለኢትዮጵያ አንድነት ከአፄ ቴውድሮስ እና ከአፄ ተክለ ጊዮርጊስ ቀጥሎ የበኩላቸውን ከፍተኛ ድርሻ የተወጡት እና የአንድነትን እርሾ ያስቀጠሉት ታላቁ ንጉሰ ነገስት አፄ ዮሐንስ 4ኛ በፀረ ቅኝ አገዛዝ ዘመቻ ላይ ክንዳቸውን አሳርፈው የድልን ችቦ አቀጣጠሉ። በመጨረሻው ዘመቻቸው ከደርቡሽ ጋር ተፋልመው አሸናፊነትን እጃቸው ቢያደርጉም በአንዲት ጥይት ህይወታቸው አጥተው በጠላት ጦር አንገታቸውን የተቀሉ መሆኑን በማሰብ።

* በ1888 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ለመውረር የተሰማራውን የጣልያንን ጦር ከጄኔራል ጋንዶልፊ ቀጥሎ የመራው ጄኔራል ባራቴሪ ዳግማዊ አፄ ምኒልክን “ከእርሶ ቀደም የነበሩ መሪዎች መጨረሻ ምን እንደነበር ያስታውሱ” በማለት በቀላሉ ተስፋ እንዲቆርጡ ለማስፈራራት ሁለት ምክንያቶች ድፍረት ሰጥተውት ነበር።

* የመጀመሪያው ድፍረቱ ምንጭ በሰገነይቲ (አሁን በኤርትራ ግዛት ውስጥ የሚገኝ ቦታ) ጣልያንን የከዱት ኢትዮጵያዊው (የአካለ ጉዛይ ተወላጅ) ደጃች ባህታ ሀጎስ ጋር ማጆር ቶዜሊ የተባለ የጣሊያን ጦር አዛዥ ተፋልሞ ጊዜያዊ ድል አግኝቶ ነበር። በጦርነቱ ህይወታቸውን ያጡትን ደጃች ባህታን አስክሬን መሬት ለመሬት እያስጎተተ ባለድል መሆኑን ማብሰሩ ጣልያን ድረስ ተሰምቶ የተፈጠረው ከፍተኛ የባለድልነት ስሜት ለባራቴሪ የአሸናፊነት ስነልቦናው እንዲጦዝ አድርጎት ነበር።

* ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ባራቴሪ በአንደኛው ደብዳቤ ላይ ለአፄ ምኒልክ ከፃፈው መልዕክት ተነስተን ስንረዳ “ከእርስዎ ቀደም የነበሩ ንጉሶች መጨረሻ ምን እንደሆነ አስበው፤ ሊዋጉን ባይሞክሩ ጥሩ ነው። የነገስታቱን መጨረሻ ያስታውሱ” የሚል ይዘት ያለው መልዕክት መላኩ የአፄ ምኒልክ መጨረሻ እንደ አፄ ቴውድሮስ አልያም እንደ አፄ ዮሐንስ እንደሚሆን መዛቱን ልብ እንላለን።

* ባራቴሪ በሮም ፓርላማ ቀርቦ የጦርነቱን በጀት ባስፀደቀበት ዕለት “ምኒልክን በቀፎ ከትቼ ይዤው እመጣለሁ” በማለት ያደረገው የወኔ ንግግር በፓርላማው አባላት የጀግና ጭንጨባን በህዝቡም የጀብደኛ ሞገስ አቀዳጅቶት ወደ ጦርነት መግባቱን እናስተውላለን።

* በአንፃሩ አፄ ምኒልክ ሀገራቸው ኢትዮጵያ የሚገጥማትን ወረራ በበቂ ሁኔታ ለመመከት የሚያስችላትን ብቃት እስክታጎለብት ድረስ ለ7 አመታት የጣልያንን ወራሪ መንግስት በዲፕሎማሲያዊ ብልሐት እያባበሉ አቆዩት።

* ለ7 አመታት ያህል የጦር መሳሪያ ሲያከማቹ፤ የስለላ መዋቅራቸውን ሲያሰፉ፤ በሀገር ውስጥ የነበሩ የእርስ በርስ ሽኩቻዎችን በባለድልነት እያሸነፉ ጠላቶቻቸው የነበሩትን ወደ ወዳጅነት ቀይረው መልሰው እየሾሙ፤ የኢኮኖሚ ሳንካዎቻቸውን እየፈቱ በረቱ።

* ይህም ከሆነ በኋላ ቁጥሩ ከጣልያን ጦር የሚበልጥ ወታደር በየአዝማቹ አደራጁ። ሁሉም ወታደር በነፍስ ወከብ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጠቀ። አይቀሬው የዘመቻ ክተት አዋጅም ታወጀ።

* ታዲያ አፄ ምኒልክ በቀደመ የሀገራቸው ጀብድ ሳይኩራሩ እንደ ንጉሰ ነገስትነታቸው የቀደሟቸው መሪዎች (የአፄ ቴውድሮስና የአፄ ዮሐንስን) የሞት ጽዋ ለመቅመስ፣ ለመሞት ጭምር መወሰናቸውን “ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም…” ሲሉ በመግለጥ፤ ነገር ግን በፈጣሪ ጥበቃ እንደሚያምኑ “እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም። አሁንም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም” ሲሉ በመግለጥ ጠላታቸውን አግንነው አክብደው በማየት ከልባቸው ተዘጋጁ።

* ይህ ትልቅ የአሸናፊነት ግምት ለወራሪው የተሰጠው የኢትዮጵያ እና የጣልያን ጦርነት፣ በ6 ሰዓታት ውስጥ ብቻ በዓድዋ ላይ በኢትዮጵያ 3 ለባዶ አሸናፊነት (በሌላ ጽሑፍ 3 ለባዶን እመለስበታለሁ) ተጠናቀቀ። ድሉም ከዓለም ጉልህ ታሪኮች መሐል ተመደበ። ለአፍሪቃም የድል ምልክት ሆነ።

* እዚህ ላይ ኢትዮጵያ በዓድዋ ያገኘችው ታላቅ ድል ምስጢሮች ፦ በቂ ዝግጅት ማድረግ፤ ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት፤ የላቀ የአመራር ጥበብ፤ የህዝቡ ለአንድ አላማ መስዋዕትነት ለመክፈል አምኖ መሰለፍ፤ ጥበብ የታከለበት ፖለቲካዊ ዲፕሎማሲ ጠንካራ የግዛት አንድነትና ለጠላት በተሰጠ የላቀ ግምት መሆኑን ልብ ይሏል።

* ለአርባ አመታት በዓድዋ ድል ስንኩራራ ነገር ግን ምስጢሩን አጥንተን ይበልጥ ከመዘጋጀት ይልቅ ከአቅማችን የላቀው የአሸናፊነት ስነልቦና ብቻውን በማይጨው ጦርነት ባለድል ሊያደርገን አልቻለም። ኢትዮጵያንም በ6 ሰዓታት ውስጥ ሊያልቅ የሚችልን ጦርነት ለ5 አመታት በጣልያን ወረራ ሙከራ ውስጥ እንድንቆይ አድርጎ ዋጋ አስከፍሎናል።

* በተቃራኒው ደግሞ በግብጽ ጦር እና በኢትዮጵያ መካከል፤ በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግስት የንጉሰነገስቱ የአንድነት ጦር፤ በጉንደትና በጉራእ በተደረጉ አውደ ውጊያዎች አፄ ዮሐንስ በታላቅ ጀብድ ሰራዊታቸውን መርተው ታላቅ ድል ተጎናጽፈዋል። እኛ ይህንን አንረሳም።

* ነገር ግን የማይጨውን ሽንፈታችንን መርምረን አናጠናውም።

* በአንጻሩ ደግሞ ግብጾች በርካታ የጦርነት ታሪካቸው የኪሳራ ቢሆንም በኦቶማን ኢምፓየር ጊዜ የተቀዳጇቸውን አነስተኛ ድሎች እና ነፃነታቸውን ካገኙ በኋላ በነበሯቸው የውጊያ ምልልሶች ያገኟቸውን መጠነኛ ድሎች አጉልተው ለዜጎቻቸው ሲተርኩ ለሽንፈት ታሪኮቻቸው እምብዛም ቦታ ሰጥተው ሲናገሩ አይደመጥም። በጦር ኃይላቸው መደርጀት ከዓለም ኃያላን ሀገሮች በተለይም ከአሜሪካ ጋር ባላቸው ከእስራኤል ድጋፍ ጋር የተቆራኘ ግንኙነት መተማመናቸው ግልጽ ነው።

* ወኔን ማጎልበት የህዝብን ቁጭትና ተሳትፎን ማዳበር የተገባ ሆኖ በሀገር አንድነት፤ በውስጥ ግዛት ሰላምና መረጋጋት፤ በኢኮኖሚ መደርጀት፤ በዲፕሎማሲ ጥረት መብለጥ፤ የሰላ የመሪነት ብቃት እና በጦር ኃይል ምከታ የላቀ ዝግጁነት ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ያላትን አሁናዊ መረጃ ተመርኩዘን ከፍተኛ ስራ መስራት ይጠበቅብናል።

* እነደ ህዝብ ለሀገራችን ሞትን በፀጋ የመቀበል ዝግጁነታችን መቼም ቢሆን የሚታጠፍ አይደለም። ለዚህ ዝግጁነት ባያስፈልገውም የእርስ በርስ ቁርሾዎች ትኩረት እናዳይነፍጉን እና ኃይላችንን እንዳያዳክም ከፍተኛ ስራ መስራት ይጠበቅብናል። ከፍተኛ ክፍተት በሚታይበት የዲፕሎማሲው ዘርፍም አመርቂ ስራም እንዲሁ።

* በዚህ ዘመን እንደ አፄ ዮሐንስ አንገቱን ለመስጠት የማይሳሳ፤ እንደ አፄ ቴውድሮስ ለሀገር ውርደትን እንዳይመጣ ህይወቱን አሳልሮ የሚሰጥ፤ በተለይም እንደ አፄ ምኒልክ ብልሐትን ከቅድመ ዝግጅት፤ ጥበብን ከአቅም መደርጀት ጋር አቀናጅቶ ህዝቡን ከፊት በህብረት የሚመራ ቆራጥ፣ ጥንቁቅ፣ ብልህ፣ አርቆ አሳቢ፣ ከግብታዊነት የፀዳ የሐገር ፍቅር ስሜቱ ከመሪነት ብቃቱ ጋር የተዋሐዱለት ሰው ያስፈልገናል።

* ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን አጎራባቾቿን

አስተባብራ የቀጠናው ተጽእኖ ፈጣሪነትን ማማ ለመቆናጠጥ፤ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ ዘርፍ ቀዳሚ ገናናነትን ለማረጋገጥ በወሳኝ ሰዓት ላይ ትገኛለች። ስለዚህም ጠላትን አክብዶ በማየት በዝግጅት ራስን ማደርጀት እና ከተራ ፉከራ ወርዶ መሬት የረገጠ ስራ መስራት እና እንደ እምዬ ምኒልክ “ሙያ በልብ ነው” ብሎ መዘጋጀት የተገባ ነው።

አዎ ሙያ በልብ ነው። ድልዋኒክሙ ንበሩ!!

Filed in: Amharic