>

ኢትዮጵያ ውስጥ  ከዚህ ሁሉ  በደል አንዱ እንኳ  ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ  ምን  ሊፈጠር ይችል ነበር? (ጣይቱ ብጡል)

ኢትዮጵያ ውስጥ  ከዚህ ሁሉ  በደል አንዱ እንኳ  ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ  ምን  ሊፈጠር ይችል ነበር?

ጣይቱ ብጡል

ኢትዮጵያ በተለይ ከነመለስ  ዜናዊ  አገዛዝ ወዲህ  በዘር/ብሔር/ጎሳ  ፖለቲካ ተተብትባ  እንዳታንሰራራ ይልቁንም ልጆቹአ  በመነታረክ ተጠምደው  ሀገራቸውን እንዳያሳድጉ  ሁነዋል::  ያውም ደሞ  አንዱ  ዘር በዳይ ሌላው  ተበዳይ  ነበር  የሚል  ፍብረካ/ድርሰት  ተደርሶ ሲደጋገም እውነት ለማስመሰል እየተሞከረበት  ያለውን  ሁኔታ ለታዘበ በእውነት ልብ ሰባሪ ነው :: በነጭ  አንገዛም ብለው  በባዶ እግራቸው   ከዳር  እስከዳር ተጉዘው  በባዶ እጃቸውና  በተራ መሳሪያ  ጠላትን  አባረው  ባርነትን እንዳናይ ያደረጉንን ነፃነት አውራሽ  አያቶቻችንን  በማመስገን ፈንታ  በሌሉበት ዘመን ማዋረድ  ምን አይነት ድንቁርና  እንደሆነ ለመግለፅ  ቃላት አይገኝለትም:;
እርግጥ  ነው  መነሻ ሃሳቡ  በእነዝያው  ቅኝ ግዛቱ ባልተሳካላቸው  ነጮች  የተጠነሰሰ  እኛን ወደ ኋላ  እንዲጎትት የተደረገ  የስልጣኔ ዘመን ያልሻረው  ነቀርሳ ሆኖ መቅረቱ ያሳዝናል:; ሌላው ቢቀር  ሀገሪቷን  ዙሪያዋን  የከበቧት ከሩቅም ከቅርብም  ያሉ ጠላቶች  የውስጥ ችግራችንን የሚያባብሱ እና  በዚያውም ተጠቃሚ ለመሆን  እንደሚሰሩ ተረድቶ  መነታረክ  ቢቆም እንዴት በታደልን የትስ በደረስን!
ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውም ዘር ለየትኛውም በባርነት  ተገዝቶ እንደማያውቅ  ልባችን እያወቀው  ከአሜሪካን ሀገር  በባርነት  ከተሰቃዩት  ጥቁሮች ጋር  ለማመሳሰል መሞከር  ከማስተዛዘቡ  ባሻገር  በእርግጥ  ጨቅላ  ወጣቶችን  ያስታል:;  ልጆቻችንን  የውሸት ታሪክ ባናስተምራቸው  ምናለበት!?
የትኛውም  ሰው በዘሩ ትምህርት ቤት አልተከለከለም:: የትኛውም ዘር በዘሩ ተለይቶ ምንም ጥቃት አልደረሰበትም:: ግማሽ ምዕተ  ዓመት በምድር ላይ እንደኖረ ሰው  ትምህርት ቤት  ስንማር  የተደበላለቀ  ዘር ያለው  ስብጥር  ግን ደሞ ስለ ዘር/ብሔር ማንም ማንንም  የማይጠይቅበት ጊዜ ነበር  ያሳለፍነው:  የዛሬዎቹም ዘረኞች  የተማሩት  ሀገሪቱ  እና ቤተሰባቸው በቻሉት መጠን ነበር:; ሰው በብርታቱና  በቤተሰቡ  ጥረት  ያሰበበት  የሚደርስበት ሁኔታ እንደ ነበር ነው እያየን ያደግነው:;
ታድያ ለምን ይዋሻል?
ባርነት ምን ይመስላል? ለሚለው  በተለይ ሰሞኑን  በአሜሪካን ሀገር በተፈጠረው  ዘግናኝ የፖሊስ  አባል የወንጀል ድርጊት ሳቢያ  የድሮዎቹ  የባርነት ማስረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ:;
ከዚህ በታች የሚታዩት  ፎቶዎች  አንዱ ጥቁር ሴት  የነጭ  ሕፃንን  ጡት  ስታጠባ የሚያሳይ ሲሆን  ሁለተኛው  ደግሞ ጥቁር ተማሪ  ዩኒቨርሲቲ  ለመግባት ቢያመለክት  ጥቁር ስለሆንክ  አልተፈቀደልህም:: አንቀበልህም የሚል መልስ  የተሰጠበት ደብዳቤ ነው::
የነጮቹ  ሚስቶች  ጡታቸውን ለልጆቻቸው ካጠቡ ውበቱን ይቀንሳል ይላላል  ብለው ስለሚያስቡ አያጠቡም ነበር:; ጥቁሮቹ  ደግሞ ልጆቻቸውን ስለሚያጠቡ  ጥሩ ሆነው ሲያድጉ  ነጮቹ  የቀኑ ነበር:;  ቀንተውም አልቀሩ  ዘዴ ፈጥረው  ልጆቻቸውን  በባርያዎቻቸው  ጡት  ለማሳደግ  ያቅዳሉ:: እናም  ባርያዎቻቸውን ያው በነሱው ልጆች ወይ ባሎች  ተደፍረው እንዲያረግዙ ያደርጉና  ጥቁሩ  ልጅ  ከእናቱ  ይነጠቅ  እና  አንድም እንዲጣል  ወይም ሌላ ቆሻሻ እየበላ  እንዲያድግ ይደረጋል;; ዝርዝሩን  ከታች  በፎቶ  መልክ  ካለው  ፅሁፍ  ማንበብ ትችላላችሁ::
ጥቁሮች  እንዲማሩ አይፈቀድላቸውም ነበር::: በኋላም  ሲማሩ  ለብቻቸው  ትምህርት  ቤት  እንደነገሩ ተከፍቶ  ተለይተው እንዲማሩ ተደረጉ:: እንግዲህ  ከእነዚያ ጥቁሮች  አንዱ  ተማሪ  በጥረቱ  ወደ  ደረሰበት  ደረጃ  እንዳይደርስ ነው  የተደረገው:;
እነዚያ በአፍሪካ  ሃገራቸው  ውስጥ ነፃነታቸውን የሚያስከብርላቸው መሪ አጥተው  ተሸጠው  በሰው ሀገር  ፍዳቸውን  ያዩት ወገኖች በከፈሉት መስዋዕትነት  ዛሬ  የእኛ ልጆች  በዓለምም ሆነ  በአሜሪካን  ሀገር  ታላላቅ  በሚባሉት  ዩኒቨርስቲዎች   ውስጥ  ውድድሩን  እስከቻሉ ድረስ በሩ  ተከፍቶ ይቆያቸዋል::  ኢትዮጵያ ግን  የኋሊት  እንድትሄድ  እየተደረገች  ነው :: ተያይዞ  የቁልቁሊት ለመንጎድ  መራቆት  ምን ይሉታል?!
ልብ በሉ – ኢትዮጵያ ውስጥ  ከዚህ ከሁለቱ  አንዱ በደል ተደርጎ ቢሆን ኖሮ  ምን  ሊፈጠር ይችል ነበር?
በግድ  ባርያ ነበርን  ብሎ  እዬዬ  ማለት ደግም አይደል  አትዋሹ!
Filed in: Amharic