>
5:13 pm - Monday April 19, 4641

" ኦሮምያ በተባለው ክልል በተዋህዶ ልጆች ላይ  መንግስት መራሹ እስር፣ ማፈናቀሉና እንግልቱ አስከፊ ደረጃ ደርሷል!!!  " (ዋሲሁን ያልማ)

” ኦሮምያ በተባለው ክልል በተዋህዶ ልጆች ላይ  መንግስት መራሹ እስር፣ ማፈናቀሉና እንግልቱ አስከፊ ደረጃ ደርሷል!!!  “

ዋሲሁን ያልማ

* በቁም የተኛችሁ እረኛ ነኝ ባዮች የእናንተ መተኛት የቅድስት ቤተክርስቲያን አጥር እንዲነቀነቅ ልጆቿ እንዲደፈሩ አድርጋችኃልና ከእንቅልፋችሁ ነቅታችሁ የተበተኑትን በጎችን ሰብስባችሁ፡ ቆራጥ ውሳኔ አሳልፋችሁ እብሪተኛውን አስፈፃሚ አካል አስተንፍሳችሁ በጎቻችሁን ከሰው በላ አራዊት ታደጉን!!!
ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤውን ግንቦት 06/2012 ባጠናቀቀበት ወቅት በኮረና ምክንያት የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲከፈቱ እና ተገቢው ጥንቃቄ እየተደረገ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጥ የወሰነ መሆኑ ይታወቃል። የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ገዥ በመሆኑ በመላው አገሪቱ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ላይ በወጥነት መተግበር ሲኖርበት በአብዛኛው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በሞላ ጎደል በውሳኔው መሰረት እየከፈቱ ለምመናን አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም በተወሰኑ ክልሎች ላይ ግን መንፈሳዊ አገልግሎቱ ለምመናን እንደተቋረጠ  ወራትን አስቆጥራል። በተለይ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትና ምዕመናን የችግሩ ገፍ ቀማሽ ሆኖ ቀጥለዋል።
የክልሉ መዋቅር በፀረ ቤተክርስቲያን አቀንቃኞችና የኦርቶዶሳዊያን ጠላቶች ከላይ እስከ ታች የተዋቀረ በመሆኑ በተዋህዶ ልጆች ላይ የሚደርሰው ጭቆና አድሎና መከራ እያዳፈኑ ዘመናትን ተሻግሮዋል። ዛሬም በኮረና ተሸሽገው በገፍ ፖሊስ አሰማርተው ድንበር ከጠላት የሚጠብቅ ይመስል በቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ አሰልፈው ልጆቿን እያሳደዱና እያሰሩ፡ አገልጋዮቿንም አንድ አስቀዳሽ ምዕመን አስገብተው ከተገኙ ለእስርና ለእንግልት በማድረግ በማን አለብኝነት በግልፅ ቀጥለዋል።
ወዳጄ የሚገርመው ደግሞ በየገቢያው ያለውን ትርምስ፡ በየጫት ተራው ያለውን ግፊያ፡ በየትንስፓርቱ ያለውን ግርግር፡ በየመስራቤቱ ያለውን መጨናነቅ መቀነስና ማስቆምን በዝምታ ያለፈው የኦሮምያ ፖሊስ አላማው ምን እንደሆነ ከድንዛዜ የነቃ፡ ከዘርና ቋንቋ ትብታብ የወጣ ሰው ይገባዋል። በጂማ ከወራት በፊት  ከአንድ ምዕመን የተጀመረው የእስር ዘመቻ ቀጥሎ ዲያቆናትን ካህናትንና ደብር አስተዳዳሪዎችን አዳርሶ ዛሬ ላይ ደግሞ የሀገረ ስብከቱ ስራስኪያጅ የሆኑትን መላከ ሰላም ተስፋ ሚካኤልን አሰፋ በማሰር ዘመቻው ተጧጥፎዋል። ምክንያቱ ደግሞ ከቅዱስ ሲኖዶስ የመጣውን ደብዳቤ መሰረት በማድረግ ለአጥቢያዎች የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ደብዳቤ በመጻፋቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰሃል ተብለው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቆአል። በዚህ ከቀጠለ ቀጣዩ ደግሞ አቡነ እስጢፋኖስ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
በዞኑ የሚገኙት አድባራትና ገዳማት መንፈሳዊ አገልግሎታቸው ለምዕመናኑ በማቋረጣቸው ምክንያት አገልጋዮች ለከፋ ችግርና መከራ ውስጥ የወደቁ ሲሆን ምዕመናን ደግሞ አድሎዓዊ አሰራሩ ደም እንባ እያነቡ ነው። በተለይ ደግሞ በገጠሩ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ አገልጋዮች በፋይናስ እጥረትና መስመር የሳቱ ግፎች በመብዛታቸው ምክንያት የእየተሰደዱ፡ ምዕመናንም በሚደርስባቸው አድሎዓዊ አሰራርና ጫና እየተበተኑ ሙሉ በሙሉ ለመዘጋት ጫፍ ላይ ደርሰዋል።
አሁን ላይ እየሆነ ያለው ነገር ከአእምሮ በላይ ሆኖዋል። በጎችን የሚጠብቁ እረኞች በቁማቸው ተኝተው ቢቀሰቀሱም አልሰማም ብለዋል። አስፈፃሚ የመንግስት አካልም የእረኛው መተኛት ተመችቶት በእብሪትነቱ ቀጥሎዋል። የቅድስት ቤተክርስቲያንን ህመም የሚያክም፡ የልጆቿን ስቃይ እስራትና ሞት በየቦታው ሲፈፀም የሚያስቆምና ደጀን የሚሆን ሀይል በመጥፋቱ የተነሳ በተዋህዶ ልጆች ላይ ግፍና መከራው መልኩን እየቀየረ ልብን እያደማ እየተጓዘ ነው።
ግፈኞች ግፍን ፍሩ ኃጢያትን አትስሩ። ህግን አክብራ ስርዓትን ይዛ፡ የምታገለግለውን ቅድስት ቤተክርስቲያንና ልጆቿ ላይ ማቶከር ከሀዲድ የወጣ አእምሮዋዊ አስተሳሰባችሁን በጊዜ ልታስተካክሉ ይገባል። ዛሬም እጅና እግራችሁ ተይዞ ፍርደ ገምድል ሆናችሁ ንፁኃን የተዋህዶ ልጆች የምታሳድዱ፡ በህግ ማስከበር ሰበብ ታሪካዊ አድሎዓዊ ስህተት የምትፈፅሙ ግፈኞች ጥንቃቄ አድርጉ። የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለምና ያጠለቃችሁትን የአራዊት ቆዶ አውልቃችሁ የሰው ልብስ ለብሳችሁ ወደ አእምሮዓችሁ ተመለሱ። ከዚህም የባሰ መቅሰፍት በላያችሁ ላይ ሳይወርድባችሁ በአስቸኳይ ያሰራችሁትን የተዋህዶ ልጆች ፍቱ። የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አክብራችሁ የቅድስት ቤተክርስቲያን ደጆች ይከፈቱ መስመር አትሳቱ።
በቁም የተኛችሁ እረኛ ነኝ ባዮች የእናንተ መተኛት የቅድስት ቤተክርስቲያን አጥር እንዲነቀነቅ ልጆቿ እንዲደፈሩ አድርጋችኃልና ከእንቅልፋችሁ ነቅታች፡ የተበተኑትን በጎች ሰብስባችሁ፡ ቆራጥ ውሳኔ አሳርፋችሁ እብሪተኛውን አስፈፃሚ አካል አተንፍሳችሁ፡ በጎቻችሁን ከሰው በላ አራዊት ታደጉ። ያለበለዚያ ከታሪክ ተወቃሽነት፡ ከሰውም ከእግዚአብሔርም ፍርድ አታመልጡምና እውነተኛ የተዋህዶ አርበኛ ሁኑ።
        ፍትህ በጂማ ለታሰሩ ለሚንገላቱ የተዋህዶ ልጆች!
Filed in: Amharic