>
5:13 pm - Sunday April 20, 8628

ጠቅላዩ ነገር...! የአስመሳዮች ሀገር...!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ጠቅላዩ ነገር…! የአስመሳዮች ሀገር…!!!

አሰፋ ሀይሉ

የቄሮ ቦዘኔዎች እየተነሱ ሠላማዊ ዜጎችን በጨፈጨፉ ቁጥር ከጠቅላዩ አፍ የማትጠፋ ፉከራም ቀረርቶም ወይ ማስፈራሪያም የምትመስል አባባል አለች፡- ‹‹ጦርነት ከተጀመረ ማንንም ለይቶ እንደማይተው፣ እሳት ከተለኮሰ ማንም ከእሳቱ ሊተርፍ እንደማይችል… ይሄ ማሳያ ነው!›› የምትል፡፡ አንዳንዴም ሲያሰኘው በቁሙ የለመደበትን የብሔር ስብጥር ስታቲስቲክስ በዜጎች ሬሳ ላይ እያዘረዘረ ለማቅረብ ይፈልጋል፡፡ የእነ እስክንድር ነጋ የሠለጠነ የኢትዮጵያዊነት የመብት ፖለቲካ ደሙን ሲያፈላው ደሞ – ምላሱ ሳት ይለውና – ‹‹እኔን ከሥልጣን ለማውረድ ቢሞከር፣ እዚሁ አዲሳባ ላይ፣ በአንድ ቀን አንድ መቶ ሺህ ሰው ታርዶ ያድራል!›› የሚል አራጆች ከጀርባዬ መኖራቸውን አትርሱ የሚል ቀረርቶ ለመንፋት ይሞክራል፡፡
ከዚህ ሁሉ መልዕክት ጀርባ – በጠቅላዩ አዕምሮ የሚመላለሰው አጀንዳ ምንድነው? ፍርሃቱና ማስፈራሪያውስ ምንድነው? መልዕክቶቹስ እንዲደርሱለት የሚፈልገው ለማን ነው? ምንን በተግባር አስደግፎ ለማስረዳት እየሞከረ ነው? በትክክል ምን ሊለን እየሞከረ ነው ያለው? የቄሮ ስትሪት ጋንግስተርስ ሰቅጣጭ ተግባራት ሰቅጥጦት ‹‹በፍፁም አይደገምም!›› ብሎ ቆርጦ ከመነሳት ይልቅ ለምንድነው ይሄ ሰውዬ እነዚህን ሰቅጣጭ ተግባራት ለፖለቲካው ‹ጀስቲፊኬሽን› ወይም ‹ዲሞንስትሬሽን› አድርጎ ለማቅረብ የሚሞክረው?
ልብ ብሎ ላየው ይሄ ሰውዬ (ጠቅላዩ) – ‹‹እኔ ከተነካሁ ኦሮሚያ በሙሉ ይነሳል፣ ነፍጠኛ ይታረዳል፣ ሪፈረንደም አካሂደን እንገነጠላለን፣ ያን የሚያስቆመን ኃይል የለም፣ አሊያ እዚች ሀገር ውስጥ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ይፈጠራል፣ ኢትዮጵያ የምትባለው ተረት ተረት በይፋ ያከትምላታል..›› እያለ ‹‹አራጆችን ከጀርባዬ አሰልፌያለሁ ትነኩኝና አያለሁ›› እያለ በያገኘው አጋጣሚ ከሚዘባበተው የቄሮው አዝማች ጃዋር ሲራጅ መሐመድ ጋር – በተለየ የትወና መድረክ ላይ የተለየን ሚና ይዞ እየተጫወተ ከመሆኑ በቀር – ምንም የስነልቦናና ዓለማዊ አመለካከት አሊያም የዓላማ ልዩነትም የለውም፡፡
ያኛው (ጃዋር) ‹‹ኢትዮጵያ የምትባለውን ተረት ተረት…›› እያለ ስንት ሚሊየን ህዝቦችን ንቆ በድፍረት ሲቀደድ…. ይሄኛው (ጠቅላዩ) ደግሞ፡- ‹‹ያው ልመና ነው ሥራዬ፣ ያው ያለ ልመና አንኖርም፣ ስለዚህ መለመኔን እቀጥላለሁ፣ ዓለምን እየዞርኩ ያላችሁን ስጡን እያልኩ እለምናለሁ፣ ደሞ የመለመን ፀጋ አለኝ፣ ለምኜ ይሳካልኛል፣ ሥራዬን መሥራቴን አጠናክሬ እቀጥላለሁ…›› እያለ የዓለም ሕዝብ በሚከታተለው ሚዲያ አደባባይ ላይ ወጥቶ በሀገራችን ያላግጣል! የሚገርመኝ ይሄ ሰውዬ ይቺ ለማኝ ሀገር… እያለ፣ የለማኝ ሀገር መሪ ብቸኛ ሥራ በልመና ህዝቡን ማስተዳደር ነው እያለ፣ ሀገሪቱን እንዲህ በአደባባይ ጥንብ እርኩሷን እያወጣ ለማሳየት የፈለገው ለማን ነው? እኛን ለማኞች ለሚሉንና እርዳታ አንቀበልም ለሚሉት ለሻዕቢያዎቹ ነው? ሀገራችንን ተረት ተረት ለሚሉት ቄሮዎቹ ነው? ኦነጎቹ ነው? እኛን ለማሳነስና ለማጥላላት፣ ለመበታተንና ለማዳከም ለዘመናት ሲዳክሩ ለኖሩት እስላማዊ ጎረቤቶቻችን ነው? ወይስ አማራውን (ነፍጠኛውን) አሊያም ትግሬውን (ወያኔውን) – የምትፎክሩላት ሀገር ይቺው ለማኝ ሀገር ናት! ለማለት ነው? ለማን ነው የአንድ ሀገር መሪነት ኃላፊነት የተሰጠው ሰው ይቺን ሀገር ለማጣጣልና ለማስጣጣት የሚፈልገው?
የጠቅላዩ ስላቆች እኮ በዚህ ብቻ የሚያበቁ አይደሉም፡፡ የውጪ መሪዎች በመጡ ቁጥር ‹‹ዘመናዊ ነኝ›› ለማለት እንደሚሞክሩ ፋራዎች – እያዞጠዞጠ መኪና ማሽከርከሩን ለማሳወቅ ከሀገር መሪነት ክብር ወርዶ በሹፌርነት ለማገልገል ተፍ ተፍ ሲል ሲታይ አንገት ያስደፋል፡፡ የትኛው የረከሰ ሀገር መሪ ነው – ራሱን ለሌሎች ሀገር መሪዎች በሹፍርና ተግባር ወርዶ ሲቅበዘበዝ የሚታየው? ከዚህ ጤንነቱ ከሚያጠራጥር ሰው በቀር የየትም ሀገር መሪ ይህን አይሞክረውም! ለሌላ አይደለም – ለሀገር ክብር ሲባል ብቻ! ይሄን ያለ፣ እና ዘመናዊ ነኝ የሚለውን የህጻን ልጅ ምኞቱን ለማሳየት የሚተጋ መሪ – በዓለማቀፍ መድረክ የኖቤል የሠላም ሽልማት ተሸለም ሲባል – ባለችው አጭር ደቂቃ ውስጥ ከስንት ነገሮች ሁሉ መርጦ – መብራትና ውሃ ከሌለባት የኢትዮጵያ ትንሽዬ የገጠር መንደር ነው የመጣሁት – በማለት ጨዋነት በሚመስል አነጋገር – ሀገራችን በዚህ በሠለጠነ ዘመን ላይ የቱን ያህል ኋላ ቀር መሆኗን ለዓለም ሕዝብ ለማሳጣት ሲፍጨረጨር ይታያል፡፡
አዎ ለማኝ ነን፡፡ አዎ መብራትና ንፁህ ውሃ የለንም፡፡ አዎ ድሆች ነን፡፡ ችግሩ ግን ሀገርህን ተሸክመህ እንድትመራ ስትታጭ – እነዚህን ለመቀየር እንድትሰራ እንጂ – እንደ ቄሮ አዝማቾች ባልደረቦችህ – እንደ ኢትዮጵያዊና እንደ ሀገር በሆንነውና በደረስንበት የቁልቁለት ጥግ ላይ በዓለም ፊት እንድትሳለቅ አይደለም፡፡
ሀገሪቱ ውጥንቅጧ ወጥቶ፣ ህገወጥነትና ውንብድና በያንዳንዱ የሀገሪቱ ጎዳናዎች ላይ ተስፋፍቶ፣ ባንዱ የተጀመረው ደም መፋሰስ ወደሌላው እየተሰራጨ የሀገሪቱ ፖለቲካ ከድጡ ወደማጡ እየተሸጋገረ ባይኑ እያየ፣ ኦሮሚያ የሚባለው ገና የወደፊት ተልዕኳቸው ምን እንደሆነ ጊዜ የሚያሳየንን ሚኒሻዎች በመንግሥት ባጀት እያሰለጠነና የጦር መሣሪያ እያስታጠቀ ተዋጊዎችን ሲያመርት ባይኑ እያየና እያገዘ፣ በያቅጣጫው በሀገሪቱ የታጠቁ ኃይሎች ጡንቻቸውን ከማፈርጠም አልፈው ወታደራዊ ትርዒት እስከማሳየት እየደረሱ እያየ – ሀገርን በህግና በሥርዓት ሥር አውሎ (ቢያንስ እየሞከረ) እንዲመራ ከፍተኛና አስጨናቂ ኃላፊነት የሚጠበቅበት ጠቅላዩ ግን – የሚዲያ መዓት ሰብስቦ የችግኝ ተከላና የእጅ መታጠብ ትያትሩን ለመተወን ጥረት ያደርጋል፡፡ የጤንነት አይመስለኝም፡፡ ወይም ከፍ ያለ ንቀት ለሀገሪቱ ያደረበት፣ አሊያም የሆነ ድብቅ አጀንዳ ያለው፣ አሊያም እጅግ ከህጻን የወረደ ጮርቃ የአስተሳሰብ ብስለት ኖሮት የተገኘ መሪ ካልሆነ በቀር – ሀገሪቱ በእሳት ተያይዛ እየተንገበገበች – የችግኝ ተከላ ድራማን አይተውንም፣ ካልጠፋ ቦታ የኮራ የደራውን መስቀል አደባባይ አስፈርሶ የመዋኛ ግንባታ አያከናውንም፡፡
በስንት ችግር የተከበበች ሀገርን እንዲመራ ከባድ ኃላፊነትን በሚጠይቅ አሳሳቢ ወቅት ሥልጣን ላይ የወጣ ግለሰብ ሆኖ ሳለ ‹‹የፓርላማ አባላት እባካችሁ ወደቦሌ መኖሪያችሁ ስትሄዱ አበባ የሚነቅሉትን እንድትጠቁሙ፣ የፍትህ አካላት የአበባ ችግኝ የሚያወድሙትን ተከታትላችሁ ለህግ እንድታቀርቡ አደራ እላለሁ…›› እያለ ይዘባርቃል፡፡ ሰውየው አንድም የጤና መቃወስ ደርሶበታል አሊያም በብስለት ደረጃው ሲበዛ እንጭጭ ህጻን ነው ማለት ነው፣ አሊያም በሀገሪቱ የፍትህና የመንግሥት ተቋማት ላይ በድፍረት እያፌዘ የሚገኝ የሆነ ሠይጣናዊ አጀንዳውን እያስፈጸመ ያለ ሰው ነው፡፡ እንጂ የዓለም ህዝብ ሊሰማው በሚችለው የተከበረ የፓርላማ ስብሰባ ላይ – ሀገር በስንት ችግር ተውጣ – ይሄ በትልቅ አጀንዳነት ቀርቦ አደራ የሚባልበት ጉዳይ ሆኖ አይደለም፡፡ የሰውየውን እያንዳንዱን ማስፈራሪያና የሚንዘረዘርባቸውን ስስ ጉዳዮች ሆነ ብሎ ለተከታተለውና ስነልቦናውን ለመረዳት ለሞከረ ሰው ስለ ሰውየው የሚረዳቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
ምሁሩ ኖአም ቾምስኪ አንድ ስለሠከረ ሰውና ስለተሳከረ ፖሊሲ የሚሰጠው ምሳሌ ነበረ፡፡ ሰውየው በጭለማ ቀኙን የመንገድ ጠርዝ ይዞ እየሄደ በኪሱ የያዛቸው የቤት ቁልፎች ድንገት ከመንገዱ ዳር ይዘረገፉበታል፡፡ ችግሩ ደግሞ በቀኙ ጠርዝ ላይ የመንገድ መብራት የለም፡፡ ድቅድቅ ያለ ጨለማ ነው፡፡ ይሄንን የተገነዘበው ሰውዬ ያደረገው ነገር – ቁልፉ በተዘረገፈበት አቅጣጫ መፈለጉን ትቶ – በዚያኛው በመንገዱ ተቃራኒ ጠርዝ ሄዶ ቁልፉን መፈለግ ነበረ፡፡ ኋላ አንድ የጭለማ መንገደኛ ያገኘውና ይጠይቀዋል፡፡ ምን እየሠራህ ነው? – ቁልፎች ጠፍተውብኝ ነው፡፡ የቱጋ ነው የጣልካቸው? – በዚያ በኩል ነው፡፡ ታዲያ አንተ በዚህኛው በኩል የምትፈልጋቸው ለምንድነው? – መብራት ያለው በዚህኛው በኩል ስለሆነ፡፡ እንዴ!? ብሎ ክው ጠያቂው፡፡
የጠቅላዩንም ሥራዎች ደጋግሞ ላያቸው እንደዚያ የጭለማ ፈላጊ ሰውዬ ይመስላሉ፡፡ ሀገሪቱ በአሁን ወቅት ልትፈታቸው የሚገቧት ፈታኝ ወቅታዊ ችግሮች ሌላ! ሰውየው የተጠመደባቸው ዋነኛ ድርጊቶች ሌላ! እስካፍንጫቸው የታጠቁ – እና የመንግሥትን ኃይል የሚገዳደሩ የጎሳ ሠራዊቶች ሀገሪቱ ላይ ይርመሰመሳሉ – ጠቅላዩ – ባሰኘው የንቀትና የአሽሙር ስም ሲጠራቸውም ይሰማል አልፎ አልፎ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ሲሰራ የሚታየው ግን – የችግኝ ተከላ ዘመቻ ነው፡፡ ገና ለገና ቀለለኝ ተብሎ – ቁልፉ ባልጠፋበት አቅጣጫ ላይ መብራቱ በርቶልኛል ተብሎ – ስንት የሀገርንና የህዝብን ጊዜ፣ ጉልበት፣ ሀብት፣ የትኩረት አቅጣጫ፣ ወዘተ በማባከን ላይ ተሰማርቶ ነው የምናገኘው!
የጠቅላዩ የምሁርነትና የብስለት አድማስ ‹‹ነኝ›› ብሎ ካቀረበው ዱክትርና ጋር በፍፁም አይሄድም፡፡ ‹‹ነኝ›› ብሎ ከሚቀርበው ከፍ ያለ የሚሊቴሪ ማዕረግ ጋር ፈጽሞ አብሮ አይሄድም፡፡ ‹‹ነኝ›› ብሎ ከሚቀርበው የቴክኖሎጂ ምጥቀትና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መሪነት ጋር በፍጹም አብሮ አይሄድም፡፡ ነኝ ብሎ ከሚቀርበው የፖለቲካ ልምድ ጋር ፈጽሞ አብሮ አይሄድም፡፡
እስቲ ትንሽ ፋታ ሰጥተን በእርጋታ እናስበው? ለመሆኑ ጠቅላዩ መብራትና ውሃ በሌለበት ገጠር አድጎ – በስንት ዓመቱ ትምህርት ቤት ገባ? እስከ ስንተኛ ክፍል ተማረ? ከዚያስ በስንት ዓመቱ ወደ ሚሊቴሪ (ውትድርና) ተቀላቀለ? ስንት ዓመትስ በሚሊቴሪ አገለገለ? በሚሊቴሪ ውስጥ የደረሰበት የውትድርና ማዕረግ ምንድን ነበር? መቼስ ነው ከሚሊቴሪ ሥራው አቋርጦ 12ኛ ክፍልን ወይም 10ኛ ክፍልን የጨረሰው? መቼ ነው ማይክሮ ሊንክ የግል ኮሌጅ – ኮምፒተር ሳይንስ ሊማር የገባው? ስንት ዓመት ፈጀበት? ሲማርስ ከሚሊቴሪ ግልጋሎቱ ከተሰናበተ ምን ሥራ እየሠራ ነበር? በዚያ የማይክሮሊንክ ዕውቀቱ ነው የኢንሳ መስራች ለመሆን የበቃው? ከዚያ በኋላስ ምን ተማረ? መቼ? የት? ለምን ያህል ጊዜ? ከዚያ የማስተርስ ዲግሪውን ለመማር ምን ያህል ጊዜ ፈጀበት? ሥራውን እየሰራ ነው የተማረው? የዶክትሬት ዲግሪውንስ? ከየትኞቹ ተቋማት ነው ያገኘው? የግል ትምህርቱን ሲከታተል – የመንግሥት ኃላፊነቱስ ምን ነበር? ከሚሊቴሪው ጋር የነበረው ቁርኝት?
ብዙው የሰውየው ነገር አያሳምንም፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር የተዛነቀ ነው፡፡ ብዙዎቹ ሰውየው ‹‹ነኝ›› እያለ የሚያቀርባቸው ነገሮች – ገና በጥልቀት መመርመር ያለባቸው ይመስላል፡፡ ለምሳሌ የውትድርና ህይወቱ የተቋረጠው የ10 አለቃ ወታደር እያለ እንደነበረ ብዙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኋላ የሚሠራበት ‹‹ኢንሳ›› የተባለ በአብዛኛው ከወያኔ ታማኝ ቤተሰብ ልጆች የተመለመለው የቴክኖሎጂ ጆሮጠቢ ተቋም ከሲቪል ተቋምነት ወደ ሚሊቴሪ ተቋምነት እንዲዛወርና በወታደራዊ የወያኔ ጄኔራል እንዲመራ ሲደረግ – የኢንሳ ኃላፊዎች ማዕረግም ከሲቪል ወደ ወታደራዊ ማዕረግ እንዲቀየር ተደረገ፡፡ በዚህ ሂደት ቀድሞ ከ10 አለቅነት ከውትድርና ተሰናብቶ ማይክሮሊንክ የግል ኮሌጅ የተማረው አብይ አህመድ – ባለው የኃላፊነት ልክ ይመጥነዋል በሚል – ባንዴ የሻለቅነት ማዕረግ ተሰጠው፡፡
የሲቪል ሥራን ለሚሠራ ሰው (ተዋጊ ላልሆነ ሰው) እንዴት የሚሊቴሪ ማዕረግ ይሰጣል – ብሎ ለሚጠይቅ – በወታደራዊ ተቋማት ውስጥ የተለያየ የሲቪል የመሰሉ ሥራዎችን የሚሰሩ ነገር ግን ወታደራዊ ማዕረግ ያላቸው ብዙ የሰው ኃይል መኖሩን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ሌላ ቀርቶ ስፖርተኞችና ሯጮች እስከ ኮሎኔል ማዕረግ የሚሰጣቸው በተመሳሳይ መልኩ ነው፡፡ በውትድርናም ሆነ በማይክሮሊንክ ኮሌጅ ቆይታው በወቅቱ ትክክለኛ ስሙ – ‹‹አብይ›› ሳይሆን ‹‹አብዮት›› የነበረው የአሁኑ ጠቅላይ ግን ከ10 አለቅነት ማዕረግ በአንዴ ወደ ሻለቅነት ማዕረግ የተደረገለትን የማዕረግ ዕድገት አንሶብኛል ብሎ ቅሬታውን ማመልከቱን ማስረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ምክንያቱስ?
ምክንያቱ ‹‹እኔ ሚሊቴሪ በነበርኩ ጊዜ አብረውኝ ተራ ወታደር የነበሩ የእኔ ዙር ምልምሎች በአሁን ወቅት የኮሎኔልነት ማዕረግ ላይ ደርሰው፣ እኔ ከእነሱ ያነሰ ማዕረግ እንዴት ይሰጠኛል፣ ስለዚህ የኮሎኔልነት ማዕረግ ሊሰጠኝ ይገባል›› የሚል የማዕረግ ጥያቄ ነበር፡፡ በሚገርም ሁኔታ ጥያቄው ተስተናግዶ – በአዲሱ የኮሎኔል ማዕረግ የኢንሳ ኃላፊነቱን ይዞ እንዲቀጥል ተደረገ፡፡ እንግዲህ የኮ/ል አብዮት አጭር የሚሊቴሪ ማዕረግ አሰጣጥ ታሪክ ይሄው ነው፡፡
ይህ ሰው ታዲያ – በየትኛው የውትድርና ህይወቱና እውቀቱ ነበረ – በለውጡ ማግስት – የሀገሪቱን የጦር ጄነራሎችና ወታደራዊ መኮንኖች ሰብስቦ – ስለ ወታደራዊ ሳይንስ ሲያስተምራቸው የሚታይበት የቴሌቪዥን ፕሮፓጋንዳ የተሠራለት? የሚሊቴሪ ብቃቴ ባይሆን ኖሮ ሲቪል ሰው ቤተመንግሥት መሣሪያ አቀባብለው የመጡበትን ወታደሮች አረጋግቶ መመለስ አይችልም ነበር – እየተባለ የሚቅራራበት የወታደራዊ ልምድ እንግዲህ ይሄ ነው ማለት ነው? ዘወትር እንደ ህጻን ልጅ በሚመስልና ፍጹም የአዋቂ ብስለት በሌለው አኳኋን – አንድ ጎረምሳ የጂንስ ሱሪውን እንደሚቀያይረው ባለ መልኩ – ጠቅላዩ የተለያዩ ወታደራዊ ዩኒፎርሞችን እየቀያየረ የሚተውናቸው የተለያዩ ድራማዎችስ ምንድናቸው? ወታደራዊ ሰው ነኝ ብሎ ለማሳመን የሚፈልገውስ ማንን ነው? ለማን ነው እንደዚያ ሆኖ መቅረቡ ‹‹ክሬዲቢሊቲውን›› (ተቀባይነቱን) ከፍ ያደርግልኛል ተብሎ የታሰበው?
ከእነዚህ ሁሉ ድራማዎች በስተጀርባ – ባለፈው በትግራይ ሚዲያ ሀውስ ላይ ቀርቦ ‹‹አማርኛ መማሬ ይቆጨኛል›› ያለው የአብዮት የቀድሞ የኢንሳ አለቃ የወያኔ ጀነራል ሲናገር አብይ ከኢንሳ የተባረረው ድርጅቱን ጎድቶ አጋሮ ላይ የፖለቲካ ምረጡኝ ዘመቻ በመጀመሩ ነው የሚል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ወርቅነህ ገበየሁም በአንድ ወቅት ለፖለቲካ ምረጡኝ ሲወዳደር የፖሊስ ኮሚሽነርነቱን እንደተወ ለተመለከተ ይሄም እውነት የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ እውነትም ይሁን አይሁን  – ዋናው ነጥብ ግን – የጠቅላዩ የፖለቲካ ጉዞ የተጀመረው ከኢንሳ የኮሎኔልነት ማዕረግ ዕደላ፣ እና ከኢንሳ አገልግሎት በኋላ – በአጋሮ ምረጡኝ ቅስቀሳ የተጀመረ የመሆኑ እውነት ነው፡፡ ይሄ ማለት – የጠቅላዩ የፖለቲካ ልምድ ገና ጥቂት ዓመታትን ያልዘለለ፣ ከትንሽዬ ያደገባት መንደር ያልዘለለ፣ ገና ጮርቃ የፖለቲካ ልምድ የተላበሰ ነው ማለት ነው! ከዚያ በኋላ የኦህዴድን ጡረተኞች አስወግዶ ወደ ሥልጣን የወጣው የቄሮው ውስጣዊ የወጣቶች የፓርቲ አብዮት ወደ ሥልጣን ባንዴ ካሸጋገራቸው ሰዎች መካከል ከእነ ለማ መገርሳ ጋር አብሮ በሥልጣን መንበር ከፍ ሊል የቻለው አብዮት (የአሁኑ አብይ) ይገኝበታል፡፡
እነዚህ በግልጽ የሚታዩ በባሌም በቦሌም ብሎ ወደ ሥልጣን የማሰባበር መንገዶችና አቋራጮች እንደተጠበቁ ሆነው – የአካዳሚን ቡራኬን መቀበልና በምሁር ካባ መንቀሳቀስን ዋነኛ የሥልጣን ጥቅማቸው አካል እንዳደረጉት እንደምናውቃቸው እንደ ብዙዎቹ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ሁሉ – አስር አለቃ (ማለትም ኮሎኔል) አብዮት አህመድና ለማ መገርሳም  – የዚሁ በወያኔ-ኢህአዴግ ዘመን ለአባላት በተርከፈከፈ የምሁርነት ፀበል ተቋዳሾች ሆነዋል፡፡ በዚህ የምሁርነት ዘመቻ – እንግሊዝኛ የማያነበው ወርቅነህ ገበየሁ የህግና የፖለቲካ ሳይንስ ዶክተር ሆኗል፡፡ አርከበ እቁባይ የኢኮኖሚክስና የከተማ አስተዳደር ዶክተር ሆኗል፡፡
ዕድሜውን በበረሃ ውጊያ ያሳለፈው፣ ከወያኔ ስልጣን ላይ መውጣት በኋላም በምስራቅና በሰሜን ዕዞች ውጊያዎችን ሲያስተባብር ያሳለፈው ሳሞራ የኑስም ያለው ጊዜ አብቃቅቶ በአካዳሚያዊ ህይወቱ ደግሞ እስከ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የመድረሱን የጉድ ስኬት ሳንሰማ አልቀረንም፡፡ ደብረፅዮን የቴክኖሎጂ ሳይንስ ዶክተር ሆኗል፡፡ ሌላ ቀርቶ ለማ መገርሳ አሁን ኦሮሚያ በብጥብጥ በምትታመስበት፣ ሀገሪቱ በወሮበሎች በምትታመስበት በዚህ ቀውጢ ወቅት – ቁጭ ብሎ በዶክትሬት ጥናቱ ላይ አተኩሮ በመመራመር ያቋረጥኩትን ጥናት ጨረስኩ ብሎ – ዶክተር ሆኗል፡፡ ብዙዎቹን የወያኔ ወርቃማ የኢንላይትመንት ዘመን የዱክትርና ማዕረግ ምሩቃንና ምሁራን በቀላሉ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ ብዙዎቹ ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች በተልዕኮ ወይም እዚያው በመሄድ የተቀበሉት ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ እዚሁ ከተከፈቱ የሲቪል ሰርቪስና ሌሎች የግልና የመንግሥት አካዳሚክ ተቋማት የተቀበሉት ነው፡፡
አብዮት አህመድም የሠላም ኢንስቲትዩት ተብሎ በሚታወቀውና በእነ ፕ/ር አንድሪያስ እሸቴ አስተባባሪነትና የበላይ ጠባቂነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥገኝነት ተሰጥቶት ከተከፈተው የኢህአዴግ መንግሥት የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ሠላም የሚመራመርበት የምርምር ተቋም የድርሻውን የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡ ዶክተሩ የተመራመረው የፖለቲካ ምረጡኝ በጀመረባት በዚያችው በፈረደባት በአጋሮ ላይ ነው – የሚል ድርሳነ ክለሳም ተመልክተናል፡፡ ወደ ላይቤሪያና ሩዋንዳ ለሠላም ማስከበር ከተሰማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር አብሮ የመሄድና በዶላር የመከፈል ዕድሉን ካገኙት ብዙዎቹ የምናውቃቸው ሰዎች መካከልም አብዮት አንዱ ሳይሆን አልቀረም፡፡ ምናልባትም ስለ ሩዋንዳ ጄኖሳይድ አጥንቶ በዶክትሬት ዲግሪው ማሟያ ምርምሩ ከዘር ፍጅት ለማምለጥ ምን ማድረግ እንዳለብን መፍትሄውን አስቀምጦልን ሊሆን እንደሚችልም መጠርጠር ሳይኖርብን አይቀርም፡፡ በጊዜ ጥናቱን አፈላልጎ ‹ሪፈር› ማድረግ ለሀገር ይበጃል፡፡
በጣም የሚያስቀው – ፕሮፌሰሩና ጄኔራሉ ሳሞራ የኑስ – በቀድሞው 10 አለቃና በኢንሳው ኮሎኔል አብዮት – ስለ ዘመኑ የመጨረሻው የተራቀቀ ወታደራዊ ሳይንስና ሀገርን ስለመከላከል ጥበብ – ቁጭ ብሎ አንገቱን አቀርቅሮ ማስታወሻ እየወሰደ ሥልጠና ሲቀበል የተሰራጨችው የኢቲቪ ፕሮፓጋንዳ ነች! የጉድ አካዳሚስቶችን የሰበሰበች፣ የጉድ ምሁራንን የምታሳይ፣ የጉድ ሀገር እኮ ነው ይዘን ያለነው! መፍትሄ የለም! ለውጥ የለም! ጠብ የሚል ነገር የለም! ሾው ብቻ! ሔለን ሾው! ኤልዳና ሾው! ሠይፉ ሾው! ታማኝ ሾው! ኦፕራህ ሾው! ጃዋር ሾው! አብይ ሾው! በቀለ ገርባ ሾው! ሙስጠፌ ሾው! ጌታቸው ረዳ ሾው! በቃ ሾው በሾው!
መልካም ሾው!
Filed in: Amharic