>
5:21 pm - Saturday July 20, 1929

ህወሃትን  ተቃዋሚ  ፈንቅሎች ሁለት የተለያየ  አቋም ያላቸው ናቸውን ፤አሁን በህወሃት ላይ ለማመጽ ያስገደዳቸው ምንድ ነው (ታጠቅ መ.ዙርጋ) 

ህወሃትን  ተቃዋሚ  ፈንቅሎች ሁለት የተለያየ  አቋም ያላቸው ናቸውን ፤አሁን በህወሃት ላይ ለማመጽ ያስገደዳቸው ምንድ ነው

ታጠቅ መ.ዙርጋ 


 

አንዳንድ ስዎች  ለራሳቸው ግልጽ የሆነ ነገር  ለሁሉም  ግልጽ እንደሆነ የሚገምቱ ፤ ራሳቸው ያወቁት ነገር ሁሉንም ሰው   የሚያውቀው የሚመስላቸው  አሉ ። አንዳንድ ሰዎች አንድን ነገር ወይም ስለአንድ ነገር ሳይገባቸው ፤አያውቁም  ላለመባል አድበስብሰው  ያልፉሉ  ። 

ከእንደ እነዚህ ዓይነቶች በተጻራሪ  ስለአንድ  ያልገባቸው  ወይም  ግልጽ  ስላልሆነላቸው ነገር/ሮች  ደጋግመው የሚጠይቁ  አሉ ። የሚጠይቅ ፈላስፋ ነው ያለው ማን ነበር? ፕሌቶ? አርስቶትል? ሶቅራጥስ? ፔርክለስ? ዴያጎ?ንቼ? ሶፎክለስ?ቦይተስ? ወዘተ..? ሶቅራጥስ ይመስለኛል። እኔም ከእነዚ መጠየቅ  ከሚወዱ አንዱ ነኝ ። 

አዎን ሶቅራጥ ስለአንድ  ሃሳብ፣ እይታ ፣ እምነት ወዘተ..   ምንነት ለማስተማር  በጽሁፍ ለማኅበረሰብ ክማከፋፈል ፤ ፊትለፊት ፡- በመጠየቅ፣ በመሞገትና በመወያየት  የተሻለ እውቀት ይገኛል ብሎ ያምን ነበር ። ስለሆነም  መንገድ ለመንግድ፣ጎዳና ለጎዳና ፣ቤት ለቤት በመሄድና በየስብሰባዎች በመገኘት የነበረበትን ዘመን ማኅበረሰብ ፥ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊ ፣ ፍትሃዊ ችግሮችና ፍልስፍናዊ  አስተሳሰቦች  ላይ  እየጠየቀ፣ እየሞገተና እያከራከረ እውቀት ያስተላልፍ ነበረ ይባላል። ስለሆነም ስለሥራዎቹና ስለእውቀቱ የሚናገሩ ጽሁፎች/ቴክስት በበቂ እንደማይገኝ የዘርፉ ባለሞያዎች ይናገራሉ። 

መንደርደርያዬ/መግበያዬ  በዚህ ልቋጭና በዚህ  ጽሁፍ አርእስት  ላስተላልፍ ወደ ምፈልገው ፍሬ ነገር ወይም መልዕክት ላምራ። ምናልባትም  ለዚህ ነው  ይህን ያህል ዝርግ  መግቢያ ያስፈለገው ትሉ ይሆናል። ያ ለማለትም ላለማለትም መብታችሁ ነው። እኔ በሚመስለኝና በሚመቸኝ መልክ መጻፍም መብቴ ነው። 

 

 ፈንቅል ማለት በትግርኛ  ወጣት ማለት እንደሆነ ሰምቼአለሁ ። ቄሮ ፣ ፋኖ፣ ዘርማ፣ ነብሮ ወዘተርፈ እንደ ማለት ይመስለኛል ። በማኅበራዊ ወሬ መረብ ወይም ሶሻል  ሚዲያ  ከፈንቅሎች ሁለት የሚጻረሩ  አቋሞች ሲንጸባረቁ  ስማሁ ። ለምሳሌ  ከወር በፊት ሚክ ተስፋዬ በመባል የሚጠራው ፣ የፈንቅል ቃልአቀባይ (spoke person) የሚመስል ወጣት ፦ ‘ንቅናቄያቸው  ዓለም አቀፋዊ እንደሆነ ፣አቋማቸው  የትግራይ  ወጣት ሥራ እጦት ፣ የኢኮኖሚና የኢ- ማብራዊ ፍትህ ችግሮች   እንዲፈቱ  ህወሃትን መጠየቅና መወትወት ወይም  እነዚህን ችግሮች  ለህወሃት አድሬስ  ማድረግ’  እነደሆነ  ሲገልጽ  ነው የሰማሁት ። ይህ  ሰው ስለ ህወሃት ሥርዓት  መታደስም /ሪፎርም  ሆነ ስለህወሃት  መወገድ አላነሳም። 

ካልተሳሳትኩ  ይማነህ የሚባል  (እንደውም የፈንቅል መሪ) ይመስለኛል ፣ የሚታገሉት  ‘የህወሃትና  የሥር ዓቱ መታደስ (reform) መሆን ሳይሆን ፣ ህወሃት ከትግራይ  የፖሊቲካ  መድረክ  መወገድ አንዳለበት ፤ ትግላቸው  ለሥር ነቀል ለውጥ እንደሆነ ሲገልጽ’  ሰምቼያለሁ ። 

» ከላይ ከተጠቀስኳችው  የመታጌያ አቋም መግለጫዎች  አንጻር፤  ሁለት ዓይነት  አቋም  ያላቸው  ፈንቅሎች  አሉን?   

» ህወሃት ወደ መቀሌ ቤትመንግሥቱ  ባይባረርና   በአዲስ አበባ  ቤተመንግሥት (ለኔ ቤተጥፋት) ተቀምጦ ኢትዮጵያን እየገዛ ቢቀጥል ኖሮ ፤ አሁን በትግራይ እየሆነ ያለው ተቃውሞ  ይከሰት ነበር ብሎ መገመት ይቻላልን? 

» አው  ይከሰት ነበር ወይም  ምናልባት የምንል ካለን – ህወሃት ለ28 ዓመታት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን  አንቀጥቅጦ ሲገዛና ያን ያህል ግፍ ሲፈጽምና ሲዘርፍ ፤ ከትግራይ ምድር  አንድም የተቃውሞ ድምጽ ያለተሰማውና አንድም  የተቃውሞ  መፈክር ያልታየው  ለምንድነው?  

» እንኳንስ በአገር ቤት በዲያስፖራው ዓለምም ፤  የህወሃት ግፎች በመቃወም በተደረጉ ሰልፎች አንድም የትግራይ ተወልጅ ስልፉን ሲቀላቀል ለምን አላየንም ? እንደውም  ህወሃት ምርጥ ገዢ ነው፤ የምትቃዎሙት ትግሬ ለምን ይገዛናል በሚል ነው  ይሉ ነበር።

»  ፈንቅሎች ያኔ  ከአቻ -ፋኖዎች፣ ቄሮች፣ ዘርማዎች፣ ነብሮዎች ወዘተርፈ ጋር ሁነው ለምን ህወሃትን አልታገሉም? 

» የኢኮኖሚ፣ የወጣቱ ሥራ አጥነት፣ የማኅበራዊ ፍትህ መጓድል ወዘተ.. ለምን ዛሬ ተከሰቱ ?

የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ  ከኢትዮጵያውያን  ይሰወራል ብዬ አልገምትም ።ባዕድና በቅኝ የገዛን አገር ይሉት የነበረው ኢትዮጵያን በጠመንጃ አፈሙዝ  በተገላቢጦሽ ቅኝ ሲያደርጉ ፤ ህወሃትና የህወሃት ዜጎች  ጭብጥ  ቆሎ ይዘው  የምጣዱን  አሻሮ በእጃቸው አደረጉ።ክዚያ በኋላ ለ28 ዓመታት የሆነውን  የማያውቅ ኢትዮጵያዊ/ዊት የለም። ቢሆንም  የሆነውን ሁላችንም እናውቀዋለን ብዬ  በደፈናው ከማልፍው ፤ ፈንቅሎች ዛሬ ህወሃትን  ለመቃወም  የገፋቸው ወይም ያስገደዳቸው  ምክንያቶች  እጅግ በጣም  አጠር ባለመልክ  ማስጨበጥ  የተሻለ ይመስለኛል  ። 

 (1) – የአሁኑን  ኤርትራን  ትተን  በድሮ አጠራር  በኢትዮጵያ  አሥራ ሶስቱ ክፍላት  ሃገራት ፥ መንግሥታዊ፣ አፍሪካ አቀፋዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶችና ካምፓኒዮች  ውስጥ  በነበሩ ክፍት የሥራ ቦታዎች ተቀጥሮ የመስራት የመጀመርያውን ረድፍ/ ዕድል ይሰጥ የነበረው  ለትግራይ ተወላጆች ነበር ። ከነሱ የተረፈው ወይም እነሱ የማይፈልጉትን ወይም  የማይችሉትን  ነበር ለሁለተኛ ዜጎች  የሚሰጠው

-በአሥራ ሦስቱ ክ/ሃገራት  ጥሩ ትርፍ ያላቸው  የንግድ ዘርፎች በሙሉ የሚሰጠው ለእነሱ ነበር

-በአሥራ ሶስቱ ክ/ሃገራት  የተመርቱ ብስል ሃብቶችና  የተፈጥሮ ጥሬ ሃብቶች በእነሱ ቁጥጥር ሥር ነበሩ

-ከባንክ የሚፈልጉትን ያህል ገንዘብ ተበድረው የሚፈልጉትን የማድረግ  ሥልጣን  ነበራቸው 

-በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም የተበደሯቸውን  የብዙ ብሊዮን -ዶላር፣ ይሮ፣ ፓወንድና  የቻይና  ዩዌን የአንብሳው ድርሻ ለትግራይና ለትግሬዎች  ነበር

– በነጻና በመንግሥት ክፍያ ለሁለተኛና ለሶስተኛ  ድግሪ  ለመማር  ወደ ፦አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ እስካንዳናቪያንና አውስትራሊያ  ከሄዱት 3/4ኛው  የትግራይ ተወላጆች ነበሩ፤ ወዘተርፈ።  

አሁን እነዚህን ሁሉ ቅንጦቶች/ፕሪቭሌችስ  ከእጃቸው  ስለወጣ ፤ የሥራ እጦት እና የኢኮኖሚ ችግር  ማለት  (ብር፣ዶላር፣ፓወንድና ይሮ) ኪሳቸውን ሞልተው  መንቀሳቀስ አበቃ 

(2) “በቁሎ ገመዱ በጠስ ሲባል ፣እንጀራው አሳጠረ”  ዓይነት ሆነና  ህወሃት ትግራውያን ባልሆኑ ኢትዮጵያውያን ይፈጸመው  የነበረውን  ግፍ ሞልቶ ስለፈሰሰ ኢትዮጵያን የሚያህል ግዙፍ አገር ከመግዛት ሥልጣንና የኢትዮጵያን የሃብት ምንጭ 90%ቱ  ከሞቦጥቦጥ ተነጥቆ  ጭብጥ ቆሎ ወዳለበት ወደ ትግራይ  ተባረረ። 

ስለሆነም  ህወሃት ሌላ መሄጃ  ስለሌው  ኅልውናውን ለማቆየት፤ ቀድሞ ትግራውያን ባልሆኑ ኢትዮጵያውያን ላይ ያደርገው የነበረውን ስለላና አፈና፤ ያኔ  አንጻራዊ ነጻነት  በነበራቸውና የኔ ናቸው በሚላቸ ዜጎቹ ማለት በትግራውያን  ላይ  መተግበር/መጫን  ጀመረ። 

በመሆኑም  ፈንቅሎች  ዛሬ  ህወሃትን እንዲጠሉትና  እንዲታገሉት የገፋፋቸው ወይም ያስገደዳቸው  ከላይ በቁጥር አንድና ሁለት በነጠብኳቸውን  ይሁንታዎች ምክንያት ነው ።  

እነዚህን ሃቆች ለማሳየት በመሞከሬ ፖለቲካዊ እርምት (political correctness) እንዳትሉኝ። ብትሉኝም ግድየለኝም፤ እውነትን ስለተናገርኩና  እውነትን ስለጻፍኩ ሁሉም ቢጠላኝ  አያስጨንቀኝም። ፖለቲካዊ እርምት(political correctness) ማለት የተወሰኑ (ሰዎች፣ቡድኖች ፣የፖለቲካ ድርጅቶች ወዘተ..) ላለማስቀየም  እውነቱን  ትተህ/ትታቸሁ  ውሸቱን ተናገሩ/ጻፉ  እንደማለት ነው። 

ይህንን የምጽፈው ቂም ከመያዝ አኳያ አይደለም። ፈንቅሎች ከትላንትናው  ስህተታቸው ተምራችሁ  ፤ ዛሬም  ነገም ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተሰለፉ ለማለት ነው።  “የዛሬን ለማወቅ  ስላለፈው ማወቅ ፤ የነገውን ለማወቅ ያለፈውና የዛሬውን መመልከት ግድ ይላልል” (ዋልተር ሮድኒ) ። 

አገሩ የሚገዛውን  ጠቅላይ ምኒስተር፣ ፕሬዝዴንት፣ ፓርቲ  ወዘተርፈ ፦ አባቴ  ስለሆነ፣ ወንድሜ  ስለሆነ፣ አጎቴ  ስለሆነ፣ የአክስቴ ልጅ ስለሆነ፣ ጎሳዬ/ዘውጌ ስለሆነ  ወዘተርፈ በሕዝብ  ላይ የፈለገውን ግፍ ቢፈጽም  አልቃወመውም  ማለት የዚያ ሰው፣ ቡድን  ጎሳ ወዘተ.. ንቃተ-ኅሊና ምንያህል ዝቅተኛ እንደሆነ  ያሳያል። እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎች፣ ቡድኖች፣ ጎሳዎች  ወዘተ.. በ21ኝው ምዕተ ዓመት ይኑሩ እንጂ በአስተሳሰብ  በጥንታዊ/ፕራሞዲያል ክ/ዘመን ወስጥ ነው ያሉት።

ከአራት  ቀናት በፊት ሁለት የትግራይ ተወላጅ  ወጣቶች  በህወሃት ላይ ያላቸውን ማንኛውም  ቅሬታና ብሶት  ባሰሙ  ቁጥር ወደ ጸረ-ትግሬነት እንደሚተረጎምባቸው  ገልጸዋል። ያንን ስሰማ  አሃ!  ሌላው የኢት/ህዝብ ለ28 ዓመታት በህወሃት ሥር የኖረውን የመከራ ህይወት፤ በትግራይ  የሚኖሩ ትግራውያን አሁን ሊጀምሩ ነው አልኩኝ።

 “Unless we feel it,we do not do it : ካልተሰማን ወይም ካላመመን አናደርገውም “ እንደ ማለት ይመስለኛል ። የሌሎችን ሃዘን በጥልቅ የሚሰማን ሃዘን ቤታችን ሲገባ ነው። የሌሎችን መራብ ምንነት የምንረዳው ራሳችን ስንራብ ነው። የታሰረን ሰው ስሜት ለማውቅ  ታስረን ማየት ወዘተርፈ። ህወሃትም የቀበራቸን ክላስተር ቦምቦች በራሱ ላይ  እፈነዱና እየለበለቡት ስለሆነ ፤ ህወሃት ሳይለበልባችሁ ቀድማችሁ ለብልቡት።  የፈንቅሎች ፀር-ህወሃት  ትግል ያለቅድመ ሁኔታ እድግፋለሁ !! በርቱ !!

Filed in: Amharic