>
8:49 pm - Tuesday June 6, 2023

አጤ ምኒልክ ፣ አሚር አብዱላሂና የሐረር ጦርነት ...!!! (ሳሚ ዮሴፍ)

አጤ ምኒልክ ፣ አሚር አብዱላሂና የሐረር ጦርነት …!!!

ሳሚ ዮሴፍ 

እንግዲህ በጥላቻ አእምሯቸው የተበላሻ፣ የሀገር አንድነት የሚያናድዳቸው፣ ኢትዮጵያ ፈርሳ ማየት የሚፈልጉ፣ እግዚአብሔር ወርዶ የሚኒልክን ሥራ ቢነግራቸው ማመን የማይፈልጉ የእፉኝት ልጆች ትልቁ  ምኒልክን ከሚወቅሱበት ወይም ከሚያጠለሹበት አንዱ ምክንያታቸው የሐረር ጦርነት ነው፤ ሐረር ምኒልክ ለምን እና ከማን ጋር እንደተዋጉ ቀጥሎ እንመለከታለን…..
“…እነዚህ የሐበሻ ሕዝቦች ሰፊ ግዛት አላቸው፤ ከቀይ ባህር ዳርቻ ከምፅዋ፣ ከሱአኪንና ከአርቂቆ ተነስቶ ግዛታቸው እስከ ሞቃዲሾና ሶፋላ ይደርሳል፤ በምዕራብ በኩልም ግዛታቸው የሚወሰነው ከኑባውያንና ከሌሎችም ሕዝቦች ጋር ነው…”
አልፎንሶ አልቡ ከርክ 1503 ዓ.ም
“…የሐበሾች ግዛት ሰፊ ነው፤ ቀይ ባህር ዳርቻ ካለው  ከትልቁ ወደባቸው ከቢሊ ተነስቶ ወደ ውስጥ ሲጓዝ በአዳል ምድር አልፎ ሐድያ ሁሉ የእነሱ ሀገር ነው፤ ወደ ሕንድ ውቅያኖስ አቅጣጫም እስከ ሞቃዲሾ ይደርሳል፤ ሐበሾች በጣም ሰፊና ሀብታም ሀገር አላቸው፤ እነዚህ ሕዝቦች ወሰናቸውን ለማስከበር ወደ ዳር ሀገር ወይም ወደ ወሰናቸው በሚጓዙበት ጊዜ ዛፍ እየቆረጡና መንገድ እየሠሩ ነው….”
ፍራንቼስኮ አልቫሬጽ 1520 ዓ.ም
“…ሐበሾች ዙሪያቸውን በአረመኔዎችና በብዙ ጠላቶች የተከበቡ ሕዝቦች ቢሆኑም ግዛታቸው ሰፊ ነው፤ ከነኩዋቸው ተዋጊ ሕዝቦች በመሆናቸው ዙሪያውን የከበቧቸው ጠላቶች በተነሱባቸው ጊዜ ከጠላቶቻቸው ጋር እየተዋጉና እያሸነፉ ይኖራሉ፤ የሀበሻ ሰዎች ለማንም ባዕድ አንገዛም እያሉ ራሳቸውን ችለው የሚኖሩና ሀገራቸውን ከማንኛውም ባእድ ገዥ እየተከላከሉ የሚጠብቁ ሕዝቦች ናቸው፤ ግዛታቸውም ቀይ ባህርን ተሻግሮ እስከ አረብ ሀገር ድረስ ነው….”
ካርታ ዳስ ኖቫስ 1521 ዓ.ም
“…ቱርኮች በኔ ላይ ክፉ  በመሥራት ወሰኔን እየገፉ አጠገቤ ደርሰዋል፤ ሐረርን ወሰዱት፣ ከዛም አልፈው ኢቱ ኦሮሞንና በርሃውን ሁሉ ሊይዙት ነው፤ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ከእነርሱ ጋር ለመዋጋት መሄዴ ነው፤ የኤሮፓ ነገሥታት ሁሉ እኔን እንደ ጠላት ስላዩኝ የተገፋው ሰው በመሆኔ ግብጾችን ለመውጋት መዝመቴ እርስዎ ምስክር ይሆኑኛል…”
ምኒልክ በግንቦት ወር 1876 ዓ.ም ለኢጣልያ ንጉሥ ከጻፉት ደብዳቤ።
“…ሐረር ከአያት ከቅድማ አያቶቼ ጀምሮ የሸዋ ግዛት ነው፤
ምኒልክ ግንቦት 27 1877 ዓ.ም ለኢጣልያ ንጉሥ ከጻፉት ሌላ ደብዳቤ።
ግብጾች ሐረርጌን የያዙት በ1867 ዓ.ም ነው። ኢትዮጵያ በመሳፍንት አገዛዝ ተከፋፍላ ሁሉም የዕለት ጥቅሙን ያሳድድ በነበረበት ጊዜ ክፍት በር ያገኘው በራኡፍ ፓሻ የሚመራው 1200 ወታደሮች ያለበት የግብፅ ጦር በቀላሉ ሐረር ገባ። በዚያን ጊዜ በሐረር ከተማ 5000 ቤቶችና 2000 ጎጆዎች ነበሩባት። የሕዝቡም ብዛት 35000 ነበር።
የሐረር ከተማ ዙሪያውን በግንብ ተከባ ወደ ከተማ የሚገባውም ከከተማ የሚወጣው በአምስቱ በሮቿ ብቻ ነው። እነዚህም በሮች የተለያየ ስም ሲኖራቸው ታላቁ መግቢያ *አስበዲን በር ይባላል፤ ይህ መድፍ ተጠምዶበት የተቀመጠበት በር የጨርጨር ሰዎች መግቢያ ነው።
ሁለተኛው *ሱቅጣጥ በር ይባላል፤ ይህ በር ደግሞ የአርሲዎችና የጋራሙለታ ሰዎች የሚገቡበት ነው።
ሦስተኛው *አርጎባ በር ይባላል፤ የፈዲሶች የአርጎባዎች መግቢያ ነው። አራተኛው *አሱም በር ይባላል፤ አሱም በር ልክ እንደ አስበዲን በር መድፍ የተጠመደባት ሲሆን፤ የኢሳዎች መግቢያ ነው። አምስተኛው *የረር በር ይባላል፤ የየረሮች መግቢያ ነው። እነዚህ በሮች ሁልጊዜ በሚገባና በጥንቃቄ ይጠበቃሉ። ማታ ሲሆን በሮቹ ይቆለፉና ቁልፎቹ ለአሚሩ ይሰጣሉ። ከዚያ በኋላ ነግቶ በሮቹ እስኪከፈቱ ድረስ የሚገባም ሆነ የሚወጣ የለም።
ኢጣልያኖች ሐረርጌን ከሞቃዲሹ፣ እንግሊዞች ደግሞ ከበርበራ ጋር ደባልቀው ለመያዝ ሀሳብ ነበራቸው። እንግሊዞች አንግሎ ኢጂፕቲያን በተባለው ከግብፅ ጋር በነበራቸው ስምምነት መሠረት የግብፅ ጦር ከሐረርጌ ወጥቶ ሐረርጌን ለእንግሊዞች ለማስረከብ ተስማምተዋል፤ ይህን ስምምነት የሰማው የኢጣልያ መንግሥት ደግሞ ሐረርጌን ከእንግሊዝ ቀድሞ በኃይልም ሆነ በፍቅር ለመያዝ አስቦ በሐረርጌ ያለውን የግብጾች ጦር የሚሰልሉ ሰላዮች በየጊዜው ወደ ሐረርጌ ይልክ ነበር።
እንግሊዞች ከግብጾች ጋር በነበራቸው ስምምነት ግብጾች ከሐረርጌ እንዲወጡ አደረጉ። ምናልባትም የኢጣልያ መንግሥት ገፍቶ የመጣ እንደሆን በማለት ከግብጾች ቀጥሎ ስልጣን ለያዘው ለሐረርጌው አሚር አብዱላሂ እንግሊዞች የሰለጠኑ ወታደሮች፣ 400 ያህል ጠመንጃና ጥቂት መድፎችን ሰጥተው ጄልደሴና ሐረር ላይ ምሽጉን እንዲያጠናክር አደረጉ።
አሚር አብዱላሂ ስልጣኑን በሚገባ ከያዘ በኋላ የግብፅን ገንዘቦች አሽራፊና መሀለቅ አስገብቶ በሐረርጌ ገበያዎች ላይ እንዲውሉ አደረገ። እነዚህን ገንዘቦች ገበያ ላይ ውሎ ያየው የሐረር ኦሮሞና የሱማሌ ብሔረሰብ ገንዘቡን አንቀበልም በማለት በአሚሩ ላይ ጥላቻ አሳድረው ገበያ ጠፋ። በገበያው መጥፋት ምክንያት የአሚሩ ወታደሮች ችግር ላይ ወደቁ፤ አብዱላሂ በዚህ ብቻ ሳይሆን በሚያወጣው አዋጅ በሕዝቡ እየተጠላ ሄደ።
በሐረርጌ የውጭ ሸቀጥ አስመጪና የሀገር ውስጥ ላኪ የነበረው ኢጣልያዊው ጋይታሎ ሲኮኒ በስለላ ተግባር ይጠረጠር ስለነበር አሚር አብዱላሂ ጋይታኖን ጠርቶ “…በእስልምና ኃይማኖት እመን፤ የማታምን ከሆነ ከሀገሬ ለቀህ ውጣ አለው…” ጋይታኖም ኃይማኖቴን አልቀይርም ብሎ ከሐረር ተባሮ ወጣ። ጋይታኖም ሀገሩ ሄዶ ሚላን ላለው ለአፍሪካ የንግድ ማኅበር የደረሰበትን በደል አመለከተ።
ማኅበሩ ለስም እንጂ የተቋቋመው ዋና ሥራው የኢጣልያን ሰላዮች ማስተባበርና መላክ ስለነበር ስምንት የታወቁ የኢጣልያ ሰላዮችን በኢጣልያ ንጉሥ ስም ስጦታ አስይዞ ወደ አሚር አብዱላሂ ላከ።
እነዚህ የኢጣልያ ሰላዮች ሚያዚያ 1 ቀን 1878 ዓ.ም የሐረርጌ ግዛት ከሆነው ጄልዴሳ ደረሱ። ከዚያም ሆነው “የተከበሩ ታላላቅ ስጦታ ይዘን መጥተናልና እንዲቀበሉን ፈቃድ እንጠይቃለን” በማለት ለአሚር አብዱላሂ ላኩ።
አሚር አብዱላሂም ክርስቲያን ኢጣልያኖች ወደ ግዛቱ በመግባታቸው ተናዶ እንዲገድሏቸው ወታደሮቹን ላከ።
የተላኩትም ወታደሮች ሰባቱን ኢጣልያኖች አርደው ገደሏቸው፤ አንዱ ግን በፈረስ አምልጦ ዘይላ ገባ። ኢጣልያኖቹን የገደሏቸው ወታደሮች የመጣውን ስጦታ ለአሚር አብዱላሂ አቀረቡ። አብዱላሂ የመጣለትን ስጦታ ተቀብሎ ወታደሮቹን አሰራቸው። አብዱላሂ ይሄን ያደረገው የተገደሉት በስህተት ስለሆነ ወንጀለኞቹን አስሬሃለሁ ለማለት ነበር። ይህ ከሆነ በኋላ ኢጣልያኖች ሐረርጌን በጦር ኃይል ለመያዝ ጥሩ ሰበብ አገኙ። “በሐረርጌ የተገደሉብን ወገኖቼችንን ደም እንበቀላለን” የሚል መግለጫ ማውጣታቸውን ሐረርን ለመያዝ ማሳባቸውን የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ሰሙ። ወዲያውኑ ለአሚር አብዱላሂ ደብዳቤ ጻፉለት።
“ቀድሞም ቢሆን ሐረርጌ ከኢትዮጵያ ውጭ ተገዝቶ አያውቅም፤ ከኢትዮጵያ አውራጃዎች አንዱ መሆኑን አንተም በታሪክ ሰምተኸው ይሆናል፤ ለአራት መቶ ዓመታት ያህል ያለ ማቋረጥ ግብሩን ለአያቶቼ ሲገብር ኖሯል፤ አሁንም ነገሩን በሰላምና በወዳጅነት ለመጨረስ ገብርና እንደ አባቶቻችን ወዳጅ እንሁን…” የሚል ደብዳቢ ለአሚር አብዱላሂ ላኩለት።
አሚሩ ደብዳቤውን ከተቀበለ በኋላ  “…በውኑ በዚህ ዓለም ላይ ከቱርክ የሚበልጥ መንግሥት አለን…” ብሎ ለመኳንንቱ ተናገረ። ምኒልክም በመጀመሪያው ደብዳቤ መልስ አለመምጣቱን እንዳዩ “ብትገብር ይሻልሃል” የሚል ሌላ ደብዳቤ ላኩ። የምኒልክ ሁለተኛ ደብዳቤ ሲደርሰው አብዱላሂ ሳቀ፤ ለምኒልክ ደብዳቤ መልስ ሲመልስ “…በእስልምና ኃይማኖት ገብተህ የሰለምክ እንደሆን ጌትነትህን እቀበላለሁ” ብሎ ሙስሊሞች የሚያሸርጡትን ሽርጥ፣ ሙስሊሞች ራሳቸው ላይ የሚጠመጥሙትን ጥምጣምና የጸሎት ጊዜ መስገጃ ምንጣፍ ላከላቸው።
ይህን መልስ ያገኙት ምኒልክ “…ጠብቀኝ ወደ ሐረር እመጣለሁ፤ እዚያ ያለውን መስጊድም ወደ ቤተክርስቲያን እለውጠዋለሁ…” የሚል መልእክት ልከውለት ይዘጋጁ ጀመር። ወዲያው በአስቸኳይ ተዘጋጅተው በአጤ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ኅዳር 4 ቀን 1879 ዓ.ም ከእንጦጦ ከተማ ተነሱ።
የምኒልክን ከእንጦጦ መነሳት የሰማው አሚር አብዱላሂ ክርስቲያኖች በሙሉ ከሐረር እንዲወጡ አዋጅ አስነገረ።
በኃይማኖት ሰበብ አውሮፓዎችም ይረዳሉ ብሎ ጠርጥሮ ስለነበር ከሀገር አልወጣም ያለ ማንኛውም ክርስቲያን ፈረንጅ ሁሉ ከቤቱ እንዳይወጣ አዘዘ፤ ጠባቂም በየበራቸው ላይ አደረገ። በዚያን ጊዜ ሐረር የነበረው እንግሊዛዊው *ፔቴን በጻፈው ማስታወሻ “…በከተማው ውስጥ እንደ እስረኞች ነን፤ ደብዳቤ የመላክና የመቀበል ነፃነት እንኳን የለንም፤ ከሐረር ከግንቡ ውጭ እንኳን እንዳንወጣ ክልክል ነው…” ብሏል።
የገና በዓል ደርሶ ነበርና ንጉሥ ምኒልክ ጨለንቆ ላይ ሰፍረው የገናን በዓል ለማክበር ወሰኑ። በዚያም ሰፈራ አድርገው እንዳለ ምኒልክም መኳንንቱን ሰብስበው “…ይህ አሚር አብዱላሂ እኛ ክርስቶስ ተወለደ ስንል እርሱ አልተወለደም የሚልበት ቀን ነውና የልደት ‘ለት ጦርነት መግጠሙ አይቀርም” ብለው ተናገሩ። ምኒልክ ጨለንቆ ከደረሱ በኋላ
“… ግባ እኔ ለአንተው እንጂ የመጣሁት፤ ሀገር ለማጥፋት አልመጣሁም፤ ከገባህ፣ ከተገዛህ ሀገር አልነሳህም ኋላ ይቆጭሃል” ብለው ለአሚር አብዱላሂ ላኩበት።
አሚር አብዱላሂ የፈሩት መስሎት የተላኩትን መልእክተኞች አሰራቸው።
*ኮንቲ ሮስኒ ሲጽፍ “… ገብር የሚለው የምኒልክ ደብዳቤ ለአሚር አብዱላሂ እንደ ደረሰው ኅዝቡን እና ወታደሩን ሰብስቦ አስተያየታቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ የምኒልክን ጥያቄ አሰማቸው። ሕዝቡም ‘…በኃይናኖታችን ላልገባና በእስልምና ኃይማኖት ለማያምን አንገብርም፤ እንዋጋለን፤ ቢያሸንፉን ሐረርን ይውሰዱ፤ ያን ጊዜ የሚፈልጉትን ግብር እንገብርላቸዋለን’ ብለው መለሱለት…” ይላል።
የሐረር ሽማግሌዎች ግን አሚር አብዱላሂ ዘንድ ሄደው ጦርነቱ እንዲቀር እንዲገብር መከሩት። እርሱ ግን “ስለ ምኒልክ ሠራዊት እንድትነግሩኝ አልፈልግም፤ እንድትነግሩኝ የምፈልገው መጽሐፋችን ለካፊር እጃችሁን ስጡ ይላልን…” ብሎ አማካሪዎቹን አሰራቸው። ካፊር ማለት በእስልምና የማያምን ነው። ከዚህ በኋላ የጀሀድ ጦርነት አወጀ። ሊያስገብሩት ሄደው የነበረውን የደጃች ወልደ ገብርኤልን ሠራዊት በጥቂት መሣሪያ አባሮ በማባረሩ፤ የምኒልክም ሠራዊት እንደዚያ በቀላሉ ይሸሻል ብሎ አሰበ። ከዚህ በኋላ የምኒልክን ጉዞ ለማስቀረት ሠራዊቱን አስከትሎ ወደ ጨለንቆ ተጓዘ። ቀኑ የክርስቶስ ልደት በዓል ስለነበር የምኒልክ ሠራዊት እየበላ እየጠጣ ይጫወታል።
ንጉሥ ምኒልክ ከድንኳናቸው ደጃፍ ተቀምጠው አሻጋሪውን ኮረብታ በመነጥራቸው ሲመለከቱ፤ የአሚር አብዱላሂ ሠራዊት ሲመጣ አዩ። ምኒልክም በፍጥነት ሠራዊቱ እንዲሰበሰብ አደረጉና “ሄደህ በለው” ብለው አዘዙ።
ከቀኑ 5 ሰዓት ሲሆን የአሚር አብዱላሂ መድፎች በሸዋ ሠራዊት ላይ ይተኮሱ ጀመር። የሸዋ ሠራዊትም በአስደናቂ ፍጥነት የአሚር አብዱላሂን ሠራዊት ከቦ መድፎቹን ማረከ።
በተማረኩት መድፎችም የአሚር አብዱላሂን ሠራዊት ይመታበት ጀመር፤ ጦርነቱ ብልጭ ብሎ ጠፋ። የአሚር አብዱላሂ ሠራዊት ሩብ ሰዓት ከተዋጋ በኋላ ሸሸ።
አብዱላሂም በፈረስ ሸሽቶ ወደ ሐረር አመለጠ። ከሠራዊትም ወደ አንድ ሺ የሚሆኑ ተገደሉ።
ታህሣሥ 29 ቀን 1879 ዓ.ም የሐረርጌው የአብዱላሂ ጦር ድል ሆነ። ምኒልክ ድል ካደረጉ በኋላ የኢጣልያ መንግሥት ሐረርን ለመያዝ እጅግ የበረታ ጉጉት ስላለው እዚያው ጨለንቆ ሆነው ለኢጣልያው ንጉሥ ኡምቤርቶ “…ኢጣልያኖችን የገደለው አሚር አብዱላሂ በፈረስ አመለጠኝ፤ ግን እግዚአብሔር ይመስገን ሰዎቹን ፈጀሁበት፤
#ሰንደቅዓላማዬንም በሀገሬ ላይ አቆምኩ፤ ወታደሮቼንም አገባሁ፤ ኢጣልያኖችን ለመርዳት ተደርጎ የነበረውን አደጋ በብዙ ሬሣ ተበቀልኩ፤ ከዚህ ደብዳቤ በኋላ ሁኔታውን የሚያስረዳ መልእክት በሰፊው እሰዳለሁ….” የሚል ታህሣሥ 30 ቀን በጦርነቱ ማግስት ላኩ። ምኒልክ ይህን ደብዳቤ የጻፉት ሐረርጌ የኢትዮጵያ ግዛት መሆኗን ለአውሮፓ መንግሥት ለማሳወቅና አውሮፓውያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ባላቸው ሀሳብ መሠረት ወደ ሐረርጌ ጦር ቢልኩ ውጊያው ከምኒልክ ጋር መሆኑን ለማሳወቅ ጭምርም ነበር።
ምኒልክ አብዱላሂን ለመያዝ ወደ ሐረር ከተማ ገሰገሱ፤
ጥር 1 ቀን አማሬሳ ሲደርሱ አብዱላሂ የሸዋ ጦር እንደደረሰበት ስላወቀ “ልግባና ልገዛ ሀገርዎን አያጥፉ” ብሎ መልእክት ላከ። ምኒልክም “እሺ ግባ ምሬአለሁ” ብለው ላኩበት። አብዱላሂ ግን ፈርቶ ሚስቱን እና ልጆቹን ይዞ ወደ ጅጅጋ ሸሸ። የአሚር አብዱላሂን መጥፋት ያወቁት ሐረርጌዎች ማለትም የአብዱላሂ አጎት አሊ አቡበከር፣ የሱፍ በርከሌ፣ ቃዲ አብደላና ሌሎች ሽማግሌዎች ሆነው ወደ ምኒልክ ዘንድ መጥተው “…አሚር አብዱላሂ ሌሊት ጠፋብን፤ ግብርዎን ይቀበሉን፣ ሕዝቡንም አያጥፉት ንጉሥ ሆይ…”  ብለው አመለከቱ። ከመልእክተኞቹም ጋር እስረኞች የነበሩ ሁለት ግሪካውያንና ሌሎቹንም ፈትተው ወደ ምኒልክ ላኩ። ንጉሥ ምኒልክም መልእክተኞቹን ተቀብለው
“…ከዚህ በፊትም ብያለሁ፤ እኔ የእስልምናን ኃይማኖት ለማጥፋት አልመጣሁም፤ ሁሉም ሰው እንደ እምነቱ ያድራል፤ እናንተም ለሰላምና ለእርቅ ስለመጣችሁ ወደ ሐረር እስከምመጣ ይህንን ለሕዝቡ ነግራችሁ ቆዩኝ…” ብለው መልእክተኞቹን መለሱ። ከመልእክተኞቹም ጋር በጅሮንድ አጥናፌ ከተማውን ለመረከብ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው እንዲሄዱ አደረጉ። የሻቃ ተክሌን፣ ባላምባራስ ዳምጠውን፣ የሻቃ አድነውን፣ የሻቃ ገበየሁን የከተማውን በሮች እንዲጠብቁ አዘዙ። እነኚህም ታዛዦች ሐረር ከተማ በሰላም ገብተው ፈረስ መጋላ በሚባለው አደባባይ ላይና በአምስቱም በር ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀሉ።
የሐረር ሕዝብ እንዳይዘረፍም በየቤቱ ዘብ አቁመው ያስጠብቁ ጀመር።
በዛሬዋ ጅቡቲ አቦክ ከተማ የነበረው *ታውሪን እ.ኤ.አ. ፌብርዋሪ 3 ቀን 1887 ወደ ሀገሩ በጻፈው ደብዳቤ
“…ከተማዋ የተያዘችው ሐበሾች ድል ሲያደርጉ እንደሚይዙት አይነት አይደለም፤ ያለምንም ደም መፋሰስና ዝርፊያ የሸዋ ጦር ድል አድርጎ ከተማዋ ገብቷል…” ብሏል።
ንጉሥ ምኒልክ ባላምባራስ መኮንንን ደጃዝማች ብለው ጥር 18 ቀን 1879 ዓ.ም የሐረርጌ የበላይ ገዥና የወታደር ሹም ብለው ሾሟቸው። 3000 ወታደሮችም ሰጧቸው። ለሕዝቡ ግን እንደ ባህሉና እንደ ኃይማኖቱ እንዲያስተዳድሩ የአሚር አብዱላሂን አጎት አሊ አቡበከርን ሾሙ። የካቲት 1 ቀን ወደ ሸዋ ለመመለስ ከሐረር ተነሱ ከሐረርጌ ጦርነትም 3000 ጠበንጃ፣ 600,000 ጥይትና አራት መድፎች ማርከው ይዘው መጡ።
ንጉሥ ምኒልክ የካቲት 28 ቀን ከተማቸው እንጦጦ ሲገቡ
ከዚያ በፊት ያልታየ አቀባበልና ሰልፍ ታየ። የዚያን ጊዜ የምኒልክን ሰልፍ ድንቅ ያደረገው፤ በሐረር የነበሩ የአሚር አብዱላሂ ግብጻውያን ሙዚቀኞች ስለተማረኩ ከሰልፉ ፊት ቀድመው ሙዚቃ (ማርሽ) በማሰማት ይጓዙ ስለነበር ነው።
ከዚያም ሌላ ከግብፅ የመጡ የአውሮፓ ውሾችንና የተለያየ ቀለም ያላቸው የእርግብ ለማዳዎችን ሌላም አውሬ ሁሉ ይዘው መጡ።
በዚያን ጊዜ አዝማሪዎች….
“የምኒልክ ነገር ይመስለኛል ተረት፣
አሞራው በቀፎ ውሻው በሰንሰለት።” ….እያሉ ዘፈኑ።
ከፋ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ይቀጥላል…..
ምንጭ :- ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ
Filed in: Amharic