>
8:48 am - Friday June 2, 2023

በኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ፣ ሐረርና ድሬዳዋ የተፈጸመውን ፍጅት ለመጣራት መረጃ ለመሰብሰብ የተላለፈ ጥሪ...!!!

በኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ፣ ሐረርና ድሬዳዋ የተፈጸመውን ፍጅት ለመጣራት መረጃ ለመሰብሰብ የተላለፈ ጥሪ…!!!

የኢትዮጵያውያን ለሰላም፣ ለፍትህና ፣ ለአንድነት ኔትወርክ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የህግ ባለሞያዎች ቡድን
 
በሰኔ 22 ቀን 2012 የተፈጸመውን የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ፤ በኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ፣ ሐረርና ድሬዳዋ ሰፊ ተቃውሞ መቀስቀሱ ይታወሳል። እነዚህ ተቃውሞዎች በአብዛኛው በታዋቂው የባህልና የፖለቲካ ትግል ፋና ወጊ በነበረው ሃጫሉ ግድያ የህብረተሰቡን ድንጋጤ ያንጸባረቁና ሰላማዊ ነበሩ። ሆኖም፤ በተወሰኑ አካባቢዎች፣ የተወሰኑ ቡድኖች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሃይል እርምጃ ወስደዋል። በዚህ እርምጃም የተወሰኑ የብሄርና የሃይማኖት ቡድን አባላት እና ጎረቤቶቻቸውን ለማዳን የተንቀሳቀሱ ንጹሀን የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የህይወት መጥፋት፣ አካል መጉደልና ንብረት ውድመት ደርሷል። የተለያዩ የዜና ማስራጫ ዘገባዎች እንድሚያስረዱት የሃይል እርምጃው በድንገት በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ የተፈጸሙ እርምጃዎች አለመሆናቸውን ነው። ጥቃቶቹ  በመረጃ፣ በሰው ሃይልና በፋይናንስ በቂ ዝግጅት ተደርጎባቸው በእቅድ፣ በመዋቅርና በሰፊው በኦሮሚያ ነዋሪ በሆኑ የተወሰኑ የብሄርና የሃይማኖት ቡድኖች አባላት ላይ ያነጣጠሩ ይመስላሉ። የእነዚህ ጥቃቶች እጅግ አሳሳቢ የሚያደርጋቸው ነገር ውሰጥ አንዱ በመንግስት የጸጥታ ሃይልና አስተዳደራዊ መዋቅር ድጋፍ የተፈጸሙ መሆናቸው ነው።
ስለሆነም የእነዚህ ጥቃቶች ሁኔታና ያደረሱት የጉዳት ዓይነትና መጠን እውነቱ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነው። እንደዚህ ያለ ፍጅት እንዳይደገም እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። በዚህ ድርጊት የተሳተፈ ወይም ድርጊቱ እንዲፈጸም ያደራጃ፣ የቀሰቀሰ፣ በፋይናንስ የደገፈ ማንኛውም ሰው ተጠያቂ መሆን ይኖርበታል። በወንጀሎቹ ጉዳት ደረሰባቸውን ወገኖች የፍትሕ ጥያቄ በከንቱ እንዳይቀር ወንጀለኞቹን ተጠያቂ ማድረግ፤ እንዲሁም ተጎጂዎቹን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊ ነው።
እውነትን የማግኝትና ፍትሕን የማረጋገጥ ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም። እነዚህን አሰቃቂ ወንጀሎችን የመመርመርና የመሰነድ ሥራ ሙያዊና ተዓማኝነት ባለው መለኩ መከናወን አስፈላጊነቱ የሚያጠያይቅ አይድለም።
እነዚህን ጉዳዮች ከግምት በማስገባት፤ በሰሜን አሜሪካ በጥብቅና ሙያ በተሰማሩ ባለሙያዎች የሚመራ የበጎ ፋቃደኞች ቡድን የሰኔውን ጥፋቶች (ፍጅት) በሚመለከት መረጃ በማሰባሰብ የተሟላ ሪፖርት ለማዘጋጀት ተቋቁሟል። ይህ ሪፖርት ለወንጀሎቹ ተጠያዊ የሆኑ ሰዎች፣ ቡድኖች ተቋማት ከፍትሕ እንዳያመልጡ ለሚደረገው ጥረት ይረዳል።
የዚህ ቡድን አባላት ከማንኛውም ድርጅት ጋር ንክኪ ያለን አለመሆኑን እየገለጽን፤ የዓላማችን ደጋፊ ከሆኑ ግለሰቦችና ተቋማት ድጋፍ ለመቀበል ግን ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።
በዚህም መሰረት፤ ማንኛውም ወንጀሎቹን በቀጥታ የተመለከተ ወይም ስለወንጀሎቹ አስተማማኝ መረጃ ያለው ሰው ምስክርነት እንድትሰጠን(ጭን) ወይም የሰነድ ወይም የኦዶቪዡዋል ማስረጃዎችን እንድትልክልን(ኪልን) ጥሪ እናቀርባለን። ምስክርነት የሚሰጠን ወይም ሌሎች አይነት ማስረጃዎችን የሚሰጠን ሰው ራሱ(ሷ) ተጎጂ የሆነ(ች) ወይም የተጎጂው(ዋ) የቤተሰብ አባል፣ ዘመድ፣ ጓዳኛ፣ ጎረቤት ወይም መንደርተኛ የሆነ(ች) መሆን አለበት(ባት)። የምስክሮችን ማንነት በሚስጢር የሚያዝ ሆኖ፤ በሪፖርቱ ላይ ሊጠቀስ የሚችለው በብልጽ በተሰጠ የምስክሩ ፈቃድ ብቻ ይሆናል።፡
ምስክርነት ለመሰጠት በቡድናችን የኢሜል አድራሻ forallethiopia@gmail.com ያሳውቁን። ከቡድናችን አንዱ አባል በስልክ ወይም እርሶ በሚመርጡት መንገድ ግንኙነት በማድረግ የምስክርነት ቃልዎን እንቀበላለን።
በተጨማሪም የፎቶና የቪዲዮ ማስረጃዎችንም በኢሜል አድራሻችን forallethiopia@gmail.com የምንቀበል መሆኑን እንገልጻለን። ማንኛውም የምንሰበስበው ማስረጃ እውነተኝነትና አስተማማኝነትን የምናጣራ መሆናችንን እንገልጻለን።፡
በኦሮሚያና አዲስ አበባ በሰኔ 2012 የተፈጸመውን ፍጅትን የሚያጣራ – በሰሜን አሜሪካ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን
ሐምሌ 11፣ 2012
Filed in: Amharic