>

"ነፍጠኛ ፤ ትምክተኛ ...»  ህብረተሰብ ላይ የሚለጠፉ አስነዋሪ ፤  አሳፋሪ ፤ አሳናሽ ፤ ቅጽል ስሞችና ምልክቶች በህግ ይታገዱልን!!! (ሉሉ ከበደ)

“ነፍጠኛ ፤ ትምክተኛ …»  ህብረተሰብ ላይ የሚለጠፉ አስነዋሪ ፤  አሳፋሪ ፤ አሳናሽ ፤ ቅጽል ስሞችና ምልክቶች በህግ ይታገዱልን!!!

ሉሉ ከበደ
ባለፈው በሁለት ትከትታታይ አጫጭር ጽሁፎች ፤ በኦሮሚያ የተፈጸመው « የዘር ፍጅት አይደለም!» አስሩን የጄኖሳይድ እርከኖች የፕሮፌሰር ግሬጎሪን ጥናታዊ ስራ መሰረት አድርጌ አቅርቤላችሁ ነበር ፡፡ ለማስታወስ ያክል « ጄኖሳይድ ዋች»  የተባለው ድርጅት ዘርን ፤ሀይማኖትን ፤ የፖለቲካ አመለካከትን ወዘት … መሰረት ያደረገ ጅምላ ፍጅት እንዳይከሰት የሚሰራ ተቋም ነው ፡፡ መሪው ዶክተር ግሬጎሪ ስታንተን ይባላሉ ፡፡ አስሩን የጄኖሳይድ እርከኖች ሲያስቀምጡ መከላከያው ፤ መፍትሄው ፤  ምን መሆን እንዳለበት ለያንዳንዱ ደረጃ አስቀምጠዋል ፡፡
ገና ዜጎችን መነጣጠል ፤ ለያይቶ ማስቀመጥ ሲጀመር ፤ መድሀኒት ብለው ባስቀመጡት ሀሳብ ውስጥ እንዲህ የሚል አለ «… The search for common ground is vital to early prevention of genocide ..»
የጋራ እሴቶቻችን ላይ መስራት የመጀመሪያው መድህን ነው ፡፡ ባለፉት ሀያ ስምንት አመታት ኢትዮጵያውያን የጋራ አሴቶቻቸው እንዲጠፉ ሲሰራ ነበር የቆየው ፡፡ ግሬጎሪ እንደሚሉት ፤ አንድ ለዘር ፍጅት ሰለባ ሊሆን የሚችል ህዝብ የጋራ ቋንቋ ከሌለው አንድ የጋራ ቋንቋ እንዲፈጠርለትና ስራ ላይ እንዲውል ማድረግ ያድነዋል ፡፡ ታንዛኒያ ለህዝቧ የጋራ ቋንቋ ፈጥራ ከዘረኝነት የላቀ ብሄራዊ ማንነት ማምጣት ችላለች ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ ፡፡ እኛ ግን ከስድስት መቶ አመታት በላይ ህዝቡ በጋራ የሚግባባበት የአማርኛ ቁንቋ ሆን ተብሎ ፤ ለአማራው የተደገሰለት ነገር ስላለ በትምህርት ቤቶች እንዳይነገር ሲከለከል ነው የተኖረው ፡፡ እየተኖረም ያለው ፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ተሰብስበው መግባቢያ ቋንቋ ያጡ ልጆች መገዳደል ስራቸው የሆነው ፡፡ የዜግነት ፖለቲካን በማስፈን የዘረኝነትን አስተሳሰብ  መዋጋትም ሌላው የመጀመሪያ መፍትሄ ነው ፡፡
አንዱ አንዱን እንዲረዳውና መግባባት እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችሉ ሁለንተናዊነት ያላቸው ተቋማትን መገንባት ከጎሳና ከዘር ማንነት የላቀ ሰብእና እንዲኖር ይረዳሉ ፡፡ ለምሳሌ ከመዋለ ህጻናት ፤ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ትምህርት ቤቶቻችን እስከ  ዩኒቨርስቲዎቻችን ለማናቸውም ህብረተሰብ ክፍት የሆኑና ፤ በጋራ ባህላችን ፤ በጋራ ታሪካችን ፤ በሰብአዊነት ዙሪያ  ትውልዱን የሚያንጹ  ፤ በአካዳሚክ አገልግሎች ላይ ብቻ ያተኮረ ስራ የሚሰሩ ሊሆኑ ይገባል ፡፡ ያስፈልጋል ፡፡ የሀይማኖት ተቋማትም እንደዚያው መቻቻልና ሰብአዊነት ላይ ትኩረት ሰተው ትውልዱን ማነጽ ይጠበቅባቸዋል ፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ በሀገራችን  ጥያቄ የሚሆነው  ከማንጋር ሆነው ያን ያደርጉታል ? ቁርጠኛ መንግስት አለ ወይ ?
« ነፍጠኛ ፤ ትምክተኛ ፤ » ምናምን የመሳሰሉ ፤ ህብረተሰብ ላይ የሚለጠፉ አስነዋሪ ፤  አሳፋሪ ፤ አሳናሽ ፤ ቅጽል ስሞችና ምልክቶች በህግ ይታገዳሉ ፡፡ አንድን ህብረተሰብ በተገቢው ማንነቱ ያልጠራ ለፍርድ ይቀርባል ፡፡ የጥላቻ ንግግሮች በህግ አጥብቆ የተከለከሉ ይሆናሉ ፡፡ የኦሮሞ ሚዲያ ኔት ወርክና የትግራይ ሜዲያ ማሰራጫዎች አፍ የፈቱበት ቋንቋ ስድብና በአማራው ላይ ጥላቻ መንዛት ፤ ሚኒሊክን መስደብ ፤ የተፈጥሮ መብታቸው እስኪመስል ድረስ ተያይዘውታል ፡፡ ለጆሮ የሚቀፍ መርዝ ሲተፉ የሚውሉት ግለሰቦች ምን አይነት አስተዳደግ ቢያድጉ ነው ያሰኛል ፡፡ አስደናቂው ነገር ደግሞ ዶክተርም ይባላሉ ፤ፕሮፌሰርም ይባላሉ ፡፡ ሰው ከደሙ ተዋህዶ አብሮት ያደገን ጥላቻ ትምህርት ሊያጸዳለት እንደማይችል ማሳያ የሆኑ ሰዎችን ቆጥረን አንጨርስም ፡፡ የሰው ጭንቅላት በዚያው ባደገበት ውሸትና ነውረኛ አስተሳሰብ ውስጥ ተጣብቆ ከቀረ ምን ቢያጥቡት የማይጸዳ ፤ ምን ቢማር የማይረዳ ፤ መሆኑ ሁለት ሰዎች እንደምሳሌ ብናገር ፤ ዶክተር ደብረጽዮን የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት 1967 ላይ የቀረ እስካሁን « ነፍጠኛ.…  እብሪተኛ … » ይላል « ታጠቅ … ተዋጋ … » ይላል ፡፡ እና ዶክተር ገመቹ የሚባሉ አዛውንት አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያሉ ይመስለኛል ፡፡ « ሚኒሊክ አምስት ሚሉዮን ኦሮሞ ገደለ»  እያሉ መንጋውን በጥላቻ ያሰክሩታል ፡፡ በዚያን ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ከአምስት እስከ ስድስት ሚሊዮን ሊሆን እንደሚችል ሙያተኞቹ ያረጋግጣሉ ፡፡
የጥላቻ ንግግሮችና ቅጽሎችን ፤ መለያ ምልክቶንች ለማገድ ህግ ስናወጣ ፤ በትምህርትና በፕሮፓጋንዳ የህዝቡን ባህል የመቀየር ስራ መስራት ይገባል ፡፡ ለምሳሌ እስከ ሰማንያዎቹ ድረስ በቡሩንዲ ውስጥ ሁቱና ቱትሲ የሚሉ ቃላት በህግ ታግደው ነበር ፡፡ ነገር ግን ህዝቡ ሁለቱንም ስሞች የሚወክሉ ሌላ ቅጽል ስሞች ፈጥሮ ለመለየት ሲጠቀምባቸው ነበር ፡፡ በመታወቂያ ላይ ዘርን ማስቀመጥም በፍጥነት መቅረት ያለበት የመጀመሪያ ተግባር ነው ፡፡ ናዚ አይሁዶችን የፈጀበት መንገድ መታወቂያ አንዱ ነው ፡፡ ሩዋንዳ ቱትሲዎችን ያረዱበት መንገድ አንዱ መታወቂያ ነው ፡፡ የኛም ዘረኞች ሰሞኑንም ሆነ ቀደም ሲል ዋና መጠቀሚያችው መታወቂያ ነው ፡፡ አዲስ አበባ ላይ አማራ ክልል የሚል ታርጋ የሰፈረባቸው መኪኖች እየተለዩ ወድመዋል ፡፡
 ናዚ ሂትለር አይሁድን የፈጀበት ሌላው መጠቀሚያ ቢጫ ኮከብ ያለበት መለያ ያለው ልብስ እንዲለብሱ በማስገደድ ነበር ፡፡ እዚህ ላይ ቡልጋሪያ አይሁዳውያን ዜጎቿን ሰማንያ በመቶ ያህሉን  ቢጫ ኮከብ ያለበትን ምልክት እንዳይለብሱ በማድረግ  እጅግ ብዙዎችን አትርፋለች ፡፡ ብዙ ያውሮፓ አገሮች ግን ከናዚ ጋር በመተባበር አስፈጅተዋቸዋል፡፡
የኛ መሰሪ ገዢዎች በቅርቡ የሰሩትን እንዳትረሱብኝ ፡፡ በሀጫሉ ግድያ ማግስት « ገዳዮቹን  ይዘናል » ብለው በመንግስት ቴሌቪዥን ሶስት ሰዎችን ለዜና ማጀቢያነት ፎቶ አሳይተውን ነበር ፡፡ አንዱ የለበሰው ጃኬት ልሙጡ የኢትዮጵያ ባንዲራ ያለበት ፤  አንድነትን የምንመርጥ ዜጎችና የአማራው ህዝብ « ባንዲራዬ » የሚለው ምልክት ነው ፡፡ ሀያ ስምንት አመት ካስተማሩን የሸፍጥ ፤ የተንኮል ፖለቲካቸው ተነስተን ያንን ባንዲራ ለምን እንዳመጡት ለማወቅ አይናችንን የምናረግብበት ያክል ጊዜ አንፈጅም ፡፡ « የገደሉት አማሮች ናቸው » ለማለት ነው ፡፡ «ቄሮ ቀጥል የጀመርከውን …»  ይቀጥላል …
Filed in: Amharic