>

በአክራሪ ወሀብያዎችና ዘረኛ የፖለቲካ መዋቅር በክርስቲያኖች ላይ የተፈፀመ ጥቃት - የአይን ምስክርነት!!! (መኮንን ሀብተሚካኤል)

በአክራሪ ወሀብያዎችና ዘረኛ የፖለቲካ መዋቅር በክርስቲያኖች ላይ የተፈፀመ ጥቃት – የአይን ምስክርነት!!!

መኮንን ሀብተሚካኤል

እውነትን ከፈለክ እንደኔ ምዕራብ አርሲ ሂድና የሆነውን አይተህ ለእውነት ታመህ ና!
ልክ እንዳንተው ምዕራብ አረሲ (ሻሸመኔ፣አርሲ ነጌሌ፣ ኮፈሌ፣ቆሬ፣ሽሬ፣ጉቺ፣ ኩየራ፣ዶዶላ……) ላይ የደረሰውን ጉዳት (የሰው መሞትን፣ ንብረት መዘረፍን፣ ንብረት መቃጠልን፣ ሶዎች መሰደዳቸውን ) በተለያዩ ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ በማህበራዊ ሚዲያ አይቼና ሰምቼ እንዳንተው በጣም አዝኜ ነበር፡፡
ነገር ግን ባለፈው ሐውስ (ሐምሌ 17) ውስጤ ለምን በአካል ሄደህ ህመማቸው አይሰማህም ሲለኝ ከቀኑ 8፡30 ላይ ተነስቼ ጉዞ ጀመርኩኝ፡፡
ዝዋይ-ባቱን በመኪና ውስጥ ሳያት በግራም በቀኝ እዛም አዚም የተቃጠሉ ቤቶች፣ፎቆች ፣መኪኖች ይታያሉ
አዳሚ ቱሉ ላይ ያን የመሰለ ትልቅ የአበባ ማቀነባበሪያው ብዙ ቤቶች ወድመዋል ይታያል
አርሲ ነገሌ ስደርስ ጨልሞ ነበርና በተጨማሪም የመንገድ ዳር መብራት ስላልነበር ብዙም ሳላይ አለፍኩኝ
ኩየራም ከድሮ ድህነቷ  ጋር ጨለማው ቢሸፍናትም ወደ አራት ተሳቢ መኪኖች ተቃጥለው ህይወት አልባ ሆነው ያለ ሰሚ መንገድ ዳር ቆመዋል
ሻሸመኔ መግቢያው ላይ አንድ ትልቅ መኪናና አራት የኮካ ኮላ ተሳቢ መኪኖች ተቃጥለው የፍርድ ያለህ ይላሉ፤ መናኸሪው ጋር ስደርስ ማታ 2፡00 ሰዓት ሆኖ ነበር ወደ ውጪ ሳይ ደነገጥኩኝ ምክንያቱም ምንም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የለም፡፡ መኪና ውስጥ ያሉትን ሰዎች ባጃጅ የለም እንዴ ስል ከ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ ተከልክሏል አሉኝ፡፡ ሹፌሩ አቦስቶ የሚባለው ቦታ አደረሰን፡፡ የተቃጠሉ ፎቆችን ሳይ ውስጤ ይባስ ይረበሽ ጀመር፡፡ ከተሳፋሪዎች አንዱ ወደየት ነህ አለን፡፡ ቦታውን ስነግረው እኔም ወደዛ ነኝ እሸኝሃለው አለኝ፡፡ ምራጫ ስለሌለኝ አመንኩት፡፡ የ30 ደቂቃ የእግር ጉዞን ጭር ባለው ጨለማ ውስጤ እየደነገጥኩን ወሬም እያወራን  መንደር ለመንደር ተጉዝን በክብር የምፈልግበት ቦታ አደረሰኝ፡፡
በማግስቱ ሻሸመኔን ከላይ እስከታች መንደር ለመንደር በእግሬ እየዞርኩኝ መከራዋን ለማየት ሞከርኩኝ፡፡ የማቃቸውን ልጆች አግንቼ  በአካል ሳወራቸውና ሀዘኔን ስገለጽ ቢያንስ በየመንገዱ የተቃጠሉት ነገሮች ስለጸዱ እንጂ ያኔ ብታያት ምን ልትን ነበር አሉኝ፡፡ በመቀጠል  በዋናው አስፋልት የተቃጠሉት ህንጻዎችና ንግድ ቤቶች  የነማን እንደነበሩ ስጠይቃቸው ሁሉም የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ቤቶች መሆናቸውን ነገሩኝ፡፡ ያልተቃጠሉ ህንጻዎች ደግሞ የሌሎች እምነት ተከታዮች መሆናቸውን ተረድቻለሁ፡፡ ውስጥ ለውስጥ መንደር ለመንደር የተቃጠሉትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ሁሉንም ተጠቂዎች አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ኦርቶዶክስ ክርስቲያን መሆናቸው ነው፡፡
ይህንን ስል ህንጻው የኦርቶዶክ ሆኖ (ተለይ የንግድ ተቋማት ላይ) ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ  ተወቀጥ በሚል ፈሊጥ የተቃጠሉ የሌላ እምነት ተከታዮች ንብረት መኖራቸውን ተረድቻለው ( ግን ዋናው ኢላማ የህንጻው ባለቤት ነው) ፡፡
ሻሸመኔ ባሉ ቤተክርስቲያናት በሰበካ ጉባዬ፣በልማት ኮሚቴ፣ በስብከተ ወንጌል የሚያስተባብሩ አካላት ሙሉ ለሙሉ የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡ በተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ተገኝቼ የተጠለሉትን ለመጎብኘት ብሄድም ከኮረና ስጋት አንጻር ደብሩ ለ130 አባወራዎች ፍራሽ፣ድስት፣ ዱቄት፣ዘይት  እንዲሁም ለቤት ኪራት 1000ብር ካሰባሰበው ላይ ሰጥቷቸው ሸኝቷቸዋል፡፡ አንድ አባት የበሽታው ስጋት እንጂ እዚህ ቢሆኑማ ጥሩ ነበር ቢያንስ ሌላው ሰው ስለሚያመጣ እንጀራ ይበሉ ነበር አሁን ግን ያው ገንፎ አገንፍተው ካልሆነ ምን ይበላሉ ያሉን በጣም ውስጤን አሳመመኝ፡፡ የእርዳታ አስተባባሪዎችን አድራሻ ተቀብዬ ወደ መረፊያ ሄድክኝ፡፡ በሰፈር ውስጥ የተቃጠሉ የግንብ መኖርያ ቤቶችን እያየው በተሰበረ መንፈስ ወደ ማረፊያ አቀናው፡፡ የማቃቸውን ሰዎች እንኳን አተረፋቹ ብዬ ወደ ቤት ገባው፡፡ በጫወታ መካከል እዛው ሰፈር ውስጥ ቤታቸውና ንብረታቸው ተዘርፎና ተቃጥሎ ነገር ግን እዛው ግቢ ውስጥ ባለው የዶሮ ማራቢያ የነበረ ቤት ውስጥ ያሉ ቤተሰብ መኖራቸውን ሳይ እመሜ እየባሰ ሄደ፡፡ እሁድ ማታ በራቸውን አንኳኩቼ የእነሱ ህመም የእኔም እንደሆነ የእነሱ መቃጠል የእኔም መቃጠል መሆኑን ገልጬ ባይጠቅማቸውም  ህመሜን ለማከም ጣርኩኝ፡፡
ቅዳሜ ጠዋት መንደር ለመንደር እየዞርኩኝ ወደ ኩየራ ለመሄድ ሻሸመኔ አዲሱ መናኸርያ ስገባ ባየሁት ነገር በጣም ደነገጥኩኝ፡፡ አንድ ወጣት ክር ያሰረች ሴት ከሁለት ልጆቿ ጋር ጥቁር ለብሰው እና  ስደተኛ የሆነ የቤት ዕቃና ጓዝ ይዘው መናኸርያ ውስጥ  ሳያት ነበር የደነገጥኩት፡፡ ቀረብ ብየ ስጠይቃት ከባሌ እንደመጣች በዚሁ የጥፋት ተልዕኮ ባለቤቷና ወንድሟን እንዳጣች ስትነግረኝ አንባየ ለመፈሰስ ግዜ አለወሰደበትም፡፡ ራሴን መቆጣጠር ስለከበደኝ ስልኳን ተቀብየ 500ብር ሰጥቻት ተለየዋት (ዛሬ ደውላ አመስግናኝ ለሟቶች  የቁርባን ፍትሐት ለማድረግ ወደ ሸዋ ወደ ቤተሰብ እንደሄደች አዲስ አበባ እንደሆንኩኝ ስነግራት ደግሞ ስመጣ ደውልልሃለው ብላን ተለያየን)፡፡
ኩየራ ከሻሸመኔ ቢበዛ 10 እስከ 15 ኪ. ሜ ቢርቅ ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የተጠለሉ ካህናትና ምዕመናን  አግኝቼ ሰፊ ቆይታ አድርጌያለው፡፡ በተለይም ቀድሞ የማቀው ሰው ስላገኘው በነበረን ውይይት ነጻ ሆነው የደረሰባቸውን መከራ ከ4 ሰዓት ለበለጠ አውግተውኛል፡፡ የሁሉም ካህናት  ቤት ተቃጥሏል፡፡ የምዕመናኑ ብሶት ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ቤት የላቸውም፡፡ ተስፋ የላቸውም፡፡ አብዛኞቹ አረጋውያን ናቸው፡፡ይህ ሁሉ የደረሰባቸው ከማንም ጋር ጠብ ኖሮባቸው ሳይሆን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ስለሆኑ ብቻ መሆኑን ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ የማንም የሌላ እምነት ተከታይ መኖርያ ቤትም ሆነ የንግድ  ቤት አልተቃጠለማ! በጣም የተጎዱ ስለሆኑ የደብሩን ቤተክርስቲያን የባንክ አካውንት ለአንድ በጎ አድራጊ ምዕመን ልኬለት  15 ሺ ብር ለዕለት ጉርስ ይሆናቸው ዘንድ  ወዲያው ልኮላቸው እኔም የፈለኩትን ህመም አግኝቼ ለሀዋሳ ገብርኤል እነሱን ብሶታቸውን እና የእኔንም ስሞታ ለማቅረብ ተለየዋቸው፡፡
እሁድ በጥዋት እትብቴ ወደተቀበረበት ከልጅነት እስከ እውቀት ያሳደገኝ የኮፈሌ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ለማንገስ እና የክርስቲያኑን ሀዘን ለመካፈል በአካል ተጓዝኩን፡፡ የሚያቁኝ ፈርተው አትሂድ ብለውኝ ነበር እኔ ግን ከዚ በላይ ምን አለ ብየ ሄድኩኝ፡፡ ስደርስ ቅዳሴው የአዘቦት ቅዳሴ ይመስላል ነበር፡፡ ያ ታላቅ ደብር ሰው አጥቷል፡፡ ሲረፋፍድ ከሻሸመኔ ምዕመናን መጥተው ንግስ አስመሰሉት፡፡ የቀደሱት ካህናትም ከሻሸመኔ እንደመጡ ተረድቻው፡፡ ሰው የለማ፡፡ ባለፈው አቶ ታምራት እና ልጁን ሄኖክን በድንጋይ ገድለው አላረካ ቢላቸው ሬሳቸውን ከተማ ለከተማ (ሁለት በአንድ እያሉ እየጨፈሩ) አዙረዉት ነበር፡፡ ያኔ ትንሽ ከነበሩት ምዕመናን የ 17 ቤት አቃጥለው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከ40 የሚበልጡትን ቤታቸው አቃጠሉት፡፡ የሚበሉት ምግብ አጡ፡፡ ሁሉም ተሰደደ በየሀገሩ፡፡ ባዶ እጃቸውን ተሰደዱ፡፡ በአከባቢው ካሉ ጥቂት አገልጋዮች እንደተረዳሁት በኮፈሌ ወረዳ ባሉ ክርስቲያኖች (ቆሬ፣ጉቺ፣ሽሬ…) ከ200 በላይ ቤት ተዘርፎ ተቃጥሎባቸዋል፡፡ ንግሱ ላይ ብዞር ብዙም የማቀው ፊት የለም፡፡ ሁሉም ተሰደዋል፡፡ የማቃቸውን ሰዎች ሳናግራቸውም ለንግሱ የመጡት እንጂ እነሱም ተሰደዋል፡፡ ምን አላቸውና እንኳን ተሰደዱ፡፡ እንኳን ነፍሳቸውን አተረፉ፡፡ ሚገርማቹ በንግሱ ላይ ለቤተክርስቲያኑ እና ለተጎጂዎች ብዙ ብር ገባ 57ሺ ብር (አይ ትብበር አይ ክርስቲያን ድንቄም መተባበር የስም ክርስቲያኖች)፡፡
ሁሉም አንግሶ ቶሎ ወደ ሻሸመሜ ይፈራላ፡፡ እኔ ግን ከየት እንዳመጣውት ባላቅም ዛሬ ደፈርኩጥ፡፡ ያሳደጉኝን ጎሮቤቶቼን ቤት፣ ቤተክርስቲያኑን አሳምረው የሰሩትን ምዕመናኖች ቤት፣ የዘመዶቼን ቤትና የንግድ ተቋማት አንድ በአንድ ጎበኘውት፡፡ ለካ አፈር እንዲ ይክዳል፡፡ አብዛናው ቤቶች በእንጨትና በጭቃ የተሰሩ ናቸው፡፡ እንኳን ነዳጅ እንኳን ጎማ ተሎክሶባቸው የግዜ ጉዳይ እንጂ እንደ ሰው ስጋ ፈራሽ ነበሩ፡፡ በሁለት ቤት መካከል አንደኛው ተቋጥሏል፡፡ ለምን ብትሉ የክርስቲያን ነዋ! እስቲ በሞቴ እንወራረድ የሌላው እምነት መቼ ተቃጠለ፡፡
የሀጫሉን ቤተክርስቲያን ቀድመው  የተደራጁ የሀጫሉ “ደጋፊዎች” አቃጠሉ፡፡ የቀረው ጥቂት ቤት  ለምን አልተቃጠለም ብል መሽቶባቸው አሉኝ፡፡ ሌሊት ጀምረው በ23 እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ሲያቃጥሉ ነበር፡፡ የከተማው ኦሮሞ ሙስሊሞች ባለፈው ታምራት ሲሞት ዝም እንዳሉት አሁን ዝም አላሉም፡፡ ቤቶች እንዳይቃጠሉ ብዙ ጥረው ነበር፡፡ አቃታቸው አሉ፡፡ ሲከላከሉ የተፈነከቱም ነበሩ፡፡ ግን ጎበዞች ናቸው፡፡ በዚህ ዙር ሰው እንዳይሞች ተከላክለዋል፡፡ አረ ብዙ ጉድ ነው የሰማሁት፡፡ቤት ላይ ታመው የተኙ ሰዎች አሉ ቢሏቸውም ቢለምኗቸውም  አብረው ይቃጠሉ  ብለው እሳት ለኳሾቹ ቤቱን ለኮሱት፡፡ እነዚህ ኦሮሞ ሙስሊሞች ናቸው ገብተው ተሸክመው ያዳኛቸው፡፡ አረ ያልሄድኩበት ሰፈር የለም፡፡ያላየሁት የተቃጠለ ቤት የለም፡፡ ኮፈሌ ከተማም ለነገሩ ትንሽ ነበረት አሁን ይባስ አሳነሷት፡፡
ኦሮሞ ጎሮቤቶቻችን ጋር ሄድኩኝ፡፡ አቅፈው ሳሙኝ፡፡ እዛ ኮቪድ የለም ቢኖርም ግድ የላቸው የትላትና ፍቅራቸውን በመሳም ገለጹልኝ፡፡ቡናም ጋበዙኝ፡፡ ሶስት ዙር ተከላክለው ያዳኑትን የክርስቲያ ቤት በአራተኛው ዙር ተሸንፈው አቃጠሉባቸው፡፡ እኔ ፊት በመሸነፋቸው ተናደው በእልህ ያወራሉ፡፡ ቢያንስ ሳይቃጠል ይቅር በሁለተናው ዙር በሶስተኛው ዙር እንዴት መከላከያ አልደረሰም ይላሉ በቁጭት፡፡ የከተማው አስተዳደር እና ፖሊሱን ተወው እኛ ስንታገል ቀሞው ያዩ ነበር አሉኝ እየተናደዱ፡፡ ሰፈራችን የነበሩ ቤቶችን በ23 ከምሸ በኋላ ነው ያቃጠሉት አሉኝ፡፡
 የሚያግዛቸው መንግስት አጥተው ተሸነፉ እንጂ የጥቅምቱ በደል እንዳይደገም፤ በሌሎች እንዳይረገሙ ጥረው ነበር፡፡
አቤት የሰው ልጅ ግፉ፡፡ የአሮጊቶቹን የሽማግሌዎቹን የሚያፈስ ቤት የፈራረሰ አጥር ይጠግናል እንጂ እንዴት ያቃጥላል፡፡ አብዛኞቹ እኮ ሞታቸውን እየጠበዉ ንብረታቸውን ተናዘው ነበር፡፡ እሳት በላባቸው እንጂ፡፡ ተሰደዱ፡፡ ተወልደው ካደጉበት ወልደው ከዳሩበት ተከብረው ከነበሩበት መንደር ወደማያቁት ሀገር ተሰደዱ፡፡
በኮፈሌ ወረዳ ባሉ ክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ግፍማ ብዙ ነው፡፡ በ1993 ዓ.ም ንብረታቸው ተዘርፎ ጉቺ መድኃኒዓለም ተቃጠለ ያኔም ተሰደዱ፤ 2001 ዓ.ም  አራት ክርስቲያኖች ታርደው፣አንሻ ማርያም ተቃጥላ ፣ ንብረታቸው ተዘርፎ ተቃጥሎ ሲያዩ ተሰደዱ፤ ጥቅምት 2012 ዓ.ም ታምራትንና ልጁን ገድለው አስክሬናቸው እያዞሩ ከተማዋን በደማቸው አዳረሷት ሁሉም ቤቱን እንደዘጋ ተሰደደ፡፡ ይህ አልበቃ ብሏቸው ሰኔ 23 ላይ የተዘጉ ቤቶችን ሳይቀር ዘርፈው አቃጠሉ፡፡ እናስ ምን ቀራቸው ምግብ ፍለጋ ተሰደዱ፡፡
ትላንት በሀብታቸው የማቃቸው በትምህርታችን ጥሩ ውጤት ስናመጣ ደብተር ገዝተው የሰጡጥ፣ ዩኒቨርሲቲ ስገባ ልብስ ገዝተው የሰጡኝ፣ ለምርቃትህ ሳትጠራን ብረው የፍቅር ኩርፊያ ያኮረፉት፣ ሳገባ ሌላ ሀገር መጥተው እልል ብለው የዳሩኝ ሰዎች ዛሬ ቤታቸው ተቃጥሎ ተሰደዋል፡፡የገብርኤል ንግስን ለማንገስ ብለው ከተሰደዱበት የመጡት የሻሸመኔ ምዕመናን ይዘው የመጡትን ዱቄትና ማካሮኒ ለመቀበል ደጅ ሲጠኑ ሳይ አመምኝ፡፡
ድሮም ፈርተው አንገታቸውን ሰብረው  በትህትና ይኖሩ ነበር ይባስ ብለው አንገታቸውን ብቻ ሳይሆን ቅስማቸውን ሰበሩት፡፡ የአዲስ አባባ ወጣት ያልሰራውን የሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ ኮፈሌ ላይ ከሌላቸው ላይ ተበድረው አሳምረው የሰሩት ሰዎች ተሰደዱ፡፡
ንጹህ ሀገር ወዳድ ከሆናችሁ ሰውን በሰውነቱ ብቻ የምታከብሩ ከሆናችሁ ብሔራችሁን ሳትሉ፣ ሃይማኖታችሁን ሳትሉ እንደኔ ሂዱና በአካል እያቸው፡፡ ያኔ ያማቹዋል፡፡ ያኔ ይገባቹዋል፡፡ እኔም እንደናንተ እንደውም በተሻለ ሁኔታ ከቴሌቪዝን ጣቢያ እያቀያየርኩኝ፣ ከማህበራዊ ሚዲያው ብሶቱን፣ መከራውን ውድመቱን አይቼ ነበር ግን አሁን ነው በደንብ የወገኖቼ ክርስቲያኞች ህመም የተሰማኝ፡፡
እንደ ክርስቲያን ህብረት ስለሌለን አዘንኩኝ፡፡ ጥቅምት ላይ ቤታቸው የተቃጠሉትን 17 የኮፈሌ ክርስቲያኖች ምንም ሳንሰጣቸው ሳንደርስላቸው ይኸው አሁን ከ200 በላይ ቤታቸው ተቃጠለ፡፡
 አወይ ሀገር ወዳድነት አወይ ክርስትና!!!
ሂዱና እዩ ያኔ ሰውነታችሁን ትጠላላቹ!!!
ሂዱና እዩ ያኔ ከሌላችሁ ላይ ተበድራችሁ ትረዳላችሉ!!!
ሂዱና እዩ የማስመሰል ክርስትናቹን ትተዋላችሁ!!!
ሂዱና እዩ ድንገት የፈዘዘውን የነቀዘውን ቤተክህነት ወይ ታነቁታላችሁ ወይ ታጸዱታላችሁ!!!
Filed in: Amharic