>
7:27 pm - Tuesday June 6, 2023

ስለወቅታዊው የሀገራችን ጉዳይ አንዳንድ ነጥቦች (ግርማ በላይ)

ስለወቅታዊው የሀገራችን ጉዳይ አንዳንድ ነጥቦች

ግርማ በላይ


በየትኛው እንደምጀምር ይቸግረኛል፡፡ አንገብጋቢ ጉዳዮቻችን ከማንም ሀገር በበለጠ አሳሳቢና የኅልውና አደጋ የደቀኑብን ናቸው፡፡

 

  1. ጠ/ሚኒስትራችን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ እንኮኮ ብለው ያቀማጥሉት በነበረው አናኮንዳ በሚባል የእባብ ዝርያ  ተነድፈው አሁን በመጠኑም ቢሆን በማገገም ላይ የሚገኙ ይመስላል – በድርድር ሊለቁት ይችላሉ – ያኔ ይጨርሳቸዋል ምናልባት፡፡ እርሳቸው ራሳቸውም ከኮቪድ 19 ያልተናነሱ እጅግ አደገኛ ቫይረስ ለመሆናቸው በአጭሩ የሥልጣን ዘመናቸው በተግባር ያሳዩዋቸው ዕኩይ ተግባራት ምስክር ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በተለይ በአማርኛ ሲናገሩ አብዛኛው የንግግራቸው ክፍል ብዙዎችን ቢያማልልም በሌሎች ቋንቋዎች ለምሣሌ በኦሮምኛ ሲናገሩ ግን የአማርኛውን እየተጣረሱ ጥቂት የማንባል ዜጎችን ለቅያሜ እርሳቸውን ለትዝብት ዳርገዋል፡፡ 

ለማንኛውም ዘር ከልጓም በመሳቡም ይሁን በሌላ ሥውር ተልእኮ ምክንያት ጃዋርንና መሰሎቹን በአንድ ወገን እየታገሱና ከፌዴራል ሥልጣናቸው ያካፈሏቸው በሚመስል ሁኔታ እንደፈለጉ ሲፈነጩ ዝም ብለው ሳለ በሌላ በኩል ግን በተለይ የአማራውን አካባቢ በርሳቸው ምስለኔዎች ፀጥ ረጭ እንዲል ማድረጋቸው፣ የኦነግን የጥፋት ዘመቻ በአማራው ክልል በተለይም በከሚሴና በአጣዬ እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች ለማክሸፍ የሞከረውን ጄኔራል አሣምነው ፅጌንና ሌሎች ሁነኛ የአማራ ክልል የሥራ ኃላፊዎችን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የተጓዙትን ርቀት ለተመለከተ የጠ/ሚኒስትሩን ዓላማ በቀላሉ ይረዳል፡፡ በአካል ወጣት እንደመሆናቸው ይህን ሁሉ ፖለቲካዊ ሸፍጥና ሤራ እንዴት እንደተካኑት በእጅጉ ይገርማል፡፡ “ተንኮለኝነት ለካንስ ዕድሜ አይወስነውም” በሚልም ልንደመም እንችላለን፡፡ ከፍ ሲል እባብን ካነሣን አይቀር የወጣበትን ጉድጓድ አለመሳቱ ጥሩ ምሣሌ ይሆነናል – አቢይና ኦህዲዳዊ ጓደኞቻቸው የሚከተሉትን ዘረኛ አካሄድ ለመግለጽ፡፡ በሚገርም ፍጥነት ሀገራችንን እያንኮታኮቷት ይገኛሉ – በጎሠኝነት፡፡

በመጨረሻው ግን ያመኑት ፈረስ በደንደስ ጥሎ አፍንጫቸው ሥር ምን እንደተከናወነና ቀጥሎም ምን እንደተከሰተ እየተከታተልነው ያለ ጉዳይ ነው፡፡ የጭቡው ሥራቸው አሁንም አላበቃ ብሎ ኦሮሞ ኦሮሞን ገድሎ በተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት ሳቢያ አማራው የጦስ ዶሮ ከመሆን አልወጣ ብሎ ይሄውና ሰሞኑንም በቤንሻንጉል ከ14 የማያንሱ አማሮች ለኦነጋውያን ዓላማ ስኬት የመስዋዕት በግ ሆነዋል፡፡ ይህ ነገር የአማራ ሕዝብ ትክክለኛ አመራር እስኪያገኝ የሚቀጥል ለመሆኑ ከፌዴራል ተብዬው መንግሥት አወቃቀርና የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ መረዳት ይቻላል፡፡ ፌዴራል መንግሥቱ በማን እየተዘወረ እንዳለ ግልጽ ሆኗልና፡፡

  1. አንድ ሰው ተገደለ፡፡ ሀጫሉ ሁንዴሣ፡፡ በርሱ ጦስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አለአበሳቸው ዘረኝነትን በተላበሰ ጭካኔ ተገደሉ፤ ቤት ንብረታቸውም ወደመ፡፡ ብዙ የመንግሥት ሀብት ንብረት ተዘረፈ፤ ተቃጠለ፡፡ ፌዴራል መንግሥት ግን የማንን ዱካ እየተከተለ እንደሆነ ለብዙዎች ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ እያላዘነ ያለው ለአንዱ ግለሰብ ነው፡፡ ያ ግለሰብ ሞቱና አሟሟቱ ቢያሳዝንም የሞላው የተረፈው ነው፡፡ ቤተሰቡም ያን ያህል በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚቸግራቸው አይደሉም፡፡ ለሀጫሉ ቅጥ ያጣ ሀዘንና የገንዘብ መዋጮ ማድረግ ትርጉሙ ግልጽ አይደለም፡፡ ሀጫሉ አፈር አያሟሽም፤ ሞትምም ሆነ በሰው መገደል በርሱ አልተጀመረም፡፡ ከሙኣለ ሕጻናት ጀምሮ እስከ መንገድና መናፈሻ በዚህ ልጅ ስም መጥራት እርሱን ከሞት አይመልስም፤ ገነትም አያስገባውም፡፡ በሌላ በኩል ለነዚያ በርሱ ሰበብ ለሞቱና ለተጎዱ ሰዎች ሀዘንን በቅጡ ካለመግለጽ ጀምሮ ምንም ዓይነት መታሰቢያም ሆነ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ አለማድረግ በትንሹ ጭካኔ ነው፤ አንድ መንግሥት እንዲህ ሲሆን ማየት ያማል፤ በጣም ያማል፡፡ የሁላችንም መንግሥት ነው የምንለው በእንደዚህ ያለ ወራዳነት ዘቅጦ ማየት የሰውን ልጅ ብቻ ሣይሆን የመንግሥታትን መዋቅራዊ ምንነት ሳይቀር ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ስንትና ስንት ታላላቅ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በሰው ሲገደሉ እንደዚህ አልተጮኸላቸውም፤ መንገድና መናፈሻ ወይም ት/ቤት በስማቸው ሊሰየም ይቅርና ለአንዴ መታሰቢያ እንኳን ሰባራ ሣንቲም አልተመደበላቸውም – የነሱ ነፍስ ከሀጫሉ አንሶ ወይም የሃጫሉ ነፍስ ከነሱ በልጦ አይመስለኝም – ዘረኝነት ያመጣው ጦስ ጥምቡስ እንጂ – አቢይ እንዲህ ነው፡፡ ስለአቢይ የምትንሰፈሰፉ ወገኖች ከዚህ ምን እንደተገነዘባችሁ ባውቅ ደስ ባለኝ፡፡ በበኩሌ እጅግ አፍሬያለሁ፤ አክራሪ ተቃዋሚን ለማስደሰት ሀገራዊ ኃላፊነትን እስከመዘንጋት መድረስ የወንበር ሱሰኝነትና አድሎኣዊነትን ያሳያል፡፡ ዴሞክራሲ ቢመጣ ዘረኝነትን በካልቾ ለማለት ከዚህ በላይ ምክንያት አይኖረንም፡፡
  2. አቢይ አህመድ አሁን ማንን እየገዙ እንደሆነ ማወቅ ያስቸግራል፡፡ ኦሮምያ የተባለው ክልል ከእጃቸው የወጣ ይመስላል፡፡ ትግራይ ከመነሻውም የርሳቸው አልነበረችም፡፡ ፌዴራል መንግሥቱም በኦነግና በአክራሪ የኦህዲድ አባላት ከተያዘ ሁለት ዓመታት አለፉ፡፡ ጥቃቅን ክልሎችም ጃዋራውያን የሚፈነጩባቸው ናቸው፡፡ እኚህ አሳዛኝ ጠ/ሚኒስትር አየር ላይ ተንሳፍፈው በሚዲያ ስለታዩ ብቻ መሪ ይመስላሉ እንጂ የማዘዝና የመናዘዝ ሥልጣናቸው እስከምን ድረስ እንደሆነ ማወቅ አይቻልም – ከሁለት ያጣ ጎመን፡፡ ሁሉንም ለመሆንና ለመምሰል ሲሉ አንዱንም ሳይመስሉና ሳይሆኑ መቅረታቸው ማስደነቁ አይቀርም፡፡ አስገራሚ ፍጡር ናቸው፡፡ ብዙ ዕውቀት እንዳላቸው መገንዘብ ቢቻልም የራሳቸው የሆነ አቋም የሌላቸው በመሆናቸውና ሁሉንም ለማስደሰት ሲጥሩ ሀገራችንንም በትነው እንዳይጠፉ ያሰጋል፡፡ ሰይጣንንና እግዚአብሔርን በአንድ ጊዜ ለማስደሰት መሞከር እንደማይቻል የማይረዳ ሰው መጨረሻው አያምርም፡፡ እርሳቸውም ሥልጣናቸውን የሚያጡ እየመሰላቸው በደነበሩ ቁጥር አንዴ ከሰይጣን አንዴ ከእግዚአብሔር ለመሆን ሲጥሩ ዕድል በሯን ልትዘጋባቸው አንድ ቅዳሜ ሳይቀራቸው አልቀረም፡፡ በዚያ ላይ የአንዲት ኢትዮጵያ መሪ መሆናቸውን የዘነጉ ይመስላል፡፡ የአማራም መሪ መሆናቸውን ይረሱትና “ኦሮሞ በነፍጠኛ ተጨቁኖ ነበር” በማለት ሁለቱን ሕዝቦች ለማናከስ ይሞክራሉ – ያልታደሉ፡፡ አራት ኪሎ የሚመጣ ሰው ወደ ሥልጣን ለመውጣትና ሥልጣንን ለማደላደል እንደጃዋር የ86 ንጹሓን ዜጎችን ደም በየወቅቱ ለማፍሰስ ሳይሆን የ86 ጎሣና ብሔር ቅን አስተዳዳሪ ለመሆን መጣር እንደሚኖርበት መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ ይሁንና ሥልጣን መጥፎ ነው፤ ያሳውራል፡፡ አቢይንም አሳወረ፡፡

ትግራይ በመቶ ሽዎች የሚገመት ፖሊስና ልዩ ኃይል አላት፡፡ ኦሮሚያ በመቶ ሽዎች የሚቆጠር ፖሊስና ልዩ ኃይል አለው፡፡ አማራም እንዳቅሚቲ ጥቂት ኃይል አያጣም – “መንግሥቱ” ለመጣው ሁሉ ቅን ታዛዥነቱና አጎብዳጅቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ይህን ሁሉ የክልል ኃይል የሚያዘው የየክልሉ ፕሬዝደንት እንጂ አቢይ አይደሉም፡፡ እንደ እውነቱና በመሠረቱም በአንዲት የመጨረሻ ድሃ ሀገር ውስጥ ከመናጢ ድሃ የሚሰበሰብን አነስተኛ ጥሪት ለዚህ ሁሉ ተዋጊ ኃይል ሥልጠናና ደሞዝ፣ የጦር መሣሪያና አልባሳት መሸመቻ ማድረግ የሀገራችንን ችግር እንደምን አድርጎ ጫፍ ላይ እንደሚያደርሰው ተመልከቱ፡፡ ትልቅ አለመታደል ነው – ዓለም አቀፍ ታዛቢስ ምን ይለን ይሆን? “ትለብሰው የላት – ትከናነበው አማራት” ማለት ለኛ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሰውና የሀገር ሀብት ወደ ልማት ቢዞር ቢያንስ ርሀብንና እርዛትን በማጥፋት ረገድ ብዙ ሚና በኖረው ነበር፡፡ አሁን ግን አራሽ ገበሬን ከእርሻው በመነጠል፣ ሙጣጭ የሀገር ሀብትን ከውድመት በቀር አሸናፊ ለማይኖረው የጦር ዝግጅት በማዋል፣ መሬትን ጦም በማሳደር፣ ጊዜንና የትኩረት አቅጣጫን በመጠፋፋት ዐውድ ላይ በማዋል … ሀገርና ሕዝብ ላይ የሚሠራው ሰይጣናዊ ተግባር ሲታይ ኢትዮጵያ በቀጥታ በዲያብሎስ ዕዝ ሥር መገኘቷን ለማመን ተጨማሪ ማስረጃ አያስፈልግም፡፡ እናስ አቢይ ማንን እያስተዳደሩ ነው? የሀገር ጥፋትንና ውድመትን ለመዘገብና በታሪክ ድርሳን ለማስቀመጥ ነው? አንዱ ሌላውን እንዲያጠፋ የዕልቂት ፊሽካ ለመንፋት ነው? ሁሉን ነገር ኦሮሞ ቢቆጣጠርስ ሰላም ከሌለ ምን ይሠራለታል? ሁሉንም ነገር ኦሮሞ ይቆጣጠር ተብሎ በነአቢይ ቢፈረድስ ለማዳና ለሀገር በጎ አስተሳሰብ ያላቸው ኦሮሞዎች ጠፍተው ነው አክራሪ ኦሮሞ ከየሥርቻው እየተፈለገ ወደ ሥልጣን የሚመጣውና ሕዝብን እንዲያስለቅስ፣ ሀገርንም እንዲያፈርስ የሚደረገው? በዚህ ሂደት የነብርሃኑ ነጋ ሚና ምንድን ነው? “በማንኛውም መንገድ ወያኔን ከአራት ኪሎ ማስወጣት” ይሉት የነበረው የትግል ሥልት በዚህ ይሆን የተቋጨው? እንደሚባለው እነብርሃኑም ከኢትዮጵያዊነት ጋር ጥል ይኖራቸው ይሆን? ሀገራዊው ሾተላይ ተባብሶ መቀጠሉ አስደንጋጭም አሳሳቢም ነው፡፡

  1. ዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ፡፡ ኮሮና በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ነው፡፡ ከዓለም አገሮች 160ኛና 170ኛ የነበረችው ሀገራችን አሁን ወደ 71ኛ ወርዳ ከ15 ሽህ በላይ በቫይረሱ የተያዙና ከ250 በላይ የሞቱ ሰዎችን አስመዝግባለች – አንዳች ኃይል ይህን በሽታ እያሰራጨ ይመስላል፤ ኤርትራ እንኳን 300 የሚጠጋ ሰው ተይዞባት እስካሁን አንድም ሰው አልሞተባትም፡፡ ትልቅ ዕድለኛ በዚህ ረገድ ዩጋንዳ ናት – ከአንድ ሽህ አንድ መቶ አካባቢ ተያዥ እስካሁን ባለው መረጃ የሞተባት ሁለት ብቻ ነው፡፡ ጣሊያን ከአንደኛነትና ከሁለተኛነት ወጥታ ወደ 15ኛ ደረጃ ስትወርድ እኛ የርሷን ደረጃ ለመሻማትና ከዚያም ወደ አሜሪካን ቦታ ለመድረስ ውድድሩን እያፋፋምነው እንገኛለን – ዕድሜ ለነጃክማን፡፡ ፍርሀትና ድንጋጤያችንንም በመጀመሪያው ጨርሰን አሁን ምንም አንፈራም፤ አንደነግጥምም፡፡ “በካፊያው ጊዜ ከቤት ተደበቅን፤ በዶፉ ጊዜ ከቤት ወጣን” አለ አንድ ታዛቢ – እውነቱን ነው፡፡  በቀን አምስትና ስድስት ሰው በቫይረሱ በሚያዝበት ጊዜ ፈርተን ከቤት አንወጣም ነበር፤ አሁን በቀን 600 እና 700 ሲያዝ ካለበቂ ጥንቃቄ በድፍረት በከተሞቻችን እንንሸራሸራለን – ነገረ ሥራችን ሁሉ በፖለቲካውም ሆነ በሌሎች መስኮች የተገላቢጦሽ ነው፡፡ “ሚስቴን ከወንዙ ወደላይ እንጂ ወደታች እንዳትፈልጓት!” አለ አሉ ነገረ ሥራዋ እንደዘመኑ ኢትዮጵያውያን ሆኖ ክፉኛ ታስቸግረው የነበረች ባለቤቱን ጎርፍ የወሰደበት ባል ለጎረቤቶቹ፡፡ ወዶ አይደለም፡፡
  2. እናጠቃልል፡፡ ጨለማው በርትቷል፡፡ መፍትሔው የራቀ ይመስላል፡፡ ግን እንዲህ ጨለማ ሲበረታ አንድ ነገር መጠርጠር ነው – ጨለማ የሚሸነፍበት የብርሃን ቀን መቃረቡን፡፡ በመሠረቱ የጨለማው ብርታት መነሻ በዋናነት የክፋታችን መብዛት ነው፡፡ ከላይ እስከታች፣ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ጠፍተናል፡፡ በሀሰት ንግግር እንደጣቃ የሚተረተር መሪ ይዘህ፣ ከፈጣሪ ህግና ትዕዛዝ የወጣ ለታይታው የሚያስመስል በሕይወቱ ግን የአጋንንት ጭፍራ የሆነ የሃይማኖት መሪና አገልጋይ ካህናትን ይዘህ፣ በባህታዊና በአጥማቂ ስም በሰይጣናዊ የአፍዝ አደንግዝ (abracadabra)  መተታዊ ፈውስ የሚያጭበረብሩ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው የሃሳዊ መሢህ ወኪሎችን ይዘህ፣ ከእውነት ጋር የተጣሉና በሙስና የበሰበሱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ወታደራዊ መሪዎችን ይዘህ፣ ለራሱ ሳያውቅ ዜጎችን አስተምራለሁ የሚል የዕውቀት ፀርና የድንቁርና ወዳጅ መምህርና የትምህርት ማዕከላትን ይዘህ፣ ከሞራልና ከባህል ዕሤቶች የተጣላ ጠፍ ትውልድ በዙሪያህ አሰልፈህ፣ የዓለም አቀፍ ኢሉሚናቲ የሚቆጣጠረውና ከነሱ ዓላማና ተልእኮ ቢያፈነግጥ ይደርስብኛል ብሎ የሚያስበውን ጫና ላለመጋፈጥ ለነሱ የሚንበረከክ የመንግሥት መዋቅር ይዘህ… የትም መድረስ እንደማትችል በተለይ ያለፉት 30 ዓመታት በቂ ምስክር ናቸው፡፡ ችግሮቻችን በዓይነትም ሆነ በብዛት እጅግ ጥልቅና ውስብስብ መሆናቸው የታወቀ ነው፤ መፍትሔው አንድዬ ብቻ ነው፡፡ ጠንክሮ መጸለይ ነው!!
  3. ንጋት ግን እየመጣ ነው፡፡ ሲነጋ ኢትዮጵያውያን ወደ አራት ኪሎ ይገባሉ፡፡ ያኔ ዘርና ጎሣ ወደ ሰገባቸው ይከተታሉ፡፡ የአሁኑ ታሪካችን ለልጆች ማስፈራሪያነት የሚጠቅም ላንቲካ ይሆናል፡፡ ይህ በግልጽ ይታየኛል፡፡ አሸናፊው ማን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የአጭበርባሪዎችና የከሃዲዎች ዘመን ያበቃል፡፡ ሊነጋ ሲል ደግሞ መጨላለሙ ግልጽ ነውና ይህ ድቅድቅ ጨለማ የሚጠበቅ ነበር፡፡ ገና ከዚህም በላይ ብዙ የክፋትና ርኩሰት ድርጊቶችን እናያለን፡፡ ብዙ ዕልቂት ይመጣል፡፡ ወደ ፈጣሪ በቶሎ ተመልሰን ካለቀስን ግን አመክሮ ሊደረግልን እንደሚችል የበቁ አባቶች ይናገራሉ፡፡ አለዚያ የተነገረ አይቀርምና ዳገቱን ካልወጡም ሜዳው ላይ አይደረስምና ለሁሉም መዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ሟርት አይደለም፡፡ በግልጽ የሚታይ ነገር ነው፡፡ አቢይና በአክራሪ ኦሮሞ የተሞላው “መንግሥታችን” እያቀላጠፉት ያሉት ዘመቻ ከጨለማው ገዢ የታዘዙትን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከምድረ ገጽ የማጥፋት ተልእኮ ለማስፈጸም ነው፡፡ ወደውም አይደለም፡፡ በርኩስ መንፈስ ስለተያዙ ነው – በነፍሳቸው ተወራርደው ነው ይህን አቢይ ተልእኮ እየተወጡ የሚገኙት፡፡ እንጂ ዲሣሣ የገደለውን የሀጫሉ ደም ለመመለስ አጥናፉን በተኛበት ከነሚስትና ልጆቹ መግደል ማለት ዶሮ ማነቂያ ላይ የጠፋችን ስሙኒ መብራት ስለተመቸው ብቻ ቸርችርል ጎዳና ላይ እንደመፈለግ ያለ የዕብድ አይሉት የሰካራም ጅላጅልነት ነው፡፡ በቃ፡፡ ዋናው  ነገር ኢትዮጵያዊ ነኝ የምትይ ሁሉ ከነአቢይና ታከለ ኡማ ገጀራ ለመትረፍ በሥጋም በመንፈስም ተዘጋጂ!! በንግግርም አንሞኝ፡፡ በንግግር ማማር ቢሆን በአቢይ ምራቅ የሚያስውጥ ዲስኩር ይሄኔ በዴሞክራሲና በልማት ዓለማችንን በቀጨን ነበር፡፡ ሴተኛ አዳሪዋ ጨርሳዋለች – “አጭበርባሪ አይተኛኝም!” ብላ፡፡ እኛ ከዚህች ምስኪን ሴት ማነስ አለብን? ወያኔ እንኳን ያልደፈራቸው ንግድ ባንክና አየር መንገድ በአክራሪው የኦነግ ኃይል ሲሽመደመዱ፣ በጠራራ ፀሐይ ከ23 ያላነሱ ባንኮች ሲዘረፉ፣ ፌዴራል መንግሥቱ ምንም ትምህርትና ዕውቀት በሌላቸው ደናቁርት ዘረኞች ሲጥለቀለቅ፣ ከሥልጡኑ የአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር በአስተሳሰብና በቋንቋ መግባባት የማይችሉ የትራፊክ ፖሊሶች ሣይቀሩ ከተማዋን ሲያደናቁሩ፣ ፍትህ ርትዕ በአፍ ጢማቸው ሲደፉ፣ የመንግሥት ፕሮጀክቶች የባለሥልጣናት መምነሽነሻ እየሆኑ ድሃው ሕዝብ መሠረታዊ የህክምና አገልግሎት እንኳን እያጣ በጠበሎች ሲንከራተትና ለአባይ ጠንቋዮች ሲሳይ ሲሆን  … የአቢይ መንግሥት ቻድና ማሊን የሚያስተዳድር ይመስል ለምን ዝም ያለ ይመስላችኋል? ሁሉም ለዓላማ ነው – ለበጎም ጭምር፡፡ ልክ እንደ ሕወሓት ሁሉ ኦነግ/ኦህዲድም ብዙ ጠያፍ ታሪክ እያስመዘገበ ነው – ሊያውም ገና በሁለት ዓመት ተኩል ዕድሜው፤ በክፍያው ወቅት እንዳንቸገር ታዲያ አእምሯችንን ከአሁኑ እናሠራውና መጠንቀቅ ያለብን ወገኖች እንጠንቀቅ – የማይከፈል የዕዳ ቁልል እንደሌለ ደግሞ ከደርግና ከወያኔ እንዲሁም ከቀደመው የዐፄዎቹ መንግሥታት ልምድ እንቅሰም፡፡ ማንም ቢሆን ያልዘራውን አያጭድም፤ የዘራውም ተበትኖ አይቀርም፡፡ አልሰማንም እንዳንል!!!!!!

EMAIL: gb5214@gmail.com

Filed in: Amharic