>
11:30 am - Saturday April 1, 2023

የክልል ልዩ ታጣቂ ኃይል ይፍረስ፤ በዘር ተደራጅቶ፣ በዘር የታጠቀ፣ የዘር ፍጅትን ያፋጥናል...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የክልል ልዩ ታጣቂ ኃይል ይፍረስ፤ በዘር ተደራጅቶ፣ በዘር የታጠቀ፣ የዘር ፍጅትን ያፋጥናል…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

የጎሳ ፖለቲካ ጡዘት ሰማይ በነካበት እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገር ውስጥ በብሔር የተዋቀረ የክልል ታጣቂ ልዩ ኃይል ወይም ሚሊሻ ማደራጀት ማለት የተጠመደ ፈንጅ በጀርባ አዝሎ እንደመዞር ነው። ክልሎች በአገር ውስጥ ያሉ አገሮች ሆነው ተዋቅረዋል። በዛ ላይ አወቃቀራቸው ቋንቋና ብሔርን መሰረት ያደረገ ነው። የብሔር ፖለቲካው እያመሳት ላለች አገር በብሔር የተደራጁ ታጣቂ ኃይሎች እያሰለጠኑ እና እያስታጠቁ በየክልሉ ማስቀመጥ ካየነው በላይ ብዙ ግፍ እንድናይ እና ኢትዮጵያንም በቀላሉ ወደ ዘር ተኮር ግጭት ከመውሰድም በላይ የአክራሪ ቦድኖች መፍለቂያነት እና ወደ ሽብር ቀጠና ሊለውጣት ይችላል። ከወዲሁም አንዳንድ ምልክቶች በግላጭ እየታዩ ነው፤
– በክልሎች መካከል ያለው ውጥረት እና ትከሻ መለካካት በየጊዜው ግጭቶችን አስከትሏል። አሁንም ተፋጠው፣ ጉድጓድ ምሰው እና ቃታ ስበው ለፍልሚያ ቀን የሚጠብቁ አሉ። ለዚህም የትግራይና የአማራ ክልል ፍጥጫ ጥሩ ማሳያ ነው።
– በብሔር የተዋቀረ ጦር የብሔር ግጭት በተበራከተበት አገር ወግኖ ባይሰለፍ እና ከሱ ብሔር ውጭ ያለውን ወገኑን ባያጠቃም እንኳ ከጥቃት አያስጥልም። ምክንያቱም እሱ የሰለጠነው፣ የተማረው፣ የተነገረው እና የታጠቀው የራሱን ብሔር ሕዝብ ለመከላከል ብቻ ነው። ኦሮሚያ ክልል ውስ በተደጋጋሚ እንዲሁም በአንዳንድ ክልሎች አልፎ አልፎ የተስተዋለው ይሄው ነው። በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በተፈጸመው ብሔር እና ኃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋ የክልሉ ታጣቂዎች ጥቃቱን ከማስቆም ይልቅ በተለያየ ደረጃ ተሳታፊዎች እንደነበሩ መረጃዎች አረጋግጠዋል፤ መንግስትም መስክሯል። የክልሉ ታጣቂዎች ትዕዛዝ አልደረሰንም በሚል ጥቃቱን ቆመው አይተዋል፣ አንዳንድ ስፍራ ነዋሪዎች እራሳቸውን ከጥቃት እንዳይከላከሉም የነዋሪዎቹን ሕጋዊ መሳሪያ ከሰዓታት በፊት ቀድመው አስፈትተዋል፣ አንዳንድ ቦታ ለቄሮዎቹ መሳሪያ በመስጠት ጥቃት አስፈጽመዋል፤ እንዲሁም ለአጥፊዎቹ ከለላ መስጠት እና ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ የማድረግ ተግባርም ፈጽመዋል።
እነዚህን መሰል ችግሮች እዛው ኦሮሚያ ክልልም ሆነ ሌሎች ሥፍራዎች ዳግም ላለመፈጠራቸው ምንም ዋስትና የለም።
መፍትሔ…!!!
1ኛ/ ከክልል ፖሊስ በስተቀር ያሉ የክልል ልዩ ኃይል እና የሚሊሻ አደረጃጀትች ሙሉ በሙሉ ከክልሎች እጅ አውጥቶ በፌደራል መዋቅር ስር ማድረግ፣
2ኛ/ በብሔር የተዋቀረውን የጸጥታ አስከባሪ ኃይል ሙሉ በሙሉ በመበታትን ወደ ሁሉም የአገሪቷ ክፍል ማሰባጠር እና በእያንዳንዱ ክልል ውስጥ ያለው ታጣቂ ኃይል ከሁሉም ብሔር የተወጣጣ እንዲሆን ማድረግ፣
3ኛ/ በየክልሉ ያለውን ስብጥር ኃይልን በበላይነት የሚመሩትንም አዛዦች እንዲሁ በተሰባጠረ መልኩ ሚዋቀር፣
4ኛ/ ይህን ኃይል በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት አይምሯቸው ውስጥ ያለውን የብሔረተኝነት ስሜት በሂደት እንዲቀይሩና ያለመድሎ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ደህንነት ዘብ እንዲቆሙ ማድረግ።
ክልሎችም ያንጃበበውን አደጋ ከወዲሁ አጢነው ለዚህ ለውጥ መሳካት ካልተባበሩ በዘር ያደራጁት የታጠቀ ኃይል ተንሸራቶ አክራሪዎች እጅ የወደቀ ዕለት የመጀመሪያዎቹ የጥቃት ኢላማዎች እነሱ መሆናቸውን ሊያጤኑት ይገባል። በዘር ተደራጅቶ በዘር የታጠቀ የዘር ፍጅትን ያፋጥናል።
ይህን ለማድረግ ግን ወሳኙ ነገር የአገዛዝ ሥርዓቱ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና ያንጃበበውንም አደጋ በበቂ ሁኔታ መረዳትን ይጠይቃል። ይሄን የተጠመደ ፈንጂ ሳያመክኑ በጀርባ አዝለው እየዞሩ ኢትዮጵያ አትፈርስም ማለት ብቻውን አደጋውን አያስቀረውም።
Filed in: Amharic