የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ወቅታዊ መግለጫ!
ሁሉንም የፖለቲካ ሀይሎች ያላካተተ ውይይት ሲጀመር የከሸፈ ነው:: ከቶውንም አገራዊ መግባባትን አያመጣም !!!
መንግስት ከሰሞኑ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚል የጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት ከመረጣቸው /ጠቅላይ ሚንስትሩ ቀልባቸው ከወደዳቸው/ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ብቻ ንግግር ማድረጉን ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን ፖርቲያችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ተከታትሏል። በዚህም ጉዳይ ላይ ፓርቲያችን ተወያይቶ ተከታዩን ዕይታ እና አቋም ይዟል።
አገራችን ኢትዮጵያን፣ ወደ ብሔራዊ መግባባት እና ልማት ይወስዳታል ተብሎ በህዝባችን እምነት ተጥሎበት የነበረው ከ2010 ዓ.ም መጨረሻ የጀመረው የለውጥ ሽግግር የመቀልበስ አደጋ አጋጥሞታል። ትናንት የነበርንበትን ሁኔታ የሚያስንቅ ተረኝነት እና የዜጎች ሰላም ማጣት ውስጥ ገብተናል። በዓለም ሶስተኛ ታላቋ የዲፕሎማት ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ብቻ ለሶስተኛ ጊዜ የህይወት መጥፋት እና ንብረት ውድመት ተጋልጣለች። ከትናንቱ ጉዳት ይልቅ የነገው ዕጣ ፈንታችን እጅግ ያሰጋናል። አገራችን በኦህዴድ/ብልፅግና ፓርቲ ዘመን፣ ዜጎች በላባቸው ያፈሩትን ሃብት በጠራራ ፀሐይ የሚያጡበት፣ ሴቶች የሚደፈሩበት እና ወንዶች የሚታረዱበት የምድር ሲኦል መሆኗን እየታዘብን ነው።
ከዚህ አሳዛኝ፣ አገራዊ እንዲሁም ትውልዳዊ ምስቅልቅል ውስጥ እንዴት መውጣት እንዳለብን ራዕይ አልባ የሆኑት ገዢዎቻችን፣ ትናንት የትህነግ ሎሌ የነበሩ እና ዛሬ ደግሞ ከመንግስት የሚሰጣቸውን አበል ብቻ የሚያስቡ የፖለቲካ አመራሮችን ፊት ወንበር ላይ አስቀምጦ የአገሪቱን ችግር ለመፍታት የተያያዘው ድራማ፣ የሽግግሩ ትልቁ ቀልድ ሆኖ አግኝተነዋል።
መንግስት በሃሳብ ገበያ ተወዳድሮ እንደማያሸንፈው የተረዳውን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን፣ ሕግ ማስከበር ተስኖት በአዲስ አበባ ከተማ ለደረሰው ጉዳት በፈጠራ ወንጀል ያለአንዳች ማስረጃ ተጠያቂ ለማድረግ አመራሮቹን እስር ቤት በመከርቸም፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቀልባቸው ከወደዳቸው ፓርቲዎች ጋር ብቻ ተሰብስቦ “ስለብሔራዊ መግባባት” ተወያየን መባሉ፣ ከመነሻው የከሸፈ ሂደት ሆኖ አግኝተነዋል። ፓርቲያችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ልጆች መካከል ተለይቶ እንዳይሳተፍ መደረጉ፣ ዜጎች በማንነታቸው እና አመለካከታቸው ምክንያት በየቦታው በኦህዴድ/ብልፅግና ፓርቲ የሚደርስባቸው መድሎ ነፀብራቅ ሆኖ አግኝቶታል። ከሂደቱ መገለላችን ለአገራችን ሰላሟ የሚጠቅም እርምጃ ቢሆን፣ ፓርቲያችን በደስታ የሚቀበለው በረከት አድርጎ ይቀበለው ነበር። ነገር ግን ከ10 ሚሊዩን በላይ የሆነው የአዲስ አበባ ህዝብ ልብ ውስጥ ያለውን ፖርቲያችንን በማሰርም ሆነ በማሸማቀቅ፣ የከተማውን እና የአገራችንን ችግር መፍታት እንደማይቻል የመጣንበት ሂደት በራሱ ይመሰክራል።
በዚች አገር እውነተኛ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት ከተፈለገ፣ መንግስት የሚፈልገውን፣ የመሪዎችን ፊት እያዩ አቋሙን ከሚደግሙ ቡድኖች ጋር ሳይሆን፣ እንደ ባልደራስ፣ ለአገራችን የሚያስፈልገውን አማራጭ ከያዙ የህዝብ ድርጅቶች ጋር ለመነጋገር መንግስት ወኔው እና ቁርጠኝነቱ ሊኖረው ይገባል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አገራችን ከገባችበት ከፍተኛ ግጭት እና የፖለቲካ ውጥረት እንድትወጣ ከብሔራዊ መግባባት ውጪ አቋራጭ መንገድ የሌለ መሆኑን በመረዳት ተከታዩን ምክረ ሃሳብ ለመንግስት እና ለተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ያቀርባል፣
1ኛ. ከብሔራዊ መግባባቱ በፊት ካለማስረጃ የተያዙት የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም እና የፓርቲው አባል የሆነው ገነነው አበራ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣
2ኛ. በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ በቀኝም ሆነ በግራ የኃይል አሰላለፍ ውስጥ ያሉ ህዝብ የሚደግፋቸው የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ጥሪ ተደርጎላቸው የውይይቱ አካል እንዲሆኑ፣
3ኛ. ጉዳዩ የሚያገባቸው የሲቪክ ማህበራት እና የኃይማኖት አባቶች የሂደቱ አካል እንዲሆኑ ጥሪ እንዲደረግላቸው።
ከዚህ በተረፈ ግን መንግስት አሁን በያዘው አካሄድ እቀጥልበታለሁ የሚል ከሆነ፣ በአገራችን እውነተኛ ብሔራዊ መግባባት ካለማምጣቱም ባሻገር፣ ያለውን ፖለቲካዊም ሆነ የደህንነት ውጥረት የበለጠ እያባባሰው የሚሄድ መሆኑን ፓርቲያችን ማስገንዘብ ይወዳል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ!
ሰኔ 27 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ