>

እየተለመዱ ያሉ ለአራጆች ጉልበት የሆኑ አጓጉል  አባባሎች...!!!! (አባይ ነህ ካሴ)

እየተለመዱ ያሉ ለአራጆች ጉልበት የሆኑ አጓጉል  አባባሎች…!!!!

አባይ ነህ ካሴ
– ”  ስትገድሉን እንበዛለን!”  [እንድንበዛ ግደሉን ማለት ይመስላል። ወይም የምንበዛው ስንገደል ነው ዓይነት መልክ አለው። ገዳዮችን የሚያበረታታ ሟቾቹን የሚያዘናጋ እንዳይኾን።]
– “ክርስቲያን እና ሚስማር ሲመቱት ይጠብቃል!”
 [ዝኒ ከማሁ። ለመጠንከር ዱላ ያስፈልገናል ብሎ መመኘት ይመስላል።]
ቤተ ክርስቲያን ፈተና ሲገጥማት አጽናኝ መልእክት ሊያስተላልፉ የሚወድዱ አንዳንድ ሰዎች አባባሎቹን ያዘወትሯቸዋል። ከዐውዳቸው ውጭ እየተጠቀሱም ይሁን ያለብንን ፈተና ካለመረዳት ብዙ ጊዜ ተደጋግመው ይነገራሉ። ቢነገሩም አይሰቡኝም። አልተሰባኝም ማለት ከልቤ አልተዋሐደም ከአስተሳሰቤ አልተጣጋልኝም ማለት ነው።
በሃይማኖት ምክንያት ሞትም ሌላም መከራ ሲመጣ በአኮቴት መቀበልና አላግባብ እየዘለሉ ወደ መሞት መግባት አንድ አይደለም።
ከተቻለ በመከራ ጊዜ ጠንክሮ መገኘት እንጅ መናገሩ ብቻ አያጠነክርም። ግደሉን እያሉ በመሞትም ሰማዕትነት አይገኝም። ካዱ አለበለዚያ እንገድላችኋለን ሲባል አንክድም ብንሞት ወይ ብንሰቃይ እንኳ ማለት ሰማዕትነት ይባላል። ከታናሽ እስያ (የዛሬዋ ቱርክ) እስከ መካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ በክርስትና የረሰረሰ ምድር ነበረ። ስንት ደማቅ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያበቡበት ምድር የዛሬ ገጽታው ሌላ መኾኑን እናዘክር። ያ ሁሉ የክርስቲያን ምድር የተፈታው በገዳዮች መኾኑን ማን ይናገር? የእነዚያ ሁሉ ክርስቲያኖች ሀገራት ነበሩን? ያሰኛል።
“ቀኝህን ለሚመታህ . . . ” ምን ማለት ነው?
“. . . ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ኹለተኛውን ደግሞ አዙርለት” (ማቴ ፭ ፡ ፴፱።) የሚለውን ቃል በነጠላው እየተረጎሙ የተዛባ ቁመና ላይ የወደቁ ጥቂቶች አይደሉም።
አበው ሊቃውንት የቃሉን ትርጉም እንዲህ ይገልጡታል። ፈቃደ ሥጋህን ተው ቢልህ ፈቃደ ነፍስህን ተውለት። ከዚህ አናጥቦ ጥቃት ቢደርስብህም ደጋግመህ ተጎዳ እንጅ ራስህን ትከላከል ዘንድ አልተፈቀደልህም ማለት ኢ-ኦርቶዶክሳዊነት ነው።
በአጭሩ ቃሉ ትሩፋት ስለማድረግ እንጅ ስለ ዱላ የተነገረ አይደለም። ከተጠየቅኸው አትርፈህ ምግባረ ጽድቅ ፈጽም ማለት ስትጠቃ ዝም በል ተብሎ የሚነገርበት ምንም መጽሐፋዊ ምክንያት የለም።
ማሳሰቢያ ፡-  ቀኝህን ለሚመታህ ግራህን ደግሞ አዙርለት የሚለውን ቃል አንዳንድ ሰዎች ጊዜው ያለፈበት ጥቅስ ሲሉ ታዝቤአለሁ። ቃለ እግዚአብሔር ነውና እንደ ታሸገ ምግብና መድኃኒት የተገደበ የአገልግሎት ጊዜ (expiry date) የለበትም። ቃሉ ዘለዓለማዊ ነውና። አለቦታው አይጠቀስ ማለትና አልፎበታል ማለት አይገናኙም። እናም እየተስተዋለ።
Filed in: Amharic