>

ምክን ትውልድ (ኤልያስ ደግነት)


ምክን ትውልድ

ኤልያስ ደግነት


ኢትዮጵያ ሀገራች በዘመኗ ካሳለፈቻቸው እጅጉን ክፉ ከሚባሉ ወቅቶች ሁሉ አንደ አሁን የከፋ እና የከረፋ መከራ እና ስቃይ ያየችበት ወቅት አለ ቢባል ለማመን ይቸግራል፡፡ በአንድ በኩል ዘመን አመጣሹ ደዌ በሌላ በኩል ደግሞ አሳፋሪው የዘር ፖለቲካ እና ውጤቱ…ደግሞ በሌላ ገጽ የግብፅ ለኢትዮጵያ አልተኛም ማለት እን የህወሓት ሽማግሌዎች አብሪትና ተንኮል  ተደማምረው የሀገርም የወገንም ራስ ምታት ሆነዋል፡፡

ሀገር እንዲህ የጭንቅ ምጧን በምታምጥበት ወቅት …ቀበቶን ፈትቶ ማሪያም ማሪያም እያሉ ወደ ፈጣሪ ከመማፀን እና ነጋ ጠባ  በስራም  በፀሎትም እየተጉ  ከገባችበት የችግር ሰርጥ ውስጥ ትወጣ ዘንድ ቅዱስ ቅዱሱን እንደመመኘት ውሃ ሆነው በቀሩ የሚያስብሉ ልጆቿ በምጧ ላይ የጋለ ብረት ይሰዳሉ፡፡

ሀገር መልኳ ለጆቿ ናቸው፡፡ብሩክ አመለካከት፣ሸጋ ግንዛቤ፣ቅን ልቦና፣ያላቸው ልጆች የሀገራቸው ሌላኛው መልክ ናቸው፡፡በተመሳሳይ መልኩም የነገር እሳት ለመጫር ክብሪት በኪሳቸው እብሪት….በልባቸው ይዘው…ሀገር ለማፍረስ ህዝብ ለማተራመስ …መንገድ ዝጋ…መንገድ ክፈት ….እንዳይገባ …እንዳይወጣ …ፍለጠው …ቁረጠው …ኦሮሞ ነው….አማራ ነው ….ትግሬ ነው …ዝባዝንኬ ቅብርጥሴ የሚሉትም ያው አሳዳጊ የበደለው ተብለው ሀገር በእነሱ ትሰደባች፡፡

ያደላቸው ሀገሮች ዜጎቻቸው በዓለም ላይ የሀገራቸውን ስም በወርቅ ያፅፋሉ፡፡እኛ ሀገር ያሉቱ ደናቁራን ደግሞ በዓለም መዝገብ ስሟን በወርቅ አጽፈው …ለፍተው ጥረው ያፈሩትን ጠሪት ወደ  ሀገር ቤት አምጥተው  ወጣቱ የዕለት ጉርሱን፣የዓመት ልብሱን ይችል ዘንድ የፈጠሩለት የስራ ዕድል በአንድ ጀንበር ዶግ አመድ ያደርጉታል፡፡ ከዚህ ወዲያ እንዴት ያለ መምከን አለ…ኤዲያ

ከዚህ ሁሉ ልቆ ልብንም የሚሰብረው…አእምሮንም የሚኮሰኩሰው…ህሊናንም እረፍት የሚነሳው አወቅን በቃን ነቃን የሚሉ በሰለጠ ዓለም ኑሮው በጠበት አስተሳሰብ  ታንቀው ሊሞቱ የደረሱ ምሁር ተብዬ ሰዎች ጉዳይ ነው፡፡እዛ የሰው ሀገር ለዚያውም ቢለጉሟቸውም ቢጭናቸውም እንዲች ብለው ትንፍሽ በማይሉበት የባዳ ሀገር ቁጭ ብለው …የአንዲትን ምስኪን ባልተቴ ያዘመመ ጎጆ እንዲቃጠል ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡ እዚህ ያሉትም የሰው መንጋዎች ለምን …እንዴት …ወዴት  የሚል አገናዛቢ መጠይቅ እንኳ ሳያነሱ ደም ለጠማቸው …ፅንፈኛ የዘር ፖለቲካ አራማጅ ጌቶቻቸው ይሁነኝ ብለው ወደው ፈቅደው  ይጋለባሉ፡፡ እንዲህ ያለ መምከን መቼም የትም ዓለም ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡

ሰው በፖለቲካ አመለካከቱ ቢለያይ እንኳ አንድ በሚያደርገው ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መቼም ቢሆን ሊለያይ አይችልም ነበር፡፡አንድ ቤት ያሉ ልጆች ቤት ውስጥ ባለ አንዳች ቁስ ቢጣሉ ወይ ባይግባቡ መቼም ቢሆን ተነስተው የቤታቸውን ቋሚ እና ወጋግራ አያቃጥሉም፡፡በአንፃሩ እነዛ ሰው ከመሆን ማማ ላይ ወርደው እጅጉን ከራቀው የአስተሳሰብ የዝቅጠት ወለል ላይ የተገኙ ምሁር ተብዬ ልቅልቅ ሊቆች በአልበላውም ጭሬ ልድፋው ህሳቤ እኛ ወይ የእኛ ሰው ሀገሪቱን ካልመራ ትውደም …..ልማቷም ዕድገቷም  አይቅደም …ቢፈልግ ገደል ይግባ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ሌላው ቢቀር የዘመናት ቁጭታችን …የዓመታት ብሶታችን በሆነውን በዓባይ ጉዳይ እንኳን ….ለጥፋት እና ለእልቂት በበረቱት መጠን አንዳች እንኳ ትርንፍስ ሲሉ አልታዩም፡፡ እንደው ለነገሩ ይህን አነሳሁት እንጂ ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ እንዲሉ …ሰለ ዓባይም ሆነ ስለ ሌላ ተያየዥ የልማት አጀንዳዎች ምንም ማለት ባይችሉ እንኳ ሌላ ነገር ባለመናገር ልቅ አፎቻቸውን እየከፈቱ በዶ ጭንቅላታቸውን በየ አደባበዩ እያሰጡ ተገምተው ሀገር ባያስገምቱ  ይሻል ነበር፡፡

አበቃሁ 

ሀገሬንም ሕዝቤንም አምላክ ይጠብቅ!!

 

Filed in: Amharic