>

አለንጋና ምስር...!! (አዳም ረታ)

አለንጋና ምስር…!!;

አዳም ረታ

. . እጃቸው ያየሁት አይነት ሸካራ አይደለም፡፡ እግሬ ላይ ሲያሳርፉት ጠንካራነቱ ይጠፋል፡፡ ፊታቸው አተኮረ፡፡ በዚህ ለስ ባለ ምሽት በትንሹ ላብ ላብ ይሸታሉ፡፡ ጺማቸው ይሆናል…. በጠላ ረጥቦ እንደባና ሲተነፍግ፡፡ እጃቸው እግሬ ላይ በቀስታ እየተንሸራተተ ከፍ ዝቅ ይላል፡፡
‹‹ምን ስታደርግ ተሰበርክ?›› አሉኝ፡፡
‹‹ሠላማዊ ሰልፍ››
‹‹እ….. ሠላማዊ ሰልፍ››
‹‹ለምንድን ነው ልጄ?›› አዩኝ፡፡ ዝም ማለቴን ሲያዩ ቀጠሉ፡፡
‹‹ሠልፉን ማለቴ ነው››
ምን እንደምመለስ አላወቅሁም፡፡ የጠየቁኝን ከመመለስ ይልቅ ሠላማዊ ሰልፉ መሐል የተሰማኝን ደስታና የሚጣፍጥ የስካር ስሜት ብነግራቸው ደስ ይለኛል፡፡ ታዲያ መሠለፍ ትክክል ያልሆነ ጉዳይ ከሆነ ለምን ደስ ይላል፡፡ ስሜቱ ደስ ካለ መነሻውም ……
‹‹እኔ እንኳን ሳሽ ብዙ አላሳምምም…… አይዞህ….. ስጠይቅህ አልሰማኸኝም?››
‹‹እ….. ሰምቻለሁ››
ግርማና ሴትየዋ በዝምታ ያዩናል፡፡
‹‹የእንዳልካቸው ካቢኔ እንዲወርድ›› አልኩ፡፡
‹‹ምን አደረገ?›› አሉ
‹‹ያው እንደሌሎቹ ነው፤ ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም ይለ የለ ተረቱ››
‹‹መቼ ታየ? እውነቴን ነው፡፡ ማነው ጉልቻ ማነው ወጡ? እኔ ቦተሊካ አላውቅም… ግን አንድ ሰው መታየት አለበት፡፡ ቁምነገረኛነቱ መታየት አለበት፡፡ በወር በሁለት ወር የአገር ሰው አይለካም፡፡ እንደው፣ በደሙ በዘሩ . . . ››
‹‹አገሪቷ በዘር ነው የምትገዛው›› አልኳቸው አቋርጬ፡፡
‹‹ተወኝ፡፡ መልከዔኛ አበረኛ ነው››
‹‹ምን ማለት ነው?››
ቆንጆ ነገር እንከን አይጠፋበትም እንደማለት ነው››
ዝም አልኩ፡፡ መከራከር አልፈለግኩም፡፡
‹‹ቅባት አለሽ የኔ ልጅ?›› አሉ፡፡
ቶሎ ተነስታ ወደ ጓደ ገባች፡፡
‹‹አሁን ያለው አስተዳደር ጥሩ ነው ይላሉ እርስዎ?›› አልኩ እየፈራሁ እየቸርኩ፡፡ የታመመ እግሬን ይዘዋል፡፡ ምናልባት የማይወዱትን ነገር ተናግሬ እጃቸው አውቆትም ሆነ ሳያውቀው በሃይል ቢጨምቀኝ…..
‹‹የሚረባስ አይደለም… የኖርንበት አይደል፡፡ በዚህ ዕድሜዬ አገሬ የሰጠችኝ ነገር ሰካራምነት ነው፡፡ ይሄን የወጌሻ ሙያ የሰጠኝ እግዜር ሰው እንድረዳበት ነው…. ገንዘብ እንዳገኝበት አልነበረም፡፡
ገንዘብ አስከፍዬበት ገንዘቡም ለጠላ ነው፡፡ ያለዓላማህ የሚያሰራህ ዘመን ነው ያለው፡፡ አንዳንዴ ምን እንደምመኝ ታውቃለህ? ዕውነቴን ነው ሰክሬ አይደለም፡፡ ትንሽ ራብ ሲለኝ ዱቤ መጠየቁ ሲያበሳጨኝ …. ምናለ የአዲስአባን ሕዝብ እግሩን
በሰበረልኝ እላለሁ፡፡ ወድጄ አይደለም፡፡ ለራሴም ይገርመኛል፡፡
እግሬን ትተው ወደመቀመጫቸው ተመለሱ፡፡ ታጥፎ የነበረ ወገባቸውን የመለሱት ከተቀመጡ በኋላ ነው፡፡ እኚህ ሰውዬ በዕውን አርጅተዋል፡፡
‹‹ለእኔ ተማሪ ጮሆ የትም የሚደርስ አይደለም….. መድረሻ የለውም›› አሉ፡፡
‹‹አንቱ ደግሞ ምን ያውቃሉ?›› አለ ግርማ፡፡
‹‹ተይ ሐይለስላሴን ቀላል አረግሻቸው?››
‹‹ምን ይታወቃል? . . . እሱ የማያመጣው የለም››
‹‹የእግዜር መንግስት ነው . . . እኛ በየበረሃው እየዞርን የተዋጋንላት አገር . . . .ምንም አላደረገችልንም፡፡ ድሮ ድሮ
የግብር ጠላና ጠጅ ይጠጣ ነበር፡፡ ዛሬ ጠላዬን እየከፈልኩ ነው የምጠጣው››
‹‹የት ነው የተዋጉት እርስዎ?›› አለ ግርማ፡፡
‹‹ሸዋና ወሎ በረሐ…. አታቅም እንዴ? …. ጠላ ቤት አትዞርም ለካ… የእኔ ጋዜጣ ጠላ ቤት ነው››
Filed in: Amharic