>

ዶ/ር አብይም ሆኑ ፓርቲያቸው ብልጽግና ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ ማብራሪያ ሊሰጡት ይገባል...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ዶ/ር አብይም ሆኑ ፓርቲያቸው ብልጽግና ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ ማብራሪያ ሊሰጡት ይገባል…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

* ጠቅላዩ ባህርዳር ገብተዋል፤ ለማስተባበል ይሁን ለማባበል፤ አልያም ግራ ለማጋባት የምንሰማው ይሆናል…!!!
 አቶ ሽመልስ በተናገሩት ክፉ እሳቤን ያዘለ እና አደገኛ እቅዶች የተገለጹበት ንግግር ላይ ግልጽ ማብራሪያ ሊሰጡበት ይገባል። ግለሰቡ የተናገሩት ነገር ፓርቲውን እና የሚመሩትን ክልል የማይወክልም ከሆነ ምክንያቱ በበቂ ሁኔታ ተገልጾ ፓርቲው እና አመራሮቹ እራሳቸውን ከእኝህ እና እሳቸውን ከመሰሉ ግለሰቦች ሊያጸዱም ይገባል። ነገርየው ከአፍ ወለምታም ባለፈ መልኩ የፖሊሲ ሃሳቦችን ጭምር የያዘ ስለሆነ እንደ ተራ ወሬ የሚታይ አይደለም። የተነገረበት ጊዜ መርዘምም ሆነ የተናገሩበት አውድ ምንም ይሁን ምን የተነገሩትን ነገሮች ግን ጥናት እና ዝግጅት ተደርጎባቸው እየተፈጸሙ ያሉ አደገኛ እቅዶች ስለሆን ፓርቲው በቂ ማብራሪያ ሊሰጥበት ይገባል።
በተለይም አዲስ አበባን በተመለከተ፣ ከቋንቋ ጋር በተያያዘ፣ ሥልጣን የዞ ለመቆየት የተነደፈውን ሥልታቸውን እና ዲሞግራፊን አስመልክተው የተናገሩት ነገር ከአፍ ወለምታም አልፎ የሕግ ተጠያቂነትንም የሚያስከትል፣ የመብት ጥያቄዎችንም የያዘ እና በዜጎች መካከል መበላለጥን እና ጥርጣሬን የሚያጭር እቅድ ጭምር ነው። እነዚህን ነገሮች የተናገረው አንድ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለ ካድሬ ወይም የፓርቲው ደጋፊ ቢሆን ችግር የለውም። አቶ ሽመልስ ግን የፓርቲው ከፍተኛ አመራር እና የክልሉም ም/ል ሊቀመንበር መሆናቸው የተነገረውን ነገር ችላ ተብሎ እንዳይታለፍ እና ትክክለኛ የፓርቲው አቋም አድርጎ ለመውሰድም በቂ ምክንያት ይሆናል።
Filed in: Amharic